Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቱሪዝም ዘርፍ አፈጻጸምና ለዘርፉ አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ ለመፍጠር የታቀደው ‹‹ቱሪዝም ፈንድ››

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት የአገር ኢኮኖሚን ያሳድጋሉ ብሎ ከለያቸው ዘርፎች ማኑፋክቸሪንግ፣ የማዕድን፣ ቴክኖሎጂና የቱሪዝም ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ 

የቱሪዝም ሴክተር ኢትዮጵያ በኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜ መቀዛቀዙ የሚታወስ ሲሆን፣ የሰሜን ጦርነትም በዘርፍ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪና ፋይናንስ ዝቅ እንዲል በማድረጉ ዘርፉን በእጅጉ ጎድቶታል፡፡ 

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሚጠበቅበትን ለማምጣት የአሥር ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ 

ሦስተኛ ዓመቱን የያዘው የዘርፍ ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑንና፣ የዘርፉን ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች ባገናዘበ መንገድ በ2013 ዓ.ም. ሥራዎችን መጀመሩን ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገናኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ 

ዕቅዱ የኮሮና ወረርሽኝና ሌሎች አገራዊ ሁኔታዎች ታሳቢ ያደረገ ሲሆን በስድስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉን ከዘጠኝ ወራት ሪፖርት ተደርጓል፡፡ 

በተያዘው በጀት ዓመቱ ሚኒስትሩ በዕቅድ የያዛቸው የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ከጠቅላላው በጀቱ 75 በመቶን ጥቅም ላይ አውሏል፡፡ 

ሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቱሪዝም ሚኒስቴርን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅዱ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቧል፡፡ 

ሪፖርቱን ያቀረቡት በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም መዳረሻና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ናቸው፡፡ ባለፉት ጊዜያት ከተከናወኑት ተግባራት አንዱ ከተለያዩ የዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በመሥራት በኩል ውጤቱ ጥሩ መሆኑን በሪፖርቱ ተቀምጧል፡፡ 

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት እንደ አገር የሚስተዋለውን የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፎች ክፍተት ለማጣጣም ከቱሪዝም አኳያ ተሠርቶ ተጠናቋል፡፡ ይህም ፖሊሲ ቱሪዝም ከሌሎች ሴክተሮች ጋር የማስተሳሰር ተግባር ሙሉ በሙሉ መከናወኑን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ 

ሌላኛው ለቋሚ ኮሚቴው የቀረበው ሪፖርት ከተሠሩ የዘጠኝ ወራት ተግባራት መካከል የአገር ውስጥ ጉብኝት ማሳደግ ላይ የተሠራው ሥራ ይመለከታል፡፡ የአገር ውስጥ ቱሪዝም በተለይም ኮሮና ወረርሽኝ ያነቃቃው ዘርፍ እንደሆነ ተጠቅሶ፣ በኢትዮጵያ በእጅጉ እየተነቃቃ ያለና ገቢ እያስገኘ ያለ መሆኑን ተገልጿል፡፡ 

በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ከአገር ውስጥ ጉብኝትን 29.8 ሚሊዮን ጎብኚዎችን ለመሳብ መታቀዱን፣ በዚህም ከታቀደው በላይ ወይም 30.9 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ቱሪስቶችን መሳብ መቻሉን ሪፖርቱ ተመላቷል፡፡ 

በዚሁ ዘርፍ የአገር ውስጥ ቱሪስቶችን ከቦታ ወደ ቦታ ከማስጎብኘትና አገራቸው ታሪክ፣ ባህልና ከማሳወቅ በዘለለ ለአገር ኢኮኖሚ የሚሰጠው አስተዋጽኦ ትንሽ የሚባል አይደለም ተብሏል፡፡ 

በዘጠኝ ወራት ብቻ ከአገር ውስጥ ቱሪዝም 47.7 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ አፈጻጸሙ 52.9 ቢሊዮን ብር መሆኑን ተገልጿል፡፡ 

የግሉ ዘርፍ የሚሠሩ ኢንቨስትመንት ሌላኛው የቱሪዝም ዕድገትን በማሳለጥ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ በዚህም በዘጠኝ ወራት ውስጥ 230 ባለሀብቶችን ወደ ዘርፍ እንዲገቡ ለማድረግ ታቅዶ፣ በዚያ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዘርፎች 187 ባለሀብቶች ሴክተሩ ተቀላቅለዋል፡፡ 

ከዚህ ውስጥ በተለይም የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኘው የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ መቻሉን የተገለጸ ሲሆን፣ በዕቅድ ደረጃ 19 ባለሀብትን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት መታለሙን ተጠቁሟል፡፡ 

ከታቀደው የውጭ ባለሀብት በቱሪዝም የማሰማራት ዕቅድ 14 ባለሀብትን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት መቻሉንና ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ኮሮና ቫይረስ፣ በአገር ውስጥ የነበረው ሁኔታ ቱሪዝም ሴክተር ላይ ያመጣውን ተፅዕኖ ችሎ ማገገሙን አስረድተዋል፡፡ 

የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱና የተመዘገቡ ባለሀብቶች ለማሳደግና ወደ 249 ለማድረስ የታቀደ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 201 የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተመዝግበዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ በበጀት ዓመቱ ዝግጅት አጠናቀው አገልግሎት ለማስጀመር የታቀደው 35 ቢሆንም፣ 48 የሚደርሱት ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ 

በዕቅዱ ከተካተቱት ሥራዎች አንዱ ለቱሪዝም ዘርፍ አማራጭ ማስፋት መሆኑን በመጠቆም፣ ‹‹የቱሪዝም ፈንድ›› አስፈላጊ በመሆኑ የሚበጀተው በጀት በቂ አለመሆን ተገልጿል፡፡ በዚህ መሠረት ቱሪዝም ዘርፍ ከሚፈልገው በጀት ከአንድ አራተኛ አልያም አንድ ስድስተኛ በመሆኑ፣ ቀሪውን ለመሙላት ‹‹በቱሪዝም ፈንድ›› ማቋቋም ግድ ማለቱን ጠቁመዋል፡፡ 

ሚኒስቴሩ ከገንዘብ ሚኒስቴር የሚያገኘው ዓመታዊ በጀት ሥራዎቹን ለመከወን ከሚፈልገው አኳያ በቂ አለመሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ደኤታው፣ ለዘርፉ በቂ ሀብት ለማፈላለግ አማራጭ የፋይናንስ ምንጮች ላይ እያማተረ መሆን ገልጸዋል። የቱሪዝም ሚኒስቴር በማቋቋሚያ አዋጁ ከተሰጡት ሥልጣኖች አንዱ የቱሪዝም ፈንድ ማቋቋምና ማስተዳደር መሆኑን በመጠቆምም፣ አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ ለመፍጠር የቱሪዝም ፈንድ ለማቋቋም መታሰቡን ገልጸዋል።

በተለያዩ የዓለም አገሮች የቱሪዝም ፈንድ ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን ከእነዚህ አገሮች መካከልም በጎረቤት አገር ኬንያ ያለውን ተሞክሮ ለአብነት አንስተዋል። በኬንያ በዓመት አንድ ቢሊዮን ብር ከቱሪዝም ፈንድ እንደሚሰበሰብ ገልጸው፣ ይህንን አሠራር ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት በዘርፉ ያለውን የፋይናንስ ጉድለት ለመሙላት መታቀዱን ሚኒስትር ደኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ጠቁመዋል። 

የሚኒስቴሩ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ሚኒስቴሩ የቱሪዝም ፈንድ ማቋቋም አንደሚችል የተደነገገ በመሆኑ ይህንን መሠረት በማድረግ የቱሪዝም ፈንድ ክፍል ተከፍቶ ባለሙያ መቀጠሩን ነገር ግን ገንዘብ መሰብሰብ እንዳልተጀመረ ተናግረዋል፡፡ 

ገንዘቡን ለመሰብበስ አስፈላጊ የሆኑ የፈንድ ምንጭ አማራጮችና በኢትዮጵያም የቱሪዝም ፈንድ እንዴት ሊሠራ እንደሚችል በዓለም ባንክ መጠናቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የቱሪዝም ፈንዱን ለማቋቋም የፕሮጀክት ንደፈ ሐሳብ ቀረጸ ተሠርቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ይህም በፈንዱ የሚሰበሰበው ሀብት ለምን አገልግሎት እንደሚውል የሚያስቀምጥ ሲሆን የዝግጅት ሥራው እንደተጠናቀቀ ፈንዱን ማስተዋወቅ አንደሚጀመር ተናግረዋል።

የቱሪዝም ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ ግኝትና የሥራ ዕድሎችን ማስፋት ሌላኛው ሲሆን፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 1.1 ማሊዮን ቱሪስት ለማስገባት ታቅዶ፣ 774,072 የውጭ ቱሪስት መግባታቸውንና አፈጻጸሙም 70.37 በመቶ መድረሱን ተጠቁሟል፡፡ 

እነዚህም በቱሪስት ቪዛ የገቡ ሲሆን፣ ለባዕላት፣ ለጉብኝት፣ ለኮንፈረንስ፣ ለኤግዚቢሽን የገቡ መሆናቸውን ተገልጿል፡፡ በዘጠኝ ወራት ከዘርፉ የሚገናኘው ቀጥተኛ የወጭ ምንዛሪ 3.18 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ፣ ከዘርፉ 3.06 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉንና አፈጻጸሙም 71 በመቶ ነው ተብሏል፡፡ 

በዚህ ዘርፍ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ሌላኛው ዕቅድ ሲሆን 90,000 የሥራ ዕድል ለማመቻቸት የታሰበ ሲሆን 69,473 ማሳካቱን፣ ቋሚ ሥራ ዕድል 24.316 እና ጊዜያዊ ደግሞ 45,457 የሥራ ዕድል በዘርፉ የተሰማሩ ናቸው ተብሏል፡፡ 

የሥራ ዕድል ለመፍጠር በቱሪዝም ዘርፍ ወቅቱ አስቸጋሪ መሆኑን፣ ከላይ የተጠቀሱት ኢንቨስትመንት መስፋፋትና ነባር ቢዝነሶች አገልግሎት መጀመራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ 

በቱሪዝም ንግድ ተሳታፊዎች ዘርፍ እንዲገቡ ለማድረግና እንዳይከስሙ የተሠራ ሲሆን፣ በዚህም አዳዲስ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡ 

የሥራ ዕድሎቹ የተፈጠሩት ተገንብተው የተጠናቀቁ ሆቴሎች፣ በአስጎብኚነት ዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶችና በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ናቸው፡፡  

የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ከ2014 በጀት ዓመት ይልቅ 2015 ዓመት የተሻለና ካለበት ከፍ ያለበት መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ 

ሌላው የተቀመጠው የቅርስ ጥገናና፣ ፓርኮችና ለሙዚየም ዙሪያ ሪፖርት የተቀመጠ ሲሆን፣ በቅርስ ጥገና የተሠሩ ሥራዎች አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ መሆኑ አመላክቷል፡፡ 

በዘጠኝ ወራት ሪፖርት ላይ ቱሪዝም ሚኒስቴር ሥራዎች በተሻለበት መንገድ እንዳይቀላጠፍ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን አስቀምጧል፡፡ 

ከእነዚህም ችግሮች መካከል በዘርፉ ካለው እምቅ አቅም ለአገር ኢኮኖሚ በተፈለገው ልክ አስተዋጽኦ እንዳያደርግ፣ የሀብት አቅርቦት ችግር እንደገጠመው ተገልጿል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ ቱሪስቶች በሚፈልጉት ልክ የቪዛ አሰጣጥ ላይ ትልቅ ክፍተት መኖሩ ትልቅ ችግር ፈጥሮብኛል ይላሉ፡፡ 

በተለይም በጉምሩክና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ጎብኚዎች ይዘዋቸው የሚመጡት ዘመናዊ ካሜራና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ለማስገባት ትልቅ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ 

የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርቱ በተመለከተ ዘርዘር ያሉ ሐሳቦች ሰጥተውበታል፡፡ ከዚህም ውስጥ በተለይም በጀት አጠቃቀም ላይ ያሉትን ክፍተቶች በተገቢው መንገድ መስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ 

በዓመቱ ካለው ካፒታል ወይም ከበጀቱ አፈጻጸሙ ሲታይ ጥቅም ላይ የዋለው 18 በመቶ ብቻ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴ አባል ገልጸው፣ በተቀሩት ወራቶች እንደ ሌሎች ሴክተሮች የበጀት መዝጊያ መሯሯጥ እንዳይፈጠር ሥጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ በተለይም የአገር ውስጥ ቱሪዝም ላይ ያለው ሀብት ሰፊ መሆኑን በመጠቆም፣ ለዘላቂነትና ትኩረት የሚሻ ዕምቅ ሀብት ያለበት ነው ተብሏል፡፡ 

በቱሪዝም ዘርፍ ኢትዮጵያ እጅግ ሀብታም መሆኗን በመግለጽ፣ ነገር ግን ከዘርፉ የሚገኘው ፋይናንስ ዝቅተኛነት ጠቅሰው፣ አሁንም ዘርፉ ላይ በትኩረትና በጥልቀት መሥራት እንደሚገባው አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች