Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበአማራ ክልል ፃግብጂን ከሰቆጣ የሚያገናኘው ድልድይ በመሰበሩ ነዋሪዎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸው ተሰማ

በአማራ ክልል ፃግብጂን ከሰቆጣ የሚያገናኘው ድልድይ በመሰበሩ ነዋሪዎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸው ተሰማ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በአማራ ክልል በዋግኸምራ ብሐረሰብ ዞን የፃግብጂ ወረዳን ከዞኑ ዋና ከተማ ሰቆጣ የሚያገናኘው ብቸኛው የጥራሬ ወንዝ ድልድይ በመሰበሩና ምንም ዓይነት ጥገና ሳይደረግለት በመቆየቱ፣ ከ75 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የወረዳው ነዋሪዎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸው ተነገረ፡፡

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሕወሓት ታጣቂዎች ሥር የነበረው የፃግብጂ ወረዳ፣ ከ30 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለው በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደነበር ይታወሳል፡፡

- Advertisement -

ይሁን እንጂ በመንግሥትና በሕወሓት መካከል በተደረገው የሰላም ስምምነት መሠረት ሚያዝያ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በመከላከያና በወረዳው ሚሊሻ በመታገዝ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ መደረጋቸውን፣ የፃግብጂ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሡ ደሳለኝ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው በጦርነቱ ወቅት ‹‹በሕወሓት ታጣቂዎች ተሰብሯል›› ያሉት የጥራሬ ወንዝ ድልድይ ጥገና የተደረገለት ባለመሆኑ፣ በከፋ ችግር ውስጥ የነበሩት ነዋሪዎች ወደ ቀዬአቸው በሚመለሱበት ወቅት ለተጨማሪ እንግልት ተዳርገው እንደነበር፣ ወንዙ በመሙላቱ ከአራት ቀን በላይ ያለምንም ምግብና ልብስ ወንዝ ዳር መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡

ከወንዙ ጀምሮ የወረዳው ዋና ከተማ ከሆነችው ፆታ ድረስ፣ ነፍሰ ጡር እናቶችና ሕፃናት ከ15 ኪሎ ሜትር በላይ በእግራቸው ተጉዘው መድረሳቸውን አቶ ንጉሡ ተናግረዋል፡፡

ከሦስት ቀናት በላይ በረሃብ የቆዩ እናቶችና ሕፃናት፣ እንዲሁም አረጋውያን ለተጨማሪ የእግር ጉዞ መዳረጋቸው በእጅጉ አሳዛኝ ነው ሲሉ ነው የገለጹት አቶ ንጉሡ፣ ወደ ቀዬአቸው ሲመለሱም ከሁለት ዓመት በላይ ለዝርፊያ ተጋልጦ የነበረ ባዶ ቤት ነው የጠበቃቸው ብለዋል፡፡

ቤታቸውን ሳይለቁ በጦርነት ውስጥ የነበሩ ነዋሪዎችም ቢሆኑ ከመንግሥት አገልግሎት ርቀው በመቆየታቸው፣ እንዲሁም የዕለት ተዕለት ሥራቸውን በአግባቡ ባለማከናወናቸው በአሁኑ ወቅት ለከፋ ረሃብና ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ ዋና አስተዳዳሪው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ቢመለሱም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀበረት ጊዜ ድረስ በወረዳው በመንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ ምንም ዓይነት ዕርዳታ ወደ ወረዳው እንዳልገባ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ከ75 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የወረዳው ነዋሪዎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን አክለዋል፡፡

መድኃኒትም ሆነ የምግብ ዕርዳታን ወደ ወረዳው ለማስገባት የድልድዩ ጥገና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ፣ ለክልሉና ለፌዴራል አካላት ሪፖርት ያደረጉ ቢሆንም ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አብራርተዋል፡፡

መንግሥት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ቅድሚያ በመስጠት እየሠራ ቢሆንም፣ ነገር ግን በፃግብጃ ወረዳ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አላደረገም ብለዋል፡፡

ድልድዩ በብረት የተሠራ ስለነበር መልሶ በመገጣጠምና ቶሎ ወደ ሥራ ለማስገባት ቀላል ቢሆንም፣ በፌዴራል ደረጃ የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ በአሁኑ ወቅት ዝናብ እየጣለ በመሆኑ የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት በአፋጣኝ ምላሽ ካልሰጡበት በወረዳው አሁን ካለው የከፋ ችግር በላይ ሊያጋጥም እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

በማኅበራዊ የጤና አገልግሎት ዘርፍ ወደ ሥራ የተገባ ቢሆንም፣ የመድኃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ መሥራት እንዳልቻሉና በዚህም ሕይወታቸውን ያጡ እናቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ከሁለት ዓመታት በላይ ከትምህርት ገበታቸው ርቀው የቆዩ ከአንድ ሺሕ አምስት መቶ በላይ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ እየተሠራ ቢሆንም፣ ግብዓት ማስገባት ባለመቻሉ ወደ ተግባር መግባት አልተቻለም ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል አሁንም ቢሆን ወረዳው ሙሉ በሙሉ ነፃ ያልወጣ በመሆኑ፣ በመከላከያ ሥር ያልገቡ በርካታ ቀበሌዎች መኖራቸውን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡ ራሳቸውን የአገው ሸንጎ ብለው የሚጠሩት ታጣቂዎች የተለያዩ የወረዳው ቀበሌዎችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ ተናግረው፣ መከላከያ ሠራዊት በሦስት ቀበሌዎች ብቻ እንደሚንቀሳቀስ አክለዋል፡፡

ከእነዚህ አካላት ጋር መከላከያ ወደ ግጭት ከመግባት ይልቅ በሰላም ስምምነቱ መሠረት መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ ይፈጸማል ተብሎ ቢታሰብም፣ ስምምነቱን ያልተቀበሉት የአገው ሸንጎ ታጣቂዎች አሁንም ገባ ወጣ እያሉ መሆናቸውን አቶ ንጉሡ አክለዋል፡፡

ታጣቂዎቹ በሚገኙባቸው ቀበሌዎች ምንነቱ ያልተገለጸ ‹‹ወረርሽኝ›› መከሰቱን ገልጸው፣ ነገር ግን ስለተከሰተው በሽታ ምንነት መረጃ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት በወረዳው ያሉ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ሙሉ በሙሉ የወደሙ በመሆናቸውና በአሁኑ ወቅትም ለመልሶ ግንባታ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ያልተጀመረ መሆኑን ያወሱት ዋና አስተዳዳሪው፣ የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ የመልሶ ግንባታ ሥራ እንዲጀምር ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...