በኢዮብ ትኩዬ
ከኦሮሚያ ክልል ወደ አማሮ ልዩ ወረዳ ተዛመተ የተባለ የኮሌራ ወረርሽኝ ከ200 ሺሕ እስከ 400 ሺሕ የሚገመቱ ነዋሪዎችን ለሥጋት መዳረጉ ተለገጸ፡፡
ወረርሽኙ በልዩ ወረዳው መከሰቱ ሚያዚያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በላብራቶሪ ምርመራ እንደተረጋገጠና በ48 ሰዓታት ብቻ አምስት ሰዎች በወረርሽኙ እንደ ሞቱ፣ ቁጥራቸው ከ200 ሺሕ እስከ 400 ሺሕ የሚሆኑ ነዋሪዎች ሥጋት እንደተጋረጠባቸው፣ በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ የጤና ጽሕፈት ቤት የጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ሥራ ሒደት አስተባባሪ አቶ አሸናፊ ሻርዳ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
የኮሌራ ሕሙማን ከኦሮሚያ ክልል ተነስተው ወደ ልዩ ወረዳው በመሄድ የሕክምና አገልግሎት ያገኙ እንደነበር የገለጹት አቶ አሸናፊ፣ ወረርሽኙ የተዛመተው ከኦሮሚያ ክልል ነው ብለዋል፡፡
የጤና ቢሮው ነዋሪዎች በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ መሆናቸውን፣ የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ቢሆንም ወረርሽኙ ፋታ ስለማይሰጥ ሰዎች በሰዓታት ልዩነት ለሕልፈተ ሕይወት እየተዳረጉ መሆኑን ነው፡፡
በልዩ ወረዳው የጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የኮሌራ በሽታ መከላከል የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ አክሊሉ ካሌብ በበኩላቸው፣ በሽታው በወረዳው በተከሰተ በሁለት ቀናት ውስጥ አምስት ሰዎች መሞታቸውንና ሕክምና ለማድረግ የመድኃኒት ዕጥረት እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል፡፡
ወረርሽኙ በልዩ ወረዳው እየተስፋፋ መሆኑን፣ የኔትወርክ አለመኖር፣ ተሽከርካሪ በማይገባባቸው አካባቢዎች ያሉ ሰዎች በፍጥነት የሕክምና አገልግሎት መስጠት እንዳልተቻለ፣ ሕሙማን ወደ ጤና ጣቢያ የሚያቀኑት በእግራቸው በመሆኑ ጤና ጣቢያ ሳይደርሱ ሕይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችል ነው ያስረዱት፡፡
የኮሌራ ሥርጭት በልዩ ወረዳው በምን ደረጃ እንደሚገኝ ማብራሪያ ሲሰጡም፣ ‹‹ትናንት ከነበረባቸው አካበቢዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው፡፡ አዳዲስ ኬዞችም እየተገኙ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ወረርሽኙ ቡርጂ፣ ገላና፣ ጋሞ በከፍተኛ ሁኔታ እንደተስፋፋ፣ አዳዲስ ኬዝ በተገኘባቸው አካባቢዎች ባለሙያዎችን ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት አቶ ካሌብ፣ አዳዲስ ኬዝ በተገኘባቸው አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ በሒደት እንዲያስታውቁ፣ በተለይ በቡርጂ ጤና ጣቢያ ተሽከርካሪ የሚያስገባ መንገድ ስለሌለ በፍጥነት ሕክምና ለመስጠት መቸገራቸውን አስረድተዋል፡፡
ከምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና መጣሬ ኮምቦልቻ ቀበሌ በሞተር ሳይክል ተጭነው ወደ በኬሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የገቡ ሁለት ታማሚዎች ለበሽታው መዛመት ምክንያት መሆናቸውን፣ የአማሮ ልዩ ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ለሪፖርተር የላከው መረጃ ያሳያል፡፡
ወረርሽኙ በላብራቶሪ ምርመራ ተረጋግጦ ኮሌራ እንደሆነ ከታወቀ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ቢሆንም፣ ወረርሽኙ እጅግ አደገኛና ገዳይ በመሆኑ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ትኩረት እንደሚሻ፣ በሽታው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በማስከተል ከአምስት እስከ አሥር ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደሚገድል፣ የሚከሰተውም በንፅህና ጉድለት እንደሆነም ተብራርቷል፡፡
ከመፀዳጃ ቤት መልስ ምግብ ከመመገብ፣ ከምግብ ዝግጅት፣ ለሕፃናት ጡት ከማጥባት በፊት፣ እንዲሁም በተቅማጥና በትውከት የታመመን ሰው ከተንከባከቡ በኋላ እጅን በሳሙና በመታጠብ ማኅበረሰቡ ከበሽታው ራሱን እንዲከላከል ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
የኩፍኝና ኮሌራ ወረርሽኝ ከነሐሴ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይ በኦሮሚያና በአፋር ክልሎች እንደተከሰተ፣ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮም ከ80 በላይ ሰዎችን እንደገደለ፣ በሽታው ወደ ሌሎች አጎራባች ክልሎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተዛመተ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡