Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበአገር ደረጃ ለመነጋገርና ለመተማመን ትኩረት እንስጥ!

በአገር ደረጃ ለመነጋገርና ለመተማመን ትኩረት እንስጥ!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

በአገራችን የጥንቱን ታሪክ ብንተወው እንኳን በዘመናዊ የመንግሥት አስተዳደር ጉዞ ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶች፣ መውደቅና መነሳቶች ታልፈዋል፡፡ በፖለቲካ ሥልጣን ሽሚያና ግብግብ ውስጥም ሚሊዮኖች ሞተዋል፣ ቆስለዋል፣ ለአካልና ለሥነ ልቦና ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ወላፈኑ የገረፋቸው የየዘመኑ ትውልድም “ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ” በማለት ግዴታቸውን ቀርቶ፣ መብታቸውንም እርግፍ አድርገው እስከመተው አድርሷቸው ቆይቷል፡፡

ዘውዳዊው ሥርዓት በወታደራዊው ጁንታ ሲተካ የተማረው ወገን ቀደም ሲል ያቀነቅነው የነበረውን ለውጥ ዕውን ለማድረግ ሲንቀሳቀስ፣ በሁሉም ወገን መፍትሔው ኃይል ተደርጎ ተወስዶ ነበር፡፡ በዚህም ከግራም ከቀኝም በተለይ በነጭና በቀይ ሽብር ሰበብ በሺዎች የሚቆጠሩ አገር ሊለውጡ የሚችሉና የትውልድ አስኳል የሚባሉ የአገር ተስፋዎችና ምሁራን ረግፈዋል፡፡ የዚያ የግፍ ዘመን ጠባሳ ዛሬም ድረስ ከሕዝባችን አዕምሮ ተወግዷል ማለት አይቻልም፡፡

ከዚያ በኋላም ደርግ በቆየባቸው 17 ዓመታት ሥልጡን የመነጋገር መንገድና የዴሞክራሲ ባህል ጭላንጭል ማየት ተስኖን እንደ አገር ያጣነው ትውልድ፣ ሀብትና አገራዊ እሴት ከፍተኛ የሚባል ነበር፡፡ የፖለቲካ ስክነቱና አለመግባባቱ በመራቁ ልማትም ሆነ ድህነት ቅነሳው ሊገፋ ካለመቻሉ ባሻገር፣ የውጭ ጫና እየታከለበት አገርን አዳክሟል፡፡ ያሳረፈው ጠባሳም እስካሁንም ፈጥጦ እየታየ ነው፡፡ ኪሳራውም በውርደት ታሪካችን ተመዝግቦ መቀመጡ አይቀሬ ነው፡፡

ለነገሩ አንፃራዊ ሰላምም ሆነ የምጣኔ ሀብት ዕድገት በታየበት የኢሕአዴግ ዘመንም ቢሆን የፖለቲካ መጠላለፉ ከግድያ የፀዳ ነበር ሊባል አይችልም፡፡ በተለይ በ1997 ዓ.ም. የተስፋ ብርሃን ፈንጥቆ የነበረው የዴሞክራሲ ሙከራ የከሸፈበትና መልሰን ወደ ፖለቲካ ትርምስና መገዳደል ብሎም መጠላላፍ የተወደቀበት የቀውስ መንገድ ሌላ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ስለማለፍ ብዙዎች የሚያስታውሱት ነው፡፡ ወደኋላ ባሉት ዓመታት ለተፈጠረው የሰላማዊ ትግል መዳከምና የአመፃ በር መከፈትም ስብራቱ የጀመረው እንዲህ ያለው ወቅት ላይ እንደነበር ያስታውሷል፡፡

ቅሬታውና የማኅበረሰቡ ተቃውሞ እየበረታ ሄዶ በሥርዓቱ ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ኃይል የለውጥ ግፊት በማድረጉ፣ ቀስ በቀስ በ2010 ዓ.ም በአንፃራዊነት ሰላማዊ ለውጥ ሲመጣ  ሁሉም ተስፋ አድርጎ የነበረው ከዚሁ መነሻ ነበር፡፡ በእርግጥም ተስፋ ሰጪ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዓውድ ተፈጥሮ ነበር ማለትም ይቻላል፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ግን በፖለቲካ መፈላቀቅ፣ በማንነትና በሃይማኖት መገፋፋት ሰበብም ይባል ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ባለማስተናገድ ልክፍት የቀጠለው የፖለቲካ ሽኩቻ ተባብሶ፣ አሁንም መገዳደሉ ሊቆም አልቻለም፡፡ ያውም አዲስ የለውጥና የመተሳሰብ ባህል ይገነባበታል በተባለውና ተስፋ ተጥሎበት በነበረው የምንገኝበት የታሪክ ምዕራፍ ላይም ሆነን የተጠናወተን ልክፍት አለመላቀቁ ነው የሚቆጨው፡፡

የሚያሳዝነው ደግሞ ከትናንቱም በባሰ ደረጃ የጎሳ ትርክቱ እየተባባሰ፣ ጥላቻና የትርክት መደነባባሩ ተስፋፍቶ መቀጠሉ ነው፡፡ በአንድም በሌላም ሕይወታቸው ያለፉ የፖለቲካ ሰዎችም ሆኑ ንፁኃን ሳይቀሩ ለፖለቲካ ሴራ መነገጃ ሲሆኑ ዓይተናል፡፡ ይህም ተጨማሪ የራስ ምታት ሆኖ እየቀጠለ መሄዱ የሚያሳዝን ነው፡፡

“ይህ አካሄድ ግን እስከ መቼና የት ሊያደርሰን ይሆን?” ብሎ መጠየቅ፣ ቆም ብሎ በጥንቃቄ ማሰለሰልና መነጋጋር ካልተቻለ በዚያው በዜሮ ድምር ፖለቲካ ተርመጥምጦ ከመጠፋፋት ውጪ የሚገኝ ነገር አይኖርም፡፡ እውነት ለመናገር አሁን በሚታየው ጫፍና ጫፍ የረገጠ የመጠላላፍና የመጠፋፋት ፖለቲካም ሆነ ፕሮፓጋንዳና መጠራጠር አገር ምን ልታተርፍስ ትችላለች? ሕዝብስ እንደምን ዕፎይ ለማለት ይቻለዋል? ሁላችንም ወደ ቀልባችን ተመልልሰን ልናጤነው የሚገባ ሀቅ ነው፡፡

በቅርብ የማውቀውን የአቶ ግርማ የሺጥላንና የግል ጠባቂዎቹን ግድያ መርዶ በሰማሁ ጊዜ የተሰማኝ አሳዛኝ ስሜት ከግለሰቦች (ለቤተሰቦቻቸው ያለው ጉዳት ባይዘነጋም) ጥቃትም በላይ፣ የአገር ውድቀት ፍርኃትና ዋስትና የማጣት ስብራት ነው፡፡ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ባለፈችና ገና ከችግር ባልወጣች አገር የሚኖር ዜጋ እንዴት በመገዳደልና በመጠፋፋት ብቻ የፖለቲካ ችግር ይፈታል ብሎ ሊያስብ ይችላል? ያውም የትናንቱን ቀውስ በሰላም ለመፍታት ደፋ ቀና እየተባለ፡፡ አምላክ ይሁነን፡፡

አሁንም መንግሥት፣ ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች፣ የፀጥታና የደኅንነት ኃይሎች፣ የእምንት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ በተለይ በውጭ አገሮች ያሉ “የማኅበረሰብ አንቂዎች” እና የፖለቲካ ኃይሎች ከጥላቻ፣ ከተካረረ ትርክትና ከእልህ፣ እንዲሁም የመጠፋፋት አዙሪት እንዲወጡ በትህትና መማፀን ይበጀናል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም እንደ መንደር አሽሙረኛ በመግለጫ ከመነዳደፍ ወጥተው ስለአጠቃላዩ አገራዊ መፍትሔ እንዲያተኩሩ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡

ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሆይ እናስብበት፡፡ አገር ፈርሳ አይደለም ተዋርዳና ተናግታም መመለሻው አይታሰብምና መደማማጥን እናስቀድም፡፡ ከሩቅም ሆነ ከቅርብ የደቀቁ አገሮችና እየተንኮታኮቱ ካሉ መንግሥታት ተምረን ከዜሮ ድምር ፖለቲካ እንውጣ ብሎ መሞገት ያስፈልገናል፡፡

እንዳው ለነገሩ ሰላማዊ ምክክር፣ በሆደ ሰፊነት መደራደርና ዘመኑን የዋጀ ሰጥቶ የመቀበል የፖለቲካ ብሒል መከተልስ እንዴት ሊከብድ ይችላል፡፡ ሁሉንም ችግሮች ወይም አለመግባባቶች በጉልበትና በጠመንጃ ለመፍታት የሚደረገው ሩጫስ እስከ መቼ ሊቀጥል ይችላል? ምን ያህልስ ሊያወጣ ይችላል ብሎ ማብሰልሰል ካልተቻለ ውድቀታችን መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ወገን ለሰላምና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንድከም፡፡

ከአምስት ዓመታት ወዲህ እንደ አገር ከተጀመረው ለውጥ ወዲህ እንኳን በትግራይ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ብቻ ሳይሆን በብዙዎቹ የአገራችን አካባቢዎች ምን ያሀል ግጭቶችና የፖለቲካ ግድያዎች እንደተፈጸሙ አንረሳውም፡፡ የወደመው ሀብትና በዜጎች ላይ የደረሰው የስነ ልቦና ጉዳት ብዛት የትዬለሌ እንደነበር መቼ ይረሳል?

በዚያው ልክ ለቀጣዩም ቢሆን የታቀደውና እየተፈጸመ ያለው ዘመቻ ትልቅ ግምት የሚሰጠው መሆኑን ማን ይስተዋል? በእስካሁኑ ሒደት የተሞከረው የፖለቲካ ጥረትና የመደራደር ሙከራው ግን እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ከሕወሓት ጋር የተደረገው ድርድርም ቢሆን ከከፍተኛ ኪሳራ በኋላ የተሞከረ ብቻ ሳይሆን፣ ገና በለጋ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

በእነዚህ የውጣ ውረድ ዓመታት ውስጥ በፖለቲካው መቃወስ ምክንያት እየተነሳ ያለውን ችግር ለመመከት፣ ሠራዊቱና መደበኛው ፖሊስ ለከፍተኛ መስዋዕትነትና መንከራተት ከመዳረግ አለማዳኑም በጥሞና ሊታይ የሚገባው ነው፡፡

ይህ ሰፊ ኃይል በአንድ በኩል በፖለቲካው መቃወስና አካታች አለመሆን በየአካባቢው ንፋስ እንደነካው የሰደድ እሳት የሚንበለበለው ነበልባል ለማጥፋት፣ እዚያና እዚህ መባካኑ አድካሚና አሰልቺ መሆኑ አይቀርም፡፡ በሌላ በኩል ግጭቶቹ በአንድም ይሁን በሌላ ሰላም አስከባሪውን ስለሚመለከቱና የእርስ በእርስ ግድያዎቹም ያለመታደል ሆኖ እንጂ፣ በወንድማማቾች መሀል እየተፈጸሙ ያሉ እንደ መሆናቸው ቅራኔ ማባባሳቸው አይቀርምና አፋጣኝ መፍትሔ ይፈልጋሉ፡፡

የምንገኝበት ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ሁሉ ነገር ለመረጃና ለሐሳብ ነፃነት የተጋለጠበት ወቅት ነው፡፡ የእውነትም ሆነ የሐሰተኛ መረጃዎች እንደ ጉድ በደቂቃዎች ውስጥ ከአንዱ አፅናፍ ወደ ሌላው በቀላሉ እየተፈበረኩ የሚዳረሱበት እንደ መሆኑ፣ የሚደበቅና የሚገደብ ነገርም የለም፡፡ ስለሆነም አካሄድን በሠለጠነና ትውልድን በዋጀ አግባብ ማስኬድ እንጂ በትናንቱ መልክ ለመራመድ መሞከር አገርን የሚጎዳ ነው፡፡

ለማንም ቢሆን “ሁሉንም አስቸጋሪ ሁኔታዎችና አለመግባባቶች በኃይልም ሆነ በመገዳዳል ብቻ ፈጽሜ አጠናቅቃለሁ” ለማለት የሚቻል አይሆንም፡፡ ያውም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሕዝቡ ጭምር አቋም እየያዘባቸው የመጡ አጀንዳዎችንና በጥላቻ ትርክት የተሳከሩ አሉታዊ ዕሳቤዎችን (የብሔር መጠራጠር ልክፍቶችን) ሁሉ፣ በኃይልና በዘመቻ ለማስፈጸም መሞከር ከቀውስ ሊያወጣ አይችልምና በጥንቃቄ ነገሮችን ማስተዋል ይገባል፣ ያስፈልጋል፡፡

ትልቁን የፖለቲካ መፍትሔና የሰላማዊ ትግል አማራጭ ዘዴ ወደ ጎን ብሎ በዚያም በዚህም ብረት መወዝወዙም የሚያስከፍለው ዋጋ ውድ መሆኑን ከጎረቤቶቻችን ብቻ ሳይሆን፣ ከራሳችንም ውድቀት መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም የብሔራዊ ዕርቅ፣ የአገራዊ ምክክርና የሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ አጀንዳዎችን የመሰሉ የጋራ ዕሳቤዎችን ወደፊት በድፍረት በማምጣት፣ አገርን ከውድቀት ለማዳን መሥራት ነው የሚበጀው የሚሉ ሰዎች መደመጥ አለባቸው፡፡

ከዚህ ውጪ ዘመቻ፣ ግብረ ኃይል፣ ወታደራዊ ግዳጅ፣ ሰላም ማስከበርም ይባሉ ሌሎች የኃይልና መሰል የመለካካት አዙሪቶች አንዴ ሳይሆን እንደ አገር በትውልድ ደረጃም የተቀባበልናቸውና የውድቀት ካባ የተከናነብንባቸው ናቸው፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በፖለቲካ አመለካከት ሰበብ መገዳደሉንም ቢሆን ዓለም ጉድ እስከሚለን ድረስ ታክተንበታል፣ መቶ ሺዎችንም ገብረነብታል፡፡ ግን ምን አተረፍን? ምንም፡፡

ከሃምሳ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሠራዊት ታሪክን መመልከት ብቻ አንዳች እውነት ይነግረናል፡፡ የየትውልዱ ጀግናና ሰፊ ሕዝባዊ ኃይል በአብዛኛው የአገር ሉዓላዊነትን ለመታደግ ከመፋለም ይልቅ (ከሶማሊያ ጋር ከተካሄደው ጦርነት በስተቀር) በውስጥ ፖለቲካ ሽኩቻና አማፅያንን በማስቆም ትግል ላይ ብዙ የታከተና ያልተገባ ዋጋ ሲከፍል የኖረ መሆኑን እንገነዘባለን። የፖለቲካ እሳት ማጥፊያ ሠራዊት ሊባልም ይችላል፡፡

በፋንታሁን አየለ (ዶ/ር) ወታደራዊ ጥናት መሠረት ከ1950ዎቹ መጀመሪያ እስከ 1983 ዓ.ም. ማብቂያ ድረስ በሰሜን ኢትዮጵያ ብቻ ከመቶ በላይ ዘመቻዎች ተካሂደዋል። ፖለቲካዊ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ በዘመቻ ጋጋታ አገር ወደ መቀመቅ ለመውረድም ተዳርጋ እንደነበር ያሳያል የጥናቱ ማብራሪያ። ለምሳሌ በገጽ 41 ላይ እንዲህ ይላል።

“…መንግሥት በኤርትራ ፀረ አመፅ ዘመቻውን ገፋበት። ከታኅሳስ 1963 እስከ ጥር 1965 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ብቻ አሥር ዘመቻዎች ተካሄዱ። ዋና ዋናዎቹም…” በማለት “ዘመቻ ዓድዋ” (ግንቦት 1963)፣ “ዘመቻ አሳምነው” (ሰኔ 1963)፣ “ዘመቻ ቀስቅስ” (ታኅሳስ 1964)፣  1ዘመቻ ቆንጥር” (ሚያዚያ 1964)፣ “ዘመቻ ግባው” (ሐምሌ 1964) እና “ዘመቻ ደምስስ” (ጥር 1965) ናቸው ይላል።

“በ1966 ዓ.ም. ደግሞ ፀረ አመፅ ዘመቻዎችን ለዓመታት ሲያካሂድ የነበረው ሠራዊት በመታከትና የፖለቲካ መፍትሔ በማጣት ዝሎ ራሱ አመፅ በማካሄድ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ንጉሠ ነገሥቱን ከሥልጣን አወረደ…” በማለት ያክላል።

ከዚያ ሁሉ አልቦ ፖለቲካዊ መፍትሔ በኋላ የበዛ ዘመቻና ጦርነት ተካሂዶም በ1983 ዓ.ም. አጠቃላይ የአገሪቱ ካርታና እውነታ መቀየሩንም በቅርብ የምናስታውሰው ነው። እናም ከእልህ፣ ከወታደራዊ ዘመቻና ከጉልበት መፈታተሽ ወጥቶ እንደ አገር ሰከን ብሎ መነጋጋርና የጋራ መፍትሔ መሻት አይሻልም ትላላችሁን? የተሻለው መፍትሔ ግን ይኼው ብቻ ነው መለት ይበጀናል። ከዘመቻና ከፖለቲካ መገዳደል ወጥቶ ስለመነጋጋርና መተማማን ማሰብ አለብን የምለው በዚህ መነሻ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...