Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉየአቶ ጃዋር መሐመድ ጽሑፍ ንድፈ ሐሳባዊ ቅንበባ

የአቶ ጃዋር መሐመድ ጽሑፍ ንድፈ ሐሳባዊ ቅንበባ

ቀን:

(ክፍል ሁለት)

 በጌታሁን  ሔራሞ

ይህ ጽሑፍ ሚያዝያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በሪፖርተር ዕትም ላይ በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ያካፈልኳችሁ ጽሑፍ ቀጣይ ክፍል ነው፡፡ በክፍል አንድ ጽሑፌ በአቶ ጃዋር መሐመድ ጽሑፍ ዙሪያ ንድፈ ሐሳባዊ ቅንበባ (Theoretical Framing) መከወን መጀመራችን ይታወሳል፡፡ ለማስታወስ ያህል የአቶ ጃዋር የኦሮሚኛው ጽሑፍ ወደ አማርኛው ሲተረጎም “ያለንበት ሁኔታና ቀጣዩ የትግል ምዕራፍ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ነበር፡፡ ለጽሑፉ ምላሽ እንድሰጥ ያነሳሱኝ በዋናነት ሁለት ምክንያቶች ናቸው፡፡ የመጀመርያው አቶ ጀዋር በትንታኔው በብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ ላይ፣ በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች በተለያዩ የዘርፉ ጠበብቶች የተደረጉትን ጥናቶች በዘፈቀደ እየተዋሳቸው ለመጠቀም መሞከሩ ነው፡፡

- Advertisement -

በተለይም ከእኛ አገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ዓውድ ጋር ፈፅሞ ሊጣጣሙ የማይችሉትን ብቻ ሳይሆን እርስ በርሳቸውም የሚቃረኑ የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳቦችንም በጽሑፉ ውስጥ ተራ በተራ መጠቀሙ ግራ ሳያጋባን አልቀረም፡፡ ስለዚህም የመጀመርያ ምክንያቴ ከአንፃራዊ የፖለቲካ/ብሔርተኝነት መርሆች (Principles of Comparative Politics/Nationalism) ጋር የሚቆራኝ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያቴ በሌሎች አገሮች የተደረጉ የብሔርተኝነት ጥናቶችን ያለ ዓውዳቸው እንደወረዱ ወደ አገራችን የፖለቲካ ምህዋር ውስጥ ማስረግ የሚያስከትለው ፖለቲካዊ ቀውስና አደጋ እንደ አንድ ዜጋ ስለሚያሳስበኝ ነው፡፡ በእርግጥ አቶ ጃዋር በጽሑፉ በአመዛኙ ያነሳው ስለኦሮሞ ብሔርተኝነት ቢሆንም አገራዊና ሌሎች ብሔሮችንም የሚመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮችንም በተደጋጋሚ አንስቷል፡፡ ስለዚህም እዚህና እዚያ እያፈራረቀ የሚያነሳቸው ፀጉረ-ልውጥ ንድፈ ሐሳቦች የማታ ማታ ተግባራዊ የሚሆኑት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ ላይ ነውና ቢያሳስበን ሊፈረድብን አይገባም፡፡

በክፍል አንድ ጽሑፌ (1.1) አቶ ጃዋር የኦሮሞን ብሔርተኝነት ውልደትና ሒደት ለመተረክ፣ ኧርነስት ገልነር የተባለው አንትሮፖሎጂስት በአውሮፓ ዓውድ ውስጥ ያደረገውን፣ የዘመናዊ ብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብን ለመጠቀም መሞከሩ ተገቢ አለመሆኑን (Irrelevant) ለመጠቆም ሞክሬ ነበር፡፡ የዛሬው ክፍል ሁለት ጽሑፌ በአቶ ጃዋር ጽሑፍ ውስጥ በተንፀባረቁ በሌሎቹ ንድፈ ሐሳባዊ ገለጻዎች ተገቢነት ላይ ያተኩራል፡፡ ታዲያ ንድፈ ሐሳባዊ ቅንበባውን የምንጀምረው ከቤኔድክት አንደርሰን የዕሳቤ ማዕቀፍ በመንደርደር ነው፡፡

1.2. የቤኔድክት አንደርሰን ዘመናዊ የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ  

ፕሮፈሰር ቤኔድክት አንደርሰን (እ.ኤ.አ.1936-2015) አንግሎ አይሪሽ የፖለቲካ ሳይንቲስትና የታሪክ ሊቅ ነበር፡፡ ከብሔርተኝነት ጋር በተገናኘ የቀመረው ንድፈ ሐሳብ እንደ ኧርነስት ገልነር በዘመናዊ ንድፈ ሐሳብ ጎራ የሚመደብ ነው፡፡ አንደርሰን በብሔርተኝነት ጽንሰ ሐሳብ ዙሪያ ከስድስት የማያንሱ መጽሐፍትን ደርሶ አስነብቧል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን አግኝተው በስፋት ከተነበቡለት መጽሐፎቹ ውስጥ “Imagined Communities: Reflections on the Origin and Spread of Nationalism” በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ የመጽሐፉ የመጀመርያ ዕትም የተለቀቀው ልክ እንደ ገልነር “Nations and Nationalism” መጽሐፍ እ.ኤ.አ. በ1983 ዓ.ም. ነበር፡፡ ኧርነስት ገልነር ለብሔርተኝነት መፈጠር ጥናት መነሻ ያደረገው በአውሮፓ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተስተዋለውን የኢንዱስትሪ አብዮትን ሲሆን፣ ቤኔድክት አንደርሰን ግን ለክስተቱ የአንበሳውን ድርሻ የሚሰጠው ለኅትመት ካፒታሊዝም (Print Capitalism) ነው፡፡ ጥናቱም በዋናነት ትኩረቱን ያደረገው በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በደቡብ እስያ (ኢንዶኔዢያና ቬትናም) በተከሰቱ የብሔርተኝነት ውልደት ላይ ነው፡፡

ለማስታወስ ያህል የቤኔድክት አንደርሰንን የዘመናዊ ብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብን በተመለከተ በአጭሩ መከለስ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በተደጋጋሚ ስለብሔር ምንነት በሚሰጡ ገለጻዎች የጋራ ማንነት፣ የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ሥነ ልቦና፣ ተመሳሳይ/ተቀራራቢ ባህል ወዘተ. የሚሉ ቃላት ጥቅም ላይ ሲውሉ ይታያል፡፡ ታዲያ የየትኛውም ብሔር አባላት ከአሰፋፈር አኳያ በጠባብ ቀዬ ተሰባስበውና ጎጆ ቀልሰው ማኅበራዊ ሕይወታቸውን በአካላዊ ቅርርብ ይከውናሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ የአንድ ብሔር አባላት ቁጥራቸው በሚሊዮኖች የሚገመት ሆኖ በጂኦግራፊ ደግሞ በብዙ ሺሕ ኪሎ ሜትሮች ተራርቀው የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በጂኦግራፊ መራራቁ ለሌሎች ማኅበረ ባህላዊ ዕሴቶች መለያየትም አሳልፎ እንደሚሰጥ ዕሙን ነው… “ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት” የሚለው ብሂል፣ ጂኦግራፊያዊ ርቀት ዘመዳሞችን ጭምር ሊያራርቅ እንደሚችል የሚጠቁም ነው፡፡ ስለዚህም በቦረናና በፍቼ በኦሮሞ፣ በጎንደርና በሸዋ አማራ፣ ማኅበረሰቦች መካከል ያለው ርቀት የኪሎ ሜትሮች ብቻ አይደለም፡፡ ታዲያ እንደዚህ ተራርቀው የሚኖሩና የአንድ ብሔር አባላት እንደሆኑ የሚነገርላቸው ብሔሮች በምን ተዓምር ነው የጋራ ሥነ ልቦና፣ የጋራ ትውስታ ወዘተ. የሚኖራቸው? የአንደርሰን ንድፈ ሐሳብ ለመመለስ የሚሞክረው ይህን መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡

የቋንቋ ተግባቦታዊ ሚና የቤኔድክት አንደርሰን ንድፈ ሐሳብ የጀርባ አጥንት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ቋንቋ ምትኃታዊ በሚመስል መልኩ የሰው ልጆችን ያቀራርባል፣ ያስተሳስራል፡፡ እስቲ ከምትኖሩበት አካባቢ ብዙ ሺሕ ኪሎ ሜትሮችን ርቃችሁ በባዕድ አገርና ከተማ፣ አንድ የምታውቁት የአገር ቤት ቋንቋ ከሆነ ቦታ ወደ ጆሮአችሁ ሲንቆረቆር የሚሰማችሁን ስሜት በምናባችሁ አስቡት፡፡ ቋንቋውን እንደ ሰማችሁ እንደ ኤሌክትሪክ የሚነዝር ስሜት በውስጣችሁ ከመቀፅበት ሰርፆ በራሳችሁና ቋንቋችሁን በተናገረ ሰው መካከል ገና ሳታነጋግሩት ምናባዊ ዝምድናና ጥምረት ይፈጠራል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በካናዳ (ኪቤክ)፣ በቤልጂየም፣ በጂዮርጂያ፣ በሞልዶቫ፣ ወዘተ. አገሮች ቋንቋን ማዕከል ያደረጉ ጠንካራ ብሔርተኝነቶች (Lingustic Nationalisms) መኖራቸው የሚያመለክተው ቋንቋ የፖለቲካ አጀንዳ የመሆን አቅም እንዳለው ነው፡፡

በቋንቋ መግባባት መቀራረብን ያጎለብታል ካልን፣ አለመግባባትስ ምንን ያስከትላል? የሚለውንም ጥያቄ መጠየቅ አስፈላጊ መስሎ ይታየኛል፡፡ አንዳንድ የብሔርተኝነት አጥኚዎች ይህን ጥያቄ ለመመለስ የሚጠቀሙት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን የባቢሎን ግንብ ሠራተኞችን ገጠመኝ ነው፡፡ ከባቢሎን ግንብ ታሪክ የምንረዳው ሠራተኞቹ ለግንባታ ሥራው የሚያስፈልጋቸው የክህሎትም ሆነ የማቴሪያል እጥረት እንዳልነበረባቸው ነው፡፡ ነገር ግን የግንቡን ፕሮጀክት ከመቀጠል ያስቆማቸው ሊያግባባቸው የሚችል “ብሔራዊ ቋንቋ” ያለመኖሩ ብቻ ነበር፡፡ ለዚህም ነው እንደ ኧርነስት ገልነር ያሉ የዘመናዊ ብሔርተኝነት አሳቢያን የቋንቋ ወጥነት (Linguistic Homogeneity) መኖርን ለአገር ግንባታ (Nation Building) ወሳኝ ሚና እንዳለው  የሚያሰምሩት፡፡ ታዲያ ተመሳሳይ ቋንቋን መናገር ተመሳሳይ ሐሳብን ለማዋለድ ዋስትና እንዳልሆነ ይሰመርበት ዘንድ ይገባል፡፡ ለአገር ግንባታው ፕሮጀክት ተመሳሳይ ቋንቋ በጋራ እሴቶችና መሻቶች (Shared Values and Interests) ካልታጀበ ዕጣ ፋንታው ከባቢሎን ግንብ ፕሮጀክት የተለየ አይሆንም፡፡ በቋንቋ ወጥነት ሥሌት ከሄድን በዓለም ላይ ጎረቤታችንን ሶማሊያን በአገር ግንባታው የሚቀድማት ባልኖረ ነበር፡፡

ቤኔድክት አንደርሰን ለዘመናዊ ብሔሮች መፈጠር መንስዔ የሆኑትን ባህላዊ ሰበዞች የምናገኘው ታሪክን የኋሊት ሄደን ስንፈትሽ ነው ይለናል፡፡ የመጀመርያው የኋላ ምክንያት የሃይማኖታዊ ማኅበራት መዳከም ሲሆን፣ ሁለተኛው የሥልጣን በትሩን ከመለኮት እንደተረከበ የሚምል ሥርዖ መንግሥት መንኮታኮት ነው፡፡ ለብሔር መፈጠር የእነዚህ ሁለቱ ሥርዓቶች መዳከም በቂ አይደለም፡፡ ቤኔድክት አንደርሰን የኅትመት ካፒታሊዝም ብሎ የሚጠራው የዘመናዊነት ዕሴት ገሃድ ሆኖ የብሔሮችን ህላዌ በየብሔሮቹ የአፍ መፍቻ (Vernaculars) ቋንቋ አሳላጭነት ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡

ከታሪክ እንደምንረዳው መጽሐፍት በብዛት መታተም የጀመሩት ጀርመናዊው ጆን ጉተንበርግ እ.ኤ.አ. በ1448 ዓ.ም. የኅትመት ማሽንን ከፈለሰፈ በኋላ ነው፡፡ ሆኖም ከእስልምናው አንፃር ከሞሮኮ እስከ ሱሉ አርክፕላጎ፣ ከክርስትናው አንፃር ከፓራጓይ እስከ ጃፓን፣ ከቡዲሂዝም አኳያ ደግሞ ከሲሪላንካ እስከ ኮሪያ የተዘረጉት ሃይማኖታዊ ተቋማት ለተግባቦት በብቸኝነት ይጠቀሙ የነበረው በየእምነታቸው “ቅዱስ” ተብሎ የሚታመነውን ቋንቋ ነበር፡፡ እኛም አገር በክርስትናው አማርኛና ግዕዝ በእስልምናው ደግሞ ዓረብኛ በብዛት ጥቅም ላይ እንደሚውለው ማለታችን ነው፡፡ ለምሳሌ በአውሮፓ በክርስትናው ሃይማኖት ለኅትመትም ይሁን ለሃይማኖታዊ ሥርዓት ይመረጥ የነበረው የላቲን ቋንቋ ነበር፡፡ ሆኖም በሒደት የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማነቆ ሆነው የቆዩት የሃይማኖት ተቋማቱ አይነኬነት መገርሰስ ሲጀምር፣ የተቋማቱ መደበኛ ቋንቋዎችም የበላይነት ማክተም ጀመረ፡፡ ለምሳሌ ያህል የፕሮቴስታንት ሪፎርሜሽንን ተከትሎ ማርቲን ሉተር እ.ኤ.አ. በ1522 ከመጽሐፍ ቅዱስ አዲስ ኪዳንን ለመጀመርያ ጊዜ በጀርመንኛ ቋንቋ ተርጉሞት አሳተመ፡፡

ይህ ለጀርመንኛ ተናጋሪዎች ምናባዊ አንድነትን በመፍጠር ረገድ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ እንዲሁም በፓሪስ ፈረንሣይኛ፣ በለንደን ደግሞ እንግሊዝኛ ላቲንን የሚገዳደሩ ቋንቋዎች ሆነው ተከሰቱ፡፡ ሌላው በአታሚዎች በኩልም ቢሆን በላቲን ቋንቋ ብቻ ኅትመቱን መቀጠል አዋጪ አልነበረም፡፡ ስለዚህም በቅናሽ ዋጋም ቢሆን በሌሎች የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች የኅትመት ገበያውን ማቀላጠፍ ነበረባቸው፡፡ እንግዲህ እነዚህን አዳዲስ የገበያ አድማሶች ተከትሎ ለተስተዋለው ሁነት አንደርሰን “የኅትመት ካፒታሊዝም” የሚል ስያሜን ሰጠ፡፡ አንደርሰን ይህ ለመጠነ ሰፊ የመጻሕፍትና የጋዜጦች ኅትመት ፈር የቀደደው የኅትመት ካፒታሊዝም ክስተት በአውሮፓ የተስተዋለው በ15ኛው ክፍለ ዘመን ነው ብሎ ያምናል፡፡

እንግዲህ የኅትመት አብዮትን ተከትሎ በአፍ መፍቻ ቋንቋዎች መጻሕፍትና ጋዜጦች መታተም መጀመራቸው ተራርቀው የሚኖሩትን የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ብሔሮችን ምናባዊ በሆነ መልኩ ለማቆራኘት ምክንያት ሆነዋል፡፡ በዚህም ሒደት በጽሑፌ መግቢያ የጠቀስኩት የጋራ ትውስታ፣ የጋራ ባህል፣ የጋራ ታሪክ ወዘተ. በማይተዋወቁ ሰዎች መካከል ጭምር በሒደት ሰርፆ ይፈጠርና በመጨረሻም ምናባዊ ማኅበረሰብ (Imagined Communities) ዕውን ይሆናል፡፡ ይህም ምናባዊ ማኅበረሰብ “ብሔር” ተብሎ ይጠራል፡፡ በአንደርሰን ብያኔ ምናባዊ ማኅበረሰቡ ከድንበር አንፃርም ብሔሩ ውስን (Limited)፣ ከነፃነት አንፃር ደግሞ ሉዓላዊ (Soverign) ነው፡፡ ውስን የተባለው ምናባዊ ማኅበረሰብ ከሰፈረበት ጂኦግራፊያዊ ክልል ውጪ ሌላ ምናባዊ ማኅበረሰብ እንደሚኖር ታሳቢ ተደርጎ ሲሆን፣ ሉዓላዊ የተባለው ደግሞ በዘመነ አብርሆት የማኅበረሰቡ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው እንደ ወትሮው በሃይማኖታዊ ዕሳቤዎች ሳይሆን በራሱ ዓለማዊ (Secular) መርሆች በመሆኑ ነው፡፡

  ታዲያ አቶ ጃዋር በጽሑፉ ውስጥ ለኦሮሞ ብሔርተኝነት መፈጠርና መስፋፋት ለአንባቢያኑ ለማስገንዘብ የቤኔድክት አንደርሰንን ንድፈ ሐሳብ ተጠቅሞ ይሆን? ከተጠቀመስ ተገቢነቱ ከአንፃራዊ ብሔርተኝት (Comparative Nationalism) መርህ አኳያ ሲጤን ምን ይመስላል? ከዚህ በመቀጠል እነዚህን ሁለቱን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት አደርጋለሁ፡፡

የአቶ ጃዋርን ጽሑፍ ከአንደርሰን የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ አኳያ ለመቀንበብ ከበቂ በላይ መረጃዎች አሉን ማለት ይቻላል፡፡ የመጀመርያው መረጃችን የአንደርሰን ንድፈ ሐሳብ መለያ ፅንሰ ሐሳብ የሆነውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ “Imagined Communities” በማለት በገጽ 6 ላይ ቃል በቃል መጠቀሙ ነው፡፡ እንደዚህ ይነበባል፣

“የብሔራዊ ትግሉ ዓላማ ሕዝቡንና ግዛቱን በመጠበቅ (Making the people and its territory congruent) ከባዕድ ጭቆና ማላቀቅ በመሆኑ፣ በሕዝቡ ዙሪያ ከሚሠሩ ፕሮጀክቶች ተግባር ውስጥ አንዱ የእንደገና መገንባት (ማቋቋም) ሥራ በአዕምሮ ውስጥ በማስረፅ (Imagined Communities) በገቢርም መንቀሳቀስ እጅግ አስፈላጊ ነው፡

  አቶ ጃዋር በጽሑፉ በሌሎቹም ገጾች የአንደርሰንን ንድፈ ሐሳብ ለመጠቀም ስለመሞከሩ ፍንጭ የሚሰጡን መረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ አሁንም ገጽ 6 ላይ አቶ ጃዋር የኦሮምኛ ቋንቋ የሚጻፍበትን ፊደል በማዘጋጀት፣ ሚዲያ ጋዜጦችና መጽሔቶች በመጠቀም የጋራ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ ወዘተ. በሕዝቡ አዕምሮ ውስጥ ማስረፅ እንደተቻለ አስረድቶናል፡፡ “በሕዝቡ አዕምሮ ውስጥ ማስረፅ” የሚለው ሐረግ በእንግሊዝኛው “Imagined” የሚለውን ቃል የሚተካ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

አቶ ጃዋር በገጽ 8 ላይ ደግሞ ብሔሩን ከጥቃት ስለመከላከል ትንታኔውን በሰጠበት ክፍል፣ ‹‹…ሰፊ መሬት ላይ የሚኖሩና የሕዝብ ብዛታቸው እንደ እኛ ብዙ ለሆነ ማኅበረሰብ ግን ይህ የሚሠራው፣ የእርስ በርስ ግንኙነቶች አካላዊ ሳይሆን ሥነ ልቦናዊ አንድነቱ በጠንካራ አለት ላይ የቆመ እንዲሆን ሲሠራ ብቻ ነው፤›› ይለናል፡፡ ይህ እንግዲህ ቀደም ሲል በጂኦግራፊ ተራርቀው የሚኖሩ የአንድ ብሔር አባላት የሚኖራቸው አንድነት ምናባዊ/ሥነ ልቦናዊ እንደሆነ ከተመለከትነው ከአንደርሰን ንድፈ ሐሳብ ጋር የሚጣጣም ነው፡፡ አቶ ጃዋር በዚያው ገጽ ላይ፣ ‹‹በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ የኢንዱስትሪ አብዮት በመባል በሚታወቀው አብዮት ውስጥ የኅትመት ማሽኖች… መፈጠር ብሔርተኝነት እንዲያብብ መንገዱን ጠርጓል፤›› በማለት የአንደርሰንን የኅትመት ካፒታሊዝምን ፋይዳም ለማንሳት ሞክሯል፡፡ በነገራችን ላይ አቶ ጃዋር በኦሮሞ የብሔርተኝነት ትግል ሒደት ውስጥ “Imagined Communities” የመፍጠሩ ተልዕኮ እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹና መጨረሻና በ1970ዎቹ መጀመርያ ላይ እንደተከናወነ በገጽ 6 ላይ ይፋ አድርጓል፡፡

ለመሆኑ የኦሮሞን የብሔርተኝነት ትግል አንደርሰን ካዋቀረው ከ”Imagined Communities” ንድፈ ሐሳብ ጋር በንፅፅር አስቀምጦ ማጤን የቱን ያህል ተገቢ ነው? በዚህ ረገድ የአቶ ጃዋር ጽሑፍ ሁለት መሠረታዊ ሕፀፆችን ስለመያዙ እንደሚከተለው ላቅርብ፡፡

ሀ. ጽንሰ ሐሳባዊ ብዥታ የፈጠረው ህፀፅ

አንድን የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ እንደ ሞዴል ወስደን ከማነፃፀራችን በፊት፣ በጽንሰ ሐሳቡ ላይ የጠራ ግንዛቤ መጨበጥ ግድ ይላል፡፡ ለምሳሌ አቶ ጃዋር በአንድ አንቀጽ ውስጥ ስለኦሮሞ ብሔርተኝነት ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ ለማስረዳት ሁለት የተለያዩ የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳቦችን አከታትሎ በመጥቀስ ሊያስረዳን ይሞክራል፡፡   ለዚህም ከላይ ገጽ 6 ላይ አስቀድሜ ያስቀመጥኩትን ገለጻውን በዋቢነት ማንሳት ይቻላል፡፡ በአንቀጹ አቶ ጃዋር መነሻ ላይ ለብሔራዊ ትግሉ ዓላማ የኦሮሞን የብሔርተኝነት ትግል ታሪክ ለማስረዳት በመጀመርያው ዓረፍተ ነገር የኧርነስት ገልነር ንድፈ ሐሳብ ይዘት ያለውን ማብራሪያ ይሰጠንና ትንሽ ቆይቶ እዚያው አንቀጽ ላይ የቤኔድክት አንደርሰንን ንድፈ ሐሳብ ደርቦ ያነሳል፡፡ በእርግጥ ሁለቱም ንድፈ ሐሳቦች ማለትም የገልነር “Nation-State Congruency” እና “Imagined Communities” ከዘመናዊ የብሔርተኝነት ዕሳቤ ጎራ ቢመደቡም ለአፈጣጠሩ ከሚያነሱት ጭብጥ አኳያ (Intellectual Orientations) ሲታዩ ግን ለየቅል ናቸው፡፡ ለምሳሌ ገልነር ለብሔሮች መፈጠር ምክንያቱ የኢንዱስትሪ አብዮት ነው ሲል አንደርሰን ደግሞ የኅትመት ካፒታሊዝም ነው ይለናል፡፡ ምናልባት የአንደርሰን የኅትመት ካፒታሊዝም ከዘመናዊነት ጋር ስለሚገናኝ ከኢንዱስትሪ አብዮት ጋርም የሚገናኝ ሊመስለን ይችላል፡፡ ሆኖም አንደርሰን በኅትመት ካፒታሊዝም እንደተፈጠረ የሚነግረን ብሔርተኝነት የተስተዋለው በኢንዱስትሪ አብዮት ወቅት አይደለም፡፡ ይልቁንም የአንደርሰን የኅትመት ካፒታሊዝም የተንፀባረቀው ከኢንዱስትሪው አብዮት ቀድሞ በተከሰተው የንግድ ሥርዓት (Pre-Industrial Mercantile Capitalism) ወቅት ነበር፡፡ ቅድመ ኢንዱስትሪ የንግድ ካፒታሊዝም ከኢንዱስትሪው አብዮት ወቅት ካፒታሊዝም የሚለይበት አያሌ ባህሪያት አሉት፡፡ አንዱም ልዩነት የቅድመ ኢንዱስትሪ የንግድ ካፒታሊዝም ማኅበራዊ እሴት ከኢንዱስትሪ አብዮት ወቅት ካፒታሊዝም የላቀ መሆኑ ነው፡፡ ወቅቱም ከ16ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡

ሌላው በገልነርና በአንደርሰን ንድፈ ሐሳቦች መካከል ያለው ልዩነት በዘመናዊነት የታሪክ ወቅት ብሔርተኝነት የተፈጠረበትን ምክንያትና ዓላማ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ገልነር ብሔርተኝነት የዘመናዊነት አገልጋይ ነው ብሎ ያምናል (Functionalism)፡፡ ለምሳሌ የዓሳ ሰውነት ቅርፅ እንደዚያ የሆነው በውኃ ውስጥ ለመዋኘት እንዲመቸው ነው ይባላል (Teleological Description):: በተመሳሳይ ኧርነስት ገልነር ዘመናዊነትም በተገቢው ሁኔታ እንዲሳለጥ የብሔርተኝነት መኖር ግድ ነው ይላል፡፡ በተቃራኒው ቤኔድክት አንደርሰን በኅትመት ካፒታሊዝም ወቅት የተፈጠረው ብሔርተኝነት የሆነ አገልግሎት እንዲሰጥ ታቅዶና ታልሞ (Non Teleological) አይደለም፡፡ በአጭር አገላለጽ አንደርሰን ክስተቱ የዕድልና የድንገቴ (Chance and Accidental) ቅንብር ነው ብሎ ያምናል፡፡

 ለ. ዓውዳዊ ህፀፅ

በቤኔድክት አንደርሰን ጥናት መሠረት በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በደቡብ እስያ የተስተዋለው የኅትመት ካፒታሊዝም ምናባዊ ማኅበረሰብን ፈጥሮ ለብሔር ህላዌ ሰበብ ሊሆን እንደቻለ ከላይ ተመልክተናል፡፡ አቶ ጃዋር በሌሎች አገሮች ላይ የተደረገ ጥናትን ለኦሮሞ የብሔርተኝነት ትግል ውልደት ማሳያነት ጥቅም ላይ ካዋለው፣ ዓውዳዊ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያ የኅትመት ካፒታሊዝም አብዮት የተስተዋለው መቼ ነበር? ከቦረና እስከ ፍቼ፣ ከወለጋ እስከ አርሲ ያለውን ኦሮሞ አገናኝቶ ምናባዊ ማኅበረሰብን ለመፍጠር የሚያስችሉ ጋዜጦችና መጻሕፍት በከፍተኛ መጠን ታትመው የተሠራጩበት ወቅት መቼ ነበር? ቤኔድክት አንደርሰን ከተጠቀሱት አገሮች ባለፈ ስለአፍሪካና ስለሌሎች የእስያ አገሮች የብሔርተኝነት ውልደት በተመለከተ በመጽሐፉ የከተበው ገለጻስ ይኖር ይሆን?

የኧርነስት ገልነርና የቤኔድክት አንደርሰን የቅርብ ወዳጅና የናሽናሊዝም ፕሮፌሰር የሆነው እንግሊዛዊው ጆን ብርዩሊ የቤኔድክት አንደርሰንን “Imagined Communities (IC)” መጽሐፍ ከገመገመበት ጭብጦች ውስጥ አንዱም ጥናቱ ለአፍሪካና እስያ አገሮች ያለው ፋይዳ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ለምሳሌ ብርዩሊ የአንደርሰን መጽሐፍ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በደቡብ እስያ አገሮች በሚደረጉ የብሔርተኝነት ውልደት ጥናቶች በማጣቀሻነት (Citation) በሚሰጠው ግልጋሎት ተወዳዳሪ እንደሌለው ከገለጸ በኋላ በተቃራኒው በአፍሪካ፣ በደቡብ እስያ፣ በምሥራቅ እስያና በላቲን አሜሪካ ያለው ተፈላጊነት እጅግ አናሳ መሆኑን በጥናታዊ ጽሑፉ የገለጸው እንደዚህ በማለት ነበር፦

“Reamarkably, despite both IC’s high number of citations and the prominent place that colonialism takes in the book, it has received very little real critical attention in the study of nationalism across Africa, South Asia, East Asia and Latin America, other than to cite IC in passing as one of the key modernist texts on nationalism.” ምንጭ፦ Benedict Anderson’s Imagined Communities: a Symposium, 2016

በመቀጠልም ጆን ብርዩሊ የአንደርሰንን ንድፈ ሐሳብ ተጠቅሞ፣ በአፍሪካና በእስያ አገሮች ብሔርተኝነት በሕዝቡ መካከል መቼና እንዴት እንደሰረፀ፣ እንዲሁም መቼና እንዴት ወደ ግጭትና ጦርነት እንደሚያመራ፣ ለማጥናት መሞከር ተገቢ አለመሆኑን የገለጸው “This has meant that Anderson’s argument is not particularly relevant when discussing both when and how national identities become relevant for people in new post-colonial states and when and how these identities lead to conflict and war.” በማለት ነበር፡፡

በእርግጥ ፕሮፈሰር ጆን ብሪዩሊ እንደዚህ ይበል እንጂ አቶ ጃዋር በኦሮሚያ “Imagined Communities” የመፍጠሩ ተልዕኮ የተፈጸመው እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ መጨረሻና በ1970ዎቹ መግቢያ አካባቢ እንደሆነ በገጽ 6 ላይ አሳውቆናል፡፡ ይህ ወቅት ደግሞ በአብዛኛው አፄ ኃይለ ሥላሴ በሥልጣን ላይ የነበሩበት ዘመን ነው፡፡ በኅትመት አብዮት ምናባዊ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ደግሞ ማንበብና መጻፍ የሚችል ትውልድ (Mass Literacy) በብዛት መኖር እንዳለበት አንደርሰን በመጽሐፉ ደጋግሞ የጠቀሰው እውነት ነው፡፡ ጆን ብርዩሊም የአንድርሰን ንድፈ ሐሳብ አፍሪካ ሲደርስ ወገቤን የሚልበት አንዱም ምክንያት ማንበብና መጻፍ የሚችል ማኅበረሰብ ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑ ነው ይላል፡፡

እናም አቶ ጃዋር በኦሮሚያ ምናባዊ ማኅበረሰብ እንደተፈጠረ በነገረን ዘመን፣ በመላው ኢትዮጵያ ማንበብና መጻፍ የሚችል ሕዝብ ከመቶኛ ሲሰላ ምን ያህሉ ነበር? ለዚህ ጥያቄ ምላሹን የምናገኘው ከራሱ ከአቶ ጃዋር ጽሑፍ ነው፡፡ አቶ ጃዋር በገጽ 9 ላይ ‹‹እ.ኤ.አ. በ1974 ዓ.ም. ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ሲወገዱ ማንበብና መጻፍ የሚችለው ሕዝብ 12 በመቶ ብቻ›› እንደሆነ የዓለም ባንክ መረጃን ጠቅሶ ነግሮናል፡፡ በተቃራኒው አቶ ጃዋር በገጽ 6 ላይ ‹‹…በሕዝቡ ዙሪያ ከሚሠሩ ፕሮጀክቶች ተግባር ውስጥ አንዱ የእንደገና መገንባት (ማቋቋም) ሥራ በአዕምሮ ውስጥ በማስረፅ (Imagined Communities) በገቢርም መንቀሳቀስ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡…›› ካለን በኋላ በማስከተል፣ ‹‹ይህ የትግል ምዕራፍ እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ መጨረሻና በ1970ዎቹ መጀመርያ ላይ የተሠራ ሥራ ነበር፤›› በማለት ምናባዊ ማኅበረሰብን የመፍጠሩ ሥራ 12 በመቶ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ዜጎች በነበሩበት ወቅት እንደተከናወነ ሊያስረዳን ይሞክራል፡፡ ከመላ ኢትዮጵያ አንፃር እንኳን ሲታይ 88 በመቶ ማንበብና መጻፍ የማይችል ሕዝብ ባለበት ወቅት በኦሮሚያ ውስጥ በንባብ የተሳሰረ ምናባዊ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የተቻለው በየትኛው አመክንዮ ነው? ምናልባት በዚህ ወቅት መጠነኛ በሆኑ መጣጥፎች አማካይነት የተፈጠረ ምናባዊ ማኅበረሰብ ሳይሆን፣ ምናባዊ የሊህቃን ቡድን (Imagined Elites) እንደተፈጠረ እየተነገረን ከሆነ ሊያስማማን ይችል ይሆናል፡፡

በነገራችን ላይ “imagined Communities” የሚፈጠሩት በፖለቲካ ሊህቃን ከላይ ወደ ታች (Top-Down) በሚወርድ የካድሬ ሞቢላይዜሽን ሥራ አይደለም፡፡ አቶ ጃዋርም “ምናባዊ ማኅበረሰብን ፈጥረናል” ሲል ጥንቃቄ ማድረግ ያለበት ከዚህ የተነሳ ነው፡፡ ማለትም ምናባዊ ማኅበረሰብ የሚፈጠረው በኅትመት ውጤቶች ምክንያት በጎንዮሽ ተግባቦት (Horizontal Communication) ነው፡፡ ለዚህም ነው ጆን ብሪዩሊ ከላይ በጠቀስኩት ጥናታዊ ጽሑፉ ገጽ 19 ላይ፣ “One must start by making some claims about what Anderson is and equally important is not arguing. His imagined community is in the first instance a societal process, not an elite project. He uses the idea of print capitalism, in particular the impact of specific kinds of writing, such as newspapers and  novels, to argue that these inadvertently generated new ways of envisioning social ties – as a series of parallel, horizontal communities coexisting in empty time and space.” በማለት ያስቀመጠው፡፡

ፕሮፈሰር ጆን ብሪዩሊ በግልና በጥምረት በጠቅላላ ወደ ስምንት ያህል ምርጥ መጻሕፍት የደረሰ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ “Nationalism and the Stae, 1982” እና “The Oxford Handbook of the History of Nationalism (Editor), 2013” ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እናም በአገራችን ነባራዊ ዓውድ፣ አብሮን ከከረመው ደካማ የንባብ ባህልና የኅትመት ዘርፍ መጠነ ሰፊ ውስንነት የተነሳ፣ በየትኛውም ብሔር ውስጥ በንባብ የተፈጠረ ምናባዊ ብሔር ይኖራል ብሎ ማሰብ እጅግ አዳጋች ነው፡፡ የአቶ ጃዋር ትንታኔ በሌሎች አገሮች የተደረጉትን ጥናቶችን ያለ አንዳች የማስማሚያ (Adaptation) ጥረት እንደወረዱ ለኦሮሞ ብሔርተኝነት መፈጠር በሰበብነት በማስቀመጡ ለዓውዳዊ ህፀፅ በሰፊው ተጋልጧል ወደሚል መደምደሚያ መድረስ ይቻላል፡፡

ወደ ቀጣዩ ርዕሰ ጉዳይ ከመሸጋገሬ በፊት የቤኔድክት አንደርሰንን የምናባዊ ማኅበረሰብ ንድፈ ሐሳብን ከሚያሄሱ ምሁራን ውስጥ፣ ስለህንዳዊው የፖለቲካ ሳይንቲስትና አንትሮፖሎጂስት ሃርተ ቻተርጂ ጥቂት ልበል፡፡ ቻተርጂ የ”Nationalist Thought and The Colonial World” መጽሐፍ ደራሲ ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ሳይንቲስት በቤኔድክት አንደርሰን ንድፈ ሐሳብ ላይ የተሰነዘሩ ሂሳዊ ሥራዎችን በያዘው በ”Mapping the Nation, 2012” መጽሐፍ ምዕራፍ 28 ላይ “Whose Imagined Community?” በሚል ርዕስ ያሰፈረው ጥናታዊ መጣጥፉ በሰፊው የሚታወቅለት ሂሳዊ ሥራው ነው፡፡ የሃርተ ቻተርጂ ሙግት የሚከተለው ነው፡፡ ቤኔድክት አንደርሰን በእስያና በአፍሪካ ያሉ ሊህቃን እንደ ሞዴል የኮረጁት በምዕራብ አውሮፓ፣ በአሜሪካና በሩሲያ የተስተዋለውን ታሪካዊ ብሔርተኝነትን ነው በማለት በመጽሐፉ አስፍሮ ነበር፡፡ ይህ ማለት እስያዊያንና አፍሪካዊያን ከኩረጃ ባለፈ በራሳቸው “Imagine” ያደረጉት አገር በቀል የብሔርተኝነት ዕሳቤ የላቸውም እንደ ማለት ነው፡፡ እናም ቻተርጂ በዚሁ በቤኔድክት አንደርሰን ማጠቃለያ ቆሽቱ ስላረረ በመጽሐፉ ውስጥ እንደዚህ ይላል፡፡

‹‹የታሪክ እውነተኛ ባለቤት እንደሆኑ የሚያስቡ አውሮፓዎችና አሜሪካኖች ለእኛ እኛን ተክተው ያሰቡልን የቅኝ አገዛዝ አብርሆትንና ጭቆናን ብቻ አይደለም… የፀረ ቅኝ አገዛዝ ተቃውሞንና የድኅረ ቅኝ አገዛዝ ምስቅልቅላችንንም ጭምር ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ቀርቶ ምናባዊ አስተሳሰባችንም ዝንተዓለም በቅኝ አገዛዝ ሥር እንዲቆይ ይፈልጋሉ፤›› ገጽ 214፡፡

የቻተርጂ ዋና መከራከሪያው አፍሪካዊያንና እስያዊያን አንደርሰን እንደሚለው አውሮፓዎቹ “Imagine” ያላደረጉላቸው የራሳቸው የብሔርተኝነት አፈጣጠር ታሪክ አላቸው የሚል ነው፡፡ ለዚህም በዋቢነት የሚጠቅሰው የፀረ ቅኝ አገዛዝ ብሔርተኝነትን ነው፡፡

በእርግጥ የቤኔድክት አንደርሰን ጥናት አንዱም ጠንካራ ጎኑ ከገልነር በተቃራኒው ከአውሮፓ አኅጉር ወጥቶ ጥናቱን በኢንዶኔዥያና ቬትናም ላይ ማድረጉ ነው፡፡ ሆኖም የአፍሪካና የእስያ አገሮች ብሔርተኝነት ምንጭ ጥናትን በተመለከተ በኤሊ ከዱሬ አዘጋጅነት ከሃያ በላይ ምሁራን የጻፉትን “Nationalism in Asia and Africa, 1970” መጽሐፍ ማንበብ የበለጠ ጠቃሚ ነው (መጽሐፉ በአንደርሰንም በገጽ 40 ላይ ተጠቅሷል)፡፡ ስለዚህም አቶ ጃዋርም ምንም እንኳን ከአንፃራዊ ብሔርተኝነት (Comparative Nationalism) ጥናት አኳያ የአንደርሰንን “Imagined Communities” መጽሐፍ ማንበብ ጠቃሚ ቢሆንም፣ ጽሑፉን ሲያዘጋጅ የኤሊ ካዱሬንም መጽሐፍ ቢጠቀም የበለጠ ተመራጭ ይሆን ነበር፡፡

በነገራችን ላይ የ“Imagined Communities” ንድፈ ሐሳብን ለማብራራት በዋናነት የተጠቀምኩት የራሱን የቤኔድክት አንደርሰንን መጽሐፍን (Imagined Communities: Reflections on the Origin and Spread of Nationalism, Revised Edition, 2016) እና የኡሙት አዚኪሪሚሊን “Theories of Natioanlism: A Critical Introdcution, 3rd edition, 2017″ መጽሐፍ ነው፡፡

  1. የአንቶኒ ስሚዝ የኢቲኖሲምቦሊዝም ንድፈ ሐሳብ

አንቶኒ ስሚዝ (እ.ኤ.አ.1939-2016) እንግሊዛዊ የማኅበረሰብ ታሪክ ሊቅና የብሔርተኝነትና የዘውጌ ጥናት ፕሮፌሰር ነው፡፡ ስሚዝ ዘመናዊነት ለብሔርተኝነት ማቆጥቆጥ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ያለመዘንጋቱ ከገልነርና ከአንደርሰን ጋር ያመሳስለዋል፡፡ ነገር ግን አንቶኒ ስሚዝ የብሔርተኝነትና የብሔር ህላዌ በዘመናዊነት ወቅት ብቅ ያለ ድንገቴ ክስተት ነው ብሎ አያምንም፡፡ በሌላ አነጋገር ምንም እንኳን ሁለቱም ሁነቶች በዘመናዊነት በሙላት ቢገለጡም ስንክሳራቸው ያለው በቅድመ ዘመናዊነት ወቅት ላይ ነው ብሎ ያምናል፣ ፕሮፌሰር አንቶኒ ስሚዝ፡፡ ይህ አቋሙ ስሚዝን ከቀድሞው አስተማሪው ከኧርነስት ገልነርና ከቤኔድክት አንደርሰን ንድፈ ሐሳብ ይለየዋል፡፡

በዘመናዊነት ወቅት ብቅ ካሉ የኢንዱስትሪና የኅትመት አብዮቶች ባልተናነሰ የአንቶኒ ስሚዝን ቀልብ የሳቡት የብሔሮች የኋላ ታሪካዊና ባህላዊ ዕሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህም አፈ ታሪኮች፣ የጋራ ትውስታዎች፣ ማኅበረሰባዊ ዕሴቶች፣ ትውፊቶችና ምልክቶች ናቸው፡፡ የኢቲኖስምቦሊዝም ንድፈ ሐሳብ የተዋቀረው ከእነዚህ መሠረታዊ አላባዊያን ነው ማለት ይቻላል፡፡

አንቶኒ ስሚዝ ከላይ የተጠቀሱትን ዕሳቤዎችን ለማስረፅ በጥቂቱ ወደ ስምንት ያህል መጻሕፍት ለንባብ ቢያበቃም ከእነዚህም ውስጥ በግንባር ቀደምትነት፣ “The Ethnic Origins of Nations, 1986, The Cultural Foundations of Nations, 2008, Ethno-symbolism and Nationalism, 2009, Myths and Memories of the Nation, 1999” ተጠቃሽ ናቸው፡፡

  ለአንቶኒ ስሚዝ ዘመናዊ ብሔሮች ከየትም የበቀሉ አይደሉም፡፡ ይልቁን በታሪክ ውስጥ ህልውናቸው በቀጣይነት የነበረ ዘውጌዎች በዘመናዊነት ውስጥ መዋቅራዊ ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟላላቸው ወደ ብሔርነት ይቀየራሉ፡፡ እነዚህን ወደ ብሔርነት የመቀየር ዕምቅ አቅም ያላቸውን ዘውጌዎችን ስሚዝ በእንግሊዝኛው “Ethnie” በማለት ይጠራቸዋል፡፡ ስለዚህም ለአንቶኒ ስሚዝ በዘመነ አብርሆትና በፈረንሣይ አብዮት ወቅት ብቅ ያሉ ብሔሮች የአንድ ውስን የታሪክ አጋጣሚ ክስተቶች ሳይሆኑ ቀድመው የነበሩ ባህላዊ ማኅበረሰቦች ማለትም “Ethnie” ቀጣይ አካል ናቸው፡፡ ከላይ ጠቀስ እንዳደረኩት እነዚህን የዘመናዊ ብሔሮች ጥንስስ የሆኑ ዘውጌዎችን አንድ አድርጎ አስተሳስሮ ለብሔርነት ወግ ማዕረግ የሚያበቃቸው የጋራ ታሪክ፣ አፈታሪክ፣ የጋራ ባህል፣ የራሳቸው የሆነ ግዛተ መሬት ወዘተ. ናቸው፡፡

“An ethnie is a named human population with sahred ancestry myths, histories and cultures, having an association with a specific territory, and a sense of solidarity.” (Antohny smith)       

  ከዚህም በተጨማሪ ለብሔርነት የታጩ የዘውጌ ቡድኖች ከሌሎች የሚለዩዋቸውን ምልክቶች (Symbols) ለምሳሌ ባንዲራ፣ ሙዚቃዎች፣ ሐውልቶች፣ የአለባበስ ሥርዓቶች የጋራ ጀግኖች፣ ወርቃማ የኋላ ዘመን፣ የጋራ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንዳላቸው በማስገንዘብ ሕዝባቸውን ያነቃቃሉ፣ ያነሳሳሉ፡፡

እንግዲህ ከርዕሰ ጉዳያችን ጋር በተያያዘ ቀጣዩ ተግባራችን የሚሆነው፣ የአቶ ጃዋርን ጽሑፍ ከኢቲኖሲምቦሊዝም ንድፈ ሐሳብ አንፃር ለመቀንበብ ይዘቱን ማጤን ነው፡፡ በእኔ ፍተሻ መሠረት አቶ ጃዋር የኦሮሞ ብሔር አፈጣጠርና ሒደት ለማስገንዘብ የኢቲኖሲምቦሊዝንም ዕሳቤዎችን ለመጠቀሙ ፍንጭ የሚሰጡን አገላለጾች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህልም በገጽ 5 ላይ የኦሮሞ ብሔር “የጋራ ምልክቶችን፣ ዓርማዎችን፣ ባህሉንና ቋንቋውን“ ከጨቋኞች መጠበቅ እንዳለበት ያሳስባል፡፡ በገጽ 10 ላይ ደግሞ፣ ”የጋራ ትውስታን (Shared Memories)፣ ታሪክና አፈታሪክ (Myths)” እየመዘገቡ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ አስፈላጊ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ በገጽ 11 እና 12 ደግሞ ስለጋራ የክልል መዝሙር (Anthem/Hymns)፤ የጋራ ታሪካዊ ጭቆና፣ የጋራ የወደፊት ዕጣ ፈንታ (Common Destiny) ያነሳል፡፡ በመጨረሻም በገጽ 6 ላይ “ኦዳን መልሶ የብሔሩ ዓርማ ማድረግ (Symbol)፣ ገዳ የሁሉም የማኅበረሰቡ አካባቢዎች የጋራ ሥርዓት እንደነበር ማስረፅ (Glorious or Golden Past)” በማለት የኢቲኖ ሲምቦሊዝም ጽንሰ ሐሳቦች ይዘት ያላቸውን ቃላት ይጠቀማል፡፡ ከላይ እንደተነሳው ኢቲኖሲምቦሊስቶች ለግዛተ መሬት ባለቤትነት (Homeland Ownership) ያላቸው ትኩረት ከልክ ያለፈ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህም የግዛተ መሬት ቁርኝት በአቶ ጃዋር ጽሑፍ ከመጀመርያው እስከ መጨረሻው በአፅንዖት የተንፀባረቀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቀደም ሲልም አቶ ጃዋር የግዛተ መሬትን ባለቤትነትን በተመለከተ በንግግሮቹም መሀል ‘ፈጣሪ በሰጠን መሬት’ የሚለውን ሐረግ ሲጠቀም ይስተዋል ነበር፡፡ ይህ የኢቲኖሲምቦሊስቶች ልዩ ምልክታቸው ነው፡፡

የኢቲኖሲምቦሊዝም አላባዊያን እንደሆኑ የጠቀስናቸው እሴቶች ለምሳሌ አፈታሪክ፣ የኋላ ታሪክ፣ ምልክቶች፣ ዓርማዎች፣ ወዘተ. ወደ ማኅበረሰቡ የሚደርሱት በዋናነት በምሁራን (Intelligentsia) እንደሆነ አንቶኒ ስሚዝ በደማቁ ያሰምራል፡፡ ነገር ግን ዋና ዋና የሚዲያ አውታሮችና የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በሆኑባቸው አገሮች ያሉ ምሁራን የዘውጌ ቡድናቸውን ለመቀስቀስ የሚችሉት በምን ዓይነት ሥልት ነው? የሚለው ጥያቄ የስሚዝን ንድፈ ሐሳብ ለሂስ የሚዳርግ ነው፡፡ ይህን ሂስ በተመለከተ በዝርዝር ማቅረብ የሚቻል ቢሆንም ለአሁኑ በአቶ ጃዋር የስሚዝ ንድፈ ሐሳብ አጠቃቀም ተገቢነት (Relevance) ላይ ጥቂት ልበል፡፡

እስካሁን ድረስ የኦሮሞን የብሔርተኝነት ውልደትና ሒደት ለማስገንዘብ አቶ ጃዋር የገልነርንና የአንደርሰንን ንድፈ ሐሳቦችን ለመጠቀም ሞክሯል፡፡ አሁን ደግሞ የአንቶኒ ስሚዝን ንድፈ ሐሳብ ሲጠቀም እናስተውላለን፡፡ ከላይ ጠቀስ እንዳደረኩት አንቶኒ ስሚዝ የኧርነስት ገልነር ተማሪ ነበር፡፡ ይሁንና የገልነርን ዘመናዊ የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብን እንደ ስሚዝ ያሄሰ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህም ስሚዝ የብሔሮች ህላዌ በቅድመ ዘመናዊ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ እንደነበረም ገሃዳዊ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ጭምር ገልነርን ከመሞገትም ባለፈ፣ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ አያሌ መጻሕፍትን አዘጋጅቶ አስነብቧል፡፡ እናም ስሚዝ የብሔሮች የአፈጣጠር የጊዜ ሰሌዳን በተመለከተ ያለው አቋም ከገልነርም ከአንደርሰን ይለያል፡፡ ደግሞም ስሚዝ የብሔር ማንነት እንደ ፒሪሞሪዲያሊስቶች ከጥንትም የነበረና በደም የሚተላለፍ ነው ብሎም አያምንም፡፡ አቶ ጃዋር ግን በጽሑፉ የፒሪሞሪዴሊዝም ዕሳቤዎች ደጋፊ እንደሆነም ፍንጭ ሰጥቶናል (በክፍል ሦስት ጽሑፌ በስፋት እንመለከታለን)፡፡ ጥያቄዬ የአንድ ብሔርተኝነት አፈጣጠር (ለምሳሌ የኦሮሞ) በአንድ ወጥ ጽሑፍ ውስጥ እርስ በርስ ከሚቃረኑ ሦስትና አራት ንድፈ ሐሳቦች ጋብቻ ውስጥ በምን ዓይነት ተዓምር ነው ገሃድ ሆኖ የሚወለደው? አመክንዮን ከቁብ የማይቆጥረውን (Irrational Myths) የአንቶኒ ስሚዝን የዘውጌዎችን አፈ ታሪክን፣ ከገልነር ዘመናዊ ዕሳቤና ከፒሪሞሪዲያሊስቶቹ ሶስዮባዮሎጂካል “ተጨባጭ ትርክት” (Objective Narration) ጋር አስታርቆ ማዋለድ የሚቻለው ምን ዓይነት ብሔርተኝነትን ነው? ለማሰብ ይከብዳል፡፡

ለማንኛውም ክፍል ሁለት ጽሑፌን እዚህ ላቁም፡፡ የመጨረሻ በሆነው ቀጣይ ክፍል ሦስት ጽሑፌ ውስጥ የአቶ ጃዋርን ጽሑፍ ከፒሪሞርዲያል ንድፈ ሐሳብ አንፃር ከፈተሽን በኋላ ወደ ማጠቃለያ ሐሳብ እናመራለን፡፡ በነገራችን ላይ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ውልደት በኢትዮጵያ የብሔር ጥያቄ ታሪክ ውስጥ አልተከሰተም የሚል ሙግት የለኝም፡፡ ሙግቴ ሙሉ በሙሉ የሚያተኩረው በአቶ ጃዋር ጽሑፍ ውስጥ በተጠቀሱ አዋላጆች ብዛትና ማንነት ዙሪያ ነው፡፡ በቀጣዩ ጽሐፌ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ውልደትንና ሥርጭትን በተሻለ ይገልጻል ብዬ የማምነውን የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብን ለመጠቆም እሞክራለሁ፡፡ በዚህም ሒደት ሌሎች የኦሮሞ ምሁራን በኦሮሞ ብሔርተኝነት ውልደት ዙሪያ የጻፉትን ከአቶ ጃዋር ጽሑፍ ይዘት ጋር በማነፃፀር ለማጤን እንሞክራለን፡፡ አመሠግናለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን የግል አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...