Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮኖች  ይጠበቃሉ

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮኖች  ይጠበቃሉ

ቀን:

በኢትዮጵያ ዕድሜ ጠገብ ከሆኑ ሻምፒዮናዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነው፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዚህ ዓመታዊ ውድድር ውስጥ አልፈው በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች መካፈል ችለዋል፡፡ ከወረዳ እስከ ዞን ባሉ ውድድሮች ውስጥ የሚያልፉ አትሌቶች የአገር ውስጥ ትልቁ ውድድራቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማንኛውም አትሌት በአገር ውስጥ ሻምፒዮና  ካልተካፈለ አገርን ወክሎ በተለያዩ ሻምፒዮናዎች መካፈል እንደማይችሉ ሲገልጽ ቢቆይም፣ የተወሰኑ አትሌቶች በአገር ውስጥ ውድድሮች ሳይካፈሉ በቀጥታ የሚመረጡበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ይህም በጊዜው በአብዛኛው አትሌትና አሠልጣኞች ዘንድ ቅሬታ ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡ በአንፃሩ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኦሊምፒክ እንዲሁም በዓለም ሻምፒዮና የተካፈሉ አትሌቶች በአገር ውስጥ ውድድሮች ሲሳተፉ መመልከት እየተለመደ ነው፡፡

የ52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከግንቦት 8 እስከ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዴሚ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

ሐሙስ ግንቦት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ስለሻምፒዮና  ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በሻምፒዮናው በአኅጉራዊና፣ በዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በኦሊምፒክ ውድድሮች የተካፈሉ አትሌቶች እንደሚሳተፉበት ገልጿል፡፡

ውድድሩ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳድሮች፣ ክለቦች፣ ተቋማትና ማሠልጠኛ ማዕከላት ምርጥ አትሌቶቻቸውን ይዘው የሚሳተፉበት መድረክ ነው፡፡

የውድድሩ ዓላማ ከነሐሴ 13 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በሃንጋሪ ቡዳፔስት ለሚካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚወዳደሩ አትሌቶችን ለመምረጥ እንዲሁም ወቅታዊ አቋማቸውን እንዲለኩ ዕድል ለመፍጠር ግብ ያደረገ መሆኑ ተብራርቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር በክልሎች፣ በከተማ አስተዳደሮች፣ በክለቦችና በማሠልጠኛ ማዕከላት ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እንደሚረዳ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተነስቷል፡፡

በሻምፒዮናው 11 ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም 30 ክለቦችና ተቋማት በአጠቃላይ 1270 አትሌቶች እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡ ለስድስት ተከታታይ ቀናት የሚከናወነው ሻምፒዮናው ከመጀመሪያው ቀን በስተቀር ሁሉም የውድድሩ ፕሮግራሞች በጠዋት ይካሄዳሉ፡፡

በውድድሩ በኦሊምፒክና በዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በግል ውድድሮች መሳተፍ የቻሉ አዋቂ አትሌቶች በወንድም በሴትም እንደሚካፈሉ የታወቀ ሲሆን፣ ኃይለ ማርያም አማረ፣ አክሱማዊት እምባዬ፣ ሰለሞን ባረጋ፣ ሰንበሬ ተፈሪ፣ ጥላሁን ኃይሌ፣ መቅደስ አበበ፣ ሳሙኤል አባተ፣ ቦሰና ሙላቴ፣ ሙክታር እድሪስ፣ ዳዊት ሥዩም፣ ኤርሚያስ ግርማ፣ ወርቅውኃ ጌታቸው፣ ጌትነት ዋለ፣ ዘርፌ ወንድም አገኝ፣ በሪሁ አረጋዊ፣  ሀብታም ዓለሙ፣ ታደሰ ወርቁ፣ ሒሩት መሸሻ፣ ሐጐስ ገብረ ሕይወት፣ ፅጌ ገብረ ሰላማ፣ ሞገስ ጥዑማይ፣ ግርማዊት ገብረ እግዚአብሔር፣ ለሜቻ ግርማ፣  ያለምዘርፍ የኋላው፣ ቦኪ ድሪባ፣ ብርቄ ኃየሎም፣ ተሬሣ ቶሎሳ፣ ፎቴይን ተስፋይና ለተሰንበት ግደይ በሻምፒዮናው እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

በእያንዳንዱ የውድድር ተግባር ከአንድ እስከ ሦስተኛ ለሚወጡ አትሌቶች በሁለቱም ፆታ የወርቅ፣ የብር፣ የነሐስ ሜዳሊያና ገንዘብ ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፣ በቡድን ውጤት ለሴቶችና ለወንዶች አሸናፊዎች በእያንዳንዳቸው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለሚወጡ የገንዘብ ሽልማት እንደሚሸለሙ ተጠቁሟል፡፡ በውድድሩ ክብረ ወሰን ማሻሻል የቻሉ ሁለትና ሦስት ወርቅ ላመጡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱ፣ አጠቃላይ የገንዘብ ሽልማት መጠንም 541 ሺሕ ብር መሆኑ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶች የምርኩዝ ዝላይ የተካተተበት የሻምፒዮናው የመክፈቻና መዝጊያ መርሐ ግብር የቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ይኖረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...