ዛሬ የምንጓዘው ከካዛንቺስ ወደ ሜክሲኮ ይሆን ዘንድ ተገደድን። በማን? በኑሮ፡፡ ትናንት ስታነደን የነበረችው ፀሐይ ቦታዋን ለዝናብ ለቃ ጥላን ሄዳለች። “አናትን ስታቃጥል ደግሞ አይጣል ነበር…” ይላል ታክሲ ጥበቃ ከተሰለፍነው ሰዎች መካከል አንደኛው ካፊያ ለመከላከል ጥላውን ዘርግቶ። “ሰው ብልጥ ነው የሚባለው ድሮ ቀረ? ወይስ አልቀረም?” ይጠይቃል አንደኛው። የጥያቄውን መነሻ ለማወቅ ታክሲ ጥበቃ የቆመው ሕዝብ ይተያያል። “ምን ለማለት ፈልገህ ነው?” አለው ከኋላው የእጅ ቦርሳ ይዞ የተሠለፈ ጎልማሳ። “እንዴት መሰለህ? ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ሥር እናደርጋለን ያለው በወጣትነቱ ኮሙዩኒስት የነበረው የያኔው የእኛ ሰው ነበር፡፡ የዘንድሮው ግን ከታች እርስ በርሱ፣ ከላይ በዝናብ ውርጅብኝ እየተመታ ዝም ብሏል። ቢያንስ የዝናብን ኃይል ለመጠቀም አልቻለም…” ብሎ እጁን አወናጨፈ። “ኧረ የታክሲ ያለህ?” ይላል አንዱ የመረረው ፀሎት አይሉት ጩኸት እያሰማ። ይኼኔ አንዱ የታክሲ ተራ ሠልፈኛ፣ “ወንድም አትጩህብን እባክህ፣ መንግሥት እንደ ቴሌቪዥን በሪሞት ኮንትሮል ቢያስተዳድረን ነው እንጂ፣ የታክሲ ችግር እንዲህ ይጫወትብን ነበር?” ይላል፡፡ “ኧረ ንገርልኝ…” እያለ ሌላው ያጋግላል። “ሕዝብና መንግሥት ሲተማማ የጤና ነው ትላላችሁ? ለነገሩ ምን ይገርማል? ዕድገት የማያመጣው ምን አለ? ዕድገታችን ከድርብ ወደ ነጠላ አኃዝ ወረደ ነው ያሉት? ወይስ ተስተካከለ? ቋንቋው አስቸገረና…” ይላሉ አንድ አዛውንት ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው፡፡ ኳስ በመሬት ማለት ይኼኔ ነው!
ሰው ተሠልፎ ታክሲ እየጠበቀ ጨዋታውን ያጦፈዋል። “ዘንድሮ ቆመንም እየሄድንም የምንጠብቀው ነገር ብዛት? ወይ አዲስ አበባ? እምዬ ምኒልክ እንኳንም ጉድሽን አላዩ…” ሲል አንዱ፣ “እንዴት?” እያለ ይጠይቃል ሌላው። ለአፍታ የጠረጴዛ ውይይት የተጀመረ መስሏል። “ምን ነካህ? እንዲህ ታክሲ ጥበቃ ተሠልፈን ቢያዩን ዝም ይላሉ?” ብሎ ልብ አንጠልጣይ መልሱን አሁንም ሸሸት አደረገው። አንዱ እየተቻኮለ፣ “እኮ ምን ይሉ ነበር ንገረን እባክህ?” ብሎ ጠበቅ አድርጎ ያዘው። “እንኳንም ዓድዋን አሁን ካለው ትውልድ ጋር ለመዝመት አልተፈጠርኩ ነዋ የሚሉት። እሳቸው ከያኔው ጀግና ሕዝብ ጋር ዓድዋ በእግራቸው ሲገሰግሱ እኛ እዚህች አፍንጫችን ሥር ወዳለች አካባቢ ለመራመድ ያቅተን? ወደው አልነበረም ለካ ፕሮፌሰሩ ታሪክ ከሸፈ ያሉት…” ብሎ የለበጣ ሳቅ ይስቃል። “የባሰ አታምጣ፣ የመፍትሔ ያለህ ስንል ደግሞ ለምን በእግር አትጓዙም የሚለን መጣ? ምኞታችን እየሆነ የመጣው ሠርቶ ማደግ ነው ወይስ ባክኖ መቅረት? ታሪክ መሥራት ወይስ ስለመክሸፍ ማነብነብ?” ሲል ጎልማሳው ያው ወጣት፣ “ፍጥነት የዕድገት መሠረት መሆኑ መቼ ጠፋኝ? ግን አሁንም ለጥቂቶች ወደፊት የሚቆጥረው ዘመን፣ ለአብዛኞቻችን ወደኋላ ስለሆነብኝ እኮ ነው እምዬ ምኒልክን ማስታወሴ…” ብሎ ነገራችን ሁሉ እንዴት ወደኋላ እየተጓዘ መሆኑን ሊነግረን ሞከረ። የአንዳንዱ ሰው ቀልድ እንዴት መራር ሆኗል እናንተ!
ከብዙ ጥበቃ በኋላ አንድ ታክሲ መጥቶልናል። ተረኞች ገብተን ስንሞላ ገና ምንም ያልተቀነሰው ሠልፍ ጭራሽ በአናቱ ይደመርበታል። “ሰው በሰው ላይ ሕዝብ በሕዝብ ላይ ይነሳል የሚባለው እኮ ይኼ ነው…” ይላሉ አዛውንቱ። ከፊት አካባቢ መቀመጫ ተለቆላቸው ተቀምጠው ያከበራቸውን ወጣት ደጋግመው ይመርቃሉ። ወዲያው ጆሯችን ወደ አንዲት ቆንጆ ንግግር ሄዶ ተደቀነ። “ይኼ ሠልፍ ስንቱን ቀማኛ ተጫወተበት? ምንም እንኳ ቆሞ የመጠበቂያው ሰዓት ቢበዛም…” ትላለች። “በበርካታ ቦታዎች ጉዳዮቻችንን ሥርዓት የሚያስይዛቸው ጠፍቶ ጉልበተኛውና አጭበርባሪው እየፈነጨ፣ ታክሲ ተራው ሥርዓት ያዘ አልያዘ የትኛውን ትልቅ ጥቅም እንዳናጣ ነው? የሆነ ሆኖ ምናለበት ተለቅ ተለቅ ያለው ችግራችን በቅጡ እንዲፈታ መብታችንን ብናስከብር?” አለ አንዱ፡፡ ምሬት፣ ስላቅ፣ አግቦ፣ ሽሙጥና ተረብ ሲጨመሩ ደግሞ ጉዞው ያስደስታል። ታክሲው ጉዞውን ጀመረ። ወያላው ዘወር ዘወር እያለ የውይይቱን ተሳታፊዎች በአግራሞት ይቃኛል። “ኮንትራት ነው እንዴ የጫንከው?” ሲለው ሾፌሩ፣ “እኔም አልገባኝም…” እያለው እርስ ተሳሳቁብን። ሁሉም ሰው ተግባብቶ ሲያወራ ከአንድ ቤት ተሰባስበን የመጣን ቤተሰብ መስለናቸዋል መሰል? ሊሆን ይችላል!
ወዲያው ሁለት አይፎን ስልኮች እኩል ጮኸው ተነሱ። “የስማርት ስልኮች ቁጥር ሲበዛ ነው መሰል የስማርት ሰዎች ቁጥር ያንስብኝ ጀመር…” ሲል መካከለኛው ወንበር ላይ የተቀመጠ ወጣት አጠገቡ ያለው ተሳፋሪ ደግሞ፣ “ምን ይደረግ? አንደኛ ሰው ለታይታ ሲኖር የውስጡን ይረሳል፡፡ ሁለተኛ ኑሮውም እንዲያ እንዲሆን ያስገድደዋል። ታዲያ ይፈረድበታል?” ብሎ መልሶ ይጠይቀዋል። ስልካቸው የጠራው ተሳፋሪዎች ሁለቱም ወጣቶች ናቸው። አንደኛው ለምሳ ምን እንደሚዘጋጅለት ከወዲሁ መመርያ ሲሰጥ እያዳመጥን ነው። “እግዚኦ ምናለበት ምራቃችንን እንዳንውጥ በቴክስት ቢነግራቸው? ዘመኑ የቴክስት ነው ብለህ ንገረውማ። ቴሌ ከሁሉም ይኼ ብቻ ነው መሰል የገባው ‘ኢን ቦክሳችን’ በቴሌ ቴክስት ሁሌም ይታጨቃል…” ይላል ጎልማሳው ባለእጅ ቦርሳ እየሳቀ። “ያለው ማማሩ ነው፣ ኧረ ተወኝ…” ይለዋል አጠገቡ የተቀመጠ በዕድሜ ብዙም የማያንሰው ተሳፋሪ። አዛውንቱ ጨዋታውን በተረት ሊያዋዙት መፈለጋቸውን ገልጸው አገጫቸውን አሸት አሸት እያደረጉ እንዲህ ይላሉ። “ድሮ ሰው አደን ሄዶ ሲቀናውና ግዳይ ሲጥል በግጥም ይሞካሻል፣ ያልቀናው ደግሞ ይተረባል። የዘመናችን ልሂቅ ዕውቀት ስላልሰረፀበት ከተገጠመለት አንድ ልበል…” ብለው ድምፃቸውን ጠራረጉ። “እንደ ሠለጠኑ አገሮች ምሁራን ካልሠራህበት፣ ስጠን ጭንቅላትህን ውኃ እንቅዳበት…” ብለው ሳቁ፡፡ የግድ ነው!
በስልክ እያተነጋገረ ወደ ነበረው ሌላኛው ሰው ተመልሰናል። “አሁን እኔ ባንክ ሄድኩኝ አልሄድኩኝ ምን እፈይዳለሁ? ብድሩን አታገኙም ተባለ አይደለም? ምን ልሠራ ነው ታዲያ የምመላለሰው?” ብሎ ከወዲያ በኩል ምላሹን ያዳምጥ ጀመር። ትንሽ ሲያደምጥ ቆይቶ፣ “ለምን ጥንቅር አይልም? ሁሉም ፕሮጀክት እንጦሮጦስ ይውረድ ሲፈልግ…” ብሎ ስልኩን በንዴት ዘጋው። ከኋላ መቀመጫ አብረውት የተቀመጡት ሰዎች ረጋ እንዲል ያባብሉታል። “ኧረ ባንኮቻችንን ምን ቫይረስ ይሆን ያገኘብን?” አለ አንዱ ነገረኛ። “ምን ያድርጉ ሰው ሁሉ ተበዳሪ ሲሆን?” ሲል ጎልማሳው ሐሳቡን ጣል አደረገ። “እኔን ግን በጣም የሚገርመኝ እንደ እንጀራ ልጅ ከአንዱ ለአንዱ ተመርጦ የሚፈቀደውና የሚከለከለው ነገር ነው…” ትላለች ሌላዋ። “ኧረ ተይኝ ሰው ቢያብድ ይገርማል እንዴ?” ይላል መልሶ ስልከኛው ጎልማሳ። “ለመሆኑ የኢንቨስተር መብዛት ነው የዚህ ችግር ምክንያት? የመከረኛው ዶላር እንዲህ ጭው ብሎ መጥፋት ይገርመኛል…” ስትል ከአዛውንቱ አጠገብ የተቀመጠች ወፈር ያለች ሴት፣ “ለእኛ ለእኛ ኑሮ ጭው ላደረገን ብሩም ሳይቀር ጭው ብሏል። ኑሮ ፋሲካ እየሆነ ላስቸገራቸው ግን ቤታቸው ድረስ ዶላር፣ ዩሮ፣ ፓውንድ ከቸች ሲል ታዝበናል…” ብሎ መለሰላት። ይኼኔ ወያላው፣ “ሰው እንዴት ልቡ ተራራ እየሆነ እንደመጣ ታያለህ? እኛ ዝርዝር ብር እያጣን የምንጠይቀው አጥተናል አዳሜ ስለዶላር ይጨነቃል…” አለ፡፡ የቸገረ ነገር!
ድንገት “እኔምለው?” በሚል ዘለግ ያለ ድምፅ አዛውንቱ ተመለሱ። “እንዲያው ከእናንተ መካከል የሰሞኑ ነገር የገባው አለ?” አሉ ዓይናቸውን አሞጭሙጨው። “ምኑን ነው አባት?” አላቸው ወያላው ቀደም ብሎ። ሒሳቡን ሲለቃቅም ቆይቶ አረፍ ማለቱ ነበር። “ነዳጅ፣ መብራት፣ ውኃና አስቤዛ ሳይቀር በቴሌ ብር ይሁን መባሉ ነዋ…” አሉ በመታከት እጆቻቸውን እያራገቡ። “ጣጣ አሉት?” ሲላቸው ወያላው፣ “መቼ ቴክኖሎጂውን አስተማሩን? ካልገባንማ ጣጣ ነው እንጂ…” ሲሉ ከኋላቸው የተቀመጠ ደግሞ፣ “አዬ ሐበሻ ሆኖ መፈጠር። እንዲያው ጥሎብን የለመድነውን መልቀቅና ለውጥ አንወድ ብለን እንጂ፣ ስልክዎን በጣትዎ ነካ ነካ እያደረጉ ጉዳይን መፈየድ ምን ችግር አለው?” አላቸው። አዛውንቱ እንደ መብሸቅ እየቃጣቸው፣ “የዛሬ ልጆች ደርሶ የሚቀናችሁ ዲስኩር ነው። ስማ እኛ የምናወራው ያየነውን፣ የኖርነውንና የሆንነውን ነው። ምን ይታሰብ፣ ምን ይታቀድ ምን አገባን? በተግባር ችግራችን ካልቀረፈልን ምን ይረበናል? ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች አሉ…” ብለውት ዞረው ተስተካከሉ። “ወይ ዘንድሮ ሰጪው ሲያቆስለን፣ እኛ እርስ በርሳችን እየተቋሰልን ከቀጠልን ምን ይሆን መጨረሻችን? ከችግራችን እንገላገላለን አይባል ሐኪሙ፣ መሐንዲሱ፣ መምህሩ፣ ነጋዴው፣ ወዘተ ይሰደዳል…” ትላለች ወጣቷ። ቀስ በቀስ ዝምታ ታክሲውን ወረሰው። ምን ይደረግ!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል፡፡ “እናንተ ቴክኖሎጂ ትላላችሁ? ስንቱን ነገር አይደል እንዴ በዕውቀት ዕጦት ምክንያት የምናጣው። በአመጋገባችንና በአኗኗራች ሰበብ በሽታ መከላከል እየከበደን፣ በሙሰኛውና በጉልበተኛው ተዳክመን፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብታችን በተሰማራንበት መስክ ለማስከበር ካቃተን ዘመን አለን እንዴ?” ሲል አንዱ እሱን መሳዮች በአዎንታ ራሳቸውን ይነቀንቃሉ። “ታዲያ ምን ተሻለን ጎበዝ?” ሲሉ ደግሞ አዛውንቱ ወያላው ፈጠን ብሎ፣ “እኔ የምፈራው እንደ ታሪካችን እንዳንከሸፍ ነው…” አለ፡፡ አዛውንቱ ግን፣ “በል ዝም በል፣ ታሪክ ከሸፈ ብሎ ወሬ አላውቅልህም፡፡ ሰው ራሱ ሲከሽፍ በታሪክ ላይ እየተንጠላጠለ ከሸፈ ቢል አትመን…” እያሉ ተቆጡ፡፡ አንድ ዝም ብሎ የነበረ ጎልማሳ ደግሞ፣ “ጠብ የተያዘው ታሪክ መሥራት ካለበት ጋር ነው ወይስ ከራሱ ከታሪክ ጋር? ስለታሪክ መክሸፍና አለመክሸፍ ይኼን ያህል ማውራት ከቻልን ተግባሩ ላይ ለምን ወገቤን እንላለን? ስንቱን ተራራ መግፋት ስንችል ለምን ገለባ እንወቃለን? ያልታደለ ፈረስ ጋሪ ይጎትታል እንደሚባለው ይኼ መራኮታችን ነው ከሰው በታች የሚያደርገን…” እያለ ሲብከነከን ወያላው “መጨረሻ!” ብሎ አሰናበተን፡፡ መልካም ጉዞ!