Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉመዘዘኛው የናይሮቢ ስምምነትና የአማራ ክልል

መዘዘኛው የናይሮቢ ስምምነትና የአማራ ክልል

ቀን:

በአያሌው አስረስ

በኢትዮጵያ መንግሥትና በአማፂው በትሕነግ መራሹ ኢሕአዴግ መካከል ሲካሄድ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. በደርግ መንግሥት መውደቅ ተደመደመ፡፡ ሰኔ 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ትሕነግ እንደፈለገ የሚያሽከረክረው የሽግግር መንግሥትና የሽግግር ምክር ቤት ተቋቋመ፡፡

በሽግግር መንግሥት ምሥረታው እንደ ኦነግ ያሉ የመሣሪያ ትግል ሲያደርጉ የቆዩ፣ እንደ ጉራጌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ጉሕዴግ) ያሉ አዲስ የተመሠረቱ ድርጅቶች የምክር ቤቱ አባል ሆኑ፡፡ የአማራ ሕዝብ በምክር ቤቱ ቦታ አልተሰጠውም ነበር፡፡

መሣሪያ ያነሱትም ያላነሱትም የንጉሡንም ሆነ የደርግን መንግሥት አማራ ያቋቋማቸው መንግሥታት አድርጎ በማየትና በማቅረብ፣ በአማራ ሕዝብ ላይ ለዓመታት ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡

ትሕነግ መራሹ ኢሕአዴግ ለአማራው ‹‹ነፍጠኛ›› የሚል ስም በመስጠት በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ አማራውን የኢትዮጵያ ሕዝብ (ብሔር ብሔረሰቦች) ጠላት አድርጎ ሲሥለው ቆየ፡፡

በሽግግሩ መንግሥት የማጥላላት ዘመቻው እጅግ በከፋ ሁኔታ ቀጠለ፡፡ በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በጨለንቆ፣ በበደኖ፣ በአሰቦት፣ በሂርናና በገለምሶ፣ በአርሲ ክፍለ ሀገር በአርባ ጉጉ አውራጃ በሚኖሩ አማሮች ላይ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ተፈጸመ፡፡ አንዳንድ ቦታም ሬሳቸው ወደ ገደል ተወረወረ፡፡ መሳደድና መገደል የአማራ ዕጣ ፈንታ ተደረገ፡፡ ችግሩን በሕጋዊ መንገድ ለመከላከልና የአማራውን ብሶት ለማሰማት በ1984 ዓ.ም. የመላ አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ተመሠረተ፡፡ ‹‹እንዴት የዘረኛን መንገድ ተከትላችሁ አማራውን በዘር ታደራጃላችሁ›› የሚሉ ተቋዋሚዎች ቢበዙም መአሕድ ተከታይ አላጣም ነበር፡፡

ሁኔታው ያሳሰባቸውና ያስደነገጣቸው ትሕነግና አቶ መለስ፣ ከምሥረታው ጀምሮ ኅብረ ብሔራዊ ሆኖ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ሲያታግል የቆየውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴንን) በአንድ ሌሊት የአማራ ተወካይ አድርገው ሠሩት፡፡ የአማራ ብሔር ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ብለው ባህር ዳር ላይ አነገሡት፡፡

የብአዴን የመጀመሪያ ከፍተኛ መሪዎች በረከት ስምኦን (ኤርትራዊ)፣ ህላዊ ዮሴፍ (ኤርትራዊ)፣ አዲሱ ለገሰ (ኦሮሞ)፣ ተፈራ ዋልዋ (ደቡብ) ወዘተ. ሆነው እያለ በአማራ ስም ወንበር ላይ ተደላደሉ፡፡ በክልሉ ያሉ ዋና ዋና የመንግሥት ኃላፊነቶች አማራ ባልሆኑ ሰዎች ተያዙ፡፡ ‹‹አማራ ያልሆኑ የአማራ ክልል መሪዎችን አንፈልግም›› የሚል የተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ ለውስጥ መካሄድ ጀመረ፡፡ በእንቅስቃሴው መሪነት የተጠረጠሩ ሰዎች በድርጅቱ እንዲባረሩ፣ አድራሻቸው እንዲጠፋና አንዲገደሉ ሲደረግ ከረመ፡፡

‹‹የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በእውነት የአማራ ልጆች ናቸው ወይ?›› የሚለው ጥያቄ ዛሬም ድረስ ለክልሉ አመራር ፈተና እንደሆነ ያለ ጥያቄ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ኢሕአዴግ ፈርሶ ብልፅግና በተቋቋመ ጊዜ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከባህር ዳር መልስ፣ ‹‹የተቀበለውን አሳምነን፣ ያልተቀበለውን አደናግረን መጥተናል፣ ብልፅግናን ያቋቋምነው ለእኛ ጥቅም ነው፤›› ብለው መናገራቸው ደግሞ ያለ መታመኑን ጉዳይ በእጅጉ አባብሶታል፡፡

‹‹የአማራ ክልል መሪዎች፣ በእውነት አማራዎች ናቸው ወይ?›› የሚለው ጥያቄ እያደር እንዲያገረሽ ያደረገው ደግሞ ከክልሉ ውጪ በሚኖሩ አማራዎች ላይ በየጊዜው የሚፈጸሙ በደሎች መብዛትና ከጊዜ ወደ ጊዜም በዓይነትም በመጠንም እየጨመሩ መምጣታቸው አልፎም ተከላካይ ማጣታቸው ነው፡፡

አንድ ቀን አይደለም ከዓመት እስከ ዓመት በተለይም በምሥራቅና በምዕራብ ወለጋ አማራው በዘር እየተለየ ቤት ንብረቱ ሲዘረፍና ሲቃጠል፣ እንደ አውሬ እየተሳደደ ሲገደል፣ አማራን እወክላለሁ የሚለው የአማራ ክልላዊ መንግሥትና ገዥ ፓርቲ የክልሉ ችግሩን ለማስወገድ የሚጨበጥ ሥራ አለመሥራታቸው አለመታመኑም አጠናከረው፡፡  

ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች አዲስ አቅጣጫ ይዘዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ የሚያስገቡ መንገዶች በአማራ ላይ ሲፈለግ የሚከፈቱና የሚዘጉ ሆነዋል፡፡ አሁንም የክልሉ መንግሥት ሆነ የፌዴራል መንግሥት አልፎም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጉዳዩ ሲያሳስባቸው ዓይታዩም፡፡

ወደኋላ እንመለስ፣ ኅዳር 2013 ዓ.ም. ስብሃታዊያኑ (ትሕነግ) በኢትዮጵያ መንግሥት መከላከያ ሠራዊት ላይ ጦርነት ከፈቱ፡፡ እንደ እነሱ መድፍና ዙ23 በእጁ የሌለው የአማራ ልዩ ኃይል የነፍስ ወከፍ መሣሪያ ይዞ ከመከላከያ ጎን ተሠለፈ፡፡ መንግሥት የተበታተነ ኃይሉን አሰባስቦ በመሣሪያ የበላይነት ታግዞ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመቀሌን ከተማ ለመያዝና የትግራይ ክልል ለመቆጣጠር ቻለ፡፡ በክልሉም ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም አደረገ፡፡

የትግራይ ክልል ተወላጆች በአደባባይ እንደመሰከሩት፣ በፖለቲካ ሴራ የተካኑት ስብሃታዊያኑ የአማራ ልዩ ኃይል ዩኒፎርምን አልብሰው፣ የራሳቸውን ሴቶች በራሳቸው ሠራዊት እንዲደፈሩ አድርገው ‹‹የአማራ ልዩ ኃይል በሺሕ የሚቆጠሩ የትግራይ ሴቶችን ደፈረ፤›› የሚል ክስ በዓለም ዙሪያ አሠራጩ፡፡ መከላከያን ተከትሎ የገባው የአማራ ልዩ ኃይል ለፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተጋለጠ፡፡ ጌታቸው ረዳ፣ ‹‹በአማራ ላይ የምናውራርደው ሒሳብ አለን›› ብሎ ተነሳ፡፡ በአማራና በአፋር ክልሎች ከፍተኛ ጥቃት በከፈቱ ጊዜ ሠራዊታቸው የአማራ ልጃገረዶችንና ሴቶችን ብቻ ሳይሆን በዕድሜ የገፉ መነኮሳትን በመድፈር መራራ በቀል ፈጸመ፡፡

የአማራን ቤት በማቃጠል፣ አንዳንዱንም መቃብር ቤትና መታኮሻ በማድረግ፣ ማጋዝ የሚችለውን ንብረት በማጋዝ፣ የማይችለውን በማውደም፣ የጓሮ አትክልቱንና ዛፉን በመጨፍጨፍ፣ ከብቱን የሚታረደውን አርዶ በመብላት የተረፈውን በጥይት በመደብደብ አማራ ያለ ሀብትና ጥሪት እንዲቀር በማድረግ ሠራዊታቸው አብዝቶ ሠራ፡፡ የስብሃታዊያን ጦር እግሩ በረገጠበት እጁ በደረሰበት አማራ ክልል የሚገኝን የመንግሥት ተቋም ትምህርት ቤትና ሐኪም ቤት ሙልጭ አድርጎ ዘረፈ፡፡ መውሰድ ያልቻለውን ከጥቅም ውጪ በማድረግ ሰባበረ፡፡

የልብ ልብ የተሰማው የስብሃታዊያን ጦር ሰፊውን የአማራ አካባቢ እያወደመ ደብረ ሲና ደረሰ፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት ሥጋት ገባው፡፡ ‹‹መሣሪያ ያለህ መሣሪያህን ይዘህ ተከተለኝ፣ የሌለ እየማረክህ ታጠቅ›› የሚል ጥሪ ለአማራ ሕዝብ አስተላለፈ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ዘመቱ፡፡

ነገሩን የህልውና ጉዳይ አድርጎ የተረዳው የአማራው ፋኖ በራሱ ስንቅና ትጥቅ ከመከላከያ ጎን ተሠለፈ፡፡ በመንግሥት አማርኛ ‹‹መከላከያና ጥምር ጦሩ›› በመልሶ ማጥቃት ወደፊት ገሰገሱ፡፡ ትግራይ ክልል በመግባትም መቀሌን በከበባ ሥር አደረጓት፡፡ የነገሩ መቋጫ ድርድር ነው ተባለ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና አሸባሪው ስብሃታዊያኑ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለድርድር ተቀመጡ፡፡ በድርድሩ፣ በአንድ ወር ውስጥ የትግራይ መከላከያ ኃይል የሚባለው የስብሃታዊያን ጦር ሙሉ በሙሉ ትጥቁን እንዲፈታ፣ የፌዴራሉ መንግሥት መሠረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ቦታቸው እንዲመልስ፣ ጊዜያዊ የክልል አስተዳደር እንዲያቋቁም፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ክልሉ እንዲገባ ወዘተ. እንዲያደርግ ከስምምነት ተደረሰ፡፡

ከዚህ ስምምነት በመነሳት የስብሃታዊያን ጦር መሪዎች የመከላከያ ከፍተኛ አዛዦች ናይሮቢ ላይ ተገናኝተው ተጨማሪ ስምምነት አደረጉ፡፡ ኬንያ ላይ የተደረገው ስምምነት ‹‹የትግራይ ታጣቂዎች ትጥቅ የሚፈቱት በክልል ውስጥ የሚገኙት ሌሎች ኃይሎች ከክልሉ ሲወጡ ነው›› የሚል የመጀመርያውን ስምምነት በከፊል የሚያፈርስ ስምምነት ተፈረመ፡፡ ይህ ስምምነት በአማራ ክልል ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ አነጋጋሪና አወዛጋቢ የሆነውን የወልቃይት ጠገዴንና የራያ አላማጣን ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ሆኖ ተገኘ፡፡ በአማራው አካባቢ ጉምጉምታ በዛ፡፡ ወዴት ሊወስዱን እያሰቡ ነው የሚል ጥያቄም ቀሰቀሰ፡፡

በስምምነቱ ምክንያት የጥይት ድምፅ ፀጥ ሲል፣ ‹‹የአማራው ፋኖ የታጠቀው ጥቁር ክላሽ የመከላከያን ሰው በመግደል የተወሰደ ነው›› የሚል ክስ መንግሥት በፋኖ ላይ ከፈተ፡፡ ‹‹ያልተገባ ትጥቅ ይዛችኋል›› በማለት በሺሕ የሚቆጠሩ የፋኖ አባላት ወደ እስር ቤት ተወረወሩ፡፡ ዛሬም በእስር ላይ የሚገኙ አሉ፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በመነሳት›› እየተከሰሰ ያለው የምሥራቅ አማራ ፋኖ መሪ ምሕረት ወዳጆ፣ ‹‹ጥቁር ክላሽ የታጠቅነው ማርከን ነው፣ ይህንን ደግሞ መከላከያ ያውቃል›› በማለት ሁኔታው አስረዳ፣ የሚሰማና የሚታረም መንግሥት ግን አልተገኘም፡፡

የናይሮቢው ስምምነት በተለይም ቀደም ሲል በጠቀስኩት የስምምነት አንዱ ክፍል በአማራ ሕዝብ ዘንድ አሁንም በጥንቃቄ የሚታይ ሆኗል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት የደቡብ አፍሪካውን ስምምነት በተገቢው መንገድ በተግባር እንዲውል አለማድረጉ አልፎም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈቃድ፣ የትግራይን ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እነ አቶ ጌታቸው እንዲመሩት መደረጉ የአማራን ሥጋት ይበልጥ የባሰ አድርጎታል፡፡

‹‹የትግራይ የመከላከያ ሠራዊት›› የሚባለው ኃይል በሚያስተማምን ደረጃ ከባድና ቀላል መሣሪያውን ባልፈታበት፣ ሠራዊቱም ወደ ተሃድሶ ባልገባበት፣ ከእነ ጌታቸው ረዳ ዕዝ አፈንግጠዋል የሚባሉት እንደ ብርጋዴር ጄኔራል አብርሃም (ወዲ ድንኩል) ከሰላሳ ሺሕ የታጠቀ ጦር ጋር እንዳሉ በሚነገርበት ጊዜ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲደርስበት ለኖረው የአማራ ሕዝብ፣ ዘብ የቆመውን የአማራ ልዩ ኃይልንና ፋኖን ወደ መከላከያና የደኅንነት ኃይሎች ለማስገባት የመንግሥት መጣደፍ ምን ታስቦ ነው የሚል ከባድ ጥያቄ ቀስቅሷል፡፡

መንግሥት ትጥቅ ለማስፈታት አልተነሳሁም እያለ ነገሩን ለማቃለል ይሞክር እንጂ፣ የዕዝ ሰንሰለት መበጣጠስ ለአንድ ሠራዊት ምንም ማለት እንደሆነ አይረዳም ብዬ ለማሰብ ይከብደኛል፡፡

የአማራው ልዩ ኃይል ጉዳይ ግድ የለም፡፡ የኤርትራ ጦር ኢትዮጵያ ውስጥ የለም በማለት ሁለት ዓመት ሙሉ ሲሟገት የቆየው መንግሥት ምን ጥቅም ቢያገኝበት ነው፣ ተደራዳሪዎቹስ እንደምን ማስተዋልና ነገር መመርመር ቢሳናቸው ነው ይህን አወዛጋቢ የናይሮቢ ስምምነት አካል የሆነውን የትጥቅ አፈታት ጉዳይ ያስገቡት? የሚል ጥያቄ በአዕምሮዬ ውስጥ ደጋግሞ መመላለሱን መደበቅ አልፈልግም፡፡

ወልቃይትና ጠገዴ፣ እንዲሁም ራያና አላማጣ በ1968 ዓ.ም. በወጣው የትሕነግ የፖለቲካ ፕሮግራም የትግራይ ክልል አካል እንዲደረግ የታሰበ፣ በኋላም የትሕነግ መንቀሳቀሻ የሆነ፣ በ1987 ዓ.ም. በፀደቀው ሕገ መንግሥት ትግራይ ክልል አካል የተደረገ ነው፡፡ የወልቃይት ጠገዴም ሆነ የራያ አላማጣ ሕዝብ አማራ ነን በአማራ ክልል ውስጥ መተዳደር አለብን? ብለው ጥያቄ ማቅረብ የጀመሩት ዛሬ ሳይሆን ከሽግግሩ መንግሥት ምሥረታ ጀምሮ ነው፡፡ በሺሕ የሚቆጠሩ የአካባቢ ተወላጆች ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉበት ጥያቄ ነው፡፡ ጦርነቱ በፈጠረው አጋጣሚ ከትግራይ አገዛዝ መላቀቃቸውን በደስታ በመቀበል አሁንም አማራነታችን ይከበር በሚል ጥያቄ እየገፉ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ደግሞ ስለጉዳዩ በተናገሩ ቁጥር፣ ‹‹ሁልጊዜ በኃይል አይሆንም›› እያሉ ናቸው፡፡ በኃይል የተያዘን አካባቢ ሕገ መንግሥታዊ ባደረገ አካሄድ፣ ግፍ በዝቶብኛል እያለ ምሬቱን እየገለጸ ባለው ሕዝብ መካከል ነገሩን የሚያበርድ ወይም ሁሉም ሰው በሰከነ ህሊና ስለጉዳዩ መምከር የሚችልበት ጊዜ እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ መንግሥት ሲያስብ ዓይታይም፡፡

እንዲያውም የተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር የነበሩ) ‹‹አስቀድሞ ትጥቅ የሚፈታው የአማራ ልዩ ኃይል ነው›› ሲሉ የሰጡት መግለጫ፣ ‹‹የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ ልዩ ኃይሉን ትጥቅ እናስፈታለን›› ከሚለው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ጋር ተዳምሮ ሲታይ ይህ ነገር የጤና ነው ወይ ያሰኛል፡፡ የአማራ ክልል የብልፅግና ቢሮ ኃላፊ የአቶ ግርማ የሺጥላ መገደል ደግሞ መንግሥት ለተያያዘው የይለይናል ዕርምጃ የተመቸ ሁኔታ እንደፈጠረ አያጠራጥርም፡፡

ለእኔ የአቶ ግርማ የሺጥላ መገደል ከሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል የተለየ አይደለም፡፡ የሁለቱም ገዳዮችና አስገዳዮች ሊያጠፉት የተነሱት ሕዝብ አለ፣ ያ ሕዝብ ደግሞ አማራ ነው፡፡ የማኅበራዊ አንቂው አቶ ሥዩም ተሾመ፣ ‹‹ኢትዮጵያን ለማፍረስ አማራን ማተራመስ›› የሚል ፕሮግራም ሰሞኑን አቅርቦ ነበር፡፡ አማራን ለማተራመስ የተነሳው ማን እንደሆነ በግልጽ ባይታይም፣ መንግሥት ግን እያገዘው እንደሆነ በድርጊቱ መገንዘብ ይቻላል፡፡

‹‹በክልላችን ዙሪያ ያለው ሁኔታ የዕዝ ሰንሰለታችንን እንድናፈርስ ወደ ልዩ ልዩ ወታደራዊ ክፍሎች እንድንገባ የሚያደርግ አይደለም›› እያለ የዋስትና ጥያቄ እያነሳ ላለው ፋኖና ልዩ ኃይል የክልሉ ሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ዋስትና የሚሰጥ ዕርምጃ ሲወስዱ ዓይታይም፡፡ ይህ ሥጋት መንግሥትና የአማራ ኃይሎች ወደግጭት እንዲገቡ በሰዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል፡፡ እንደ ከሚሴ፣ አጣዬ፣ ሸዋ ሮቢት፣ ደብረ ማርቆስ፣ ወዘተ. የግጭት አካባቢ ሆነው መሰንበታቸውም የታወቀ ነው፡፡

በጎንደር እንደተደረገው የክልሉም ሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ነገሩን በትዕግሥት ሊይዙት ይገባል፡፡ ከሁሉም አስቀድሞ ደግሞ የአማራን ሕዝብ ከሥጋት ነፃ የሚያደርግ ዋስትና ሊሰጥ ግድ ይላል፡፡

ደግሜ እናገራለሁ፣ የችግሩ ምንጭ ፋኖ ወይም ልዩ ኃይል ሳይሆን የናይሮቢው አልፎም የደቡብ አፍሪካው ስምምነት በመንግሥት በተገቢው መንገድ በተግባር አለመተርጎም ነው፡፡ አሁንም መንግሥት ራሱን ምን እየሠራሁ ነው ብሎ ሊጠይቅ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ሆይ ፈጣሪ ከክፉ ነገር ይጠብቅሽ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...