Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መባባስ ጋር በተያያዘ ፓርላማው አስፈጻሚውን እንዲጠይቅና እንዲያሳስብ ኢሰመኮ ጠየቀ

የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መባባስ ጋር በተያያዘ ፓርላማው አስፈጻሚውን እንዲጠይቅና እንዲያሳስብ ኢሰመኮ ጠየቀ

ቀን:

  • የተጠርጣሪዎችን ቤተሰቦች አስሮ ማቆየት አሳሳቢ መሆኑ ተጠቁሟል

በተለያዩ አካባቢዎች እየተባባሱ ናቸው ለተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈጻሚውን አካል እንዲጠይቅና እንዲያሳስብ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጥያቄ አቀረበ፡፡

ኢሰመኮ ጥያቄውን ያቀረበው ሰኞ ሚያዝያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ ነው፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ባቀረቡት ሪፖርት፣ በአማራ ክልል እየተከናወነ ባለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ እስካሁን ድረስ በንፁኃን ሰዎች ላይ የሞት፣ የመቁሰል፣ የሀብት ውድመትና የመፈናቀል ጉዳት ከመድረሱም በላይ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ድርጊቱ በሰብዓዊ መብት ላይ ከፍተኛ ሥጋት ያሳደረ በመሆኑ፣ ችግሩ ሳይባባስ ፓርላማው አስፈጻሚውን የመንግሥት አካል እንዲያሳስብ ጠይቀዋል፡፡

- Advertisement -

የዘፈቀደ እስርና በእስር ወቅት የሚፈጸሙ ተገቢ ያልሆኑ አያያዞች መኖራቸውን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፣ በአንዳንድ ማቆያ ቦታዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ድብደባ፣ እስራትና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለመከበር አሁንም መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በተወሰኑ ቦታዎች ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የቤተሰብ አባላትን የሚያጠቃ የዘፈቀደ እስር መኖሩን የጠቀሱት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ለአብነትም ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ውስጥ የክልሉ ፖሊሶች ለምርመራ የፈለገውን ሰው አስገድዶ ለማስመጣት፣ የአንድ ዓመትና የአምስት ዓመት ሕፃናት ልጆች የያዘች ባለቤቱን ለሦስት ቀናት አስረው ማቆየታቸውን ለማሳያነት አቅርበዋል፡፡

ግለሰቧ ከሕግ አግባብ ውጪ መታሰሯን ለኮሚሽኑ ጥቆማ በመድረሱ በተደረገ ክትትል፣ ታሳሪዋ በሦስተኛው ቀን መፈታቷን አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች መሰል ክስተቶች እየታዩ መሆናቸውን የጠቀሱት ዳንኤል (ዶ/ር)፣ ተጠርጥረው የሚፈለጉ ሰዎችን ለመያዝ በሚደረገው እንቅስቃሴ፣ ልጆች ሲፈለጉ ወላጆችን መያዝና በእስር የማቆየት የሕግ ጥሰቶች መቀጠላቸውን ገልጸዋል፡፡

በተቃውሞ ሠልፎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል እየተጠቀሙ መሆኑን ሲያብራሩም፣ ሕይወት የሚያጠፋ መሣሪያ በመጠቀም ሠልፍን የመቆጣጠር ድርጊት ኮሚሽኑ መመልከቱንና በተደጋጋሚ የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት እንደደረሰ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል አሳሳቢነቱ እየጨመረ መሆኑን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ በጋዜጠኞች፣ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በተቃዋሚ ድምፆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነው፡፡     በዚህ አሳሳቢ ችግር ውስጥ የፀጥታና የአስፈጻሚ አካሉ በሚወስዱት ዕርምጃ ግለሰቦቹ ለጥቃት የተጋለጡት በጋዜጠኝነታቸው ወይም በሚዲያ ሥራቸው አይደለም በሚል አበክረው ቢከራከሩም፣ ሁኔታው ብዙም አሳማኝ ሆኖ አልተገኘም ብለዋል፡፡   በተደጋጋሚ የሚታሰሩ ሰዎች ሲለቀቁ እንደተፈጸመው ሁሉ፣ ወንጀል ለመፈጸሙ ማስረጃ ተደርጎ ሲነገር የሚሰማው በሚሠሩበት የሚዲያ ተቋም አማካይነት ጽፈዋል የሚል መሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

ይሁንና በጋዜጠኝነት ሥራቸው ተፈጸመ ከተባለም፣ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እንደተደነገገው በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ለተፈጸመ ወንጀል የቅድመ ክስ እስር አለማስፈለጉን፣ የተፈጸመ ወንጀል ካለ ደግሞ በቀጥታ በዓቃቤ ሕግ አማካይነት ክስ መቅረብ ነበረበት በማለት፣ ‹‹ነገር ግን በአጠቃላይ በፖለቲካ ሁኔታው ላይ የተቃውሞ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት የሚመስል ዕርምጃ በተደጋጋሚ እየተመለከትን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በተለይም ፌስቡክና ዩቲዩብ በመሳሰሉት መገናኛ ዘዴዎች መንግሥት ራሱ መረጃ የሚያሠራጭባቸው ሆነው ሳለ፣ አሁንም እንደተገደቡ መቀጠላቸው ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ዳንኤል (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብት ላይ የተጣሉ የዘፈቀደ ገደቦች አሳሳቢ መሆናቸውን አውስተው፣ በተለይ ከአማራና ከትግራይ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ለሚፈልጉ ሰዎች ሁኔታው ቀላል አይደለም ብለዋል፡፡

‹‹አንድ ሰው ምናልባት ነገ ከትግራይ ክልል በአውሮፕላን ተሳፍሮ አዲስ አበባ ለመምጣት ቢፈለግ ሰዎች እንደሚያስቡት ቀላል አይደለም፣ መሥፈርቶች አሉ፡፡ የሚፈቅዱና የሚከለክሉ ሰዎች አሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ሁኔታው ቀላል አይደለም፤›› ብለው፣ እነዚህ የዘፈቀደ ክልከላዎች ፈፅሞ ተቀባይነት የሌላቸውና አንዳችም ሰብዓዊ ምክንያት ያላቸው አይደሉም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የሰላም መደፍረስንና በታጠቁ ቡድኖች የሚደረግ እንቅስቃሴን በተመለከተ ያስረዱት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ይህ ችግር የሰዎችን በሕይወት የመኖር፣ በሰላምና በደኅንነታቸው ላይ ሥጋት ደቅኗል ብለዋል፡፡

ሕጋዊ ሒደትን ያልተከተለ ቤቶችን ማፍረስና በግዳጅ ማስነሳት ሌላው አሳሳቢ ሆኖ የቀጠለ ችግር ሆኖ መቀጠሉን ያብራሩት ዳንኤል (ዶ/ር)፣ በዚህም ሳቢያ በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ከመድረሳቸው በተጨማሪ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በጦርነቱ የተጎዱ የትግራይ፣ የአፋርና የአማራ ክልሎች አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ ገና እጅግ ብዙ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸው፣ ዜጎች በዚህ ችግር የተነሳ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተጋለጡ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ታሳሪዎችን ለመጠየቅ በሚሄዱበት ወቅት ታሳሪዎችን ማግኘት አለመቻሉን የጠቀሱት ዋና ኮሚሽነሩ፣ የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች በወታደር ካምፕ፣ በሥልጠና ካምፕ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በትክክል ምንነቱ ያልታወቀ ነገር ግን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ ቦታ ውስጥ መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ ችግር አሳሳቢነቱ መቀጠሉን ዋና ኮሚሽነሩ ጠቁመው፣ በማረሚያ ቤቶች ያለው አያያዝ ትርጉም ያለው መሻሻል እንዳለው አክለው ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት አስፈጻሚ አካል በተወሰነ ደረጃ ኮሚሽኑ የሚያቀርባቸውን ምክረ ሐሳቦች የመቀበል ሁኔታ ቢያሳይም፣ በተለይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በኮሚሽኑ የሚሰጡት ምክረ ሐሳቦች ተፈጻሚ ባለመሆናቸው ምክር ቤቱ አስፈጻሚ አካሉን ሊጠይቅ ይገባል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...