Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቡና በማከማቸት ለውጭ ገበያ ያላቀረቡ ላኪዎች መጋዘን እየታሸገ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገበያ አፈላልገው ኮንትራት ሳይዋዋሉ ቡና ያከማቹ ላኪዎችን መጋዘኖች ማሸግ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

የቡና ላኪዎች ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳያገኙ ተደርጎ፣ ቡናውን በገቡት ኮንትራት መሠረት ወይም ደግሞ ኮንትራት ከሌላቸው ደግሞ ኮንትራት ላላቸው እንዲሸጡ በማድረግ ቡና ወደ ውጭ ገበያ እንዲቀርብ እያደረገ መሆኑን፣ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ሰባት መጋዘኖች እንደታሸጉ ታውቋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን ጋር ሆኖ በሚመራው መድረክ፣ ከቡና ላኪዎችና አቅራቢዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ ላኪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ወደ ውጭ ልከው አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ማድረግ እንዳለባቸው በማስታወቅ ግፊት እየተደረገ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የግብይትና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት ከቡና አቅራቢዎችና ከላኪዎች ጋር በተደረገ ውይይት በእጃቸው ላይ ያለውን ቡና አውጥተው እንዲሸጡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

ሰሞኑን የቡናና ሻይ ባለሥልጣን መጋዘኖችን እያሸገ እንደሚገኝ፣ በዚህ ዕርምጃ የማይሻሻሉ ካሉና የንግድ ፈቃዳቸው መቀማት ካለበት ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር በጋራ እየሠራበት እንደሆነ የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት የቡና ዓለም አቀፍ የመሸጫ ዋጋ ጥሩ ስለነበረ ላኪዎች የተበረታቱበትና ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና የተላከበት ነበር ያሉት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ በዚህ ዓመት ግን ፈታኝ የነበረው በዓለም አቀፍ ገበያ የቡና ዋጋ ዝቅ ማለትና የአገር ውስጥ መሸጫ ዋጋ ከፍ ማለት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ላኪዎች ‹‹እንከስራለን›› በሚል ምክንያት ስለያዙት ኤክስፖርቱ በሚፈለገው ልክ አልሄደም ብለዋል፡፡

‹‹በአቅራቢዎች እጅ ከፍተኛ ቡና አለ፣ አቅራቢዎች ደግሞ ከአርሶ አደር ሲገዙ በከፍተኛ ገንዘብ ነው የገዛነው የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ እኛ ደግሞ አርሶ አደሩ ከልፋቱ አኳያ አሁንም በቂ ተከፍሎታል የሚል እምነት ባይኖረንም፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋ ተቀባይ እንደ መሆናችን ያንን ተቋቁመን ኤክስፖርታችንን ማሳደግ እንዳለብን በተደጋጋሚ እንናገራለን፣ ማሳሰቢያም እንሰጣለን፣ የምንችለውን ያህል እየገፋን ነው፤›› ሲሉ ሚኒስትር ደኤታዋ ተናግረዋል፡፡

‹‹መቅጣት መፍትሔ አይሆንም፣ ቡናው እንዲወጣ አብሮ መሥራቱ የተሻለ ነው፤›› ያሉት ሶፊያ (ዶ/ር)፣ ከላኪዎችና ከአቅራቢዎች ጋር በተደረገ ውይይት፣ ‹‹የዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋ ስለወረደ እንጎዳለን›› የሚል አስተያየት እንደሚቀርብ፣ ሆኖም ጥራትን ከፍ በማድረግ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ መሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በታየው ዕድገት በመነሳሳት በተያዘው የበጀት ዓመት ከቡና የሚገኘውን ገቢ ከ1.8 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ ቢታቀድም፣ እስካሁን ድረስ ባለው እንቅስቃሴ የተገኘው ገቢ አንድ ቢሊዮን ዶላር የተጠጋ እንደሆነና ኢትዮጵያ ካላት አቅም አንፃር በቂ አለመሆኑን ሶፊያ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

ሶፊያ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሰፋ ያለ ክትትልና ቁጥጥር በማድረጉ ባለፈው ወርና በተያዘው ወር የቡና ኤክስፖርት መነቃቃቶች እየታየበት እንደሆነ፣ በቀን እስከ አንድ ሺሕ ሜትሪክ ቶን ለውጭ ገበያ እየቀረበ ቢገኝም፣ በቂ የሚባል ግን አይደለም፡፡

አዱኛ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳስረዱት፣ በዘንድሮ በጀት ዓመት የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ እጅግ በጣም በመቀዛቀዙ የቡና ምርት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ተቀዛቅዟል፡፡

አቅራቢዎች ዓምና ከአርሶ አደሮች ከፍ ባለ ዋጋ የገዙትን ቡና ዘንድሮ ቅናሽ ባሳየው ዓለም አቀፍ ገበያ ለመሸጥ በመቸገራቸው፣ ምርቱ በአብዛኛው በአቅራቢዎች እጅ እንደሚገኝ አዱኛ (ዶ/ር) ባለፈው ወር የተቋማቸውን የስምንት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት አስረድተው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከጥቅምት ወር ጀምሮ ዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ እየቀነሰ በመምጣቱ ምክንያት በ394 የግብይት ውሎች ለውጭ ገበያ መቅረብ የነበረበት 28 ሺሕ ቶን ቡና የውጭ ገዥዎች ውል በማፍረሳቸው ሽያጭ ሳይፈጸም መቅረቱን በወቅቱ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህ የግብይት ውል ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ 133 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይገኝ እንደነበር ገልጸው ነበር።

ከላይ የተጠቀሰው መጠን ቡና በዚህ ወቅት የአሠራር ሥርዓቱን በመከለስ ከአገር እንዲወጣ እየተደረገ እንደሚገኝ አዱኛ (ዶ/ር) ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከቡና ኤክስፖርት ቢያንስ የባለፈውን ዓመት ያህል አቻ ገቢ ለማግኘት በተቀሩት ሁለት ወራት አዳዲስ የኮንትራት ውሎች እንዲገቡ በማድረግ፣ ቡናን የማውጣት ሥራ መጀመሩንና በዚህም ዕቅዱን ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች