Wednesday, October 4, 2023

የሱዳን ጦርነትና የአማራ ክልል ግጭት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሱዳን በአፍሪካ ትልቅ አገር ናት፡፡ በአኅጉሩ በቆዳ ስፋት ሦስተኛ የሆነችው ሱዳን 46 ሚሊዮን ሕዝብም አላት፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሱዳን ከብዙ አገሮች ጋር የምትጎራበት የአኅጉሩ ዕምብርት የምትባል አገር ናት፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር 753 ኪሎ ሜትር ድንበር የምትጋራው ሱዳን በአፍሪካ ከሰባት አገሮች ጋር ትጎራበታለች፡፡ ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ፣ ከግብፅ፣ ከሊቢያ፣ ከቻድ፣ ከማዕከላዊ አፍሪካና ከደቡብ ሱዳን ጋር ድንበር ትዋሰናለች፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ሱዳን የቀይ ባህርን ተጎራብታ የምትገኝ ሰፊ የባህር ወሰንም ያላት አገር ናት፡፡

ሦስተኛ ሳምንቱን ያስቆጠረው የሱዳን ጦርነት ወደ ጎረቤት አገሮች ሊሸጋገር ይችላል የሚለው ሥጋት ያለ ምንም መነሻ የሚሰጥ ግምት አይደለም፡፡ ሱዳን ለባህርም ሆነ ለብዙ የአፍሪካ አገሮች ካላት ቅርበት አንፃር፣ በአገሪቱ የሚከሰት የፀጥታ ሥጋት የሌሎችም የደኅንነት ዋስትና ችግር ስለሚሆን ነው ይህ መላምት በተደጋጋሚ የሚነሳው፡፡ በሱዳን አሁን የተፈጠረው ጦርነት በዙሪያዋ ባሉ አገሮች ውስጥ ካሉ ግጭቶች ጋር የሚገጣጠምበት ዕድል ከተፈጠረ ደግሞ ይህን ሥጋት የበለጠ አስፈሪ ያደርገዋል ይባላል፡፡

በሱዳን ጦርነቱ እየተባባሰ ባለበት በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ደግሞ በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር እየተባባሰ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአማራ ክልል ደግሞ ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር በድንበር ከሚያገናኙ ክልሎች አንዱና ዋናው ነው፡፡ በክልሉ እየተፈጠረ ያለው የፀጥታ ችግር እየተባባሰ ከሄደና ከሱዳን ጦርነት ጋር የሚገጣጠምበት ዕድል ከተፈጠረ ደግሞ ሊፈጥር የሚችለው ቀጣናዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑን ነው ተንታኞች እየተናገሩ የሚገኘው፡፡

“What will the war in Sudan mean for Ethiopia?”  በሚል ርዕስ የቀረበው የአልጄዚራው ‹ኢንሳይድ ስቶሪ› ፕሮግራም የሱዳን ጦርነት የደቀነውን ቀጣናዊ ሥጋት በጥቂቱ ለማሳየት ይሞክራል፡፡ የጀምስ ማዲሰን ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰርና የፕሮግራሙ አንዱ ተጋባዥ የሆኑት ኢታና ዲንቃ፣ የሱዳን ጦርነት በአማራ ክልል የፀጥታ ችግር ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ በቀጥታ ሲያነሱት ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ኢመደበኛ አደረጃጀትና የታጠቁ የልዩ ኃይል ፖሊሶችን ትጥቅ ለማስፈታትና ወደ መደበኛ የፀጥታ ኃይል ለመቀላቀል ያደረገው ጥረት ውዝግብ መፍጠሩን ተንታኙ አውስተዋል፡፡

‹‹የተወሰኑትን ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ ማደራጀት ቢቻልም፣ ነገር ግን የተወሰኑት ትጥቅ አልፈቱም፡፡ እነዚህን ወገኖች ትጠቅ ለማስፈታት መንግሥት እየወሰደ ባለው የኃይል ዕርምጃ መነሻነት ደግሞ፣ በአማራ ክልል ከሰሞኑ ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ችግር አጋጥሟል፤›› በማለትም ተንታኙ ይናገራሉ፡፡

‹‹የፌደራል መንግሥቱ በአማራ ክልል ያለውን ችግር ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር የማይችል ከሆነና ግጭቱ እየተባባሰ ከሄደ ደግሞ፣ በሱዳን ካለው ቀውስ ጋር በመገጣጠም ድንበር ተሻጋሪ ችግር ሊፈጠር ይችላል፤›› ሲሉ ነው ኢታና ዲንቃ (ረዳት ፕሮፌሰር) ያስረዱት፡፡

ተንታኙ እንደሚሉት፣ የአማራ ክልል ታጣቂዎች እንዲሁም የሱዳን ጦርነት ተፋላሚዎችና ሌሎች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የትጥቅ ቡድኖች በሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን አዋሳኝ የድንበር ቀጣና እንደ ልብ የሚጠቀሙበት ዕድል ይሰፋል፡፡ በሁለቱ አገሮች ውስጥ ያለው የፀጥታ ችግር አንዱ በሌላኛው ላይ ተፅዕኖ አሳዳሪና ሊያያዝ የሚችልበት ዕድልም የሰፋ መሆኑን ነው ተንታኙ በሰፊው የዳሰሱት፡፡

የዓረብ የፖሊሲ ምርምር ማዕከል ባልደረባዋና ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ኅብረት፣ እንዲሁም በሱዳን ድንበር የተመድ ልዑክ ቃል አቀባይ ሆነው የሠሩት አይሻ አል ባስሪ ይህንኑ ግምት የበለጠ አጠናክረውታል፡፡

‹‹ሱዳን እጅግ ወሳኝ ጂአ ስትሪቴጂክ አቀማመጥ ያላት አገር ናት፡፡ በዙሪያዋ ያሉ አገሮች ሁሉ የሱዳንን ችግር በጥንቃቄ ለመከታተል የሚገደዱበት ብዙ ምክንያት አለ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ገና ያልተሰመረና የይገባኛል ውዝግብ የሚነሳበት ድንበር የምትጋራ አገር ናት፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አቋም በዚህ ዙሪያ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በጎረቤት ባለው የአማራ ክልል የታጠቁ ኃይሎችን ችግር የሚፈቱበት መንገድም ቢሆን በዚያው ልክ ወሳኝነት አለው፤›› በማለት ነው ተንታኙ ያብራሩት፡፡

ይህንኑ የሱዳን ጦርነት የጎረቤት አገሮችን ተጋላጭ ያደርጋል የሚል ግምት ራሳቸው የሱዳን ዜጎችም ቢሆን ሲጋሩት ይሰማል፡፡ ከሳምንት በፊት ከሪፖርተር ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆኑት የአፍሪካ ቀንድ ምሁር በሽር ናስር የሱዳን ጦርነት ወደ ጎረቤት አገሮች ሊጋባ ይችላል የሚል ሥጋት ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች በማንኛውም መንገድ ጦርነቱ እንዲያቆም ማድረግ አለባቸው፤›› በማለት ነው ያስረዱት፡፡

በተመሳሳይ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት የአፍሪካ ጉዳዮች ምሁሩ ሱዳናዊ ሉትዊ ቴቢን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹የሱዳን ጦርነት የሱዳኖች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ጦርነት ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ለሱዳን ቀውስ መስጠት አለባቸው፤›› በማለትም ነበር የተናገሩት፡፡

አሁን ያለውን የቀጣናውን ሥጋት በሁለት አቅጣጫ መነሻ እንዳለው በርካታ ተንታኞች እየተናገሩ ነው፡፡ በሱዳን ያለው ጦርነት እስከቀጠለ ኢትዮጵያን ጨምሮ የጎረቤት አገሮች በስደተኞች ፍሰት ከመጨናነቅ ባለፈ፣ የፀጥታ ሥጋት ይገጥማቸዋል የሚለውን በቀዳሚነት ያስጠነቅቃሉ፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የሰሜኑን ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ብትቋጭም፣ ሆኖም ወደሌላ ዙር ግጭት እንዳትገባ የሚል ፍራቻቸውንም ያክላሉ፡፡

በአልጄዚራ ኢንሳይድ ስቶሪ ላይ የቀረቡት ተንታኝ ኢታና ዲንቃ (ረዳት ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ችግሩን የበለጠ ያወሳስበዋል ያሉትን ጉዳይ በግልጽ አስረድተዋል፡፡

‹‹የሱዳን ችግርና የኢትዮጵያ ችግር በቀጥታ ሊቆራኝ ይችላል፡፡ የሱዳን ችግር ግን ከኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ከኤርትራ ጋርም ሊቆራኝ ይችላል፤›› በማለት ተንታኙ ገልጸዋል፡፡

ወልቃይት (ምዕራብ ትግራይ) እየተባለ የሚጠራውንና ሦስቱን አገሮች የሚያስተሳስረውን የኢትዮጵያ ክፍል ውዝግብ መነሻ በማድረግም፣ የሦስቱ አገሮች ቀውስ አንዱ ከሌላው እንዴት እንደሚወሳሰብ አውስተዋል፡፡

‹‹ኤርትራ ከወልቃይት (ከኢትዮጵያ) ገና አልወጣችም፡፡ የአማራ ክልል ኃይሎችና የትግራይ ክልል ኃይሎች ይህ አካባቢ ይገባኛል በሚል ተፋጠው የሚገኙበት ቀጣናም ነው፡፡ ወልቃይት በሌላም በኩል፣ ኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ይገባኛል ውዝግብ የሚያነሱበት ቀጣና ነው፡፡ ሁለቱን አገሮች በቅርብ ዓመታት ወደ ውዝግብ የከተተው አወዛጋቢው የአልፋሽቃ/ጋ ለም የእርሻ መሬት በዚሁ ቀጣና ነው የሚገኘው፤›› በማለትም የጉዳዩን ውስብስብ ገጽ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሱዳን በሦስት አቅጣጫ የሚዋሰኑበት የወልቃይት አካባቢ በሱዳን የተፋፋመው ጦርነትም ሆነ፣ በኢትዮጵያ በአማራ ክልል እየባሰ የመጣው የፀጥታ ችግርን በቀላሉ ከአንዱ አገር ወደ ሌላው ለማሸጋገር የሚያስችል ቀጣና መሆኑን ነው ተንታኙ በትኩረት ያስረዱት፡፡

ሌላኛዋ ተንታኝ አይሻ አል ባስሪም ቢሆኑ ኢትዮጵያና ሱዳን ከድንበር ባለፈ ታላቁን የዓባይ ወንዝ ተጋሪ መሆናቸውን ይናገራሉ፡ ሁለቱ አገሮች በተለይ ኢትዮጵያ በምትገነባው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በመካከላቸው አለመግባባት ተፈጥሮ ቆይቷል ብለዋል፡፡ ‹‹ሱዳን ከግብፅ ጎን በመቆም ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ውኃ አጠቃቀም ላይ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም ለማድረግ በተለያዩ መንገዶች ጫና ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ሁለቱ አገሮች በድርድር ያልተፈታና ያልተካለለ የጋራ ድንበርም የሚጋሩ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ባለበት በሱዳን ጦርነት መፈጠሩና በአማራ ክልልም የፀጥታ ችግር ማጋጠሙ ቀጣናውን ወደ ሌላ ዙር ቀውስ የሚከት ነው፤›› በማለት ተንታኟ ተናግረዋል፡፡

የሱዳን ጦርነት አዳዲስ ሥጋቶችን በቀጣናው አገሮች ላይ ይዞ መምጣቱ ከሰሞኑ በሰፊው እየተዘገበ ነው፡፡ ወትሮም ከግጭት ሥጋት ተላቆ በማያውቀው የሱዳን ዳርፉር ግዛት የሚንቀሳቀሱ ሚሊሻዎች ከሰሞኑ የአገሪቱን ሁኔታ በመጠቀም ጥቃት መሰንዘራቸውን እንዳፋፋሙ በሰፊው እየተነገረ ይገኛል፡፡

የሱዳን ማዕከላዊ መንግሥት በሁለቱ ጄኔራሎች ማለትም በጦር ሠራዊቱ አዛዥ አብዱልፈታ ቡርሃንና በፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዛዥ መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) መካከል በተፈጠረው ደም አፋሳሽ ጦርነት መረጋጋት ማጣቱ፣ በተለያዩ የሱዳን ግዛቶች ሥርዓት አልበኝነት እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑ ይነገራል፡፡

በዳርፉር ያሉ ሚሊሻዎችም ይህን ተጠቅመው እየከፈቱት ባሉት ጥቃት ከሰሞኑ ብቻ ከ20 ሺሕ በላይ ስደተኞች ከግዛቱ ወደ ጎረቤት ቻድ መሰደዳቸው ተነግሯል፡፡ ቻድ ከዚህ ቀደም የተሰደዱትን ጨምሮ ከ100 ሺሕ በላይ ሱዳናዊያንን ለማስጠለል እንደተገደደች ተሰምቷል፡፡

የሱዳን ጦርነት እስከቀጠለ ድረስ በዙሪያዋ ያሉ አገሮች ዕጣ ፈንታ ከዚህ የተለየ እንደማይሆን ዓለም አቀፍ ተቋማት በመገመት ላይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሱዳን ጎረቤቶች በርካታ ስደተኞችን ለማስጠለል እንደሚገደዱ ይነገራል፡፡

የተመድ መረጃ እንደሚያመለክተው ሱዳን 3.7 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችና 1.1 ሚሊዮን የውጭ ስደተኞችን የምታስተናግድ አገር ናት፡፡ ይህ ሳያንስ በአገሪቱ እ.ኤ.አ. ከሚያዝያ 15 ጀምሮ የፈነዳው ጦርነት ደግሞ ቀጣናውን በተፈናቃዮችና ስደተኞች ቀውስ እንዳያምሰው ክፉኛ እየተሠጋ ነው፡፡ በተመድ ትንበያ መሠረት ጦርነቱ ከቀጠለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ270 ሺሕ በላይ ሱዳናውያን ወደ ጎረቤት አገሮች ይሰደዳሉ፡፡ ሁኔታው መሻሻል ሳያሳይ እስከቀጠለ ድረስ ደግሞ የሱዳን ስደተኞች ኢትዮጵያን ጨምሮ የጎረቤት አገሮችን ማጥለቅለቃቸው እንደማይቀር ነው የተገመተው፡፡

የሱዳን ጦርነት የፍልሰትና ስደት ቀውስ በመበራከቱ ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ያሉ ነባር ችግሮችን በማባባስ በኩልም የደቀነው ሥጋት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በማዕከላዊ አፍሪካ የሴሌካ እስላማዊ ቡድን ከአንቲ ባላካል ታጣቂዎች ጋር እስከፊ ግጭት ሰፍኖ ቆይቷል፡፡ የሱዳን ስደተኞች ወደዚህ አገር መግባታቸው ከጨመረ በቀጣናው ላለው ቀውስ ተጨማሪ እርሾ እንደሚሆን ነው የሚገመተው፡፡

ቻድ፣ ሊቢያና ግብፅን የመሳሰሉ የሱዳን ጎረቤቶች ቦኮ ሀራም፣ አይኤስአይኤስና አልቃይዳን በመሳሰሉ ጽንፈኛ የሽብር ብድኖች ሥጋት ያጠላባቸው አገሮች መሆናቸው ይነገራል፡፡ የሱዳን ጦርነትና የስደተኞች ቀውስ ደግሞ ከእነዚህ አገሮች ነባር የሽብር ቀውስ ጋር ሊተሳሰር ይችላል የሚል ሥጋት እየፈጠረ ነው፡፡

በሌላም በኩል በሱዳን ፖለቲካ ጊዜ እያደባ የሚበቅለው የሃይማኖት ጽንፈኝነትን ዝንባሌ የያዘ ፖለቲካ በካርቱም ዳግም እንዳያገረሽ እየተሠጋ ነው የሚገኘው፡፡

ሁለቱ ጄኔራሎች ሲዋጉ በመሀል ግን እንደ ሙስሊም ወንድማማቾች ያሉና ሌሎች የሃይማኖት ቡድኖች በጀርባ በር ሥልጣኑን ሊጠቀልሉት ይችላሉ የሚለውን ሥጋት በርካቶች እያስተጋቡት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በሱዳን ፖለቲካ የተፈጠሩ ተመሳሳይ አጋጣሚዎችንም ማሳያ በማድረግ ያቀርባሉ፡፡

በእስላማዊው ኡማ ፓርቲ ድጋፍ የመጡትን ሀሰን አልቱራቢ፣ እንዲሁም የፕሬዚዳንት ኒሜሪ ሥልጣን የመጠቅለል አጋጣሚ ከዚህ ጋር ያዛምዱታል፡፡ ሱዳን የሃይማኖት ጽንፈኛ ኃይሎች ወደ ሥልጣን በመምጣታቸው በሼሪያ ትተዳደር በሚል የተፈጠሩ የፖለቲካ ውዝግቦችንም ሲያነሱ ይሰማል፡፡ በአዲስ አበባ በሆስኒ ሙባረክ ላይ እስከተካሄደው የግድያ ሙከራ ድረስ የሱዳን ፖለቲካን ቅኝት የሃይማኖት ቡድኖች መለወጣቸውንም ይናገራሉ፡፡

አሁን በተፈጠረው የሱዳን ጦርነት ከሁለቱ ጄኔራሎች ጀርባ የተሠለፉ የውጭ አገሮችና ቡድኖች መኖራቸውን ራሳቸው ሱዳናዊያኑ ይናገራሉ፡፡ ሉትዊ ቴቢን (ዶ/ር) ‹‹የውጭ ኃይሎች ቢተውን የራሳችንን ችግር ለመፍታት አያቅተንም ነበር፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡ እንደሚነገረው ከሆነ ኢራን፣ ቱርክ፣ ኳታር እንዲሁም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ዳጋሎ (ሄሜቲ) ጎን ቆመዋል ይባላል፡፡ ሰውየው ከቻድ ደጋፊ የሚሊሻ ጦር ሊመጣላቸው ሁሉ ይችላል ይባላል፡፡

ምዕራባውያኑን ጨምሮ፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና አንዳንድ የሱዳን ጎረቤት አገሮች ደግሞ ከጦር ሠራዊቱ አዛዥ ከአልቡርሃን ጎን መቆማቸው በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ እስካሁን በገለልተኝነት ነው ስሟ ሲነሳ የቆየው፡፡ ተንታኙ ኢታና ዲንቃ (ረዳት ፕሮፌሰር) ለአልጄዚራው እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሁለቱም የሱዳን ተፋላሚ የጦር መሪዎች ጋር መልካም ግንኙነት ነበራቸው፡፡ የትግራይ ጦርነት እንደ ጀመረ ከአብዱልፈታ አልቡርሃን ጋር ተገናኝተው ነበር፡፡ በሒደት ግን ሱዳን የአልፋሽጋ/ቃ ድነበር ግዛትን እንደወረረች አልቡርሃንም ‹‹ግዛቱን እንድንቆጣጠር ዓብይ ነግረውኛል፤›› የሚል አወዛጋቢ መግለጫ መስጠታቸውን ተንታኙ ያስታውሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ የትግራይ ጦርነት በሚካሄድበት ወቅት ሱዳን አጋጣሚውን ተገን በማድረግ ድንበሬን ወራ አጥቅታኛለች የሚል ስሜት ተፈጥሮባት እንደቆየ ተንታኙ ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የሱዳን ጦርነት እየተፋፋመ ባለበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት በግልጽ አንዱን ተፋላሚ ኃይል ለይቶ ሲቆም አለመታየቱን ተንታኙ ያስረዳሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ጦርነቱ እየቀጠለ የሚሄድ ከሆነ ሊቀየር እንደሚችልና ኢትዮጵያን ጨምሮ የጎረቤት አገሮች ሠልፋቸውን ሊቀይሩ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

አንዴ ከአልቡርሃን ሌላ ጊዜ ደግሞ ከሄሜቲ ጎን በመቆም ሲታሙ የቆዩት የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሰሞኑ በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን፣ ‹‹ግጭት ፈጣሪዎችና ቀውስ ጠማቂዎች የተሞላ ቀጣና›› ሲሉት ተደምጠዋል፡፡

ኢሳያስ ይህን ቢሉም የሱዳን ጉዳይን በተመለተ ግን ሰላም እንዲሰፍን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ ለመጠቀም የምንንቀሳቀስበት ወቅት አይደለም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ እውነታቸውን ከሆነ አዎንታዊ ነው ሲሉ ተንታኞች ጉዳዩን አስተጋብተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -