Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ነዳጅ ማደያዎችን የሚቆጣጠር አዲስ ቴክኖሎጂ በሥራ ላይ ሊውል ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዚህ ቀደም ቁጥጥር ከሚደረግባቸው የነዳጅ ቦቴዎች በተጨማሪ፣ ማደያዎች የያዙትን ነዳጅ በተገቢው መንገድ ለአገልግሎት እያዋሉ መሆን አለመሆኑን ቁጥጥር የሚደረግበት አዲስ ቴክኖሎጂ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ይህንን ያስታወቀው በዲጂታል ነዳጅ ግብይት ላይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ እንደተናገሩት፣ በነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ ለሕገወጥ አሠራሮች የሚዳርጉ ችግሮችን ለመቅረፍ ዲጂታላይዜሽን ሥርዓት አስፈላጊ ነው፡፡

ሕገወጥ የነዳጅ ግብይትን ለማስቀረት ከሚያግዙ ዘዴዎች አንዱ ዲጂታል ግብይት መዘርጋት መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይ የነዳጅ ‹‹ኦርደር ማኔጅመንት ሲስተም›› ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ይህም አሠራር የነዳጅ ማደያዎች ትዕዛዝ ሰጥተው ከጂቡቲ ተጭኖ ሲመጣላቸው ጭምር ያለውን እንቅስቃሴ በቅርበት ለመከታተል የሚያግዝ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የዲጂታል ግብይቱ አሠራር ከጂቡቲ መንግሥት ጋር ንግግር ተደርጎ ሙሉ ለሙሉ በቅርቡ ወደ ትግበራ ይገባል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡ የዲጂታል ግብይት በነዳጅ ቦቴዎች ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ከውጭ አገሮች ገዝታ የምታመጣውን ነዳጅ ጭምር የኤሌክትሮኒክ ግብይት የሚደረግበት ሲስተም ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑንና አሁን ባለው አሠራር 3,500 የነዳጅ ቦቴዎች 3,416 ያህል ጂፒኤስ እንደተገጠመላቸው ተናግረዋል፡፡

የቦቴዎች ቁጥጥር በአንድ ቋት የተደረገ መሆኑንና ሥራውም ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኤጀንሲ ጋር እየተከናወነ መሆኑን አክለዋል፡፡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ሙሉ በሙሉ ለተመግበር፣ በተለይ ሁለት የነዳጅ ማደያዎች ከ1930 እስከ 1940ዎቹ የተቋቋሙ በመሆናቸው ስታንዳርድ አያሟሉም ብለዋል፡፡

የሌሎች አገሮችን ልምድ በመቅሰም አስገዳጅ የሆነ ስታንዳርድ በማዘጋጀት፣ በዚህ መሠረት አንዳንድ ኩባንያዎች ማደያዎቻቸውን ማዘመንና ምቹ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

በመላ አገሪቱ ከግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የተጀመረው የነዳጅ ዲጂታል ግብይትም በዘርፉ የሚያጋጥመውን ማጭበርበር ለማስቀረት ከፍተኛ ጠቀሜታ  እንዳለው፣ ነዳጅ በዲጂታል ግብይት እንዲፈጸም  የተፈለገው ግብይቱን ለማዘመንና ማጭበርበርን  ለመቀነስ እንደሆነ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ተሻለ በልሁ ገልጸዋል።

መንግሥት የነዳጅ ድጎማን እየቀነሰ ወደ ቀጥታው ግዥ ለማስገባት እየሠራ  ሲሆን፣ ይሁን እንጂ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ድጎማው  ይቀጥላል ብለዋል።

እስካሁን ናፍጣ  በሊትር 29 ብር ቤንዚን ደግሞ 25 ብር እየተደጎመ መቀጠሉን ሚኒስትር ደኤታው ገልጸዋል። ነዳጅ በገንዘብ፣ በካርድ፣ በካሽና በኩፖን ግብይት  ሲፈጸም መቆየቱን፣ የካሽ ክፍያ  ከግንቦት ወር ጀምሮ የሚቆም መሆኑን፣ የኩፖንና የካርድ  አገልግሎት የሚጠቀሙት ግን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም.  ይቀጥላሉ  ብለዋል። 

 ወ/ሮ ሳህረላ  በበኩላቸው፣ በቁጥር 40 ሚሊዮን ያህል ግብይት በዲጅታል ደረጃ ክፍያ ተካሂዷል ብለዋል።  ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ ኅብረተሰቡ  እየለመደው እንደሚሄድ ያሳያል ሲሉ አክለዋል።

 በክልሎች ደግሞ 41 ሚሊዮን ብር በኤሌክትሮኒክ ግብይት መከናወኑን ገልጸዋል። በዚህም የነዳጅ እጥረት ያለባቸው ማደያዎችን ለማወቅና ሥርጭቱን ለማፋጠን ይረዳል ብለዋል።  በአዲስ አበባ ያጋጠመው ከፍተኛ ሠልፍ የተፈጠረው ተጠቃሚዎች የይለፍ ቃላቸውን ረስተው በመምጣታቸው መሆኑን፣ ይህንን ለመቅረፍ የግንዛቤና የውይይት ሥራዎች ተሠርተዋል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፣ በአሁኑ ጊዜ ዲጅታላይዝ  በሚደረገው የነዳጅ ግብይት ከቦቴዎች ላይ መሆኑን አውስተው፣ በአብዛኞቹ ቦቴዎች ጂፒኤስ ተገጥሞላቸዋል።  በዚህ ምክንያት በነዳጅ ማጓጓዝ  ቅሸባ ላይ ይታጣል ተብሎ የሚታሰበውን ሁለት ቢሊዮን ብር ያስቀራል ብለዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም  የሞባይል መኒ ኃላፊ አቶ  ብሩክ አድሀና  እንዳሉት፣ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የነዳጅ ግብይት በቴሌ ብር ተፈጽሟል።

  ባለሙያዎች በማደያዎች በመገኘት ደንበኞች የይለፍ ቃል እንዲያገኙ  እየተሠራ ነው ብለዋል።  የቴሌ ብር ደንበኞች 31 ሚሊዮን ደርሰዋል ያሉት ኃላፊው  100 ማደያዎች ቴሌ ብር ይጠቀማሉ ሲሉ አስረድተዋል።

ደንበኞች በማንኛውም ማደያ እንዳይቸገሩ  ባለሙያዎችን በመመደብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን፣ የገለጸው  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣  በሲቢኢ ብር (CBE Birr)  አገልግሎቱን በቀጥታ ማግኘት የሚቻልበትን ዕድል ማመቻቸቱን፣ የሲቢኢ ብር ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ እንዳለማው ገልጸዋል። 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች