Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሳይሠሩ በተቋቋሙ ፋብሪካዎች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዓመታት በፊት ሲቋቋሙ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሳይሠሩ የተቋቋሙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ፋብሪካዎች እየተለዩ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ ሳይኖር የተቋቋሙ በርካታ ፋብሪካዎች እንደሚገኙ የገለጹት የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ድዳ ድሪባ፣ ፋብሪካዎቹ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ አሠርተው እንዳልተቋቋሙ ተናግረዋል፡፡

የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ማለት አንድ ፕሮጀክት ወይም መንግሥታዊ ሰነድ ተግባራዊ ሲሆን፣ የሚያስከትለውን ገንቢም ሆነ አፍራሽ ውጤት በቅድሚያ ለይቶ የማወቂያና የመመዘኛ ዘዴ እንደሆነ የአዋጁ ትርጓሜ ያስረዳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በከተማዋ ውስጥ በካይ ነገሮችን የሚያመነጩ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን እየለየ፣ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ስለመሥራታቸው የማመሳከር ሥራዎች ከመሥራት ባሻገር፣ የሌላቸውን ተቋማት የአካባቢ አስተዳደር ዕቅድ (ኢንቫይሮመንት ማኔጅመንት ፕላን) አዘጋጅተው የሚያመነጩዋቸውን በካይ ቆሻሻዎች በራሳቸው ቁጥጥር እንዲያደርጉ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የልማት ሐሳብ ንድፍ ሲዘጋጅ፣ ቦታው ሲመረጥ፣ ሲገነባ ወይም ሲተገበር እንዲሁም በመተግበር ላይ ያለ እንቅስቃሴ ሲሻሻል ወይም ሲቋረጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ በመተንበይና አስቀድሞ በማረም በውል የታሰበበትን ልማት ለማምጣት የሚያግዝ ጥናት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በተያያዘም ከኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የሥነ ምኅዳር ሥርዓት አገልግሎት ግምገማ (Evaluation of eco system service) የሚል ጥናት እያስጠና እንደሚገኝ ያስታወቀው የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ጥናቱ በአካባቢ ሥነ ምኅዳር ላይ ብክለት ያደረሱ አካላት መክፈል የሚገባቸውን ክፍያ ምን ያህል መሆን አለበት የሚለውን ጭምር የሚመለከት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ50ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም አካባቢ ጥበቃ ቀን በኢትዮጵያ ለ30ኛ ጊዜ በተያዘው የግንቦት ወር መባቻ እንደሚከበር የታወቀ ሲሆን፣ ‹‹ለፕላስቲክ ብክለት መፍትሔ›› በሚል መሪ ቃል ይከበራል ተብሏል፡፡

በየዓመቱ ግንቦት 28 ቀን የሚከበረውን የዓለም አካባቢ ቀን ምክንያት በማድረግ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ካሪቡ ኢቨንትስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር በመሆን፣ ከግንቦት 25 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ጎልፍ ክለብ ከ80 በላይ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ የተሰማሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ኤክስፖ እንደሚዘጋጅ አዘጋጆቹ ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በጎልፍ ክለብ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡

ከፕላስቲክ ምርቶች ጋር ተያይዞ የሚከሰት የአካባቢ ብክለት ዓለማችንን በእጅጉ የሚያሳስባት ጉዳይ እንደሆነና ይህንን ለመቆጣጠር የተባበሩት መንግሥታት አገሮችን ከስምምነት እንዲደርሱ ግፊት መደረግ እንዳለበት፣ ከዚህ በፊት ይፋ የተደረገ ጥናት ጠቁሟል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለምን የሚያሠጓት ነገሮች ብሎ ሦስት ጉዳዮችን ሲያስቀምጥ የመጀመሪያው የአየር ንብረት ለውጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው የብዝኃ ሕይወት መጥፋት፣ እንዲሁም ሦስተኛው ደግሞ ብክለት ነው። ድርጅቱ እንደሚለው እነዚህ ሦስት አሳሳቢ ችግሮች በፍጥነት መልስ ሊሰጣቸው ይገባል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለም ኅብረተሰብን ያሳሰበው የፕላስቲክ ውዳቂዎች ክምችት ብቻ ሳይሆን፣ በሒደት በአፈርም ሆነ በውኃ አካላት ላይ የሚያስከትሉት ብክለት መሆኑ ይነገራል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች