Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የአፍሪካ ኅብረትን ፋይዳ ትልቅ የምናደርገው እኛው ራሳችን ነን›› አየለ በከሪ (ፕሮፌሰር)፣ የታሪክ ተመራማሪ

የታሪክ ተመራማሪው አየለ በከሪ (ፕሮፌሰር) እ.ኤ.አ. በ1974 ነበር ከዓለማያ ዩኒቨርሲቲ በዕፅዋት ጥናት ሳይንስ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁት፡፡ ሆለታ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ውስጥ ሲሠሩ ቆይተው ወደ አሜሪካ ለከፍተኛ ትምህርት አቀኑ፡፡ በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አፈርና ማዳበሪያ ላይ፣ እንዲሁም በጤፍ ሰብል ላይ ጥናት በማድረግ እ.ኤ.አ. በ1979 የማስተርስ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡ ለ21 ወራት ትምህርት አሜሪካ ያቀኑት ተማሪው አየለ፣ በጊዜው በአገር ቤት የቀይ ሽብር ግርግር በመፈጠሩ የተነሳ መመለሱ ስላሠጋቸው ፈቃድ አግኝተው የአሜሪካ ቆይታቸውን አራዘሙ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ከተፈጥሮ ሳይንስ መስክ የትምህርት ዘርፋቸውን ወደ ማኅበራዊ ሳይንስና ሂዩማኒቲ የመቀየር ሐሳብ የመጣባቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1989 በዚያው በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካን ስተዲስ ሁለተኛ የማስተርስ ዲግሪ ለመያዝም በቁ፡፡ በታሪክ መስክ ትምህርት መግፋትን በመምረጣቸው እ.ኤ.አ. በ1994 በኢትዮጵያ ፊደል ታሪክ ላይ ጥናት በማካሄድ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን (ፒኤችዲ) ለመሥራት ችለዋል፡፡ ከመማር ጎን ለጎን በቴምፕል ዩኒቨርሲቲ ለአምስት ዓመታት፣ ከዚያም ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ ለ14 ዓመታት በመምህርነትና ተመራማሪነት ሲሠሩም ቆይተዋል፡፡ በመጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለአሥር ዓመታት አስተምረዋል፡፡ ጦርነቱ ሲጀመር ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን የሚናገሩት አየለ (ፕሮፌሰር)፣ በዋናነት በአፍሪካ ዴይ ኢኒሼቲቭ አማካሪነት ከመሥራት ጎን ለጎን የተለያዩ የማኅበረሰብ ግልጋሎቶችን እየሰጡ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የሠፈራቸውን ልጆች ደብተርና መጻፊያ ወጪ እየቻሉ በእረፍት ቀናትም እየሰበሰቧቸው እንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማሩ ልዩ እርካታ እንደሚሰጣቸውም ይናገራሉ፡፡ በቅርቡ የአፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመት ምሥረታ ቀንን በልዩ ድምቀት ለማክበር ስለተዘጋጀውና የአፍሪካ ቀን መታሰቢያ በየዓመቱ እንዲከበር ሐሳብ ስለሰነቀው የአፍሪካ ዴይ ኢኒሼቲቭ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡበት ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- አፍሪካ ዴይ ኢኒሼቲቭ ብሎ የአፍሪካ ኅብረት ምሥረታ ቀን ማክበር መሠረታዊ ዓላማው ምንድነው? ይህን ዓይነት እንቅስቃሴ መጀመሩ ፋይዳውስ ምንድነው?

አየለ (ፕሮፌሰር)፡- በሴኔጋል ዳካር ለምሳሌ የአፍሪካ ባህል ፌስቲቫል ይከበራል፡፡ በአልጄሪያ አጀርስም የአፍሪካ የባህል ፌስቲቫል እየተባለ ትልልቅ ክብረ በዓላት ይከበራሉ፡፡ በናይጄሪያ አቡጃም ሆነ በሌጎስ ተደርጎ ያውቃል፡፡ የአፍሪካ ትልቅ የባህል ፌስቲቫል በቋሚነት ቢከበርና ይህንን በዓለም እ.ኤ.አ. ግንቦት 25 እየጠበቅን በየዓመቱ እኛ ብናካሂደው የሚኖረውን ድምቀት ማሰብ ይቻላል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የተመሠረተበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ትልቅ ፌስቲቫል በመደገስ ዓለምን ብንጋብዝበት የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ነው፡፡ የክብረ በዓሉን ይዘትም ሆነ ቦታ ሳንገድበው በተለያዩ መርሐ ግብሮች በተለያዩ ከተሞቻችን ብናደርገው ውጤታማ ነው የሚሆነው፡፡ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ወዘተ ዓለም አቀፍ በዓል ቢስተናገድ ጠቀሜታው ትልቅ ነው፡፡ ባህላችንን በአለባበስ፣ በጽሑፍ፣ በሙዚቃ፣ በጥበቡና በሌላም መንገድ እናስተዋውቅበታለን፡፡ ሌሎች አፍሪካዊያንም የራሳቸውን ይዘው ስለሚመጡ የባህል ልውውጡ ትልቅ ነው የሚሆነው፡፡ አስተሳሰብህን፣ ፈጣሪነትህን፣ ዓለም አቀፍ እውቀትህን የሚጨምር ዕድል ነው፡፡ ይህ ፌስቲቫል መከበር በተለመደ ቁጥር በሒደት የእኔነት ስሜት ስለሚፈጥር አፍሪካዊ ማንነት ማላበሱ ይጠነክራል፡፡ የእኛ የአፍሪካዊያን ቀን መጣ ማለት ይለመዳል፡፡ ለቅኝ ገዥዎች አንወድቅም፣ በሰውነታችን መከበር አለብን፣ ከሌላው የዓለም ሕዝብ እኩል ነን የሚል ሥነ ልቦናም ያሰርፃል፡፡ ይህን ስሜት ደግሞ በቴአትር፣ በፊልም፣ በሙዚቃ፣ በፓናል ውይይት፣ በባህል መድረክ በሌላም መንገድ ማንፀባረቅ ይሰፋል፡፡ ለአፍሪካ ችግሮች ዙሪያ ትልቅ ግንዛቤ ለመፍጠርም መድረኩ ይረዳል፡፡ ለምሳሌ ሁለት ጄኔራሎች ስለተጣሉ ሱዳን መንደድ አለባት ወይ? አፍሪካዊያን በጣም የወረድንበትን ሁኔታ ነው አጋጣሚው የሚያሳየው፡፡ ሁለቱ ጄኔራሎች ሲጀመር ሥልጣን መያዝ የለባቸውም፡፡ ሁለተኛ የእነሱ ፀብ የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ ይወስናል ብለው ወደ ፀብ በመግባት ሕዝቡን ማሰቃት የለባቸውም፡፡ አፍሪካዊያን የመጨረሻው ዝቅታ ላይ መሆናችንን ማሳያ ነው የሱዳን ግጭት፡፡ እዚህ ደረጃ እስክንደርስ ድረስ የሄድነው ደግሞ የአፍሪካዊ ማንነት ግንዛቤያችን በማነሱ የተነሳ ነው ብለን እናምናለን፡፡ የአስተሳሰብ አድማሳችን ነፃ ሆኖ መስፋት አለበት፡፡ በትንሽ ነገር እየተታኮስን አንገዳደልም፣ በጠባብነት ታምቀንና ታፍነን አንኖርም የሚል ግንዛቤ መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ደግሞ የሚመጣው አፍሪካዊያን እርስ በርሳችን የበለጠ የምንገናኝበትና ሐሳብ የምንካፈልበት መድረክ ተፈጥሮ እየተጠናከረ ሲሄድ ነው፡፡ አንድነቱ ሲጠናከርና ተቀራርቦ መኖሩ ሲጎለብት በተለያየ መንገድ ልጫን የሚለውም የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ (ኒዮ-ኮሎኒያሊዝም) ኃይል ሥርዓት ይይዛል፡፡  

ሪፖርተር፡- የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ሞቷል ይባላል፡፡ እንደ ቀድሞው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ወይም ክዋሜ ንክሩማ ዘመን እንደነበረው ሳይሆን ተዳክሟል ይባላል?

አየለ (ፕሮፌሰር)፡- የፓን አፍሪካኒዝምን ንቅናቄ እ.ኤ.አ. ከ1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ጋር የተያያዘ አደረግከው፡፡ በጊዜው እነ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጥሩ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የፓን አፍሪካን እንቅስቃሴ ቀደም ያለ ንቅናቄ ነው፡፡ ደግሞም አፍሪካ ውስጥ አልተጀመረም፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄ ተከትሎ የተመሠረተ ብቸኛው ተቋም አይደለም፡፡ ከዚያ ቀድሞ በአፍሪካዊያን ዳያስፖራ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ነበር፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በካሪቢያንና በአውሮፓ የሚኖሩ አፍሪካዊያን ከታሪካቸው የመጣ ጥንታዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የእንቅስቃሴው ዋናው ዓላማ የሰው ልጆችን ክቡርነትና በነፃነት የመኖር መብት ማሳካት ነው፡፡ አፍሪካዊያንን በሚመለከት ደግሞ ከሌሎች የሰው ልጆች እኩል ክቡር ማንነት ያላቸው መሆኑን ማንፀባረቅ ነበር የእንቅስቃሴው አንዱ መሠረታዊ ዓላማ፡፡ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት እንዲያከትም ማድረግ ነው፡፡ አውሮፓዊያኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አፍሪካን የገዙበትን ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያ በፊት የነበረውንና እነሱ ያስፋፉትን የባርነት ሥርዓት እንዲያከትም መታገል ነው፡፡ በአጠቃላይ አፍሪካዊያንን ከሰውነት ተራ አውጥቶ ጉልበታቸውንና ሀብታቸውን የሚበዘብዝ ሥርዓት በዓለም ላይ ተንሰራፍቶ ከ400 ዓመታት በላይ ቆይቷል፡፡ አውሮፓዎቹ የፈረንሣይ፣ የእንግሊዝ፣ የስፓኝ፣ የፖርቹጊዝ፣ የደች፣ የቤልጂግ፣ ወዘተ እያሉ አፍሪካን ጨምሮ ዓለምን የተቀራመቱበት ዘመን የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ባይባልም፣ የእሱ መሠረት የሆነው ባሪያ ፍንገላና ወረራ ከተጀመረ ግን 400 ዓመታትን የተሻገረ ነው፡፡ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ አፍሪካዊያን ነፃነታቸውን እስከተጎናፀፉበት እስከ 1960ዎቹ አካባቢ በዚህ ሥርዓት ነው ያለፉት፡፡ ለምሳሌ ጋናን ብናያት እ.ኤ.አ. በ1957 ነበር ነፃነት ያገኘችው፡፡

የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ወደ አፍሪካ ከመምጣቱ በፊትና አፍሪካዊ ተቋም እንዲመሠረት ምክንያት ከመሆኑ በፊት ግን፣ በዳያስፖራው ብዙ የታሪክ ሒደቶችን አልፏል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1900 ጀምሮ ብዙ ስብሰባዎችና ጉባዔዎች በውጭ ተካሂደዋል፡፡ በለንደን የተካሄደው የመጀመሪያው ጉባዔ አለ፣ በፓሪስ የተደረገም አለ፣ ኒውዮርክ የተካሄደ አለ፡፡ በትንሹ አራትና አምስት ጉባዔዎች ተካሂደዋል፡፡ የመጨረሻውና ፍሬያማ ነው የሚባለው ግን እ.ኤ.አ. በ1945 በማንቼስተር የተካሄደው ነበር፡፡ እነዚህ ስብሰባዎች ደግሞ በታወቁ የፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኖች የሚመሩ ነበሩ፡፡ ደብሊውኢቢ ደቦይስ፣ ማርክስ ጋርቬይ፣ ጆርጅ ፓድሞር፣ ሲልቨስተር ዊሊያምስን የመሳሰሉና ሌሎችም የጥቁር አፍሪካዊ ማንነት አቀንቃኝ ምሁራን ነበሩ የመሩት፡፡ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በካሪቢያን የሚኖሩ ብዙ ዕውቀት ያላቸውና በርካታ መጻሕፍት ያበረከቱ ሰዎች ናቸው ንቅናቄውን የፈጠሩት፡፡ የአፍሪካ አኅጉር በቅኝ ግዛት እየማቀቀች ጨለማ ውስጥ ሆና መኖሯ ትክክል አለመሆኑን የሞገቱ ቀድመው የነቁ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች የአፍሪካዊያንን ችግር መላው ዓለም እንዲረዳው ለማድረግ ዓለም በሚረዳው ቋንቋ በመጻፍ የነበረውን የተዛባ ትርክት በመቀየር ትልቅ ሥራ የሠሩ ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ሕጎች እንዲሻሻሉና የሰዎችን እኩልነት ያማከሉ እንዲሆኑ ሠርተዋል፡፡ የሰው ልጆችን መብት በእኩል ደረጃ የሚያከብሩ ተቋማትም (የሊግ ኦፍ ኔሽን በኋላም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት) እንዲመሠረቱ የራሳቸውን እርሾ አበርክተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1945 የማንቼስተር ጉባዔ ከአፍሪካም እንደ የጋናው ክዋሜ ንክሩማ፣ የኬንያው ጆሞ ኬንያታ፣ የናይጄሪያው አዚጉዌና ሌሎችም አፍሪካዊያን ተካፍለው ነበር፡፡ በዚህ ጉባዔ ላይ ነበር የጥቁር አፍሪካዊያን መበዝበዝ መቆም አለበት የሚለው ነጥሮ የወጣው፡፡ አፍሪካ ከቅኝ ተገዢነት ነፃ ልትወጣ ይገባል ተብሎ የተጠየቀውና ከቅኝ ግዛት ተፅዕኖ ራስን የማላቀቅ ፍላጎት በይፋ የተንፀባረቀው በዚህ የተሳካ የፓን አፍሪካዊ መድረክ ላይ ነበር፡፡ ይህ ተነሳሽነት ነው እንግዲህ የአፍሪካ አኅጉራዊ ድርጅትን ለመመሥረት መነሻ የሆነው፡፡ ጋና ነፃ በወጣች ማግሥት እ.ኤ.አ. 1968 በአክራ ትልቅ ስብሰባ ተደርጎ ነበር፡፡ ይህ ስብሰባ ደግሞ የበለጠ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይመሥረት የሚለውን ሐሳብ አጎላው፡፡ በሒደት ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ጀመሩ፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ብዙ ደክመዋል፡፡ እንደ ከተማ ይፍሩ፣ ምናሴ ለማ፣ አክሊሉ ሀብተወልድ ያሉ ታላላቅ ምሁራን ባደረጉት የነቃ ተሳትፎ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት ብቻ ሳይሆን ምሥረታውንና ዋና መቀመጫውን በኢትዮጵያ እንዲያደርግ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡   

ሪፖርተር፡- የአፍሪካ ኅብረት በመመሥረቱ አፍሪካ ብሎም ኢትዮጵያዊያን ምን አተረፉ?

አየለ (ፕሮፌሰር)፡- በዚህ ጉዳይ የዕይታችንን አድማስ ሰፋ ማድረግ አለብን፡፡ ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኒውዮርክ በመሆኑ ብቻ ከኒውዮርክ አልፎ አሜሪካን የሚጠቅም ፀጋ ያመጣ ነው፡፡ ኒውዮርክ በተመድ መቀመጫነቷ የዓለም መዲና የመሆን ዕድል አግኝታለች፡፡ ከመላው ዓለም የመጣ የሚኖርባት ዓለም አቀፍ ከተማ በመሆኗም ከ800 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት የብዝኃነት ከተማ ሆናለች፡፡ በባህል ልዩ ስብጥር የፈጠረች ከተማም ሆናለች፡፡ ኢኮኖሚው ከዓለም ቀዳሚ የሆነ ከተማም ሆናለች፡፡ የአፍሪካ አንድነት ኅብረት/ድርጅት አዲስ አበባ መሆኑ ልክ እንደ ኒውዮርክ ትልቅ ፀጋ ሲሆን በቀላሉ የመጣ ዕድልም አይደለም፡፡ የዓድዋ ድልን እንደ ታላቅ የጥቁር ሕዝቦች ድል በመቁጠራቸውና የራሳቸው በማድረጋቸውና ለኢትዮጵያ ባላቸው አክብሮት ነው፣ የእኛ ወንድምና እህት ጥቁር ሕዝቦች መዲናው አዲስ አበባ እንዲሆን ድጋፍ የሰጡት፡፡ የዓድዋ ድልን ታሪክ ስለተቀበሉት ነው ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ሳይነካት ነፃነቷን ጠብቃ በመኖሯ፣ ለኢትዮጵያ ባላቸው ክብር የተበረከተ ዕድል ነው፡፡ በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት ፋሽስቶች ከከተሞች አካባቢ ሰፊውን የኢትዮጵያ አካባቢና ገጠሩን መያዝ ሳይችሉ ነው በአርበኞች ተጋድሎ የተባረሩት፡፡ ኢትዮጵያ ለነፃነት የከፈለቻቸው መስዋዕትነቶችን በመረዳት ነው፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካዊያን መዲና ልትሆን ይገባል ብለው የወሰኑት፡፡ የእኛም ሰዎች በጊዜው ያደረጉት ጥረት ትልቅ ነበር፡፡ እነ አፄ ኃይለ ሥላሴ አርቀው መመልከት የቻሉ መሪዎች ነበሩ፡፡ ያለ ድርጅት መደመጥም ሆነ መወከል የማይቻልበት ዓለም ውስጥ ነው ያለነው ብለው የድርጅቱ መቋቋምን አስፈላጊነት ያጠናከሩት እነሱ ነበሩ፡፡ የእኛ ድምፅ፣ ሐሳብና አመለካከት እንዲደመጥ አፍሪካ የአንድነት ድርጅት እንደሚያስፈልጋት ያሰረፁት የእኛ መሪዎች ነበሩ፡፡ ድርጅቱ እዚህ በመሆኑ በታሪክ ላበረከትነው አስተዋጽኦ መመሥገኛችን ነው፡፡ ሁለተኛም በጋራ ቆሞ መደመጥንና መሰማትን የሚፈጥርም ነው፡፡

15ኛው ክፍለ ዘመን ጥቁሮች ለአስቀያሚ ባርነት የሚዳረጉበት ነበር፡፡ ሰዎች አማራ ነህ አሮሞ፣ ዩርባ ነህ ምናምን ሳይባሉ አካላዊ ተክለ ቁመናቸው ብቻ እየታየ እንደ እንሰሳ ታስረው በመርከብ ታጭቀው ወደ አሜሪካ የሚጋዙበትና በሰፋፊ የእርሻ ማሳዎች ላይ ጉልበታቸው እየተበዘበዘ የሚሰማሩበት ሥርዓት ነበር፡፡ ይህ ሥቃይና ግፍ ግን ቀስ በቀስ ፓን አፍሪካዊ ማንነትን የሚያሳድጉ ባህሎችን እንዲፈጥሩ አደረጋቸው፡፡ እነዚህ በባርነት የተጋዙ አፍሪካዊያን ጥቁር አፍሪካዊ ማንነታቸውን የሚያጎሉ ማንነቶችን ፈጥረዋል፡፡ የጃዝ ሙዚቃ፣ የብሉዝ ሙዚቃ፣ የወንጌል (Gospel Tradition) ባህል ፈጥረዋል፡፡ የራሳቸውን አብያተ ክርስቲያን ሲመሠርቱና ሃይማኖታዊ ማንነት ሲገነቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› የሚለውን የመሳሰሉ ወደ 60 ጥቅሶች ወስደው ነበር ራሳቸውን ያነቁት፡፡ በዚህ መንገድ ነው ነፃነታቸውንና ሰብዓዊ ክብራቸውን ለማስከበር ሲንቀሳቀሱ የኖሩት፡፡

የማንነት ግንባታ ሒደት አልፎ የተመሠረተውን የአፍሪካ አንድነት ኅብረት/ድርጅት ደግሞ በእኛ አዲስ አበባ መቀመጫውን አድርጓል፡፡ ይህን መጠቀምም ሆነ የእኛ ማድረግ ላይ ግን ብዙ ይቀረናል፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ሥራ መሥራት አለብን ብለን ነው እኛ የአፍሪካ ዴይ ኢኒሼቲቭ ሐሳብን ይዘን የመጣነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረትን ፋይዳ ትልቅ የምናደርገው እኛው ራሳችን ነን፡፡ ኒውዮርክ የተመድ መቀመጫ በመሆኗ ብዙ ጥቅም እንድታገኝ ያደረጉት ራሳቸው የኒውዮርክ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያንም የአፍሪካ ኅብረት ከሚያመጣው በረከት ለመጠቀም መሥራት አለብን፡፡ አፍሪካዊነታችንን መቀበል ብቻ ሳይሆን በተግባር አፍሪካዊ ሆነን መታየት አለብን፡፡ የአፍሪካ አኅጉር እጅግ በርካታ ሀብት የሞላበት ነው፡፡ ዴሞክራቲክ ኮንጎን ብቻ ብናየው ወደ 24 ትሪሊዮን ዶላር የማዕድን ሀብት ያለው አገር ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካን ብትወስድ ያላት ወርቅ አሁን በምታመርትበት ሁኔታ እየተመረተ ለ150 ዓመታት ሳያልቅ ሊቆይ ይችላል፡፡ እኛ ያለን የእርሻ መሬት ደግሞ ለራሳችን በቂ ስንዴ አምርቶ አፍሪካን ሊቀልብ ይችላል፡፡ እነዚህ ሥራዎች ሊከናወኑ የሚችሉት ደግሞ ራስን ከፍ በማድረግ ነው፡፡ ታሪካችንና አስተሳሰባችን የተያያዘ ነው፡፡ የተዛባ የታሪክ አረዳድ ይዞ ምዕራባዊያን በነገሩን መሠረት መሄድ አያሳድግም፡፡ ራስን ማክበር፣ ራስን መረዳት፣ አፍሪካዊነታችንን መገንዘብና ማንነታችንን ማክበር ያስፈልጋል፡፡ ለራስ ክብር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ዓይነት አረዳድ የሚመጣ ለውጥ ነው አፍሪካን ሊያሳድግ የሚችለው፡፡ አሁን ባለው መንገድ የውጭ ዕርዳታ ለጋሾች ጥገኛ በመሆንና በብድር ታስረን ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን በአፍሪካ ሊመጣ አይችልም፡፡    

ሪፖርተር፡- እንደ ዓድዋ ያሉ ታላቅ የጥቁር ሕዝቦች ገድሎች ሲከበሩ የአፍሪካ ኅብረትን መመሥረቻ ቀን ለማክበር ቅድሚያ መስጠቱ ትርጉም ያለው ነው?

አየለ (ፕሮፌሰር)፡- የዓድዋ ድል ብሔራዊ በዓል ነው፡፡ አላከበርነውም ማለት ትክክል አይመስለኝም፡፡ ዘንድሮ ትንሽ ውዝግብ ቢኖረውም መንግሥት በመከላከያ ሠራዊት ታጅቦ በጀትና በሔሊፕብተር ትርዒት ጭምር በብሔራዊ ደረጃ ሲከበር ዓይተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ዓድዋን ጨርሶ አልተከበረም ሳይሆን ትልቅ ዓለም አቀፍ ክብርና ዝና ያተረፈ የታሪክ አጋጣሚ ነውና በሚገባው ልክ ለምን አይከበርም ለማለት ነው፡፡ የተለያዩ አገሮች ትንሹን የታሪክ አጋጣሚ ወይም አፈ ታሪኮቻቸውን ጭምር በዓለም ከፍ ብለው እንዲታዩ ያደርጋሉ፡፡ የውጭ አገሮች ተረቶች ሳይቀሩ ትልልቅ የሆሊውድ ፊልም ግብዓት ሲሆኑ ይታያል፡፡ በኢትዮጵያ ዓለም በተጨባጭ የሚያውቀው አስደናቂ የዓድዋ ታሪክ እያለ ከዚህ በላይ መጠቀም ያልተቻለው ለምንድነው?

አየለ (ፕሮፌሰር)፡- ትክክል ነው ዓድዋ ትልቅ ነው፡፡ ነገር ግን ለሁሉም ነገር መሠረትና ማጣቀሻ መሆን ያለበት ታሪክ ነው፡፡ ላለፉት 35/40 ዓመታት የነበረውን የታሪክ ሒደት እንመርምረው፡፡ ታሪክ የተደረገውን ነገር መመርመር ነው፡፡ የተደረገ ነገርን ደግሞ አትቀይረውም፡፡ ለረዥም ጊዜ ያሳለፍነው ከዋናው ዓላማ ዓድዋን ማክበር በተቃራኒ አቅጣጫ የሚያስት፣ እጅግ አላስፈላጊና አታካች ሙግቶች ውስጥ ስንዳክር ነው የቆየነው፡፡ ያ ደግሞ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ዓድዋን ስናከብር ለምንድነው የምንወዛገበው? መንግሥት በራሱ መንገድ ያከብረዋል፣ ሕዝቡም በራሱ መንገድ ያከብረዋል፡፡ ሕዝቡ አራዳ ጊዮርጊስ ምኒልክ አደባባይ ላይ ነው የማከብረው ካለ ለምን እንዲያከብር አንፈቅድለትም? በዚህ መንገድ ውዝግብ መፍጠሩ የክብረ በዓሉን ትኩረት የሚያስቀይር ነው፡፡ የዓድዋ ድል የተመዘገበው በመላው ኢትዮጵያዊያን መስዋዕትነት ነው፡፡ በዘመቻው ብዙ ጀግና ጄኔራሎች ነበሩ፡፡ በጊዜው የጄኔራሎቹ ጄኔራል ደግሞ አፄ ምኒልክ ናቸው፡፡ አፄ ምኒልክ ያን ጦር መርተው ታላቁ የዓድዋ ድል መመዝገቡ የማይቀየር የታሪክ ሀቅ ነው፡፡ አንድ ንጉሥ አገር ሲያስተዳድር የሠራውን ክፉም ሆነ ደግ ነገር ነቅሶ ማስቀመጥ ትክክል ነው፡፡ ሆኖም ዓድዋን በሚመለከት ንጉሡ ሳይነሳ ይከበር ስትል ግን ስተሃል ማለት ነው፡፡ ድሉ ምን እንደሆነም ሆነ ያመጣውን ትሩፋት አልተረዳህም ማለት ነው፡፡ እዚያ ውጊያ ላይ ሕይወታቸውን የሰጡት እኮ ለእኛ ሲሉ ነው የሞቱት፡፡ እዚያ ቦታ የተቀበረውን አፅም አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ወዘተ ብለህ አትለየውም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ናቸው ለኢትዮጵያዊነት ሲሉ ክቡር ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገዋል፡፡ የዚያን ፀጋ ትልቅነት ብዙዎች ዘንግተውታል፡፡ ረብ የለሽ ጥቃቅን ሙግት ይዘው እየመጡ በማዳከም ትልቁ ዓላማን በተመለከተ ሥራ እንዳይሠራ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ አሁን ያለውን የሰላም ሁኔታ ስታይ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መግባት ነበረብን? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ላይ ለመድረስ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ማለቅ አለበት? ይህ ሁሉ ታሪካችንን የምናከብርበት መንገድ በተሳሳተ አቅጣጫ መሆኑን ያሳያል፡፡ ታሪክ ያስተምራል፣ ወደፊት እንድትገሰግስ ያደርጋል እንጂ ወደኋላ ተመልሰህ ምኒልክ ጡት ቆርጧልና እኔም ካልቆረጥኩ እንድትል የሚያደርግ አይደለም፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ይህ ነው ትልቁ ችግር፡፡ ዓድዋ ትልቅ የታሪክ አጋጣሚ ነው፡፡ ብዙ ፊልም መሥራት፣ ብዙ መጻፍ፣ ብዙ መዝፈን፣ ብዙ መከበር አለበት፡፡ እንደ ፊታውራሪ ገበየሁ ያሉ ሰዎችን በምትወስድበት ጊዜ ለምሳሌ የወገን ጦር ሊበተንና ሊያፈገፍግ ባለበት ወቅት እኮ ነው፣ ነጥረው ወጥተው ቀድመው ገብተው ግንባራቸውን ተመተው የሞቱት፡፡ የእዚህ የጦር ሥልት አዋቂ ጀግና ታሪክ ለብቻው ብዙ መጻፍና ብዙ መነገር የሚችል ነው፡፡ ነገር ግን ሴራና ሁሉንም ነገር ፖለቲካ የማድረግ ዝንባሌ ነው ወደኋላ እየጎተተን ያለው፡፡ እኔ በግሌ ዓድዋን በልዩነት የማየውና ብዙ የምጽፍለት ታሪክ ነው፡፡ ታሪኩ ደግሞ የሁሉም ነው፡፡ የሁሉም ሕዝብ፣ የወንዱ ብቻ ሳይሆን የሴቱ፣ የእግረኛውና መድፈኛው ብቻ ሳይሆን የፈረሰኛው በአጠቃላይ በሁሉም ወገን የተመዘገበ ድል ነው፡፡ ዓድዋን የመሰለ ታሪክ በትንንሽ ጠብ ጫሪ ሙግት ባናበላሸው ደስ ይላል፡፡ የሕዝብ በበዓል እንዲሆን ማድረግና አከባበሩንም ክፍት ማድረግ የተሻለ ነው፡፡ ስለዓድዋ አሜሪካ ታሪክ አስተምር ነበር፡፡ የፈረንጆቹ ልጆች እንኳን ደስ ብሏቸው የሚማሩትና ጥናትም ካልሠራንበት የሚሉት ጉዳይ መሆኑን ታዝቤያለሁ፡፡ 

ሪፖርተር፡- የዓድዋ ድል በተመዘገበበት ቦታ የፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ የመመሥረት፣ በአካባቢው ልዩ ምልክቶችን የማኖር ሥራና የሙዚየም ግንባታ ለማካሄድ ጥረት ቢጀመርም የት እንደደረሰ አይታወቅም፡፡ የአሁኑ የአፍሪካ ዴይ ኢኒሼቲቭስ ዘላቂነት ያለው ነው?

አየለ (ፕሮፌሰር)፡- የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ምሥረታ ፕሮጀክት ውስጥ እኔም ነበርኩበትና ብዙ ጥረት ተደርጎ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ አስቆመው እንጂ ነገሩ መስመር ይዞ ብዙ ርቀት ሄዶ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አሁን ነገርን አዳምጦና አላምጦ አይደለም የሚኬደው እንጂ፣ ብዙ ሥራ ተሠርቶ የፖለቲካ ሁኔታው አመቺ ባለመሆኑ ነበር የቆመው፡፡ የዓድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ ከመላው አፍሪካና ከመላው ዓለም ተማሪዎች መጥተው ስለፓን አፍሪካኒዝም እንዲማሩ፣ ስለአፍሪካ ባህል፣ ቴክኖሎጂና ዕውቀት፣ ታሪክና ማንነት እንዲማሩ ማድረግ ነበር፡፡ አፍሪካን የሚያሳድግ ዕውቀት የሚፈልቅበት የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ነበር የታሰበው፡፡ አሁን በዓለማችን ያለው አውሮፓዊያን ያመረቱት ቅኝ ገዢያዊ ዕውቀት (ኮሎኒያል ኖውሌጅ) ነው፡፡ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የፈጠሩት ነው፡፡ በራስህ ዳታ ሰብስበህና አገናዝበህ አዲስ አፍሪካዊ ዕውቀት እንድታፈልቅ የሚያስችል ማዕከል መገንባት ነበር ሐሳቡ፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ዕቅድ ቀርቦ ተቀባይነት አግኝቶ በክልሉ መንግሥት ጭምር ወደ 250 ሔክታር መሬት የዓድዋ ድል በተመዘገበበት ቦታ ላይ ተሰጥቶት ብዙ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የፖለቲካው አለመረጋጋት በዋናነት በፈጠረው ተፅዕኖ ፕሮጀክቱ ለጊዜው ተስተጓጉሎ ቆይቷል፡፡ ነገሩ መሬት ላይ ያረፈ በመሆኑ በዚሁ ይቆማል ብሎ መገመት አይቻልም፡፡ ነገሮች ሲስተካከሉና ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ ሲፈጠር፣ እንዲሁም ሁሉንም ነገር ፖለቲካዊ የማድረግ ዝንባሌያችን ሲቆም ፕሮጀክቱ ይቀጥላል፣ የታሰበውንም ዓላማ ያሳካል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያዊያን ስለአፍሪካ የምር ተቆርቋሪና ተሟጋች መሆናቸው እየታወቀ፣ ራሳቸውን ከሌሎች ጥቁር አፍሪካዊያን የመነጠል ዝንባሌ ይታይባቸዋል ስለሚባለው ምን ይላሉ?

አየለ (ፕሮፌሰር)፡- ይህን ዓይነት የተንሸዋረረ ዕይታ የተፈጠረብን ባለው የትምህርት ሁኔታ ነው፡፡ የምንማረው አውሮፓዊ አተያይ ባለው የትምህርት ሥርዓት ነው እንጂ በራሳችን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ጥናት (ኢትዮጵያን ስተዲስ) ሲባል ብዙ ጊዜ ሴማዊ (ሴሜቲክ) ጥናት ነው፡፡ አውሮፓዊያኑ የኢትዮጵያ ታሪክ የሰሜኑ ኢትዮጵያ ታሪክ ነው፣ በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ሥልጣኔ የሚባል አልነበረም ብለው ቀምረው ከፋፋይ የሆነ ትምህርት ይሰጡናል፡፡ ከዚያ በላይ ደግሞ አፍሪካዊያን በቅኝ ግዛት ቀንበር ወድቀው የኖሩና በባርነት የተገዙ እንጂ ምንም ታሪክ የሌላቸው ናቸው የሚል ሐሳብ ይሰጡናል፡፡ ፈረንጆቹ በሚሉት መንገድ እኛም የተዛባ የታሪክ አረዳድ እንይዛለን፡፡ ይህ ነው ከሌሎች የአፍሪካ ወንድምና እህቶቻችን ጋር በጋራ እንዳንቆም የሚፈታተነን፡፡

አስቂኙ ትራጀዲ ያለው ግን ፈረንጆቹ ደንቆሮ የሚሉትን አፍሪካ በሀብት የሚበልጥ አንዳችም አኅጉር አለመኖሩ ነው፡፡ አኅጉሩ በግዝፈት ከዓለም ሁለተኛ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 2,000 ዓይነት ቋንቋዎች የሚናገሩ ወደ 1.4 ቢሊዮን ሕዝቦች በአፍሪካ ይኖራሉ፡፡ አውሮፓውያን ሀብቱን ለመበዝበዝ ስለሚፈልጉ ደንቆሮና ታሪክ የለውም የሚሉትን የአፍሪካ አኅጉር ለመዝረፍ ሲያሰፈስፉ ኖረዋል፡፡ አፍሪካን ለመበዝበዝ ሲሉ ደግሞ የአኅጉሩን ሕዝብ የቋንቋ፣ ባህልና ማንነት ልዩነት እርስ በርስ ለማጋጨትና ጥላቻ ለመዝራት በደንብ ይጠቀሙበታል፡፡ ይሁን እንጂ የአፍሪካ ሥልጣኔም ሆነ ታሪክ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረና ሁሉንም አፍሪካዊ በጋራ የሚያኮራ ነው፡፡ የዛሬይቱ ግብፅ አፍሪካዊት አይደለችም ሊባል ቢችልም የጥንቱ የግብፅ ማንነት ግን ፍፁም አፍሪካዊ መሠረት ያለው ነው፡፡ የጥንት ግብፆች ሙሉ ለሙሉ አፍሪካዊ ሥልጣኔን የመሠረቱ፣ ከእኛ ከኢትዮጵያዊያን ጋርም ዓባይን ተከትሎ የሚጓዝ ግንኙነት የነበራቸውና አፍሪካዊ ሥልጣኔ የገነቡ ነበሩ፡፡ በምዕራብ ሱዳን የበቀለ ሥልጣኔም ነበር፡፡ በመካከለኛው ዘመን ደግሞ በብዙ የአፍሪካ ክፍሎች የበቀሉ ሥልጣኔዎች ነበሩ፡፡ ይህንን ሁሉ የጋራ ታሪክ መሠረት በማድረግ አፍሪካ ወደ አንድነት ብትመጣ፣ አፍሪካ ያላትን ሀብት በመጠቀም ከአውሮፓም ሆነ ከሌሎች ጋር የሚወዳደር ኢኮኖሚ ልትፈጥር የምትችልበት ዕድል ይፈጠራል የሚል ሥጋት ነው ምዕራባዊያኑ ያለባቸው፡፡ የፓንአፍሪካዊ ስሜት መፈጠሩም ሆነ አንድነት መመሥረቱ ብቻ ሳይሆን፣ አፍሪካ የራሷን ትልቅ የወደፊት ትልም ፈጥራ በጋራ ለመበልፀግ ትችላለች የሚለው ዕሳቤ ነው የሚያስፈራቸው፡፡

አፍሪካ ዴይ ኢኒሼቲቭን ስናቋቁም ይህን ኋላቀር አተያይ የመቀየር ሐሳብ ተይዞ ነው፡፡ ከአፍሪካዊያን ጋርም ቢሆን ራስን ሙሉ ለሙሉ በመለጠፍ ወይም በመነጠል ሳይሆን፣ የሰመረ ግንኙነት መፍጠርን ታሳቢ በማድረግ ነው የተመሠረተው፡፡ እነሱ የእኛን ታሪክ አጥንተው የአፍሪካ ኅብረት በመዲናችን እንዲመሠረት እንዳደረጉት ሁሉ፣ እኛም የተለየ ነገር በመፍጠር እነሱ የበለጠ እንዲደነቁብን የመሪነት ሚና መጫወት አለብን ብለን እናምናለን፡፡ የሆነ ኮሽታና ችግር በተፈጠረ ቁጥር እንደ ጋዳፊና ኢዲ አሚን ያሉ መሪዎች የአፍሪካ ኅብረት ከኢትዮጵያ መነጠቅ አለበት ሲሉ ቆይተዋል፡፡ ወደፊትም ቢሆን ይህን መሰል ሙግት ማስቀረት ያለብን አፍሪካን የበለጠ በማቀፍ ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በመኖሩ እንጠቀማለን፡፡ አካባቢያችንን ተመልከተው፡፡ ሱዳንን፣ ሶማሊያን፣ የእኛ የራሳችንን ሦስትና አራት ዓመታት ሁኔታ ተመልከት፡፡ ጦርነት አውዳሚ ነው፣ ሕዝብን ያንገላታል፣ ያጠፋል፡፡ በዚያ ሁኔታ ውስጥ የምንቆየው እስከ መቼ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አውሮፓ ወይ አሜሪካ ውስጥ እንሰማለን ወይ? አንሰማም፡፡ ይህን መሰል ሁኔታ የምናቆመው አንድነት በመፍጠር ብቻ ሳይሆን አንድነቱ ለኢኮኖሚ፣ ለማኅበራዊ፣ ለፖለቲካዊና ለሁለንተናዊ ዕድገታችን አስፈላጊ ነው ብለን አምነንበት ስንሠራ ነው፡፡ አፍሪካ ዴይ ኢኒሼቲቭ የአጭር ጊዜ ዓላማው የአፍሪካ ኅብረት የተመሠረተበትን 60ኛ ዓመት በበዓል በድምቀት ማክበር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሒደት ኢኒሼቲቩን ወስደው ማክበሩን እንዲለማመዱት ጅማሮ መፍጠር ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ መሆናችን ተመድ ለኒውዮርክ እንደሆነው ሁሉ ትልቅ ፀጋ በመሆኑ ይህን ዕድል ለቱሪዝም፣ ለንግድ፣ ለባህል ልውውጥና ለዲፕሎማሲ እንዴት የበለጠ እንጠቀምበት የሚል ሐሳብ ማመንጨት ነው የኢኒሼቲቩ ሌላው ዓላማ፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ ጉዳዮች የሚነሱባት ከተማ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ አገሮች ባህልና ማንነት የሚንፀባረቅባት ታላቅ ከተማ እንድትሆን ማድረግ ነው፡፡ የአፍሪካ ኅበረት የተመሠረተበት ቀን ትልቅ ብሔራዊና አኅጉራዊ ክብረ በበዓል እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡     

ሪፖርተር፡- ስለ ‹‹ሀይብሪድ ዋር›› ብዙ ጊዜ እርስዎ ያነሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ምዕራባዊያኑ ያሳደሩት ተጨባጭ ጫና ስላለ ነው ወይስ ነገሩ የመሪዎቻችን የፍራቻ ፖለቲካ ፈጠራ ብቻ ነው? ምዕራባዊያኑ በኢትዮጵያ ላይ በተጨባጭ ጥቃት የከፈቱበት ሁኔታ አለ? ወይስ ፖለቲከኞች በሕዝብ ውስጥ ለመደበቅ የሚያደርጉት ሐሳባዊ ነገር ነው?

አየለ (ፕሮፌሰር)፡- በውስጥ ጦርነት ኖሮ በውጭ ኃይሎች ሲደገፍ ነው ሀይብሪድ ዋር (ቅይጥ ጦርነት) የሚከሰተው፡፡ በመሠረታዊነት ያለፉትን ሁለትና ሦስት ዓመታት ስታይ ምዕራባዊያኑ በተጨባጭ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድሩ ነበር፡፡ በጦርነቱ ወቅት በመካከሉ እኔ ወደ አሜሪካ ሄጄ ነበርና ያየሁት ነገርም ይህንን የሚደግፍ ነው፡፡ እዚያ ያሉትን ጋዜጦች በየቀኑ እመለከት ነበር፡፡ እጅግ የተቀናጀና ሥልታዊ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ መካሄዱን ዓይቻለሁ፡፡ እጅግ የተከበረ የሚባለው ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በየቀኑ ስለኢትዮጵያ ዘገባ ያወጣ ነበር፡፡ የሚያወጣው እያንዳንዱ ዘገባ ደግሞ ሥልታዊ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያን የሚያጠቃ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ሊቆይ አይገባም የሚልና መንግሥት መፍረስ እንዳለበት የሚሰብክ አቋም ነበር የሚያራምደው፡፡ ሌሎች ሚዲያዎችም ተመሳሳይ ነበር አዘጋገባቸው፡፡ ሲኤንኤን ዘጋቢ መድቦ ነበር የተዛባ ዘገባ ይሠራ የነበረው፡፡ ሚዲያዎቹ አንዱን ደግፈው ሌላውን በማውገዝ ይሠሩ ነበር፡፡ መንግሥትን የሚወጋው ኃይል ሥልጣን መያዝ አለበት ብለው የሚሰብኩ ነበሩ፡፡ በጊዜው ጦርነቱ የእኛ የእርስ በርስ መሆኑ ቀርቶ የውጭ ኃይሎች የተነከሩበት ሆኖ ነበር፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ሥልጣን በያዘ ወር ሳይሞላው ነበር እኮ ስለወልቃይት ማውራት የጀመረው፡፡ እኛ ስለዴላወር ስናወራ አስበው እስቲ፡፡ በዴላወር የሚኖሩ ጥቁሮች ተጨቁነዋል ብለን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይ በሌላ የሥልጣን አካል ነፃነት ያግኙ የሚል መግለጫ ስንሰጥ ማሰብ ይቻላል? በጊዜው መንግሥታቶቻቸው ስፖንሰር እያደረጉት በሚመስል መንገድ እጅግ ኃይለኛ ጫና በኢትዮጵያ ላይ ይደረግ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥትን ለመለወጥ፣ አገሪቱንም ለመከፋፈል ይሠራ ነበር፡፡ ራሱን በራሱ መቻል ያቃተው ሦስትና አራት አገር በኢትዮጵያ ለመፍጠር እስከመፈለግ ነበር ሴራው የሚካሄደው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተዋይ፣ ረጋ ያለና ታሪኩን የሚያውቅ በመሆኑ ሊበታተን አልቻለም፡፡ እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች አንድነታችንን ለመጠበቅ የረዱን ናቸው፡፡ እጅግ ከጠበበውና ብሔርን ማዕከል ካደረገው የፖለቲካ ዝንባሌያችን የምንወጣውም ሆነ እንደ አገር ጠንካራ አንድነትን መፍጠር ምንችለው፣ በእኔ እምነት እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ የአንድነት አሻራ ያረፈባቸውን ብዙ ፕሮጀክቶች ስንሠራ ነው፡፡ እኛ አሁን የጀመርነውን ፓንአፍሪካዊ ማንነትን የበለጠ የሚያጎላው አፍሪካ ዴይ ኢኒሼቲቭም ለዚህ አንድ አጋዥ መሆን ይችላል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- አፍሪካ ዴይ ኢኒሼቲቭ ምን ዓይነት መርሐ ግብሮችን ይዞ ነው ዘንድሮ የሚካሄደው?

አየለ (ፕሮፌሰር)፡- በቂ ድጋፍ ልናገኝ ባለመቻላችን ልናካሂድ ያሰብነውን የኮንሰርት ዝግጅት ለመሰረዝ ተገደናል፡፡ ፓናል ውይይት ይኖረናል፡፡ ልጆች የሚሳተፉበት ቀን ይኖረናል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት ባለው መናፈሻ የሚደረግ የመታሰቢያ ዝግጅት አለን፡፡ ወደ 60 አርቲስቶች የሚካፈሉበት የአርት ሾው ይኖረናል፡፡ ሐሳቡን በተለይ የፕሬዚዳንቷ ቢሮና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደንብ ደግፈውታል፡፡ በቅርቡ ደግሞ መንግሥትም ከጎናችን ሆኖ ለማክበር ሐሳቡ እንዳለው በቃል ያሳወቁን የሥራ ኃላፊዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ቢሮክራሲው ቀልጣፋ ባለመሆኑና በቃል የተነገረው በተግባር አለመተርጎሙ ትንሽ ጎትቶናል፡፡ ብዙ የጠበቅናቸው አንዳንዶች የሐሳቡን ግዝፈት ባለመረዳት ይመስላል ከጠበቅነው በታች ነው ምላሽ የሰጡን፡፡ በዚህ ዓመት ሕዝቡም ሆነ ተቋማት ብዙም ላይረዱን ቢችሉ ችግር የለውም፡፡ ዋናው ሥራው መጀመሩ ነውና በቀጣይ ዓመታት ትልቅ ድጋፍ ይመጣል፣ እየተጠናከረም ይሄዳል ብለን ነው የምንጠብቀው፡፡   

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...