በተሾመ ብርሃኑ ከማል
ከታሪክ እንደምንረዳው የእስልምና እምነት በዓለም የተሰራጨው በሦስት ዋና ዋና ወቅቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ከ632-800 ባለው ዘመን ሲሆን በዚህም ዘመን እስልምና በኢትዮጵያ፣ በፋርስ፣ በሶሪያ፣ በሰሜንና በምሥራቅ አፍሪካ፣ በሰፓይንና በሲሲሊ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ሁለተኛው ከ1000-1480 የነበረው ዘመን ሲሆን ይህም ዘመን ቱርኮች እስልምናን ተቀብለው በሩቅ ምስራቅ አቅጣጫ ቱርክ፣ ሕንድ፣ ቻይና፣ በስተምዕራብ አቅጣጫ ደግሞ የባልካን አገሮች የሚባሉትን አገሮች አቋርጦ እስከ ኦስትሪያ ቬና ተሻግሯል፡፡
የባይዛንታን ኢምፓየር ማዕከል የነበረችው ኮንስታንቲኖፕል በ1453 በቱርክ ሙስሊሞች እጅ ገባች፡፡ ሦስተኛው እስልምና የተስፋፋበት ዘመን ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ዘመን ነው፡፡ በዚህም ዘመን እስልምናን የተቀበሉ ሙስሊሞች ሁሉ በንግድ፣ ከሐጅ የተመለሱ እማኞች፣ ወደ ዓረብ ሀገሮች በመሄድ ተምረው በተመለሱ ዑለማዎች፣ የበለጠ አስፋፍተውታል፡፡
እስልምና በሦስቱ ወቅቶች ይስፋፋ እንጂ በመካከሉ ችግሮች አልገጠሙትም ማለት አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት በአማኖችና እምነቱን በተቀበሉ ምናባትም በወቅቱ ለመቀበል ፈቃደኛ ባልሆኑ ሰዎች ከፍተኛ ቅዱስ ጦርነት ተካሂዷል፡፡
እስልምና ቀጥተኛ የእምነት መንገድ ከመሆኑም በላይ አዲስ ሕብረተሰብ፣ ኪነጥበብ፣ ስነጽሑፍ፣ ግብርና፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በሰዎች መካከል የሙስሊም ወንድማማችነትን መንፈስ በመዝራት በዓለማችን ሰላምና ብልፅግና እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ይህም ቁርአን በውስጡ ዛሬ እውን የሆነው ዘመናዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያኔም ይዞ ስለወረደ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ሙስሊም በግብፅ፣ በባግዳድ፣ በሜስፓታሚያ፣ በኮርዶቫረ ስፔይን እጅግ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎችን አቋቁመዋል፡፡ እነዚህም ዩኒቨርሲቲዎች የግሪክ-ሮማ ባህሎች ተጠብቀው እንዲቆዩ በማድረግ በዓለማችን ቅርስ መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበረክተዋል፡፡ ኢስላማዊ ስሜት በተሞላበት ስሜት ከአገራቸው እንዲወጡ፣ እንዲያጠኑና እንዲፅፉ ዕድል ያገኙ ሙስሊም ዑለማዎችም የጥንታዊውን የኢስላማዊ ትምህርት ዕውቀት ቀስመዋል፡፡ እስልምናውን በዓለም ያሰራጩት ሙስሊሞች አስቸጋሪ የነበረውን የሮማውያን ቀላልና ለሥራ አመቺ የሆነውን ቁጥር በዓረብኛ ቁጥር የተኩ ከመሆናቸውም በላይ አልጀብራን፣ ጂኦሜትሪን፣ ትረግኖሜትረን አስተምረዋል፡፡ በሳይንስ ረገድ ሰልፊሪክ አሲድ እንዴት እንደሚዘጋጅ፣ አልኮል እንዴት እንደሚሠራ ብረት እንዴት እንደሚቀልጥ፣ ልብስ እንዴት እንደሚሠራ፣ በብርሃንና በዕይታ መካከል ስላለው ግንኙነት አሳውቀዋል፡፡
ሙስሊም መምህራን የሃይማኖት አባቶች ብቻ ሳይሆን ሐኪሞችም ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት የቀዶ ሕክምናን በማደንዛዝ ይሰጡ ነበር፡፡ ይልቁንም በዓይን ቀዶ ሕክምና የታወቁ ነበሩ፡፡ የሕክምና ጥበብ የማስተማሪያ መጽሕፍትም ነበራቸው፡፡ በግብርና ረገድም ይከተሉት የነበረው ዘመናዊ አስተራረስ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ ይልቁንም አፈር በመገደብ ፣ አዝርእትን እያፈራረቁ በመትከል፣ በመስኖ በመጠቀም፣ የማዳበሪያን አስፈላጊነት በማስገንዘብ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል ማለት ይቻላል፡፡ የኮርዶሽ የቆዳ ሥራ፣ የደማስቆ ብረታ ብረት ሥራ በተለይም የጎራዴ ጥበብ፣ የደማስቆ ልብስ ሥራ፣ የብርጭቆና የጠርሙስ ጥበብ፣ የወረቀት ሥራም ከኢንዱስትሪው ዘረፍ የሚጠቀስ ሲሆን ይህም ሁሉ ዕውቀት ከእስልምና ሃይማኖት ጋር ተስፋፍቷል፡፡
በኮምፓስ ጭምር እየተመሩ እስከ ቻይና የሄዱት ሙስሊም አባቶች ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ሌላ በስነ ጽሑፍ፣ በቋንቋ፣ በሕንድ ሥራ ያበረከቱት አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ከታወቁት ሙስሊሞች ፈላስፎች ሳይንቲስቶች መካከል ከ980-1037 የኖረው አቪቸና፣ ከ1126-1198 የኖረው ሐኪሙና ፈላስፋው አቬሮስ፣ ከ1135-1204 የኖረው ማኢምናድስ ይገኙበታል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የታሪክ ማስረጃዎችና ክስተቶች ሁሉ በኢትዮጵያም የተፈፀሙ በመሆናቸው ደረጃ በደረጃ እንመለከታቸዋለን፡፡
እስልምና በኢትዮጵያ
ቀደም ሲል በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው እስልምና በመላው ዓለም የተሰራጨው በሦስት ወቅት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ይህም የሦስት ወቅት ስርጭት በታሪክ ጸሐፊዎች ዘንድ ስምምነት ያገኘ ጉዳይ ስለሆነ አሁን የምንከራከርበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ዋናው ጥያቄ በሀገራችን ኢትዮጵያ እስልምና ከመቼ ጀምሮ ተሰበከ፣ ለመሰበኩስ ምን ተጨባጭ መረጃ አለን? የሚለው ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ሁኔታዎችን ከረዥም ታሪካችን አንጻር መዳሰስ፣ የአፍሪካ ቀንድንና የዓረቡን ዓለም ጂኦ-ፖለቲካዊ ግንኙነት ማጤን፣ ያስፈልጋል፡፡ ከሁለቱም አኳያ ስንመለከታቸው ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሁሉ ከብዙ ሺ ዓመታት ጀምሮ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን የጠበቀ ማኅበራዊ ግንኙነት እንደነበራት የታሪክ መረጃዎች ይጠቀማሉ፡፡
ከበርካታ መረጃዎች አንዱን ብቻ በአጋጣሚ ብድግ አድርገን ብንመለከተው «ኢትዮጵያ በጥንታዊነታቸው ከሚታወቁ የንጉሠ ነገሥት ግዛቶች አንዷ ስትሆን ስልጣኔዋ ከግብፅ ስልጣኔ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ንጉሥ ሰለሞን የተባለ የሄብሩ ንጉሥና ንግሥተ ሳባ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት ሁለቱን አገሮች አስተሳስረዋል የሚል ታሪክ አለ፡፡ በ3ኛው ክፍለ ዘመን የግሪኩ ቅኝ ገዥ ግብፅን በቀኝ ግዛትነት ይዞ በነበረበት ጊዜ ኪነጥበቡን ወደ ኢትዮጵያም አምጥቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ ጊዜ የአይሁዶች ሃይማኖት ለረዥም ምዕት ዓመታት በኢትዮጵያ ተሰንስራፍቶ የነበረ ቢሆንም እንኳን ከ330 ጀምሮ ክርስትና ገብቷል፡፡ ምንም እንኳን ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ይህን ያህል ዓመታት ቢወስድበትም በአረቢያና በኢትዮጵያ መካከል በነበረው ጂኦ ፖለቲካዊ ቀርቤታ እስልምና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በራሱ በሳዑዲ ዓረቢያ እንደተጀመረ በራሳቸው በነቢዩ መሐመድ ዕድሜ ነው፡፡
ይህም የሆነበት ምክንያት ነብዩ መሐመድ የእስልምና እምነት በመካና በአካባቢውም በሚሰበክበት ጊዜ በአንዳንዱ ቀንደኛ ነጋዴዎች፣ ባለስልጣኖች፣ መተተኞችና በአጠቃላዩም አሳማኞች ከተቃውሞ ሲደርስበት እምነቱ በትክክል የገባቸው ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ በመላቸው ነው፡፡ በአል-ነጃሺ (አስ-ሐማ) የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥትም ከዓረቢያ የመጡትን ሙስሊም ስደተኞችን ተንከባክቦ ከመያዙም በላይ የእስልምና ሃይማኖት በመቀበል በዓለም የመጀመሪያው መንግሥት ሆነ ስደተኞቹንም ተንከባክቦ ይዞ ከቆዩ በኋላ ወደ አገራቸው ሲመለሱ በክብር ሸኛቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ኢስላም በኢትዮጵያ እየተሰራጨ እንደሄደ የታሪክ ማስረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ለአቀራረብ እንዲያመቸን ግን ከ632-1000፣ ከ1000-1500፣ከ1500-1700፣ ከ1700-2000 ዓመት ወዲህ ብለን ከፋፍለን እንመልከተው (ሆኖም ከ1700-2000 በዚህ ጋዜጣ የሚቀርበው ወደፊት ይሆናል)፡፡
እስልምና ከ632-1000
ይህ ዘመን መካከለኛው ጊዜ ተብሎ የሚጠራው ዘመን የሚገኝበት ሲሆን የሮማ መንግሥት ውድቆ አውሮፓ በአነስተኛ መንግሥታት የተከፋፈለችበት፣ መካከለኛው ምስራቅ ደግሞ የባይዛንታይን መንግሥታት የሙስሊም መንግሥት ተብሎ በሁለት መልክ በሚታይበት ሁኔታ ነበር፡፡ የባይዛንታይን መንግሥትን ለጊዜው እናቆየውና የሙስሊም መንግሥት የሚባለውን እንመልከት፡፡
የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚያስረዱት የእስልምና በኢትዮጵያ መሠራጨት የጀመረው ነቢዩ መሐመድ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ሲሆን እርሳቸው ከሞቱ በኋላ ማለትም በ7ኛው ክፍለ ዘመንና በ8ኛው ክፍለ ዘመን ሁሉም የዓረብ አገሮች እስልምናን ተቀብለው አንድነታቸውን አጠናክረው ነበር፡፡ አንድነታቸውን አጠናክረው ስለነበረም በስተሰሜን ፍልስጤምንና ሶሪያን ከዚያም የባይዛንታይን መንግሥትን ባይደመስሱም ሞሶፓታሚያን ገዙ፡፡ ወደ ምሥራቅም ሞስፓታሚያን፣ ፐርቪያንና ሰሜናዊ ሕንድን፣ በስተምዕራብም ግብፅን፣ ሰሜን፣ አፍሪካንና አብዛኛውን የሰፔይን ግዛትን ያዙ፡፡ በ10ኛው ክፍለ ዘመንም ቱርኮች እስልምናን ከመቀበላቸውም በላይ የአቶማን መንግሥት በመሠረቱበት ጊዜ በምሥራቅ አውሮፓና በሩቅ የአቶማን መንግሥት ግዛታቸውን መሠረቱ፡፡ በተጠቀሱት ጊዜያት እስልምናም ወደ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ በኩል ማለትም በግብፅና በሱዳን በኩል አድርጎ ወደ ሰሜንና ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በቀይ ባሕር በኩል በዳህላክ፣ በአዶሊስ፣ በዘይላዕና በሌሎችም የባህር ዳርቻዎች አድርጎ ወደ ሰሜንና ምሥራቅ ኢትዮጵያ ተስፋፍቷል፡፡
ከ632-1000 የነበረውን ዘመን ከኢትዮጵያ ታሪክ አንጻር ስንመለከተው የአክሱም ዘመነ መንግሥት የነበረበት ዘመን ሲሆን በዚህም ዘመን አክሱማውያን በአንድ በኩል ከዓረብ ወራሪ ኃይሎች፣ በሌላ በኩል ደግሞ በውስጥ በነበረው የሥልጣን ሹኩቻ ምንክንያት መንግሥታቸው ተዳከመ፡፡ እንደ ዳህላክና አዶሊስ ያሉት የባህር ወደቦች በዓረቦች እጅ የወደቁትም በዚህ ጊዜ ነው፡፡
በሌላ በኩልም የሮማን ኢምፓየር ተንኮታኩቶ ወደ አነስተኛ መንግሥታት ተበታትኖ የነበረበት ዘመንና የአውሮፓ አገሮች በጨለማው ዘመን ውስጥ ገብተው ከውጭው ዓለም ግንኙነታውን አቋርጠው የነበረበት ዘመን በመሆኑ ከኢትዮጵያም ጋር የኢኮኖሚና የኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን አቋርጠው የነበሩበት ጊዜ ነበር አውሮፓውያን ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ባለማድረጋቸው የራሱ የሆነ ተፅእኖ የነበረው ቢሆን ከሌላው ዓለም ጋር ግንኙነት እንደተደረገም የባህር መውጫዋ በዓረቦች ተይዞ ስለነበር መንቀሳቀሻ አልነበራትም፡፡ ስለዚህ የጨለማ ዘመን በአውሮፓ እንደነበረው ሁሉ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ዕጣ እንደደረሰ በአንድ በኩል እንመለከታለን፡፡
በዚህ ዘመን የምናገኛትና ስሟ በአፄዎቹ በኩል ጥሩ ስም የማይሰጣት ነገር ግን ለ40 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን እንደገዛች የሚነገርላት ንግሥት ዮዲት ናት፡፡ ስለዚች ገናና ንግሥት ግን የታወቁ የታሪክ ሰዎች ጽፈውላታል፡፡ ትሪሚንግሃም «ኢስላም ኢን ኢትዮጵያ» በሚል ርዕስ ባሳተመው እውቅ መጽሐፉ (ከገጽ 52-53) ኢብን ሐቃል የተባለውን ዓረባዊ የታሪክ ጸሐፊ በመጥቀስ «በአሌክሳንደሪያ ጳጳሳት ታሪክ ሰፍሮ እንደሚገኘው የሐበሻ ንጉሥ ከ979 ትንሽ ቆይቶ ለኑቢያው ንጉሥ ጆርጅ (979-1003) የበኒ አልሐዊያ ንግሥት ከቦታ ቦታ እያሳ ደደች እንደምታድነው ጠቅሶ ክርስቲያንና ክርስትና ከምድረ ገጽ እየጠፋ መሆኑን አስመልክቶ እርዳታ እንዲያደርግለት ጽፎለታል፡፡
በወቅቱ የነበረው ሐቃል የተባለ ዓረባዊ ጸሐፊ በ978 ባሳተመው መጽሐፉ እንዳሰፈረው ንግሥቲቱ ንጉሡን አሳዳ የገደለችው ሲሆን እሷም ከሰሜን ኢትዮጵያ እስከ ምዕራብ ኢትዮጵያ ድረስ መግዛቷ ጠቅሷል፡፡ ኮንቲሮዚም (ሒስቶሪያ ደ ኢትዮጵያ) ጠቅሶ እንደገለጸው «የንግሥት ዮዲት ግዛት ከደቡብ አባይና ደቡብ ሸዋ ያለውን የጉራጌና የሲዳማን ግዛት ያጠቃለለ ነበር፡፡»
በትሪሚንግሃም አገላለጽ በክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ጥፋት በ16ኛው ክፍለ ዘመን (በኢማም አሕመድ ዘመን) ከደረሰው ጉዳት በእጅጉ የላቀ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ክርስቲያኖች ባሮች ሆኑ፣ ባዕድ አምልኮ (ከልት) ተስፋፋ፡፡ የዮዲት ለረዥም ዓመታት በአካባቢው መቆየትም ከሷ ጋር ጠብ ላልነበረው እስልምና እግር መትከል አመቺ ሁኔታን እንደፈጠረ ትሪሚንግሃም ይተርካል፡፡
እስልምና እያደገና ሥሩን እየሰደደ መሄድ የጀመረውም በዚህ ዘመን እንደነበረ ከታሪክ ምዕራፎች እንረዳለን፡፡ ይህም የሆነበት ዋና ምክንያት የንግሥት ዮዲት ጦርና የክርስቲያኑ መንግሥት ጦር ያለ ምሕረት ሲቀጣቀጡ የሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች መዳከም ለእስልምና በሰላም መስፋፋት አስተዋጽኦ በማድረጉ ነው፡፡
የአክሱም መንግሥት 10ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ሕልውናው አክትሞ ከ10ኛው-13ኛው ክፍለ ዘመን የዛጉዌ መንግሥት ሊተካ የእስልምና እምነትም በሰሜንና በምሥራቅ ኢትዮጵያ ይስፋፋ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ከዛሬ አፋር እየተባለ የሚጠራው አካባቢ እስከ ሰሜን ሸዋ ደብረ ሲናና ደብረ ብርሃን፣ ከዘይላ እስከ ሐዲያ ድረስም ሥር ሰዷል፡፡ በመሰደዱም የክርስቲያኑን መንግሥት በመጣል የሙስልም መንግሥት ስልጣን በማስያዝ ፍልሚያ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
እስልምና ከ1000-1500
ምንም እንኳን እስልምና ከ615 ጀምሮ በኢትዮጵያ እንደገባ ቢታወቅም የእስልምና ሃይማኖት በሰሜን ኢትዮጵያ ከመቼ ጀምሮ እንደተስፋፋ የሚያመለክቱ መረጃዎች እስከ ቅርብ ጊዜ አልነበሩም፡፡ እንዲያውም በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል እንጅ በሰሜኑ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ያልነበረ አስመስሎታል፡፡ ሆኖም ከነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) ተከታዮች ጀምሮ ወደ ሀገራችን መግባት የጀመሩት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ትግራይ ውስጥ ካሉት መረጃዎች ውስጥ ከመቀሌ ደቡብ ምሥራቅ ኩዊሐ አጠገብ ቢሌት ከሚባል ስፍራ ከ1000 ዓመታት የነበረ መቃብር ሲኖር ይህም እውነት መሆኑ በፈረንሳይ አርኪዮሎጂስትች የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በዚያው በደቡብ ትግራይ ዓዲጉዶም ተብሎ ከሚጠራው ከተማ በስተ ምሥራቅ አራ በሚባል ጥንታዊ ከተማ ከ800 ዓመታት በፊት መጻፉ የሚያመለክት የመቃብር ድንጋይ እንደነበር የዓዲጉዶም ጥንታዊ መስጊድ ኢማም የነበሩት ሸኽ ሰዒድ ዘርአይ ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ገልጠውለታል፡፡ ይህንም ዓይነ ብራዎቹ፣ ኩናባ እና ኢስላማዊ ሥነጽሑፍ በሚሉ አርእስት ለንባብ ባቀረባቸው መጻሕፍት አስፍሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አጽቢ ወንበርታ፣ ነበለት፣ ዓቢይ ዓዲ (ተቐራቒራ)፣ ሐውዜን ሸኽ ባህሮ በሚገኙበት መቃብር ቢያንስ 500 ዓመት ያስቆጠሩ መቃብሮች እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡ ለተጨማሪ መረጃ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ‹‹ኢስላማዊ ሥልጣኔ በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በ2014 ለንባብ ባቀረበው መጽሐፍ በምዕራፍ ዘጠኝ ከገጽ 201-224 በትግራይ ስለነበረው ኢስላማዊ ሥልጣኔ ሰፋ ያለ ትንታኔ ሰጥቶበታል፡፡
ይህም ሁሉ ሆኖ ኢስላም በኢትዮጵያ ገኖ መውጣት የጀመረው በ13ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የወላስማ ስልጣኖች ተከሰቱ፡፡ ከ1270-1285 በሥልጣን ላይ የነበረው የአፄ ይኩኖ አምላክ መንግሥት ሱልጣን ዑመረን በ1275 አካባቢ እንደሾመው የኢትዮጵያ ዜና መዋዕላት ያመለክታሉ፡፡ ሱልጣን ዑመር አራት ወይም አምስት ልጆቹ ተክተውታል፡፡ ከዑመር ልጆች የመጨረሻው ሰብረ አዲን ናህዊ ኢብን ማሱር ኢብን ዑመር መላስማ ወይም ቀዳማዊ ሰብር አድዲን ነው፡፡ ይህ ሡልጣን ለብዙ ዓመታት ከኖረ በኋላ በሱልጣን ዓሊ ተተካ፡፡ አል-መቅረዚ የተባለው የታሪክ ፀሐፊ እንደዘገበው ከሆነ በክርስቲያኑ መንግሥት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመፅ መሪ ነበር፡፡ ከሱልጣን ዓሊ በኋላ በአፄ አምደፅዮን (1312-1342) ያመፀው ቀዳማዊ ሱልጣን ሐቀዲን ነበር፡፡ መንዝ ላይ በተለይም መደራ ዘጋ በተባለው ስፍራም የሱልጣን ሐቀዲን ልጅና የጦር መሪ የነበረው ተገደለ፡፡
ከሐቀዲን በኋላ ወንድሙ ዳግማዊ ሱልጣን ሰብረዱን ተተካ፡፡ ሰብረዲንን ሐንቲንግ ፎርድ የተባለ የታሪክ ፀሐፊ እንደገለፀው የክርስቲያኑ መንግሥት ይዞት የነበረውን ግዛት ሁሉ በመያዝ ዓላማ የነበረው ሲሆን ፋጣጋረንና አይመለልን (ጉራጌ) ዳሞትን፣ አማራን፣ አንጎትን፣ እንደረታን፣ ጎንደርንና ጉጃም በግዛቱ ከሚያጠቃልላቸው ክፍለ ሃገራት ውስጥ ነበሩ፡፡ የአፄ ዓምደጽዮን መዋዕለ ዜና ጸሐፊዎች ይህን ሲገልጹ ‹‹ዳግማዊ ሰብረዲን መላው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያናትን ወደ መስጊድነት፣ ንጉሠ ነገሥቱ እሽ ካለ የአንድ ክፍለ ሀገር ገዥ ሊያደርገው እንቢ ካለ ደግሞ የወረጅዎች በግ እረኛ ሊያደርገው፣ የአፄ አምደጽዮን መናገሻ ከተማ የነበራቸውን ተጉለት መራድ ብሎ ሊጠራት፣ ሚስቱ ንግሥት ጃን መንገሻን ወፍጮ ፈጪው ሊያደርጋት ጫት ለመትከል ነበር፡፡›› ይላሉ፡፡ ይህ አባባል ለማረጋገጥ ከዳግማዊ ሰብረዲን በኩል የተገለፀ ነገር የለም፡፡ ይሁንና የክርስቲያኑ መንግሥት ሕዝብን ለማሰባሰብ ሲል ‹‹ሚስትህን የሚደፍር፣ ሃይማኖትህን የሚያጠፉ ወዘተ›› እየተባለ ቅስቀሳ ስለሚደረግ ይህም ምናልባት በአፄ ዓምደጽዮን ጋሻ አጃግሬዎች ያስወሩት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይችላል፡፡ የሆነ ሆኖ ሰብረዲን ሰራዊቱን በሦስት አቅጣጫ በመክፈት አንዱን በአማራ ግንባር፣ ሁለተኛውን በአንጎት ግንባር፣ ሦስተኛው በሸዋ ግንባር እንዲሰለፍ አደረገ፡፡ የአፄ አፄ አምደጽዮን ጦርም እጅግ ከፍተኛ ኃይል አሰልፎ ስለነበር ድል አደረገ፡፡ ሰብረዱን ተሸንፎ ሸሸ፡፡ ከሰብረዱን በኋላ ወንድሙ ቀዳማዊ ጀማል አዲን ሱልጣን ይዞ የአካባቢው ገዥ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
የዓምደጽዮን ልጅ አፄ ሰይፈ አርእድም ሲነግሥ አሕመድ ዓሊ ወይም ሐረብ አብን ዓሊን ሱልጣን አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ የሰብር አዲን ልጅ የሆነው አህመድ ዓሊም እንደሌሎቹ ሱልጣኖች በማመፅ የእስር ቅጣት ለስምንት ዓመታት ያህል ታስሯል፡፡ በኋላ አፄ ሰይፈ አርእድ ጋር ስለታረቁ ተፈቶ የነበረ ሲሆን ቆይቶም በተደረገው አመጽ ተገድሏል፡፡
ከሱልጣን ከአሕመድ ዓሊ በኋላ ዳግማዊ ሐቀዲን ወደ ስልጣን መጣ፡፡ አል መርዙቂ የተባላው የታሪክ ፀሐፊ ስለዚህ ሰው ሲጽፍ በእጅጉ ጦርነት ወዳጅ፣ ጀግናና ተወዳጅነት ያለው መሪ ነበር፡፡ ይኸው ለጠላቱ መሪርና ፈጣን የነበረ መሪ በ1370 ላይ አፄ ሰይፈ አርእድን በጦርነት ላይ ገድሏል፡፡ ሐቀዲን መራር ጀግና ስለነበር ከአፄ ሰይፈ አርእድ በኋላም የነበረው ውድም አስፈሬን (1370-1381) ቁም ስቅል አሳይቶታል፡፡ ይሁንና ሐቀዲን በተደረገው ተከታታይ ጦርነት በ1376 ላይ ሞተ፡፡ እርሱ ሲሞትም ወንድሙ ሱልጣን ሳዕደዲን አብዱል ሙሐመድ ተተካ፡፡ ሱልጣን ሳዕደዲንም እንደወንድሙ ኃያል ስለነበር የሀዲያውን መሪ አማኖን አሸነፈ፡፡ በአካባቢው የነበሩትን አጎራባች ዘላኖችን ሁሉ በቁጥጥር ስር አደረገ፡፡ 40 ሺ ከብቶችን ማርኮም ለድሆች እንዲከፋፈል አደረገ፡፡ ከዚያም አፄ ዳዊትና የጦር አዝማች የኢፋቱን የሙስሊም ገዥ ልክ ለማስገባት ከፍተኛ ሠራዊቱን ይዞ ገሠገሠ፡፡ ነገር ግን ከአንድ ከወሬ ነጋሪ በስተቀር የተመለሰ አልነበረም፡፡ አፄ ዳዊት የደረሰውን ሸንፈት እግምት ውስጥ በማስገባት ከፍተኛ ሠራዊቱን ይዞ ዘመተ፡፡ በዚህ ዘመቻ ከፍተኛ ጦርነት ተካሂዶ የሳዕደዲን ኃይል በእጅጉ ተመታ፡፡ ሌላው ሁሉ ሳይቆጠር ከ400 የማያንሱ ታላላቅ የጦር አለቆች ተሰው፡፡ በርካታ ምሁራን አለቁ፡፡ በዚህም ምክንያት የአፄ ዳዊት ጦር ሳዕደዲንን እስከ ዛይላ ድረስ አባሮ በ1415 ላይ ገደለው፡፡ ከዚህ በኋላ አሰሩ የሱልጣን ሳዕደዲን ልጆች ወደ ዓረቢያ ተሰደዱ፡፡ እዚያው እንደደረሱ ነስር አሕመድ አብን አሰራፍ ኢስማኤል የተባለ መሪ ጥገኝትን ሰጣቸው፡፡ አፄ ዳዊትም መዲናቸውን ኢፋት ውስጥ ልዩ ስሟ ቶቢያ በምትባለው ስፍራ አድርጎ ራሱ አካባቢውን ይገዛ ጀመር፡፡
ዳሩ ግን የሱልጣን ሳዕደዲን ልጆች ለተወሰነ ጊዜ በዓረቢያ በስደት ከቆዩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ሐረር አጠገብ ከምትገኘውን ዲከር ተብላ በምትጠራው ስፍራ መኖሪያቸውን መሠረቱ፡፡ እነርሱም እዚህ ስፍራ ላይ ሆነው የአዳሎች ንጉሥ የሆኑት ኢፋቶች መሆናቸውን ይፋ አደረጉ፡፡ አዲሱ የአዳሎች ስርወ መንግሥትም የሰዕዳዲን የመጀመሪያ ልጅ የሆነው ስላሳዊ ሱልጣን ሰብረዲን ነበር፡፡ ከአስር ፈረሰኞች ጋር ከዓረቢያ የተመለሰው ሰብረዲን ናስር አሕመድ የተባለ ዓረባዊ የጦር መሪም ነበረው፡፡ ሁኔታዎች በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ባሉበት ወቅት ሱልጣን ሰብረዲን ሳልሳዊና ወንድሞቹ የሸዋ አፄዎች መንግሥትን ለመውጋት ወደ ሰሜን ገሠገሡ፡፡ ምንም እንኳን ያነሰ ሠራዊት ቢኖራቸውም ዚክረ አምሐራና ሰርጃን በተባለ ስፍራ ጦር ገጥመው አሸነፉ፡፡ ከፍተኛ ምርኮም ማረኩ፡፡
የሸዋ አፄዎች እንደዚህ ያሉት ሽንፈት በእጅጉ ስላስቆጣቸው 20 ሺ ያህል ሠራዊት አሰልፈው የሱልጣን ሰብረዲን ሳልሳዊን ጦር ገጠሙት፡፡ በዚህም ጦር ሰብረዲን ተሸንፎ ሸሽቶ ነበር፡፡ ሆኖም ሰብረዲን ኃይሉን እንደገና በማጠናከር የአፄውን ሠራዊት ተመልሶ ወጋ፡፡ ከዶከር እስከ ኢፋት በመግፋትም፡፡ የንጉሡን መዲና አቀጠላት፡፡ ነገሩ አንድ ጊዜ አንደኛው ሲያሸንፍ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላው ስለሚያሸንፍ የሱልጣን ሰብረዲን ሠራዊት በድጋሚ ተሸንፎ ነበር፡፡ ያመለጠውም በፈጣን ፈረሱ ሸሽቶ ሲሆን በ1422-3 ላይ በተፈጥሮ ሞት አለፈ፡፡
ሱልጣን ሰብረዲን ሳልሳዊ ከመቶ በኋላ ወንድሙ ሱልጣን መንሱር ተተካ፡፡ መንሱርም የአፄ ዳዊትን 30 ሺ ጦር ሞሃ በተባለ ተራራ ላይ ከቦ ለሁለት ወር ያህል መውጫ መግቢያ አሳጣቸው፡፡ በመጨረሻም አንድም እስልምናን እንዲቀበሉ ካበለዚያም በርሃብና በጥማት ባሉበት እንዲያልቁ ምርጫ ሰጣቸው በዚህ ጊዜ 10 ሺ ያህሉ የእስልምናን ሃይማኖት ተቀበሉ የተቀሩትም ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡
በ1424 ንጉሠ ነገሥታት ይሰሃቅ ስልጣን ሲይዝ ከፍተኛ ኃይል በማሰባሰብ ሱልጣን መንሱርንና የጦር አዝማቹና ወንድሙ የሆነውን ሙሐመድን ማረኳቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የአዳሉ መንግሥት ተመልሶ በክርስቲያኑ መንግሥት ሥር ወደቀ፡፡ ከሱልጣን መንሱር በኋላ ወንድሙ ሱልጣን ጀማል አዲን መሐመድ ተተካ ዳግማዊ ጀማለዲ በዛም ብልህ ስለነበረ ለአፄ ይሰሐቅ የሰላም መልእክተኛ ላከ፡፡ ይሁንና አፄው የቀረበለትን የስላምና የስምምነት ሐሳብ ባለመቀበሉ ነገሩ ውድቅ ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት ጦርነት እየተካሄደ አንድ ጊዜ የሡልጣኔቱ ወገን በሌላ በኩል ደግሞ የጼዎቹ ወገን ሲያሸንፍ ከቆየ በኋላ አፄ ይስሃቅ ሞቱ፡፡ ሆኖም የአዳሱ ጦር በጣም ተዳክሞ ስለነበር ዳግማዊ ጀማል ዲንም በአጎቱ ልጅ በ1432 ተገደለ፡፡
ምንም እንኳን ደግማዊ ጀማል ዲን በዘመዱ ቢገደልም አል-መርዙቂ በምሥራቅ ኢትዮጵያ የተገኘ ከፍተኛ ችሎታ ያለው መሪ እንደነበር ጽፎበታል፡፡ በሰባት ዓመት የስልጣን ዘመኑም የማርካቸውን በርካታ ሰዎች ባሪያ አድርጎ ወደ ሕንድ፣ ሆርሙስ፣ ሒጃዝ፣ ግብፅ፣ ሶሪያ ግሪክ ኢራቅና ፐርቪያ ልኳል፡፡ ጀማሉዲን ከዚህም በላይ ጥሩ ፍትህ አዋቂ እንደነበረ ይነገራል፡፡
ከጀማል ዲን በኋላ ወንድሙ ሱልጣን በድላይ ኢብን ሳዕድ አዲን ተተካ፡፡ ይህ ሱልጣን ሺሐብ አዲን አሕመድ በድላይም ይባላል፡፡ መናገሻ ከተማው ደከር አድርጎ የክርስቲያን አፄ ዘርአያቆብን መንግሥት በመውጋት ከፍተኛ ስፍራዎችን ይዞ ነበር፡፡ በኋላ ግን አይን ፈረስ በተባለው ስፍራ ከፍተኛ ሽንፈት ደረሰባት፡፡
ከባድባይ በኋላ ሱልጣን መሐመድ (1445-1471) ተተካ፡፡ እርሱም 26 ዓመት ያህል ገዛ፡፡ ሱልጣን መሐመድ በ1452 ግብፅ ላይ ኤምባሲ መስርቶ ነበር፡፡ ከአፄ ዘርአያዕቆብ በኋላ ስልጣን የያዘው አፄ በዕደ ማርያምም፣ የሙስሊሙን ግዛት ለመያዝ ቢሞክርም አልተሳካለትም፡፡ እንዲያውም ከጦርነት ይልቅ ሰላምን የመረጠ ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት ስፔንሰር ትሪሚን ‹‹ኢስላም ኢን ኢትዮጵያ›› በተሰኘ መጽሐፉ እንደገለጸው ሁሉ ከሱልጣን መሐመድ የተላከለትን ልብሶችንና የስምምነት ሐሳብ ተቀብሎ ነበር፡፡ ስምምነቱም የአዳል ገዥዎች አስፈላጊውን ግብር ለአፄ በዕደማርያም እንዲልኩ አፄውም የጦርነት ትንኮሳ እንዳያካሂድ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ በአዳል ግዛት ሹመኞች አንዱ የሆነው የዘይላው ገዥ ለዳኢ ዑስማን ስምምነቱን ማፍረሱን በአፄ ባዕደማርያም ዘንድ ተሰማ፡፡ ከፍተኛ ዝግጅት ካደረገ በኋላም በመሐሪ ክርስቶስና በገብረ እየሱስ አዝማችነት ጦርነት ከፈተ፡፡ ከብዙ እልቂት በኋላም አሸነፈ፡፡ ከአፄ ባዕደ ማርያም በኋላ ስልጣን የያዘው ልጁ አፄ እስክንድርም (1798-1494) አሚር ሸምስ አዲን ኢብን ሙሐመድን (1472-1487) ደከረ ላይ አሸንፎ ነበር፡፡ ዳሩ ግን በተደረገው መልስ ማጥቃት ተሸነፈና ወደ ይዞታው ሲመለስ ከፍተኛ ሠራዊቱ ያለቀበት መሆኑን ለማስታወስ ደብረ መስዋዕት የምትባል ቤተክርስቲያን አቋቋመ፡፡
ከአሚር ሸምሰዲን በኋላ መሐመድ ኢብን አዝሃረ አደን (1488 – 1518) ተተካ፡፡ይህም ሱልጣን ለክርስቲያኑ መንግሥት ገብሮ በሰላም ለመኖር ፍላጎት የነበረው ቢሆንም እጅግ ኃይለኛና ዝነኛ የነበረው የዘይላው አሚር ማሕፉዝ አይሆንም በማለቱ ጦርነት ከማድረግ በስተቀር ሌላ አማራጭ አልነበረም፡፡
ማሕፉዝ በኋላም የኢማምነትን ማዕረግ በማግኘት የአሚር መሐመድ የጦር አዛዥ በመሆን በአፄ እስክንድር ላይ የቅዱስ ጦርነት አዋጅን አወጀ፡፡ እሱም ያስነሳው ጦርነት የአፄ እስክንድር ወራሽ በሆነው በአፄ ናአድ (1491-1508) ቀጠለ፡፡ ከፍተኛ ጥቃትም አደረሰ፡፡ አፄ ናዖድ፡፡ በኋላም ከአፄ ልብነ ድንግል (1508-1540) ጦር ጋር ገጠሙ፡፡ በርካታ ስፍራዎችን ያዘ፡፡ ሆኖም የአፄ ልብነ ድንግል ጦር ድል እያደረገ ሲሄድ ሱልጣን መሐመድ ሸሸ፡፡ ኢማም ማህፉዝ ግን ከንጉሡ ወገን ጀግና የሆነ በጎራዴ እንዲፋለሙ ጠየቀ፡፡ በዚህ ጊዜ አባገብረ እንድርያስ የተባለ መነኩሴ ሊቀዳኛ ሆነ መነኩሴው በለስ ቀናመና የማህፉዝን አንገት ለመቅላት ቻለ፡፡ ከዚያ በኋላ የንጉሠ ነገሥቱ ሠራዊት የአሚር መሐመድን ሠራዊት እስከ ዘይላ እያሳደደ ጨፈጨፈው፡፡ በርካታ ሀብትን ንብረትም ማረከ፡፡ ዘይላም በ1517 እንዳልነበረች ሆነ ተቃጠለች፡፡
አሚር አሕመድ ከአንድ ዓመት በኋላ ኃይሉን አጠናክሮ የልብነ ድንግልን ሠረዊት ለመውጋት ቢሞክርም አልሆነለትም፡፡ እንዲያውም በጦር ሜዳው ላይ ሞተና ግዛቱ ተከፋፈለ፡፡ አምስት ስልጣኖችም በሁለት ዓመታት ውስጥ ተፈራረቁበት፡፡
ከአሚር አሕመድ በኋላ አል-ገራድ አቡን ኢብን አዳሸ የተባለ ተተካ፡፡ ስለሆነ መሪ የኢማም አሕመድ ኢብን ኢብራሂም (አህመድ ግራኝ) ዜና መዋዕል ዘጋቢ የሆነው ሻሂብ ኢድ-ዲን አሕመድ አብደል ቃድር እንደ ጻፈው የነቢዩ መሐመድ ዝርያዎችን የበለጠ ያቀረበ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የሸረዓን ሕግ አስፍኖ ይኖር ነበር፡፡ ከሱ በኋላ የመጣው አቡበከር ኢብን ሙሐመድ ግን መናገሻ ከተማውን በ1520 ላይ ከደከር ወደ ሐረር አዛወረ፡፡ በዚህም ጊዜ የአዳሉ መንግሥት ዘይላን ብቻ ሳይሆን ከበርበራንና እስከ ጋረዳፉሪይ ተዘረጋ፡፡ ልብነ ድንግልም በበኩሉ የአዳል ገዥዎች ሳይገብሩለት ግዛታቸውን ያስፋፋ ስለነበር ከፖርቱጋሎች ጋር ሆኖ በኃይል ሊያንበረክካቸው ይፈልግ ነበር፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በአዳሉ መግዛት አሕመድ ኢብራሂም አልጋዚ (አሕመድ ግራኝ) የተባለ መሪ በ1506 ተወለደ፡፡ አሕመድ ግራኝም የተወለደው በሱልጣን አቡበከር ዘመን ነበር፡፡ ሺሐብ ኢድ-ዲን አሕመድ ኢብን ዓብዳልቃድር ወይም ዓረብ ፈቂህ የተባለው አሕመድ ኢብራሂም አልጋዚ (አሕመድ ግራኝ) ዜና መዋዕለ ጸሐፊ እንደዘገበው በሱልጣን አቡበከር ዘመን ሞዝበራና ጭቆና በአያሌው ተስፋፍቶ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት አሕመድ ኢብራሂም አልጋዚ (አሕመድ ግራኝ) ሱልጣን አቡበከር፣ ወታደሮቹና በርካታ ሱማሌዎች በሕዝቡ ላይ የሚፈጽሙትን በደልና ቅዱሱን ሕግ በመጣስ የሚፈጽሙት አስፀያፊ ድርጊት በማቃወም ከተወሰኑ ተከታዮቹ ጋር ከሐረር ወጥተው ሑባት እተባለው ስፍራ ተቀመጡ፡፡ እነዚህም ተከታዮቹ የቀድሞው ሱልጣን ገራድ አቡን አገልጋዮች ነበሩ፡፡ አሕመድ ኢብራሂም አልጋዚ (አሕመድ ግራኝ) ከነዚህ ሰዎች ጋር ከሐረር 30 ኪሎ ሜትር ከምትርቀው ሀብት ለጥቂት ጊዜ እንደተቀመጡ ተከታዮቻቸው ወደ መቶዎች ከፍ አሉ፡፡ ከመካከላቸውም ገራድ ዑመር አዲንን መሪ አድርገው መረጡ፡፡
ዓረብ ፈቂ ፉቱሕ አልሐበሻ በተሰኘው መጽሐፍ እንደተገለፀው አሕመድ ኢብራሂም አልጋዚ (አሕመድ ግራኝ) ሑባት በነበረበት ጊዜ ፍኑኤል የሚባል የዳውሮ ገዥ የነበረ ከፍተኛ ባለሥልጣን ወደ እየሩሳሌም ለመሳለም በዚህ ስፍራ አካባቢ ሲያልፍ ሙስሊም ሴቶችንና ሕጻናትን መያዙ ተሰማ፡፡ በዚህ ጊዜ አሕመድ ኢብራሂም አልጋዚ (አሕመድ ግራኝ)ና ተከታዮቹ ፈጥኖ ወደ ስፍራው በመሄድ ጦርነት ገጠሙ፡፡ በዚህ ጦርነት ጎራዴና የጋሻ እርስ በርሱ ሲጋጭ በስተቀር ሌላ ከቶ አይሰማም ነበር፡፡ በመጨረሻም በርካታ ባላባቶችን ወታደሮቻቸው ተገደሉ፡፡ ተይዘው የነበሩት ሴቶችና ሕጻናትም ተለቀቁ፡፡ ሱልጣን አቡበከርና ሱማሌ ተከታዮቹ ይህንን ዜና ሲሰሙ ሐረር ከተማን ለቀው ወደ ሱማሌያ ግዛት ሸሹ፡፡ በኋላ ግን ኃይላቸውን አጠናክረው የአሕመድንና የጓደኞቹን ኃይል ለማዳከምና ተመልሰው ሐረርን ያዙ፡፡ በሁለቱ መካከል በተደረገው ተደጋጋሚ ጦርነት የእነ አሕመድ ኢብራሂም አልጋዚ (አሕመድ ግራኝ) መሪ ዑመርዲንና ዑስማን ኢብን ያሲን ተገደሉ፡፡ አልሰመረም እንጂ የተደረገውን ጦርነት እግምት በማስገባትም ለመታረቅ ሞክረው ነበር፡፡ በመጨረሸም ሱልጣን አቡበከር አሕመድ ግራኝ የሐረር ገዥ ሆነ፡፡ ጭቆናን አስወግዶም ፍትሕን አሸነፈና ተገደለና በምትኩ ወንድሙ የዑመር ዲን ወንድም ተተካ፡፡ በዚህ ጊዜም የአህመድ ግራኝ ወንድም መሐመድ ኢብን ኢብራሂም ሁኔታውን በዓይነ ቁራኛ እንዲከታተል ሐረር ውስጥ እንዲቀመጥ አደረገ፡፡ ከዚያም እንደማሕፉዝ ሁሉ በአፄ ልብነድንግል ላይ ጂሐድ አወጀ፡፡ ይህም አዋጅ የታወጀው በምድር አዳል ያለ ሕዝብ ለአፄ ልብነድንግል መንግሥት እንዳይገበር ባዘዘበት ወቅት ነው፡፡ አፄ ልብነ ድንግልም አማቹና የባለ ገዥ የነበረውን አዝማች ደግለሐንን አዘመተ፡፡ ሆኖም የአዝማች ደግልሃን ጦር እድር በተባለ ቦታ ሸንፈት ደረሰበት፡፡
ከዚያ በኋላ የማሕፉዝ ልጅ የሆነችው ባቲ ድል ወንበራን ያገባው ኢማም አሕመድ ኢብራሂም አልጋዚ (አሕመድ ግራኝ) ዝናው እየገነነ መጣ፡፡ በተለይም የዘይላዎቹ የማህፉዝ ወገኖች ከፍተኛ ድጋፋቸውን ሰጡት፡፡ ዘይላ የባህር ወደብ ከመሆኗም በላይ ከዓረቦች ጋር በነበራት ግንኙነት ከዓረቦች የጦር መሣሪያ ድጋፍ እንዲገባ ለማድረግም እጅግ አመቺ ነበረች፡፡ ለምሳሌ በልብነ ድንግል ላይ ከመዝመቱ በፊት ሰባት መድፎችና ሰባ በደንብ የሰለጠኑና ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቁ ወታደሮች ነበሩት፡፡ በየጊዜው የጦር መሣሪያ ለማስገባት በመቻሉም በአካባቢው ከነበሩት ባለስልጣኖች ብቻ ሳይሆን ከልብነ ድንግል የበለጠ ኃይል ለመሰብሰብ ችሎ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት እስከ 1532 ባለው ጊዜ ደቡባዊና ምስራቃዊ ኢትዮጵያን በተለይም ደዋሮን፣ ባሌን፣ ሐዲያን፣ ገንዝን፣ ወጂን፣ ፋጣጋሪንና ኢፋትን አጠቃሎ ይገዛ ነበር፡፡ ከዚያም እስከ 1543 ባለው ጊዜ ግዛቱን እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ ዘርግቶ ነበር፡፡ በገዛበትም ዘመን መናገሻ ከተማውን ሐረር አድርጎ በሸረዓ ሕግ ሊያስተዳድር እንደነበረ የሚታወቅ ነው፡፡
የኢማም አሕመድ ኢብራሂም አልጋዚ (አሕመድ ግራኝ) መገደል ለ300 ዓመታት ያህል በእስልምናና በክርስትና ሃይማኖት መካከል የተደረገውን ጦርነት እንዲያከትም ያደረገው ከመሆኑም በኋላ ለኦሮሞ መስፋፋት አመቺ ሁኔታን ፈጠረ፡፡ የኦሮሞ መስፋፋት መላው ኢትዮጵያን አጠቃሎ የነበረ ቢሆንም እስከ ዘመነ መሳፍንት የነበረው ታሪካዊ ወቅት ምን እንደሆነ ምን እንደተደረገና መቼ እንደተደረገ ጠለቅ ያለ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ አንድና የማይታሰበው ሃቅ ግን በኦሮሞዎች የመስፋፋት ዘመንም ቢሆን እስልምና መስፋፋቱን እንደቀጠለ እንደነበረ አያጠያይቅም፡፡
እዚህ ላይ መታወስ የሚገባው አብይ ጉዳይ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ በጨለማ ውስጥ የነበረ ቢሆንም በሐረር አካባቢ ግን በተለይም እስልምናን በሚመለከት ጥሩ መረጃ ተጠናክሮ የሚገኝ መሆኑ ነው፡፡ ይህን በሚመለከት ወደፊት የሚቀርብ ይሆናል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በዚህ ጸሐፊ ለኅትመት የበቁትን 1) ኢማም አሕመድ ኢብራሂም አልቓዚ (2005)፣ 2) ኩናባ (2011)፣ 3) ዓይን አብራዎቹ (2011)፣ 4) ሌላው የኢትዮጵያታሪክ ገጽታ (2013) 5) የሐረር አሚሮች (2013)፣ 6) ኢስላማዊ ሥልጣኔ በኢትዮጵያ (2014)፣ 7) ኢስላማዊ ሥነጽሑፍ (2014) መጻሕፍትን ይመልከቱ፡፡
ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡