Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

አገራችንን ያለችበት መላ ቅጥ ያጣ ውጥንቅጥና እኛ በየጎራው ተሠልፈን የምንተራመስበትን አጉል ፖለቲካ ጉዳይ ሳስብ፣ ምን ያህል ማስተዋል የጎደለበት ጊዜ ውስጥ እንዳለን ይታየኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ከሚታወቅባቸው መልካም እሴቶቹ መካከል አንዱና ዋነኛው፣ አርቆ አሳቢነትና ማስተዋል እንደሆነ ብዙዎችን ያስማማናል፡፡ ነገር ግን እኛ የእዚህ ዘመን ሰዎች ለአርቆ አሳቢነትና ለማስተዋል ትዕግሥት ያለን አንመስልም፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚለቀቁልንን አጥፊ አጀንዳዎች እያመነዠግን እርስ በርስ ለመበላላት እንጂ፣ ኢትዮጵያ ከገባችበት ቀውስ ውስጥ መንጥቆ ለማውጣት የሚያግዙ መላዎችን ለማፈላለግ ፍላጎት አይስተዋልብንም፡፡ በመናኛ አጀንዳዎች ተጠልፈን በብሔርና በሃይማኖት ሊያጫርሱን ለሚፈልጉ ደመኞች እየተመቻቸን ነው፡፡

አንዲት አገር ኢትዮጵያን እየረሳን በብሔር ማንነት ካባ ውስጥ ተሸጉጠን ነገር ስናደራ ውለን እናድራለን፡፡ በተለይ ደግሞ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ የደረሱ ምሁርና ልሂቅ ተብዬዎች፣ ከእኛ ተራ ሰዎች በባሰ ማስተዋል ጎድሎዋቸው በከንቱ ፖለቲካ ተጠልፈው አገር እየጎዱ እንደሆነ ለመረዳት አለመቻላቸው ያሳፍራል፡፡ ምሁራንና ልሂቃን ተብዬዎች ካለፉት የታሪክ ስህተቶች ተምረው አገርን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ማውጣት ሲገባቸው፣ በትናንቱ የሰሜን ኢትዮጵያ ዕልቂትና ውድመት የተደቆሰች አገርን ለማፍረስ እየተራወጡ መሆናቸው ያበሳጫል፡፡ እስቲ ከተማሩት ይልቅ ተራ ዜጋ የሚባሉ ሰዎችን አመዛዛኝነት የሚያመላክት አንድ ገጠመኝ ልንገራችሁ፡፡

ከዓመታት በፊት አንድ ማለዳ ወደ ሳሪስ አቦ የሚጓዘው ሐይገር ባስ ውስጥ ተሳፍሬያለሁ፡፡ ረዳቱ እየተጣራ ተሳፋሪዎችን ያስገባል፡፡ ሁሌም በዚህ አውቶቡስ ስጓዝ ወደ ሥራ ከሚጓዙት ባልተናነሰ ሁኔታ ቃሊቲ እስር ቤት የታሰሩ ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ስንቅ ቋጥረው የሚጠይቁ ወገኖቻችንን አስተውላለሁ፡፡ ሁሌም የምጓዘው በዚህ መስመር ስለሆነ ከበርካቶች ጋር ሐሳብ ተለዋውጬ አውቃለሁ፡፡ ከዕለት ግጭት እስከ ነፍስ ማጥፋት፣ ከዘረፋ እስከ ፖለቲካ ጉዳይ በሕግ ጥላ ሥር የዋሉ ሰዎችን የሚጠይቁ ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጆቻቸውን አዋይቻለሁ፡፡ በችግር ተቆራምደው ወገኖቻቸውን የሚያስታውሱ አሉ፡፡ ያለቻቸውን በማካፈላቸው ደስተኞች ሆነው የሚኖሩ ብዙ አሉ፡፡ የዛሬም ገጠመኜ ይህንኑ ይመለከታል፡፡

ሾፌሩ ከሚቀመጥበት በስተጀርባ ያለው ወንበር ላይ አንዲት 22 ዓመት ያልሞላት ለጋ ወጣት ሕፃን ልጇን አዝላ የቋጠረችውን ስንቅ እግሯ ሥር አድርጋ ተቀምጣለች፡፡ አጠገቧ ትልቅ ሴት ተቀምጠዋል፡፡ እኔ ደግሞ ሞተሩ ላይ እነሱ አጠገብ ነኝ፡፡ መኪናው የመገናኛ አደባባይን ዞሮ ወደ ቦሌ አቅጣጫ ሲያቀና ትልቋ ሴት በሐዘኔታ እያዩዋት፣ ‹‹ልጄ ሕፃኗን አዝለሽ የት እየሄድሽ ነው?›› በማለት ጥያቄ አቀረቡላት፡፡ ልጅቷ አንገቷን ደፋ አድርጋ ቂሊንጦ እስር ቤት እንደምትሄድ መለሰችላቸው፡፡ ይኼኔ የእኔም ጆሮ ነቃ አለ፡፡

ሴትዮዋ ደንገጥ ብለው፣ ‹‹ልጄ ማን ታስሮብሽ›› ነው? በማለት በሐዘኔታ ዓይን ዓይኗን ማየት ጀመሩ፡፡ ያቺ አንድ ፍሬ ልጅ በመቦረቂያዋ ጊዜ ልጅ ወልዳ ማዘል በዝቶባት እንደገና የእስር ቤት ስንቅ አመላላሽ መሆኗ አንጀቴን እየበላው እኔም እንደ ትልቋ ሴት መልሷን በጉጉት መጠባበቅ ጀመርኩ፡፡ ልጅቷ አፈር እያለች፣ ‹‹የታሰረውማ ባሌ ነው፤›› ስትል እኔም ሴትየዋም በድንጋጤ ተያየን፡፡ ሴትዮዋ የሰሙትን ባለማመን ነው መሰል፣ ‹‹በእርግጥ የታሰረው ባልሽ ነው? ለምን ታሰረ?›› በማለት ጠየቋት፡፡

ልጅቷ ለአፍታ ያህል ትክዝ ብላ ከቆየች በኋላ፣ ‹‹አዎን ባሌ ነው፡፡ የሁለት ልጆቼ አባት ነው፤›› በማለት መለሰችና ዓይኖቿን በመስኮቱ በኩል ወደ ውጭ ላከቻቸው፡፡ ሴትየዋ እየተቁነጠነጡ፣ ‹‹ልጄ ለምን ታሰረ?›› ሲሉ ጠየቁ፡፡ ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡም ፊታቸው በሐዘን ተሰብሮ ዓይናቸው እንባ አግቷል፡፡ ልጅቷ በረጂሙ ከተነፈሰች በኋላ፣ ‹‹እኔን ደብድቦ ነው፡፡ ሁለት ጥርሶቼን በማርገፉ ነው ሁለት ዓመት የተፈረደበት፤›› ስትል ውስጤ ተሸበረ፡፡ ሴትዮዋ በንዴት፣ ‹‹ይኼንን ነው ሰው ብለሽ የምትጠይቂው?›› ብለው በንዴት ሲንጨረጨሩ ላያቸው ቢያገኙት ምን ያደርጉት ነበር ያሰኛል፡፡ ‹‹ይኼንንማ መጠየቅ የለብሽም፡፡ እኔ ብሆን ድርሽ አልላትም ነበር፤›› አሉ፡፡

ይህች አንድ ፍሬ ልጅ ግን ከእሳቸው ተሻለች፡፡ ሳቅ ብላ እያየቻቸው፣ ‹‹አይ እማማ! ብቻዬን ብሆን ኖሮ እንዳሉት ነበር የማደርገው፡፡ ነገር ግን እነዚህን ልጆች እኮ አፍርተናል፡፡ በመሀላችን ያሉት ልጆች እኔ እሱን እንድጠይቅ ግዴታ ውስጥ ይጥሉኛል፡፡ በተለይ ትልቁ ልጄ አራት ዓመቱ ነው አባቴን አሳስረሽው እያለ አኩርፎኛል፤›› ብላ ስትነግራቸው ውስጤን የሆነ ነገር ወረረው፡፡ ሴትዮዋ የልጅቷ በሳል አነጋገር ስላሳመናቸው፣ ‹‹ልክ ነሽ ልጄ ተባረኪ፣ መውለድ አይደል ስንቱን የሚያስረው?›› ብለው በሐሳብ ጭልጥ አሉ፡፡ ትንሽ ቆይተው፣ ‹‹ባለቤትሽ ከታሰረ እንዴት ትኖራላችሁ? አንቺስ ሥራ አለሽ ወይ?›› ሲሉ ሌላ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ሥራ እንደሌላት ነገር ግን አባቷና ወንድሞቿ እንደሚረዷት ተናገረች፡፡ በዚህ መራር የኑሮ ውድነት ሕፃናት ልጆች ይዞ በሰው ትከሻ ላይ መኖር በጣም ከባድ ነው፡፡ ሴትዮዋ አሁንም፣ ‹‹ቤት ኪራዩን እንዴት ቻልሽው?›› አሉ፡፡ ለጊዜው የቤት ችግር አንደሌለባትና በአባቷ ቤት እንደምትኖር ተናገረች፡፡

ልጅቷ በጣም የተረጋጋችና አስተዋይ መሆኗን የተረዳሁት በዚህ አነጋገሯ ነው፡፡ ‹‹ባሌ መጠጥ ጠጥቶ ድንገት በተፈጠረ ግጭት ጉዳት አደረሰብኝ፡፡ አባቴ ተናዶ ክስ በመመሥረቱ ፍርድ ቤት ሁለት ዓመት ፈረደበት፡፡ ከሚታሰር ይልቅ በሽማግሌ አማካይነት ተግሳጽ ተሰጥቶት ልጆቹን ቢያሳድግ ይሻል ነበር፡፡ በተለይ ትልቁ ልጄ በዚህ ምክንያት በማኩረፉ አዝናለሁ፡፡ ትንሿም ስታድግ አባታችንን አሳስራው ነበር ብሎ ሲነግራት ምን እንደምትል እያሰብኩ ይጨንቀኛል፤›› አለች፡፡

በልጅቷ የበሰለ አስተሳሰብ የተማረኩት እናት በሐዘን ተውጠዋል፡፡ ቀና ብዬ በአካባቢያችን ያሉትን ሰዎች ስመለከት ሁሉም እዝን ብለዋል፡፡ በዚህ አስተዋይነት ብርቅ በሆነበት ጊዜያችን አንዲት ፍሬ ልጅ ስለወደፊቱ ተጨንቃ ስታስብ፣ ስንቶቻችን እንሆን ራሳችንን የምንታዘበው? ስንቶቻችን እንሆን ከራስ ወዳድነት ተላቀን ለአገራችንና ለወገኖቻችን የምናስብ? ስንቶቻችን ነን የደረሰብንን ጥቃት ረስተን በዳዮቻችንን ይቅር የምንል? ስንቶቻችን ነን ከክፋት ተግባር ተወግደን በንፅህና ለመኖር የምንሞክር? እንዲህ ዓይነቱን አጋጣሚ ራሳችንን ብንመለከትበትስ?

(ታሪኩ ካሌብ፣ ከመገናኛ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...