አገሮች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን የሚቃኙበትና የሚያስተዳድሩበት ፖሊሲ አላቸው፡፡ አገሮቹ በስፖርት ከሚያሳዩት ዕድገት አንፃር ደረጃቸው የተለያየ ቢሆንም፣ የአብዛኛዎቹ መነሻ ፅንሰ ሐሳብ ግን ተመሳሳይነት አለው፡፡ ይህም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መሠረት ያለው ነው፡፡
በዚህም መሠረት ስፖርት በማኅበራዊ እሴቱ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ወጣቶች በአዕምሮና በአካል የዳበሩ እንዲሆኑ ለማስቻል ቀዳሚ ሥፍራውን ሲይዝ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ጠቀሜታው በሒደት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ሲሆን ይስተዋላል፡፡
የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲም በማኅበራዊ መስተጋብሩ በአዕምሮ የበለፀገና በአካል የዳበረ ወጣት ለማፍራት የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በቀበሌ፣ በወረዳ እንዲሁም በዞን ውድድሮች ይከናወናሉ፡፡
በአገር ውስጥ ውድድሮች እየዳበረ የሚመጣው ስፖርትዊ እንቅስቃሴ ከአኅጉር አልፎ በዓለም አቀፍ ውድድሮችም ተሳትፎ ይኖረዋል፡፡
በዚህ ተዋረድ ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ ሻምፒዮናዎች የደመቁና የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ የቻሉ በርካታ ስፖርተኞችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ስፖርት ከማኅበራዊ መስተጋብሩ አልፎም ሌላው የቢዝነስ አቅም እየፈጠረ ከመጣ ሰንባብቷል፡፡ በተለይ በአትሌቲክሱ፣ አትሌቶች አገርን ከመወከል በዘለለ መጠነ ሰፊ የቢዝነስ አማራጭ ይዘው እየመጡ ነው፡፡
በምሥራቅ አፍሪካ በረዥም ርቀት ውድድር ከኢትዮጵያ ጋር የሚፎካከሩት የኬንያ አትሌቶች፣ አትሌቲክሱን በአግባቡ እየተጠቀሙት እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም የሆነው አትሌቶች የአጭር ጊዜ ውጤትን ግብ አድርጎ ከመሥራት ይልቅ፣ በረዥም ጊዜ ዕቅድ ታዳጊ አትሌቶችን ከታች መልምሎ ማሰናዳቱ ላይ በማተኮራቸው ነው፡፡
ኬንያ በአትሌቲክሱ የተረዳችውን አቅም በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን እየተጠቀመች እንደምትገኝ በርካቶች ያነሳሉ፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ…›› ሳይሆንባት እንዳልቀረ እየተገለጸ ይገኛል፡፡ የየክልሉ ከተማ አስተዳደር፣ የተቋማት እንዲሁም የድርጅት ክለቦች በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች በአገር ውስጥ ሻምፒዮናዎች ይሳተፋሉ፡፡
አብዛኛዎቹ ክለቦች ከመንግሥት ካዝና በሚወጣ ገንዘብ የሚተዳደሩ ሲሆን፣ ታዳጊ አትሌቶችን እየመለመሉ ሥልጠና በመስጠትና በማካተት በአገር አቀፍ ውድድሮች አገራቸውን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶችን ማብቃት መሠረታዊ ተግባራቸው መሆን እንደሚገባው ይታመናል፡፡
ሆኖም ክለቦቹ መሠረታዊ ሥራቸውን ዘንግተው ታዳጊዎችን በደመወዝ እያማለሉ መቀራመት ላይ መጠመዳቸውን ባለሙያዎች ያነሳሉ፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ አስተያየት ከሆነ ክለቦቹ ወደ ታች ወርደው ታዳጊዎች እየመለመሉ በሥልጠና ማብቃቱን ችላ ብለውታል፡፡
ከመንግሥት በጀት እየተቆረጠላቸው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ክለቦች ከ2,500 ብር ጀምሮ ወርኃዊ ደመወዝ ለአትሌቶቻቸው ይቆርጣሉ፡፡ አብዛኞቹ የመንግሥት ክለቦች የተነሱበት ዓላማ ተመሳሳይ ቢሆንም፣ አንደኛው የመንግሥት ክለብ ከሌላው ጋር በደመወዝ ጣሪያ እየተለያየ ወደ ታዳጊዎች ወርዶ ከመሥራቱ ይልቅ፣ ጥሩ ሰዓት ያላቸውን አትሌቶች በደመወዝ በማማለል መጠመዳቸው ይነሳል፡፡
ችግሩ ከአምስት ዓመታት በላይ መሻገሩን የሚያነሱት ባለሙያዎቹ፣ አትሌቶች ከአንድ ክለብ ጋር የገቡትን ውል እንኳን ሳያጠናቅቁ ወደ ሌላ ክለብ እንደሚወሰዱ ይናገራሉ፡፡
‹‹ጥሩ ሰዓት ያላቸው አትሌቶች ለክለባቸው የፈረሙትን ውል እንኳን ሳያጠናቅቁ አቋርጠው የሚሄዱበት አጋጣሚ ተበራክቷል፤›› በማለት የሱሉልታ አትሌቲክስ ክለብ አሠልጣኝ ኢንስትራክተር ፈጠነ ታደሰ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን የሚያነሱት ኢንስትራክተር ፈጠነ፣ ክለቦች ስማቸውን እንዲሞገስ ብቻ የሚያደርጉት እንደሆነና ይህም አገርን የሚጎዳ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በመንግሥት ድጋፍ የሚተዳደረው የሱሉልታ አትሌቲክስ ክለብ ለአትሌቶች ከሁለት እስከ አምስት ዓመታት ድረስ ውል ይሰጣል፡፡ በክለቡ በሁሉም ርቀት የሚካፈሉ አትሌቶች ከ2,500 እስከ 3,600 ብር ድረስ ወርኃዊ ደመወዝ የሚቆረጥላቸው ሲሆን፣ የምግብና የመኝታ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ በአንፃሩ አንዳንድ ክለቦች ጥሩ ሰዓት ላላቸው አትሌቶች እስከ 20 ሺሕ ብር ድረስ በማቅረብ ይቀራመታሉ፡፡
በዚህ አሠራር የተማረሩ ክለቦች የተለያዩ ሕጎችን መከተል መጀመራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ በሱልልታ አትሌቲክስ ክለብ አንድ አትሌት የአምስት ዓመታት ውል ቢፈርምና ወደ ሌላ ክለብ ማምራት ቢፈልግ፣ የስድስት ወር ደመወዙን እንዲሁም ጥቅማ ጥቅሙን የሚወስደው ክለብ እንዲከፍል እንደሚያደርግ፣ በአንፃሩ አትሌቶች ወደ ፌዴራል ክለቦች መግባት ሲፈልጉ አንድ ዓመት ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እንዲከፍሉ እንደሚደረግ ኢንስትራክተር ፈጠነ ሪፖርተር አብራርተዋል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ የክልል ክለቦች ታዳጊዎች መልምለው ቢያበቁም በፌዴራል ክለቦች እንዲሁም የተቋማት ክለቦች ተጨማሪ ደመወዝ በማቅረብ አትሌቶቹን ነጣቃ ላይ መጠመዳቸው ኢንስትራክተሩ ያስረዳሉ፡፡
‹‹በርካታ የፌዴራል እንዲሁም የተቋም ክለቦች ታዳጊዎችን መልምሎ ከማብቃት ይልቅ፣ ከክለቦች በተሻለ የደመወዝ መጠን መውሰድን ይመርጣሉ፤›› በማለት የሚናገሩት ኢንስትራክተር ፈጠነ፣ ይህ አሠራር ክለቦችን እያፈረሰ እንደሚገኝና ተተኪ አትሌቶች እንዳይገኙ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የሱሉልታ አትሌቲክስ ክለብ በመንግሥት በጀት የሚተዳደር ቢሆንም፣ ሁሉም የመንግሥት ክለቦች ግን በተመሳሳይ መዋቅር እንደሚመሩና አንዱ ክለብ የተጋነነ የደመወዝ ክፍያ ሲኖረው፣ ሌላው ዝቅተኛ ክፍያ እየከፈለ ክለቦቹ ‹‹ለዓለም ሻምፒዮናና ለኦሊምፒክ አትሌቶችን አበረከቱ›› እንዲባልላቸው ብቻ አትኩረው እየሠሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የክልል ክለቦች የሚያሠለጥኑ አሠልጣኞች ታዳጊ አትሌቶችን ከትምህርት ቤቶችና ፕሮጀክቶች መልምለው ቢያመጡም፣ በመጨረሻ የፌዴራል እንዲሁም የተቋማት ክለቦች እየተቀራመቷቸው የልፋታቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ ተነስቷል፡፡
የሱሉልታ አትሌቲክስ ክለብ ከ10 በላይ አትሌቶች የፌዴራል ክለቦች እንደወሰዱበት ኢንስፔክተር ፈጠነ ይናገራሉ፡፡ ይህም የመንግሥት ክለቦች ያላቸው ግብ ተመሳሳይ ሆኖ እያለ፣ በደመወዝ ክፍያ በማበላለጥ ተገቢ እንዳልሆነና በሕግና በደንብ መመራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር በክልል ደረጃ ያሉ ክለቦች ተቀራራቢ አሠራር እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡ ለዚህ ችግር ተጠያቂ ባለሙያው እንደሆነ የሚያስረዱት የረዥም ርቀት አሠልጣኙ ብርሃኑ መኮንን ናቸው፡፡
አሠልጣኙ አያይዘውም፣ በክለብ ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች አትሌቱ ወደ ክለብ እስኪመጣ ከመጠበቅ አትሌቱ ወደሚገኝበት ወርዶ መሥራት ይጠበቅበታል ሲሉ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ሰንዝረዋል፡፡
አሠልጣኙ ሲያክሉም፣ የመንግሥት ክለቦች በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ መሆናቸውን ተከትሎ፣ ታዳጊዎችን መልምለው እንዲበቁ ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል እንጂ፣ እርስ በእርስ አትሌቶች መነጣጠቅ ላይ ጊዜ መፍጀት እንደማይገባ ያሳስባሉ፡፡