የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከኢትዮጵያ ጋር በሕክምናው ዘርፍ የልምድ ልውውጥ በማድረግ፣ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ፣ በሌሎች አገሮች ውድ የሚባሉ ሕክምናዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመስጠትና በአጠቃላይ በሜዲካል ቱሪዝም ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር መሥራት እንደምትፈልግ የዱባይ የኢኮኖሚና ቱሪዝም ዲፓርትመንት (ዲኢቲ) አስታውቋል፡፡
ከሚያዝያ 23 እስከ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በዱባይ ለ30ኛ ጊዜ የተካሄደውን የዓረቢያን ትራቭል ማርኬት አስመልክቶ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ለመጡ ጋዜጠኞች ቃለ መጠይቅ የሰጡት የዱባይ ኢኮኖሚና ቱሪዝም ዲፓርትመንት ዓለም አቀፍ ኦፕሬሽን ተባባሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስ ሆር አልካጃ እንዳሉት፣ ዱባይ በዓለም በሕክምናው ዘርፍ በቴክኖሎጂ ከበለፀጉና በተለይም ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ዘመናዊ ሕክምና ከሚሰጡ ቀዳሚ አገሮች የምትመደብ ናት፡፡ ይህንን ልምዷን ለኢትዮጵያ ማካፈልና በሜዲካል ቱሪዝም ዘርፍ በኢትዮጵያ የማይገኙ የሕክምና አገልግሎቶችን ለመስጠትም እየሠራች ትገኛለች፡፡
በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ሕክምና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወደሚታገዝበት ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን፣ ይህም ሕሙማንን በተመጣጣኝና ከሌሎች አገሮች ሲነፃፀር ዝቅተኛ በሚባል ወጪ ጥራቱን የጠበቀና ፍቱን ሕክምና ለመስጠት እንደሚያስችል አክለዋል፡፡
እንደ ሚስ ሆር፣ አገራቸው በሕክምና ባለሙያ፣ በዘመናዊ መሣሪያ፣ በመድኃኒትና በሕክምና ግብዓት የተሟሉ የሕክምና ተቋማት ያሏት ሲሆን፣ የሕክምና ወጪ ሙሉ ለሙሉ ከፍለው መታከም ለማይችሉ አስተያየት የሚደረግበት አሠራርም አለ፡፡
‹‹አንድ ታካሚ ገንዘብ ስላጠረው ብቻ ሳይታከም አይመለስም፤›› ያሉት ሚስ ሆር፣ የዱባይ የጤና ባለሥልጣን በሜዲካል ቱሪዝም እየሠራ እንደሆነ፣ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ በሜዲካል ቱሪዝም ዘርፍ አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ስትራቴጂ መነደፉንም አክለዋል፡፡
‹‹በዱባይ ሜዲካል ቱሪዝም እንዲያድግ የምንፈልገውና እየሠራንበት ያለ ዘርፍ ነው፣ ከዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካውያን ሊጠቀሙ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡
በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በዱባይ ብቻ 56 ሆስፒታሎችና ከ1,600 በላይ ምርመራ የሚያካሂዱና በተመላላሽ የሚያክሙ ስፔሻላይዝድ ክሊኒኮች የሚገኙ ሲሆን፣ የኩላሊት ንቅለ ተከላን ጨምሮ የሰውነት ኦርጋንና የቲሹ ትራንስፕላንት አገልግሎትም ይሰጣል፡፡፡
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በአፍሪካ በኢትዮጵያ፣ በናይጄሪያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በኬንያና በጋና በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዘርፎች እየተሳተፉ መሆኑ ይታወቃል፡፡