- ክቡር ሚኒስትር አተገባበሩ ጥሩ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ወቀሳ እየደረሰብን ነው።
- ዲጂታል የግብይት ሥርዓቱን ለማስፋፋት በመጣራችን መመስገን ሲገባን እንዴት እንወቀሳለን?
- የሚገርመው በዲጂታል ክፍያ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ናቸው በዋነኛነት እየወቀሱን ያሉት።
- ለምን?
- እኛም የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት ብንሰጥም፣ አንድ ተቋም ብቻ በአድሎ ገበያውን እንዲቆጣጠርና ከጫወታ ውጪ እንድንሆን ተገፍተናል እያሉ እየወቀሱን ነው።
- ይህ ተቋም የተመረጠው የተሻለ ልምድና ተደራሽነት ስላለው ነው ብላችሁ በበቂ ሁኔታ አላስረዳችሁም ማለት ነው?
- ኧረ አስረድተናል ክቡር ሚኒስትር።
- ታዲያ ለምን ወቀሳ መጣብን?
- ማኅብረሰቡ ልምድ የላችሁም፣ ተደራሽ አይደላችሁም ብሎ የፈለገውን ይምረጥ እንጂ መንግሥት እንዴት ይወስናል ነው የሚሉት።
- መንግሥት ለማኅበረሰቡ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ግዴታ እንዳለበትማ መዘንጋት የለበትም።
- እኛም ይህንኑ አስረድተናል ነገር ግን የመንግሥትና የግል ባንኮች እንዲሁም አዲስ የገባው የውጭ ቴሌኮም ሳይቀር ውሳኔውን ተቃውመውታል። እንዲያውም አንዳንዶቹ …
- እ … አንዳንዶቹ ምን?
- ብዙ ተከታይ ያላቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ተዋናዮችን በማሰማራት እየተሳለቁብን ነው።
- ምን እያሉ ነው የሚሳለቁት?
- የቀጣዩ ምርጫ ድምፅ አሰጣጥም በዚሁ ነው እያሉ።
- የማይሆን ነገር ነው የሚያወሩት!
- ሌላም ብዙ ተሳልቀዋል።
- ምን አሉ?
- ነገሩ በዚሁ ከቀጠለ ቤንዚን የሚስቡ የጎዳና ልጆችንም ተጠቀሙ መባለቸው አይቀርም ሲሉም ተሳልቀዋል።
- ምን?
- ቴሌ ብር!
- በሉ ይሄንን ነገር በፍጥነት ተቆጣጠሩ።
- እንዴት አድርገን?
- ሁሉም ንግድ ባንኮች በግብይቱ እንዲሳተፉ ይደረግ።
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ሰሞኑን የተላለፈው መልዕክት ማንን እንደሚመለከት ሚኒስትሩን እየጠየቀ ነው]
- የትኛውን መልዕክት ነው የምትለው?
- ደቡብ ምዕራብ ላይ የተገነባው ሪዞርት ሲመረቅ የተላለፈውን ማለቴ ነው። እርስዎም እኮ ቦታው ላይ ነበሩ?
- አዎ። ተገኝቼ ነበር፣ ግን የተላለፈውን መልዕክት ዘነጋሁት፣ ምን ነበር?
- ‹‹በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብታችሁ የምትፈተፍቱ የውጭ ኃይሎች፣ የእኛን ጉዳይ ለእኛ ተውሉን›› የተባለውን ማለቴ ነው።
- እ … አስታወስኩት። ልክ ነው ማቆም አለባቸው!
- ግን የውጭ ኃይሎች የተባሉት እነማን ናቸው?
- በአጠቃላይ የውጭ ኃይሎችን የሚመለከት ነው።
- ጎረቤት አገርን ይሆን እንዴ?
- ለምን ጎረቤት ጠረጠርክ?
- መልዕክቱ ላይ ጎረቤት አገር ልትሆን እንደምትችል የሚጠቁም ነገር የሰማሁ ይመስለኛል።
- ምን የሚል?
- ብዙ ያልሠራችሁት ነገር ስላለ የእኛን ጉዳይ ለእኛ ተውሉንና በምድራችሁ ያልሠራችሁትን ሥሩ የሚል መልዕክት አብሮ ተላልፏል።
- ታዲያ ይኼ ጎረቤት አገር መሆኑን ይጠቁማል እንዴ?
- መቼም ኃያሏን አገር ሊሆን አይችልም ብዬ ነው። በዚያ ላይ …
- በዚያ ላይ ምን?
- በዚያ ላይ የታሰበው ሳይለቀቅ አይናገሯትም ብዬ አስቤ ነው።
- ለማንኛውም መልዕክቱ ጎረቤት አገርንም ሆነ ኃያሏን አገር በስም አልጠቀሰም።
- ምን አልባት እርሶ የሚያውቁ ከሆነ ብዬ እንጂ በስምማ አልተጠቀሰም።
- መልዕክቱ ሁሉንም የውጭ ኃይሎች የሚመለከት ነው።
- እንዴት ሁሉንም ሊሆን ይችላል ክቡር ሚኒስትር? ቢያንስ በውስጥ ጉዳይ የሚፈተፍቱ መሆን አለባቸው።
- እኮ እንደዚያ የሚያደርጉትን ሁሉንም ማለቴ ነው።
- ግን ጎረቤት አገር እንደምትሆን ይሰማኛል።
- እንዴት? በምን ምክንያት?
- ምክንያቱም ቅድም ከጠቀስኩት ውጤት ሌላ ጠቋሚ ነገር ያለ ይመስለኛል።
- ምን?
- የውጭ ኃይሎችና በተለይ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ኃይሎች የሚል ጠቋሚ ነገርም በመልዕክቱ ተላልፏል።
- ታዲያ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ የሚለው ምን ይጠቁማል?
- መረጃ እየተቀበሉ የሚጽፉትን ትውልደ ኢትዮጵያዊ ለማለት ፈልገው ይመስለኛል።
- መረጃ የሚቀበሉት ከማን ነው?
- ከጎረቤት አገር መረጃና ደኅንነት ይመስለኛል።
- እኔ ግን እሳቸውን ለማለት የፈለጉ አይመስለኝም።
- ታዲያ ረሺድ አብዲ ነው ሊሉኝ ነው።
- እሱማ እዚህ መጥቷል?
- የት? አዲስ አበባ?
- አዎ!
- በኢንተር ፖል ነው?
- ለምን?
- ታዲያ እንዴት መጣ?
- ተጋብዞ ነዋ!
- ተጋብዞ?
- ለምን አይጋበዝም?
- ከተጋበዘ አይቀርማ በደንብ መጋበዝ አለበት።
- ምን?
- ፍትፍት!