Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ጣት እየተቀሳሰርን የዴሞክራሲን አካሄድ እናሳድጋለን ማለት ዘበት ነው›› የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

‹‹ጣት እየተቀሳሰርን የዴሞክራሲን አካሄድ እናሳድጋለን ማለት ዘበት ነው›› የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ቀን:

  • ኢሠፓ የፓርቲ ምዝገባ መከልከሉ ጥያቄ አስነስቷል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ‹‹ጣት እየተቀሳሰርን የዴሞክራሲን አካሄድ እናሳድጋለን ብለን አስበን ከሆነ ዘበት ነው የሚሆነው፤›› ሲሉ፣ ተናገሩ፡፡

ምክትል ሰብሳቢው ይህን የተናገሩት የቦርዱን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡

በቅርቡ በደቡብ ክልል ‹‹ደቡብ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ አዲስ ክልል ለመመሥረት በስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዶ፣ በወላይታ ዞን የተካሄደው የሕዝበ ውሳኔ ውጤት መሰረዙ ይታወሳል፡፡

የሕዝበ ውሳኔውን ውጤት መሰረዝ በተመለከተ የቋሚ ኮሚቴው አባል ወ/ሮ አረጋሽ ተክሌ በወላይታ ዞን በተደረገው የሕዝብ ውሳኔ በምዝገባም ሆነ በምርጫው ቀን የተፈጠረው ችግር 88 በመቶ የሚሆነው የሕግ ጥሰት የተፈጸመው፣ በምርጫ አስፈጻሚዎች መሆኑን በዓቃቤ ሕግ የምርመራ ሒደት መለየቱን አስታውሰዋል፡፡ ይህ ቀድሞ የተፈጠረ ችግር የደቡብ ክልል በሕዝበ ውሳኔው ተሳታፊ እንዳይሆን ክፍተት መፍጠሩን ጠቅሰው፣ ችግሩን በወቅቱ እየተፈታ ለምን መሄድ እንዳልቻል ለቦርዱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

አቶ ውብሽት ለተነሳው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ የወላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔ ውጤት መሰረዝን ተከትሎ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከወላይታ ዞን አስተዳዳሪዎች፣ እንዲሁም ከክልሉ ባለሥልጣናት ጋር በነበረ ስብሰባ የአስፈጻሚዎቹን በደል ከፍ በማድረግ፣ 88 በመቶ የችግሩ መንስዔ እነሱ ናቸው ተብሎ እንደቀረበ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ከፍ ያለ ቁጥር ቦርዱ የምርጫ አስፈጻሚዎቹን አሳልፎ በመስጠቱ የተገኘ ቁጥር መሆኑን ጠቅሰው፣ 250 ብር አበል ይከፈላቸው የነበሩ የምርጫ አስፈጻሚዎችን በአካባቢው ባሉ የፀጥታ ሹሞችና አስተዳዳሪዎች በቃለ ጉባዔ የተዘጋን መዝገብ እንደገና በማስከፈትና በማስፈራራት፣ እያንዳንዳቸው ለአምስትና ለስድስት ሰዎች መፈረማቸውን አስረድተዋል፡፡

በዚህም ከእያንዳንዱ መዝገብ ጋር ቁርኝት ያለውን አስፈጻሚ ቦርዱ አሳልፎ ለሕግ መስጠቱን ጠቅሰው፣ ‹‹ከዚህ በኋላ ፖሊስ በምርመራ ከጀርባው ያሉትን ማግኘት ካልቻለ፣ በእኛ እምነት በዚህ የዴሞክራሲ ጥሰት ላይ ፍትሕ ተሰጥቷል ብለን አናምንም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን እርግጠኛ ነኝ የፌዴራል ፖሊስም ሆነ የፍትሕ ሚኒስትር ከዚህ ጀርባ ያሉትን አካላት የማያዳግም ዕርምጃ የሚወሰድበትን ምርመራ ያካሂዳሉ ብለን እናስባለን፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

አቶ ውብሸት ለቋሚ ኮሚቴ አባሏ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹እርስዎም እዚህ ቤት ለመቀመጥ ምክንያት ለሆነው የዴሞክራሲ አካሄድና ሒደት ሲሉ፣ በሌላ በኩልም በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ላይ ያሉት የዞኑ ኃላፊዎችም በደንብ ቁጭ ብለው ተረጋግተው እንዳያስቡና እንዳይደገም ሊያደርጉ ይገባል፡፡ እውነት ነው የምላቹሁ 250 ሚሊዮን ብር ነው በድጋሚ ለሚካሄደው ምርጫ የሚወጣው ገንዘብ፡፡ ተመሳሳይ ነገር ቢፈጸም እንሰርዘዋለን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እኛም ለዚህ አገር ነው የምንሠራው፣ ገንዘቡም የዚህ አገር ነው፡፡ በመሆኑም ሁላችንም በዚህ ዓይነት መንገድ እንድናየው አደራ እላለሁ፡፡ አለበለዚያ ጣት እየተቀሳሰርን የዴሞክራሲ አካሄድን እናሳድጋለን ብለን አስበን ከሆነ ዘበት ነው የሚሆነው፤›› በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩል አቶ መስፍን እርካቤ የተባሉ የቋሚ ኮሚቴ አባል ከፓርቲዎች ምዝገባ ጋር በተገናኘ የቦርዱን መመዘኛ ነጥብ አሟልተው ምዝገባ የሚከለከሉ ፓርቲዎች ስለመኖራቸው ገልጸው፣ ለአብነትም የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) እንደ ማንኛውም ፓርቲ ጠንካራና ደካማ ጎን እንዳለው ፓርቲ ሁሉ፣ እንደ አዲስ ለመመዝገብ ያቀረበው ስያሜ  ለምን ውድቅ እንደሆነበት ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ ለሠርቶ አደሩ ጥቅም ከሁሉም በላይ ለኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት፣ እንዲሁም ዘረኝነትንና ጽንፈኝነትን በመታገል የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደረገ ፓርቲ ነው ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል፡፡

የኢሠፓ ስህተቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው እንደ ፓርቲ የምዝገባ መመዘኛውን ካሟላ ሊከለከልበት የቻለበት ምክንያት ምንድነው በማለት የጠየቁት አቶ መስፍን፣ አገር ለማፍረስ በትጥቅ ታግዘው የታገሉና በአሸባሪነት የተፈረጁ ፓርቲዎች በቦርዱ ዕውቅና እያላቸው ለኢሠፓ ዕውቅና ለመስጠት የቸገረበት ጉዳይ ምንድነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ በሰጡት ማብራሪያ ኢሠፓ በሚል የቀረበው ፓርቲ በዚህ ስም እንዳይደራጅ የተደረገበት ምክንያት፣ ፓርቲው የታገደበት ቁጥር 3/1983 አዋጅ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 2 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለመነሳቱ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ አዋጅ ስለተቀመጠው አንቀጽ በሰጡት ሀተታ፣ ‹‹የኢሠፓና የደኅንነት አካላት ምክር ቤቱ ሌላ ሕግ እስካላወጣ ድረስ በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ታግደዋል፡፡ ድርጅቶቹም ፀረ ዴሞክራሲና ወንጀለኛ ድርጅቶች ስለሆኑ ፈርሰዋል፤›› የተጠቀሰው አዋጅ እንደሚል አስታውሰዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካልተሻረ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ ስም ለመደራጀት የሚመጡትን ከመከልከል ውጪ ሌላ ምንም ሊያደርግ አይችልም፣ ሕግ ነው ያስከበርነው፤›› ብለዋል፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. እና መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በተለያዩ ምክንያቶች የስድስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ባልተካሄደባቸው አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ሱማሌ ክልሎች በሚገኙ የምርጫ ክልሎች ውስጥ ምርጫ ለማከናወን የፀጥታ ችግር ያለባቸውንና የሌለባቸውን አካባቢዎች የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች እንዲያሳውቁ በማሳሰብ፣ መረጃውን ማደራጀቱን አቶ ውብሸት ተናግረዋል፡፡

ቦርዱ በ2016 በጀት ዓመት የትግራይ ክልልን ጨምሮ የስድስተኛው ዙር ቀሪ ምርጫዎችን በተለያዩ ጊዜያት ለማከናወን ዝርዝር ዕቅድና በጀት አዘጋጅቶ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳቀረበ አስታውቀዋል፡፡

በስድስተኛው ዙር አገራዊ ምርጫ ያልተካሄደባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች 96 ናቸው ተብሏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ትግራይ 38፣ ኦሮሚያ 8፣ አማራ 19፣ አፋር 9፣ ቢኒሻንጉል ጉሙዝ 19፣ ደቡብ 2፣ እንዲሁም ሶማሌ 1 ሲሆኑ በአብዛኛው ምርጫ ያልተካሄደውም በፀጥታ ችግር ምክንያት እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የሚደርሰውን በደል አስመልክተው ምክትል ሰብሳቢው ሲያብራሩ፣ ፓርቲዎች የተቋቋሙበትን ዓላማ መሠረት አድርገው ሥራቸውን በመሥራት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ በየደረጃው ካሉ ከአስፈጻሚ አካላትና የፖሊስ ኃይሎች ጥቃት እንደሚደርስባቸው፣ ይህም ለሥራ እንቅፋት እየሆነባቸው መሆኑን በተደጋጋሚ አቤቱታ ለቦርዱ እየቀረበ መሆኑ ተናግረዋል፡፡ በአብዛኞቹ የአገሪቱ ክልሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች አባሎቻቸውና ሥራ አስፈጻሚዎቻቸው እየታሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ እስካሁን በአመራር ደረጃ ያሉ የፓርቲ አባላት እስር ቤት እንደሚገኙም አውስተዋል፡፡

‹‹የፓርላማው የዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን ልታግዙን ካልቻላችሁ በሥራ ሒደት ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፤›› ያሉት አቶ ውብሸት፣ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የእስረኞችን ሁኔታ ለመከታተል ተሞክሮ የክልሉ ፖሊሲ ኮሚሽንን ማግኘት እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡

ምክትል ሰብሳቢው፣ ‹‹መስማት መቻል አለብን፣ መደመጥ መቻል አለብን፣ ውሳኔያችን መከበር አለበት፤›› ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ አለመቻላቸውን ሲያብራሩ፣ የመጀመሪያው ችግር የመንግሥትን አዳራሽ አለማግኘት መሆኑን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሆቴሎች ለፖለቲካ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ አዳራሽ ለማከራየት መፍራት መጀመራቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ ችግር በመባባሱ ምክንያት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች አዳራሽ እየተከራየ መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹ለምን እንደዚህ ይደረጋል?  ፓርቲዎቹ የሕግ ሰውነት እያላቸው ይህ ጉዳይ በምንም ዓይነት መንገድ ለአንድ ደቂቃም ሊታሰብ የማይገባ ጉዳይ በመሆኑ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለክልል ፕሬዚዳንቶች ደብዳቤ ጽፈናል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ውብሸት ‹‹የሚገርም ነገር ልንገራችሁ›› በሚል ለቋሚ ኮሚቴው ባደረጉት  ንግግር፣ ‹‹በአንድ ወቅት የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩና አሁን የመንግሥት ካቢኔ አባል የሆኑ ግለሰብ እንኳ የመንግሥት አዳራሽ በፓርቲዎች ሲጠየቁ አልፈቀዱም፡፡ ነገር ግን ያኔ እሳቸው የመንግሥት አዳራሽ ጠይቀው ሲከለከሉ እኛ ላይ ነበር ያሳሰቡት፡፡ ስማቸውን መጥራት አልፈልግም፣ ያዳምጡኛል ብዬ አስባለሁ፣ መፍትሔም ይሰጡበታል የሚል እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ብዛት ያልገለጸው ቦርዱ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው አስፈጻሚዎች በምርጫው ወቅት ሥራ ላይ የዋለውን የምርጫ ቁሳቁስ ባለመመለሳቸው ንብረቱን እንዲመልሱ ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መጻፉን አስታውቋል፡፡  

ቋሚ ኮሚቴው ብሔራዊ ምርጫ፣ ቦርድ የተጠናከረ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንዲፈጠር ሚናውን እንዲጫወት የጠየቀ ሲሆን፣ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ፣ ‹‹ሕዝብን ለመምራት የሚፈልግ፣ ሕዝብ የሚወሰነውን ለመቀበል የሚፈልግ ማንም ፓርቲም ይሁን ሰው ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ብቻ ነው መሥራት ያለበት፡፡ ከዚህ ወጣ ያለ ነገር ሲኖር ዋጋ ያስከፍላል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ዴሞክራሲ እንዲያብብ ከፈለግን የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር አለባቸው፡፡ ሌሎች የሕዝብ አደረጃጀቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ አማራጭ ሐሳብ የሚያቀርቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሌሉበት ሁኔታ ዴሞክራሲን መገንባት ምንም ፋይዳ የሌለው ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ዋና ሰብሳቢው በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይም የሕግ መተላለፍ ሊኖር እንደሚችል፣ ነገር ግን ይህን ማረም እንጂ አዳራሽ መከልከልና አመራሮችን ማሰር ምንም ዓይነት መፍትሔ አያስገኝም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...