Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሕግ አስከባሪ አካላት የሚደርሱ የማሰቃየትና ተገቢ ያልሆኑ አያያዞች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ ተጠየቀ

በሕግ አስከባሪ አካላት የሚደርሱ የማሰቃየትና ተገቢ ያልሆኑ አያያዞች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ ተጠየቀ

ቀን:

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችን አያያዝና አፈጻጸም የሚከታተለውና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም አቀፍ ስምምነቶች አካላት (United Nations Human Rights-Treaty Bodies) በመባል የሚታወቀው የገለልተኛ ባለሙያዎች ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሕግ አስከባሪ አካላት የሚፈጸሙ ማሰቃየትና እንግልቶች፣ በገለልተኛ አካላት እንዲጣሩና ተጠርጣሪዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ እንዲያደርግ አሳሰበ፡፡

የሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ የፀረ ማሰቃየት ኮሚቴ ይህን ያስታወቀው፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ ካዛኪስታን፣ ሉክሰምበርግና ስሎቫኪያ ላይ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ የተናጠል ግምገማ ማጠቃለያ ሪፖርት ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በጄኔቫ ስዊዘርላንድ ይፋ ባደረገበት መግለጫ ነው፡፡

ኮሚቴው በተለይም በኢትዮጵያ በፖሊስ መኮንኖች፣ በእስር ቤት ጠባቂዎችና ሌሎች ወታደራዊና የፀጥታ ኃይሎች በፖሊስ ጣቢያዎች፣ በማቆያ ማዕከላት፣ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ በወታደራዊ ካምፖችና በግልፅ በማይታወቁ ወይም በሚስጥራዊ እስር ቤቶች ቅሬታ አቅራቢዎች የሚደርስባቸው ስቃይና እንግልት እጅጉን እንዳሳሰበው አስታውቋል፡፡

አሁንም ቢሆን በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚስተዋሉ ማሰቃየት ወይም እንግልት ቅሬታዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ገለልተኛ፣ ምቹና ሚስጥራዊ ዘዴ አለመኖሩንና አሁናዊው የምርመራ አካላት ሁኔታ ተፈላጊው ገለልተኝነት እንደሚጎለው ግንዛቤ መወሰዱን ጠቅሷል።

ኮሚቴው አክሎም የኢትዮጵያ መንግሥት በሕግ አስከባሪ አካላት የሚደርሱ ማሰቃየቶችና ተገቢ ያልሆነ አያያዝና እንግልቶችን በተመለከተ የቀረቡ ቅሬታዎች፣ በገለልተኛ አካል እንዲጣሩና ተጠርጣሪ ድርጊት ፈጻሚዎችንና ድርጊቱን እንዲፈጸም ያዘዙና በቸልታ የተመለከቱ የሥራ ኃላፊዎች ለሕግ ቀርበው እንዲጠየቁና እንዲቀጡ ጠይቋል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የተደረሰው የሰላም ስምምነትን በበጎነት ያየውና ያደነቀው ኮሚቴው በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ በተለይም በትግራይ ተወላጆች ላይ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞችና ተቃዋሚዎች ላይ ተፈጸመ ያለውን መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት፣ የሰብዓዊና የስደተኛ ሕግጋት ጥሰት በተመለከተ የተሰማውን ጥልቅ ሥጋት ገልጿል።

ኮሚቴው ተጠቃሎ በቀረበው ሪፖርት ውስጥ በተመለከተው ሆን ተብሎ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መሰንዘር፣ ማሰቃየትና እንግልት፣ የዘፈቀደና የረዥም ጊዜ እስራት ሪፖርቶች፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳይደረስ ማስተጓጎልን ጨምሮ በሌሎች ተያያዥ ክስተቶች መሸበሩን አስታውሶ፣ ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይና አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ላይ ሁሉንም የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተለይም በጦር ወንጀል የሚያስጠይቁትንና በሰዎች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን እንድትመረምር ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት የተሟላና ያልተቋረጠ የሰብዓዊ አገልግሎት በሁሉም ግጭት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች አቅርቦትን እንዲያረጋግጥ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ስዊዘርላንድ ጄኔቭ ለሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የፀረ ማሰቃየት ኮሚቴ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሪፖርቷን በማቅረብ የተገመገመችው ኢትዮጵያ፣ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችን መርምሮ በማቅረብ መወቀሷን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

በፍትሕ ሚኒስትር ደኤታው አቶ ዓለምአንተ አግደው ወንድሜነህ የተመራ 11 አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ልዑካንም፣ ኮሚቴው ፊት ቀርቦ የአገሪቱን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሪፖርት ማቅረቡ፣ ሪፖርቱን በጽሑፍ ያቀረቡት ሚኒስትር ደኤታው በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ከለውጡ በኋላ ስለመሻሻሉ በሰፊው ዘርዝረው ነበር፡፡

በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች አያያዝም ቢሆን መሻሻሉንና በእስር ቤቶች ይፈጸም የነበረው ማሰቃየት መቆሙንም የለውጡ አንዱ ትሩፋት መሆኑን አስረድተው የነበሩት አቶ ዓለምአንተ፣ ይሁን እንጂ መንግሥታቸው ‹‹ገና በሽግግር ላይ ያለና ሽግግሩም ሙሉ ለሙሉ በተሳካ ሁኔታ ያለ እንቅፋት እየሄደ አለመሆኑን›› አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ለውጡ ተቃውሞ፣ የሚዲያ ዘመቻና ማጥላላት ሲገጥመው መቆየቱንም አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...