የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከገባች 12 ዓመታትን ያስቆጠረችውን ሶሪያ፣ ከገባችበት ጦርነት ለማውጣት ከወራት በፊት ጀምሮ እንቅስቃሴ የጀመሩት የዓረብ አገሮች ሶሪያ ወደ ዓረብ ሊግ አባልነት ዳግም እንድትቀላቀል ፈቅደዋል፡፡
በሶሪያ መንግሥትን ለመለወጥ እ.ኤ.አ. በ2011 የተቀጣጠለው አብዮት መስመር ስቶ አገሪቱን ለእርስ በርስ ጦርነት በመዳረጉና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ መንግሥት በመፍረክረኩ የዓረብ ሊግ ሶሪያን ከአባልነት አግዶ የነበረ ሲሆን፣ ከወር ወዲህ በሶሪያና በዓረብ አገሮች መካከል ያሉ ግንኙነቶች መታደሳቸውን ተከትሎ ሊጉ ሶሪያ ዳግም እንድትቀላቀል መወሰኑን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በተያዘው ወር ማብቂያ በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ ከሚደረገው የዓረብ ሊግ ጉባዔ አስቀድሞ ሶሪያ ዳግም ወደ ሊጉ እንድትቀላቀል መወሰኑም፣ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ በጉባዔው እንዲሳተፉ ያስችላል ሲል ቢቢሲ ገልጿል፡፡
ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በግብፅ ካይሮ የተሰባሰቡት 22 የዓረብ ሊግ አባል አገሮች ሚኒስትሮች ሶሪያ ወደ ሊጉ እንድትመለስ የወሰኑ ሲሆን፣ በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የተፈጠሩ በርካታ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በጎረቤት አገሮች የሚገኙ የሶሪያ ስደተኞች፣ የአደንዛዥ ዕፅ ሕገወጥ ዝውውርና በርካታ ችግሮች መፍትሔ ሊያገኙ ይገባልም ብለዋል፡፡
የሶሪያ ወደ ዓረብ ሊግ ዳግም መቀላቀል ‹‹አዎንታዊ ዕርምጃ ነው›› ያሉት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ዲፕሎማቲክ አማካር አንዋሪ ጋርጋሽ፣ አገራቸው ቀጣናው እንዲረጋጋ ከሶሪያ ጋር ያለውን ግንኙነትና ትብበር ማጠናከር ያስፈልጋል ብላ እንደምታምን ተናግረዋል፡፡
ኳታር የሶሪያን ዳግም ወደ ሊጉ መመለስ ብትደግፍም ከሶሪያ ጋር ያላት ግንኙነት ወደ መደበኛ የሚለወጠው በሶሪያ ያለው ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሔ ሲያገኝ እንደሆነ አስታውቃለች፡፡
የዓረብ ሊግ አባላት ሶሪያ ወደ ሊጉ ዳግም እንድትመለስ ቢወስኑም፣ አሜሪካ ‹‹ሶሪያ አይገባትም›› ስትል ቅሬታዋን ገልጻለች፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ‹‹የሶሪያን ወደ ዓረብ ሊግ መመለስ አሜሪካ አታምንበትም፣ ይህን ለሁሉም የእኛ አጋሮች ግልጽ ማድረግ የምንፈልገው ነው፤›› ብለዋል፡፡
በሶሪያ ላለው ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማበጀት፣ የሰብዓዊ ዕርዳታን ተደራሽ ለማድረግ፣ የኢራንን ተፅዕኖ ለመቀነስና ሰላምን ለማስፈን የተቀመጡ የጋራ ግቦች ላይ ግን ከሌሎች ዓረብ አገሮች ጋር እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡
ሩሲያ የሶሪያን ወደ ዓረብ ሊግ መመለስ በአዎንታዊ ጎኑ የተቀበለች ሲሆን፣ ሶሪያ ወደ ሊጉ እንድትመለስ ኢንሺየቲቩን ያስጀመረችው ጆርዳን፣ ውሳኔው ሶሪያ ለገባችበት ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንድታመጣ ያግዛል ብላለች፡፡
በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት በተጀመረበት በ2011 የመጀመርያዎቹ ዓመታት ሳዑዲ ዓረቢያ ለአማፂ ቡድኖች ታግዝ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ነገሮች ተቀይረዋል፡፡ በተለይ በቻይና አሸማጋይነት ከኢራን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር ከተስማሙ በኋላ፣ በሶሪያ ያለውም ግንኙነት ከመራራቅ ይልቅ ወደ መቀራረብ ተለውጧል፡፡
በሳዑዲ ዓረቢያና ኢራን መካከል የተፈጠረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም ሳዑዲ ዓረቢያ በሶሪያ የኮንሱላር አገልግሎት ዳግም ለመጀመር የሚያስችላትን ውይይት እንድታደርግ ዕድል ፈጥሯል፡፡
አልጀዚራ እንደሚለውም፣ ሶሪያን ወደ ዓረብ ሊግ መመለስ የቀጣናውን ሰላም ለማስፈን ወሳኙ ዕርምጃ ነው፡፡