Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሙዚቃ ልዕልቷ ሒሩት በቀለ (1935 - 2015)

የሙዚቃ ልዕልቷ ሒሩት በቀለ (1935 – 2015)

ቀን:

‹‹ኢትዮጵያ…. ሀገሬ

መመኪያዬ ……ነሽ ክብሬ

በጣም ያኮራኛል ኢትዮጵያዊነቴ

የሀገሬ ፍቅር ፀንቶ በስሜቴ…..

ኢትዮጵያ ….ሀገራችን

ኢትዮጵያ …. እናታችን››

ይህ ዘመነ ዘመናትን እየተሻገረ እንደ ሕዝብ መዝሙር ሲደመጥ፣ ሲዘመር የነበረ፣ ትውልዱ በፍቅረ ሀገር እንዲፀና በማድረግ የበኩሏን ተግባር ከውናለች፡፡ የእሷን ፍኖት በመከተልም የእሷን ዘፈን እንበል መዝሙር በቅብብሎሽ የዘፈኑት የዘመሩት ድምፃውያን ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ከብሉይ ተርታ ደርሷልና፡፡ እየዘመሩ፣ እየዘፈኑ ትውልድ እንዲታነፅበት ተግተውበታል፡፡

ይቺ ድምፃዊት ማን ናት ቢሉ ከሦስት አሠርታት በላይ በዘለቀው ፍኖተ ሙዚቃዋ ለልዕልና የበቃችው፣ ጊዜ በማይሽረው ሙዚቃዋ በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅ የነበረችው ሒሩት በቀለ ናት፡፡

ገና በልጅነቷ ፍቅረ ሙዚቃ ያደረባት ሒሩት በሠፈሯ ለጓደኞቿና ለሚሰሟት ሁሉ መዝፈኗ ሰሚዎቿ በሙዚቃው እንድትገፋበት ማትጋታቸው አልቀረም፡፡

በገጸ ታሪኳ እንደተወሳው፣ በ16 ዓመቷ ወደ ምድር ጦር ኦርኬስትራ ጎራ በማለትም እንደ ሙያ መዝፈን የጀመረችበት ሲሆን፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት በዕለተ ዕንቁጣጣሽ ያቀረበችው የመጀመሪያ ዘፈኗ ‹‹የሐር ሸረሪት›› ተወዳጅ ሆኖላታል። በምድር ጦር ኦርኬስትራ ለሁለት ወራት ብቻ ከሠራች በኋላ፣ ከ1952 ዓ.ም. ጀምሮ በፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃ ክፍል በመቀጠር ለ35 ዓመታት አገልግላለች።

‹‹ገድሉን ሰምቼ በአድናቆት

ከግንባር ሄጄ አየሁት

ሳንጃ ለሳንጃ ተሞሻልቆ

አልፏል በታሪክ አሸብርቆ›› እያለች በምሥራቅና በሰሜን ጦር ግንባር ለአገር ሉዓላዊነት ዘብ ለቆመው አብዮታዊ ሠራዊት ግንባር ድረስ በመዝለቅ ስታጃግን ነበረች ድንቋ ሒሩት በቀለ፣ ከበርካታ ሥራዎቿ መካከል ሕይወት እንደ ሸክላ፣ እንደ ገበቴ ውኃ፣ ነፍስ ነገር፣ ዘሟል ጎራዴው፣ አዲስ አበባ ነው ቤቱ፣ መላ መላ፣ ጎዳዴ፣ እንዲያው ዝም፣ ሐኪሙን ጥሩልኝ፣ የበረሃ ቴምርና ገላዋ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሒሩት ጥቂት ከማይባሉ ድምፃውያን ጋር በቅብብሎሽ የተጫወተች ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ሻምበል መስፍን ኃይሌ (የትዳር ጓዴ)፣ ዓለማየሁ እሸቴ (ቢተረ በያ – በማዘር ኢንዲያ)፣ ታደለ በቀለ (ውብ ዓይናማ)፣ መልካሙ ተበጀ፣ ማህሙድ አህመድ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ (አካሌ) እና ካሳሁን ገርማሞ ( ኧረ ንካው – ኧረ ንኪው) ይገኙበታል። አምባሰል ሙዚቃ ቤት ‹‹አራቱ ዕንቁዎች በጋራ›› በሚል የጋራ መጠሪያ የጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ሒሩት በቀለና ማህሙድ አህመድ ሥራዎች በአንድ ካሴት ማሳተሙም ይታወሳል፡፡

ከፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ ባሻገር በወቅቱ ገናና ከነበሩት ሸበሌ፣ ዋሊያስ፣ ዳህላክና ሮሃ ባንዶች ጋር በመሆን መጫወቷም ይወሳል፡፡

ብዙዎቹ ዘፈኖቿ በነጠላና በአልበሞች በአምሃ ሪከርድስ፣ ካይፋ ሪከርድስ፣ ፊሊፕስ ኢትዮጵያ፣ ሱፐር ሶኒክ፣ ወዘተ ተለቅቀዋል። ሒሩት ከ200 በላይ ሥራዎችን የሠራች ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 38ቱ በሸክላ፣ እያንዳንዳቸው 10 ዘፈኖች የያዙ 14 የካሴት አልበሞችን አሳትማለች፡፡

ከ1980ዎቹ መገባደጃ በኋላም ዓለማዊውን ሙዚቃ በማቆም ወደ መንፈሳዊ ሕይወት በማዘንበል ዘማሪት በመሆን ሦስት መዝሙሮችን አበርክታለች፡፡

ከአባቷ ከሌተና ኮሎኔል በቀለ ክንፈና ከወ/ሮ ተናኘወርቅ መኮንን መስከረም 28 ቀን 1935 ዓ.ም. አዲስ አበባ የተወለደችው ሒሩት ዕድሜዋ ለትምህርት ስትደርስ ከቄስ ትምህርት ቤት በመቀጠል በቀበና አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ገብታ የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃለች።

ባደረባት ሕመም ምክንያት በአገር ውስጥና በውጭ ሕክምናዋን ስትከታተል የቆየችው ሒሩት በ80 ዓመቷ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ማረፏ ተነግሯል፡፡

በርካታ ሽልማቶችን ያገኘችው ሒሩት የ7 ልጆች እናት የነበረች ሲሆን፣ 10 የልጅ ልጆችና 6 የልጅ ልጅ ልጆችን አይታለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...