Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ላይ ለውጥ ሲታሰብ አደጋውም መዘንጋት የለበትም!

የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት አሁንም መረጋጋት አይታይበትም፡፡ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች ዋጋ ያለማቋረጥ እየጨመሩ ነው፡፡ የሰብል ምርቶች ዋጋም ከመቼውም ጊዜ በላይ እየወጣ ነው፡፡ የመለዋወጫ ዕቃዎች የኢንዱስትሪ ግብዓቶችም በተመሳሳይ የተጋነነ ዋጋ እየወጣላቸው ቀጥለዋል፡፡ 

በሰዓታት ውስጥ ሳይቀር ዋጋቸው የሚጨምሩ ምርቶች ቁጥራቸው በዝቷል፡፡ በግብይት ውስጥ የሚታየው ይህ ከፍተኛ ተግዳሮ አሳሳቢ ሆኖ በመቀጠሉ ሳያንስ ‹‹የምንዛሪ ዋጋ ሊለወጥ ነው›› በሚል መሠረት ባልያዘ መረጃ  ገበያው የበለጠ እየተረባበሸ ነው፡፡ በዚህ በተሳሳተ መረጃ በርካቶች ዕቃ መሸሸግ መጀመራቸውና እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ የዋጋ ንረቱን እያባባሱት ስለመሆኑ በግልጽ እያየን ነው፡፡

አጋጣሚዎች በመጠቀም ያላግባብ ኪሳቸውን ለመሙላት የሚታትሩ አንዳንድ ነጋዴዎች እጃቸው ላይ ያለውን ዕቃ ፈጽሞ ያልተገባ የትርፍ ህዳግ በመያዝ ለመሸጥ የሚደረጉ ጥረቶች ንረቱን ከድጡ ወደ ማጡ እያደረጉት ነው፡፡ 

የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ከ100 ብር በላይ መሆኑን በመጥቀስም የምርትና ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ በዚሁ ሥሌት እየታሰበ የሚካሄደውን ግብይት መፍትሔ ሳያገኝ፣ ከሰሞኑ ባልተረጋገጠ ወሬ እየተፈጸመ ያለው ሸፍጥ ደግሞ ገበያውን እየበረዘ የዋጋ ጭማሪዎችንም እያስከተለ ነው፡፡ 

በእርግጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መኖሩ ግልጽ ቢሆንም፣ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የሚፈጸሙ ያልተገቡ ተግባራት ዕርምት የማይደረግባቸው ከሆነ ደግሞ ችግሩ ሕገወጥ ተግባራቱ እየሰፉ፣ በኋላም ለመቆጣጠር አዳጋች እንዳይሆን ያሠጋል፡፡

በሕጋዊው የውጭ ምንዛሪና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ እጥፍ በሚባል ደረጃ ልዩነት ማሳየቱ በራሱ ገበያ ውስጥ እየፈጠረ ያለው ችግር እየታወቀ ጉዳዩን በቸልታ ማለፉ ለምን? የሚል ጥያቄ ደጋግመን እንድናነሳ ያደርጋል፡፡ 

ሕገወጦች ‹‹የውጭ ምንዛሪ ተመን ከፍ ሊል ነው›› በሚል የሚያናፍሱት ወሬ እንዲጎላ፣ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ይኼው በሕጋዊና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው የውጭ ገንዘቦች የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ ነው፡፡  

ከልክ በላይ እየሆነ የመጣውን የዋጋ ንረት እንዲህ ባሉ ሕገወጥና ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የሚካሄዱ የዋጋ ጭማሪዎች ከማስከተሉም በላይ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚው ተጨማሪ ራስ ምታት መሆናቸው አይቀርም፡፡ የጥቁር ገበያ መድራትና በጥብቅ ቁጥጥር የማይደረግበት ሆኖ መገኘቱ ሌላም መዘዝ አለው፡፡ ይህም የኮንትሮባንድ ንግድ መጦፉን፣ ሕገወጥ ግብይቶች መበራከታቸውን ሁሉ ጠቋሚ በመሆኑ ነው፡፡

ስለዚህ በሰበብ አስባቡ የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎችን መቆጣጠሩ አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ የጥቁር ገበያ በገበያ ውስጥ መንሰራፋቱ የገበያ መርህን ከማዛባት በላይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ ከባድ ሊሆን እንደሚችል በማመን ጥንቃቄ የተሞላበት መፍትሔ ማስቀመጥ ይገባል፡፡ በዋናነት ግን የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ረሃብን የሚያስታግስ ጥናት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት የግድ እያለ ነው፡፡ በጥቁር ገበያውና በሕጋዊ የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ መካከል እየታየ ያለውን እጅግ ሰፊ ልዩነት ማጥበብ ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲዎችን በድጋሚ መፈተሽና ሕጋዊ አሠራር እንዲሰፍን ካልተደረገ በቀር አሁን እየታየ ባለው አካሄድ በእጅጉ የሚያሳስብ ነው፡፡ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ አለማበጀትና ለዕርምጃ መዘግየት በኋላ ላይ ጥቁር ገበያውን ከማስፋት በላይ ሕገወጥ የምንዛሪ ዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ከማያስችልበት ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል መታሰብ አለበት፡፡ 

ከጥቁር ገበያ ዶላር እየተገዛ የሚመጣ ምርት እስካለ ድረስ፣ በሕጋዊ መንገድ በተሰጠ የውጭ ምንዛሪ የሚመጣውንም ዕቃ በገበያ ዋጋ ለመሸጥ ፈጽሞ የማያስችል በመሆኑ ጉዳዩ ጊዜ የማይሰጠው ነው ሊባል ይችላል፡፡ 

በመሆኑም በተወነባበደ ወሬ ገበያው ሲበለሻሽ እያዩ ዝም ማለት፣ እንዲሁም ገበያው ጥቁር ገበያ የምንዛሪ ዋጋን እያሠሉ የሚካሄድ የግብይት ሒደት ዝም ከተባለ አደጋው የዋጋ ንረቱን ከማባባስ በላይ ይሆናል፡፡ ይህ ለመንግሥት የሚጠፋው ባይሆንም፣ መንግሥት ጊዜውን የዋጀ ዕርምጃ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ዕርምጃው ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲውን ማስተካከል ወይም የምንዛሪ ተመን ነፃ በማድረግ ሕገወጥ አሠራርን መቆጣጠር የሚችልበት ሁኔታ እስከ ከመፍጠር ሊደርስ ይችላል፡፡ 

በእርግጥ የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ እንዲወሰን ማድረጉ የራሱ ተፅዕኖ ሊኖረው ቢችልም ጥቁር ገበያን እያጣቀሰ የሚደረገው ግብይት ጡንቻ እያወጣ እንዲቀጥል ግን መሆን የለበትም፡፡ በዶላር እጥረት ሰበብና የጥቁር ገበያ የምንዛሪ ዋጋ እየገነነ መምጣት እያስከተለ ካለው ችግር አንፃር መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ተመንና ከዚህ ጋር የተያያዙ አሠራሮችን ሁሉ መስመር ያስይዝ ሲባልም አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶችም ይጠገኑ ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ዕርምጃው ዘላቂ የሆነ መፍትሔ እንዲያመጣና አጠቃላይ ኢኮኖሚ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን የዳሰሰ መሆን ይገባል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከሰሞኑ የተደረገው የነዳጅ ጭማሪና ሌሎች ሁነቶችንም ከዚሁ አግባብ ማየት ያስፈልጋል፡፡ አንድ ዕርምጃ ሲወሰድ ሊመጡ የሚችሉ ተግዳሮቶችንም በማሰብ ችግሮችን አባባሽ እንዳይሆን ጉዳዩን በጥልቀት ማሰብ ተገቢ ይሆናል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት