Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትዛሬ ለዓለም ሰላም ያልተጮኸ መቼ ሊጮህ!

ዛሬ ለዓለም ሰላም ያልተጮኸ መቼ ሊጮህ!

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ አገሮች ጎራዊ ግጥሚያዎች ነበሩ፡፡ በእነዚህ የዓለም ጦርነቶች ውስጥ የቀጥተኛ ግብግብ ሥፍራዎችና ተዋናዮች ቶሎ ሲበረክቱ ታይተው ነበር፡፡ አሁን ዓመት ገዳማ በሆነው አሜሪካና አውሮፓ ከሩሲያ ጋር በገጠሙት ጦርነት ይህ አልሆነም፡፡ በድብስብስ ዲፕሎማሲና በንግድ ከማገዝ በቀር የሩሲያ ባልንጀሮች በጦርነቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ አልሆኑም፣ አሁን ድረስ የጦርነት ሜዳዋ ዩክሬን ነች፡፡ አሜሪካና አውሮፓ ጦርነታቸውን የሚያካሂዱት በጦር መሣሪያ አጋዥነት ተቆጥበው፣ የዩክሬንን ዜጎችና ውስን ቅጥረኞችን በተዋጊ ኃይልነት እየተጠቀሙ ነው፡፡

የጦርነቱ ተራዝሞ መቀጠል ከማንም በላይ ሩሲያን እንደሚያደቅ፣ የሩሲያ መድቀቅም የቻይና መድቀቅ መሆኑ ሁለቱ ሸሪክ ኃያላን (ቻይናና ሩሲያ) ዘግይቶ ታውቋቸዋል፡፡ ግን ጦርነቱን ለማስቆም የጠነከረ ሥራ እየሠሩ አይደሉም፡፡ ሁለቱም ወጥመድ ውስጥ የገቡ መስለዋል፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ ዓላማ ፈጣን የጦር ሜዳ ድል ሳይሆን ልዕለ ኃያላዊ አቅምን/አቅሞችን እየገዘገዙ የመዘረር ነው፡፡ የዩክሬን ጦር ሜዳነት ቶሎ እንዲያበቃ ፍላጎት የላቸውም፡፡ የጦር መሣሪያ አረዳዳቸው የረዥም ዕቅድ አመጣጠን ያለበት ነው፡፡ ሩሲያ ከዩክሬን ውጪ ሌሎች የኔቶ ቃል ኪዳን አገሮች ላይ እንድትተኩስም የትንኮሳ ግብዣ እየቀረበላት ነው፡፡ የፖላንድና የስሎቫኪያ የውጊያ አውሮፕላን ለዩክሬን መርዳት የቀድሞ ቂምን ያስታወሰ ትንኮሳ ነው፡፡ የፊላንድም ኔቶን መቀላቀል በረዥም ድንበር ኔቶ የሩሲያ ወሰንተኛ የሆነበት አዲስ ክስተት ነው፣ ‹‹ዩክሬይን ላይ ዘራፍ እንዳልክ ፊላንድ ላይ እስቲ እንይሃ!›› የሚል መልዕክትም አለበት፡፡

በኢንዶ ፓስፊክ እስያ በኩልም ጦርነት እንዲከፈት በተለይ አሜሪካ እየሠራች ነው፡፡ ቻይናን በቻይና ለመውጋት አገልግሎት ታይዋን ሌላ ዩክሬንነትን ታጭታለች፡፡ ፊሊፒንስ ከእነ ሕዝቧ የፀረ ቻይና – ሰሜን ኮሪያ የጦር ካምፕ መሆንን ፈቅዳለች፡፡ የአሜሪካ፣ የብሪታኒያና አውስትራሊያ (አውከስ) ጥምረት ደግሞ ታይዋንና ፊሊፒንስን ከራስጌ አድርጎ አውስትራሊያን ዋና ጣቢያ ሊያደርግ ያቀደ ይመስላል፡፡ በዚህ ከበባ መሀል ውስጥ ያሉት ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ከአሜሪካ ጋር የጦር ልምምድ ቢያደርጉም፣ የአሜሪካ ጦርነት ንቁ አጋር በመሆን ረገድ ገና እንዳደቡ (ንቁ ተሳታፊነት የሚያስከትለውን ትርፍና ኪሳራ እየመረመሩ) ናቸው፡፡ ጃፓን የሩሲያ ነዳጅ አንዷ ሁነኛ ገዥ መሆኗም ይህንኑ ወዝወዝ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቻይና ትዕግሥቷ ተሟጦ ታይዋንን አኝ እንድትል ግፊቷን ማሞቅ ቀጥላለች፡፡

ሩሲያ ብዙ ኃይሎችን የገጠመችበት የአሁኑ ጦርነት በዚሁ ከቀጠለ የሩሲያ የጦርነት ‹‹ድሎች›› እዚያም እዚያም ቢታዩ እንኳ፣ እያንዳንዷ ቀን ለሩሲያ አቅም እያነሰ የሚሄድበት ነው፡፡ ለቻይናም እያንዳንዷ ቀን ብቻዋን ተጋልጣ የምትገኝበት ቀን መቅረብ ይሆናል፡፡ እነ ቻይና፣ ሩሲያና ሌሎች አጋሮቻቸው የሻንጋይ ትብብርንም ሆነ ሌሎች ሽርክናዎቻቸውን ከአዲሱ የሳዑዲ ዓረቢያና የኢራን ቅርበታቸው ጋር ሆነው፣ ምዕራብ አውሮፓን እንደ ምንም ወደ ሰላም እንዲመጣ የሚገፋ የእጥረት/የግሽበት ጭንቅ ውስጥ ካልከተቱት በቀር፣ አውሮፓና አሜሪካ በአሁኑ ሰዓት ሊቀበሉት የሚችሉት ከጦርነት የመውጣት ‹‹መፍትሔ›› ሩሲያን አሸንፎ ከመቅጣት ብዙም የራቀ አይደለም፡፡ ማለትም የተወሰዱ መሬቶችን መልሶ የዩክሬን ውድመትና የጦርነት ወጪ ካሳ ከማስተፋት ያነሰ አይሆንም፡፡ ይህ ደግሞ ሩሲያ በተሸናፊነት ምርኮኛ ብትሆን የሚከተላትን የግዛት መበታተን ወዲያውኑ ይዞ የሚመጣ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ተኩስ አቁሞና ከእነ አሜሪካና ዩክሬን ጋር ሰላም መፍጠር በአሁኑ ሰዓት የሁለት በኩል ፍላጎት መቻቻል የማይገኝበት ነው፡፡ እጅ ሰጥቶ የጦርነት ወጪን እጥፍ በእጥፍ ለማስመለስ የተራበ ጅብ የሩሲያ የተፈጥሮ ሀብት ላይ እንዲሰፍር ከመፍቀድ ብዙም የራቀ አይደለም፡፡

ተኩስ አቁሞ ሰላም መፍጠር በአሁኑ ሰዓት እጅ እንደ መስጠት ያለ ወጥመድ የሆነባት ሩሲያ፣ ሄዳ ሄዳ ወደ ኑኩሌራዊ አጥፍቶ መጥፋት ዓይነት ቀቢፀ ተስፋ ውስጥ ብትገባ ተጎጂነቱ የዓለም ይሆናል፡፡ ከኑኩሌር በመለስ በሆነ ጦርነት የትኛውም ጎራ ተቀናቃኙን ቢዘርር ደግሞ፣ ከማንም በላይ ደሃና ታዳጊ አገሮች እንደ ሰርከስ እንስሳት በአለንጋ ሾጥ እየተደረጉ ሁኑ የተባሉትን መሆን ዕጣቸው ይሆናል፡፡ ይህ ላይሆን የሚችለው ጦርነቱ ‹‹አሸናፊ››ንም ተሸናፊንም ካደከመና የኃያል ኃያልነት ክፍተት ከተፈጠረ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመሟላት ዕድሉ ጠባብ ነው፤ ምክንያቱም ከአሸናፊዎቹ ውስጥ እንደ ተሸናፊዎቹ የልዕለ ኃያልነት አቅሙ ዝሎ ቦታ የሚለቅ አሮጌ ቢኖርም ጉልበት ቆጥቦ ቦታ ለመረከብ ያደባ አይታጣምና፡፡

እናም የአሁኑ ሰዓት የአውሮፓና የአሜሪካ ፍላጎት በጦርነት ሩሲያን ማድቀቅ ነው የሚል ትንታኔ የሚሰጥበት ሳይሆን፣ የዓለም አቀፍና አኅጉራዊ ተቋማትና የሲቪል ማኅበራት ኃይል አስተባብረው ለዓለም ሰላም የሚጮሁበት ነው፡፡ የቀደሙት ሁለት ‹‹የዓለም›› ጦርነቶች ገና ከፍጥጫቸው ጀምሮ የነቃ ተቃውሞ ነበረባቸው፡፡ ጦርነቱ ከዩክሬን ባሻገር በፓስፊክ እስያ ውስጥ ጦር ሜዳዎችን ከከፈተ በዚያ አካባቢ የተፈጠረ ብልፅግና ሁሉ ዶጋ አመድ ለመሆን ይጋለጣል፡፡ ኑክሌር ጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ ባይውል እንኳ ምድራችን በጥቅሉ ምን እንደሚተርፋት ለመናገርም ይቸግራል፡፡ እናም ቅጠል ጥለው እንደሚደነቁሩ ተክሎች ዛሬ በዝምታ መጋገር ናዳን ወይም ጎርፍን ተኝቶ ከመጠበቅ ብዙም አይርቅም፡፡ ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ የዩክሬኑ ዘለንስኪ ይዋል ይደር እንጂ ድል የእኛ ነው ባይነት ነው፡፡ የሆነ መለኮታዊ ኃይል ገንዟት የኑክሌር አቅሟን ሳትጠቀምበት ሩሲያ ብትሸነፍ ዘለንስኪ ከተመለሱ መሬቶች ጋር ፍርስራሽ በፍርስራሽ የሆነች አገር ላይ ቆሞ በኩራት ‹‹ይኼው አሸናፊነታችን ዕውን ሆነ!›› ሊል ይሆን!

ነገዋ ያልለየላትን ዓለማችንን ዕጣ ለማቃናት የተከፈተ ልቦናና የጎበዘ ድምፅ ይስጠን!!

በዚህ መንፈስ ውስጥ ሆነን ወደ ቤታችን አንዳንድ ጉዳዮች እንግባ፡፡

መሠረታዊ ዕሳቤዎች ከብሔርተኝነት ወደ ኅብራዊነት ለመሻገር

 1. ኢትዮጵያን ስንጠራ ወይም ስናስብ ምን ድቅን ይልብናል? ዝንጉርጉርነትና መወራረስ/ዓይነተ-ብዙነትና ድፍርስነት ገጽታዎቹ የሆነ አገር፡፡ በዓይነተኛ ማኅበረሰብነቱ ንፁህ የሆነ ማኅበረሰብ የለም፡፡ በእያንዳንዱ ማኅበረሰባችን የአመጣጥ ታሪክ ውስጥ ድፍርስነት አለ፡፡ ዛሬ ባለ ዓይነተኛነት ውስጥ ድፍርስነት አለ፡፡ ዓይነተኛ ማኅበረሰብ ከሌላ ማኅበረሰብ ባለው ጉርብትና ውስጥ የተቀላቀለ ድፍርስ አለ፡፡ ንፁህ ሶማሌ፣ ንፁህ ኦሮሞ፣ ንፁህ ጌዴኦ፣ ንፁህ ሲዳማ፣ ንፁህ ኮንሶ፣ ወዘተ የለም፡፡ ንፅህና ያለው ከየት እስከ የት ነው የሚል ነገር ውስጥ ብንገባ፣ ወይም የእያንዳንዱን ማኅበረሰብ ‹‹ትክክለኛ›› መለያ ወሰን ለመለየትና ለማስመር ብንባዝን ራስን አለማወቅ ይሆንብናል፣ ከእውነታ ጋር መላተም ይሆንብናል፡፡ ዓይነተኛነትን ከድፍርስነቱ (ከተወራራሽነቱ) ጋር መቀበል ይኖርብናል፡፡ ዓይነተኛነታችንን ከዝንጉርጉርነታችን ጋር አጣምዶ ማየት ማኅበረሰባችንንም አገራዊ ማንነታችንንም ማወቅ ነው፡፡ ስለዝንጉርጉርነት (ዳይቨርሲቲ) ሲወራ ብዙ ሰው ድቅን የሚልበት ኢትዮጵያ ብዙ ብሔረሰቦች የሚገማሸሩባት አገር መሆኗ ነው፡፡ ይህ አንድ ዓይና ግንዛቤ ነው፡፡ ግንዛቤያችን ሙሉ እንዲሆን ከፈለግን የየብሔረሰብ ጥንቅራችን ራሱ በዝንጉርጉርነት የተሞላ መሆኑን ማጤን አለብን፡፡ ሶማሌነት በዝንጉርጉርነት የተሞላ ነው፡፡ ኦሮሞነት ራሱ ዝንጉርጉር ነው፡፡ አማራነት ዝንጉርጉር ነው፡፡ አገውነት ዝንጉርጉር ነው፣ ወዘተ፣ ወዘተ…፡፡ ይህንን ለማስረዳት የመረጃ ችግር የለም፣ ጥልቅ ምርምር የሚሻም አይደለም፡፡
 2. ኅብረ ብሔራዊ ጥንቅርና ኅብራዊ አመለካከት በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ ጥንቅር በማኅበር፣ በተቋም ወይም በፓርቲ ውስጥ ያለ ብሔረሰባዊ ስብጥርን (ዝንጉርጉነትን) የሚመለከት ነው፡፡ ‹ኅብረ ብሔራዊ ጥንቅር› በማለት ፈንታ ‹ዝንጉርጉር ጥንቅር› የሚል አባባል ከተጠቀምን ደግሞ ከብሔረሰብ ባሻገር በፆታ፣ በዕድሜ፣ በሙያ፣ በሃይማኖት፣ ወዘተ ስላሉ ስብጥሮች ለማውራት ያስችለናል፡፡ ከየት ይምጣ ከየት ለማናውቀው ሰው ጉዳት ማዘን፣ አነሰም በዛ ሁላችንም ዘንድ አለ፡፡ ለአኅጉራዊ ወገንና ለአገር ልጅ መቆርቆርም እንዲሁ የትኛውም ሰው ዘንድ አለ፡፡ ግብታዊ ግንዛቤ መያዝና የጎለበተ ግንዛቤ መያዝ ግን ይለያያሉ፡፡ የሰው ልጅን ያለ አድልኦ የሚያገለግል ተቋምን የሥራ ተልዕኮ የሚቀበል ሰው ከጥላቻዎችና ለአገሬ/ለአኅጉሬ በየት በኩል ላድላ ከሚል አባዜ መላቀቅ ግዱ ነው፡፡ አኅጉራዊ ተልዕኮ ባለው ተቋም ውስጥ የሥራ ድርሻ የሚቀበልም ሰው ለአኅጉራዊ ማንነትና ዓላማ መታመን አለበት፡፡ በአገር ደረጃም እንዲሁ ከጎጥ/ከብሔረሰብ፣ ወዘተ ከለር መውጣት አለበት፡፡ ከዚህ ቀደም ለግንዛቤ እንዲረዳ የተጠቀምኩበትን የብርሃንን ኅብራዊ ባህርይ ልድገመው፡፡ ብርሃን ሁሉንም ከለር ብርሃኖች አካቶ ሲይዝ ከለር አልባ ነው፡፡ ከለር አልባው ብርሃን ሲሰተር (ሲተነተን) ግን የሁሉንም ከለር ብርሃኖች በሠልፍ ይዞ እናገኘዋለን፡፡ እንደ ሰው፣ እንደ አኅጉር፣ እንደ አገር በማሰብና በመሥራትም ረገድ ከለር አልባ መሆን ማለት በየማዕቀፉ ውስጥ የሚገኙትን ከለሮች ሁሉ አካቶ ለአንዱም ሳያዳሉ ማስተዋል ማለት ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ/ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ነን የምንል ሁሉ ይህን ባህርይ በማሟላት ረገድ ገና ገና ብዙ ይቀረናል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ አገራዊ ነኝ የሚል ፓርቲ ኅብረተሰቧ የሚሻውንና የሚያሻውን (ሕይወትን የሚያራምድ) ሐሳብና ዕቅድ ማንገብ ይፈለግበታል፡፡ በጥንቅር ኢትዮጵያን መምሰል ይጠበቅበታል፡፡ ከለር አልባ መሆን ግዱ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ያለው በስመ ትግል ጠመንጃ ተኳሽ የተቃለለበትና የፌዴሬሽን አባል አካባቢዎች የአካባቢዬ የሚሉት ጦር የማያደራጁበት፣ ከመራራ ልምድ የተማረ የሰላም ሁኔታ፣ ሦስቱን ነገሮች በአግባቡ የያዙ ፓርቲዎች እየፈኩ እንዲወጡ የሚመች ነው፡፡ ‹‹የአማራ ክልል/የአማራ ሕዝብ›› የሚል አነጋገር ይዞ የማወራችሁ በአካባቢው ስላለው ስለአማራ፣ ቅማንት፣ አገውና ኦሮሞ ሁሉ ነውና እንደዚያ ተረዱኝ ማለት አይቻልም፡፡ አጠራርን ማረም ግድ ነው፡፡ በአካባቢያዊው የመንግሥት መዋቅር ውስጥም ዝንጉርጉርነት ሲገማሸር ማየት እንጠብቃለን፡፡ በየአካባቢው ማኅበረሰቦችን ያልዘነጋ ሁኔታ ውስጥ መግባት፣ የሁሉም ማኅበረሰብ ሰዎች በየአካባቢያቸው የሥራ ቋንቋ ሲምነሸነሹበትና ለየአካባቢያቸው ግስጋሴ ቤቴ/ወንዜ ብለው በንቃት አንድ ላይ ሲተምሙ ማየት አካባቢንም አገርንም ያጠነክራል፡፡

ድሮ ኢሕአፓ የሰሜን ሰዎች 80 በመቶ የሆኑበት የፓርቲ ጥንቅር ይዞ ሲዳሞ ውስጥ የትጥቅ ትግል ሊጀምር ሲያቅድ አንዱ ችግር፣ ‹‹ስለአማራ ገዥዎች/ባለርስቶች›› ጭቆና በሚወራበት ዘመን የአማርኛ አንደበት ይዞ የአማራ ገዥዎችን እንታገላለን ሊባል ነው? የሚል እንቆቅልሽ ገጥሞት እንደነበረ አንድ የኢሕአፓ ሰው በጻፈው መጽሐፍ ላይ አንብቤ ነበር፡፡ ዛሬ ካሉት ‹‹አገራዊ ነኝ›› ከሚሉ ፓርቲዎች ውስጥ ከብልፅግና ሌላ የጥንቅር ዝንጉርጉርነት በማሟላት ረገድ ተስፋ የሚደረግበት ኢዜማ ነው፡፡ ኢዜማ በሕዝብ ዘንድ የእኔ/የሁላችን ፓርቲ ለመባል ሁሉን የሚረታ ሐሳብ፣ ሁሉም አለሁበት የሚለው ዝንጉርጉርነት ላይ መድረሱና በከለር የለሽነት መታወቁ እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚያ ውስጥ ቢሮ ከፍቶ የዚያን ቅርንጫፍ መሪ ኦሮሞ ማድረግ፣ ወይም ተሟሙቶ ኦሮሞ የሆኑ ቀስቃሾችና የምርጫ ዕጩዎች ማዘጋጀት በቂ አይሆንም፡፡ በኦሮሚያ አባላቱ ውስጥ ኦሮሞዎች ከሌሎች የማኅበረሰብ አባላት ጋር እንደ ልብ ሲገማሻሩ ለማየት ሲቻል ጭምር ነው ኢዜማ ኦሮሞም የእኛ ፓርቲ የሚለው መሆኑ የሚሳካለት፡፡ ከዚህ ግንዛቤ ሌሎች ‹‹አገር አቀፍ ፓርቲ›› ነን የሚሉም ትምህርት እንደሚያገኙ ይታመናል፡፡ ከተጠቀሰው መመዘኛ አኳያ፣ የብልፅግና ፓርቲና የኢፌዴሪ መንግሥት ወደፊት ሕዝብ አቀፍ ለውጥና ልማትን የሚያንቀሳቅሱ ከዋክብትን እንደሚያበራክት ይጠበቃል፡፡ ከፅንፈኝነትና ከጨለምተኝነት ጋር በተያያዘ የጦርነት ሁኔታ የዳሸቁት የሰሜን አካባቢዎች በቶሎ እስካልፈጠኑ ድረስም፣ ኢትዮጵያ ብዙ ከዋክብት የምታፈራበት አካባቢ ወደታች (እስከ ደቡባዊ ምዕራብና ምሥራቅ ድረስ) የተንሸራተተ ይመስላል፡፡

በዴሞክራሲ ውስጥ የመኖር ፍላጎትና እንጭጭነት

ሀ) በኢትዮጵያችን ውስጥ የዴሞክራሲ ግንባታ ገና መጀማመሩ ነው (ዴሞክራሲን መኖር የጀመርነው ገና የቅምሻ ያህል ነው)፡፡ ጅማሪውን የዴሞክራሲ ግንባታ እያፋፋን ለመሄድ የማንችልበት ሁኔታም ውስጥ ነበር የቆየነው፡፡ ይህ አባባል የነበርንበትን ፈተና በደንብ አይገልጸውም፡፡ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥታዊ ዓምዶች የተሰባበሩበትና የአንድ ክልል ገዥ ቡድን ክልሉን አገር ብሎና ‹‹መከላከያ ሠራዊት›› ገንብቶ አገርን የወረረበት ቀውስ ውስጥ ነበርን፡፡ አሁንም ይህ ቀውስ እንዳይደገም የታጠቀ ኃይል አደረጃጀት ሕጋዊ አስተዳደርን ገና በማስተካከል ላይ ነን፡፡ በአጭሩ የቆየነው አገራዊ የህልውና ግብግብ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ‹‹አገራዊ አርበኝነትን ከማጠናከር በስተቀር የሚረብሽና የሚያዳክም ማናቸውም የንግግርና የጽሑፍ ተግባር ሁሉ ያስጠይቃል›› የሚል አዋጅ ቢታወጅ ኖሮ እንኳ አግባብ እንጂ ጥፋት አይሆንም ነበር፡፡ ውድመቱ፣ ሽብሩ፣ ግድያው፣ ማፈናቀሉ፣ አሉባልታው፣ ሐሰተኛ ወሬው ፋታ የሚሰጥ አልነበረም፡፡ መረጃ አደራጅቶ ከሶ የመፋረድ መደበኛ ሒደት በጊዜው ኢትዮጵያ ከነበረችበት የፀጥታ ችግሮችና የዕርምጃዎች አጣዳፊነት ጋር የሚግባባ አልነበረም፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ያሉ አገር ወዳዶች በኅብረት የተዋደቁበት ታሪክ የፈካ ቢሆንም፣ ኃላፊነታቸውን ያላወቁ (ኢትዮጵያን እንወዳለን እያሉ የዞረባቸውም) ነበሩ፡፡

በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ዴሞክራሲን የመኖራችን ጉዳይ ገና በመቀማመስ ደረጃ መሆኑን የሳትን፣ ለዴሞክራሲ ያለ መዘጋጀት ቀርነት ያለብን፣ ዴሞክራሲን መኖር እንዴት እንደሆነ ያልገባን፣ ጋሪውና ፈረሱ በአግባቡ ባልተገናኙበት ሁኔታ ውስጥ በሠረገላ መንፈላሰስ የሚያምረንና በምዕራባያውያን ቤት ያየነው አይቅረን የምንል ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥ እንገኛለን፡፡

 • የመንግሥት ለሕግ የመታዘዝ ልምምድ ገና ጥሬ ነው፡፡ ሕግ አክብሮ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ድርጅታዊና ባህላዊ አቅማችን ገና አልጎለበተም፡፡ የመንግሥት አውታራት የአለቃና ምንዝርም ሆነ ከሕዝብ ጋር ያላቸው መስተጋብር ገና በአስደግዳጊነትና በ‹እከክልኝ ልከክልህ› ዘይቤ ውስጥ የሚዳክር ነው፡፡
 • ለዴሞክራሲያዊነት ምሳሌ የሆኑና ለፉክክር የበቁ ትልልቅ ውስን ፓርቲዎች ገና ኢትዮጵያ አላሟላችም፡፡ የብዙኃን ነፃ ማኅበራትና ነፃ አስተሳሰብ የዴሞክራሲ ካስማነት፣ እንዲሁም የጋዜጠኝነትና የሚዲያ አራተኛ መንግሥትነት ገና ከወሬ ያላለፈ ነው፡፡ ለአገራዊ ጥቅም፣ ለእውነትና ለሕዝብ የመታመን ኃላፊነቱን ጋዜጠኝነት ገና በወጉ አልተቆናጠጠም፡፡ በፓርቲ በሲቪል ማኅበራት በሚዲያ እንቅስቃሴ፣ በፌዴራላዊና አካባቢያዊ የመንግሥትና የፖለቲካ መሪነት ልቀው ያበሩ ከዋክብትን ገና አገሪቱ በአግባቡ አላፈራችም፡፡ አንድ ብለን ምናልባት እስከ ሦስትና አራት መቁጠር ብንችል፣ ከዚያ በኋላ ከመገላመጥ በቀር እከሌ ለማለትና ለመስማማት ሳንቸገር አንቀርም፡፡
 • የሰፊው ኅብረተሰባችን ግንዛቤ ለዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ለሳይንሳዊ ግንዛቤ ግንባታ እንዲሆን ሆኖ ገና አልተነቃነቀም፡፡ ግንዛቤውና የኑሮ ዘልማዱ በደደረ ትውፊታ ትውፊትና የተተበተበ፣ የአካልና የአዕምሮ ኃይጅናዊ የኑሮ ክህሎት የሚጎድለው ነው፡፡ ፈጣሪ ያውቃል/ይጠብቀኛል ፈጣሪ ያለው አይቀር በማለት፣ ለሳይንሳዊና ለሕክምና ምክር ገና ጆሮው ያልነቃ ብዙ ነው፡፡ በወጣቶቻችን ውስጥ ፊደላዊ ተማርኩ ባይነትና መኃይምነት ተጋብተው ሲኖሩ ማየት እንደ ልብ ነው፡፡ በመንግሥት የመረጃ ንፉግነትና የተጣራ እውነተኛና ሚዛናዊ መረጃ በመስጠት ረገድ የሕዝብ አመኔታን የተቀዳጀ ኮኮብ ሚዲያ ባለመኖሩ፣ መንግሥትም በመረጃ ንፉግነት ስመ ጥር በመሆኑ፣ ዛሬም ብዙ ሰው የአፍ ለአፍና የማኅበራዊ ሚዲያ ሹክሹክታ መጫወቻ ነው፡፡ መንግሥት የሚያናፍሰው መረጃ ፕሮፓጋንዳዊ ጥቅም የሚሰጠውን እንደ መሆኑ፣ መንግሥት የሚናገረውን ሁሉ ‹‹ፕሮፓጋንዳ ነው›› የሚልና መንግሥትን ለይምሰል አንድ ነገር ብሎ ከጀርባ ሌላ የሚሠራ አድርጎ የሚረዳ ሰው ጥቂት አይደለም፡፡ መንግሥትነትን በሕግ የተወሰነ የሥልጣን ገደብ ያለበት ተቋማዊ እንቅስቃሴ እንደሆነ አድርጎ የሚረዳ ምን ያህል ነው የሚለው ጥያቄ ዛሬም ቀላል መልስ የለውም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትርን ብሔረሰባዊና አካባቢያዊ አመጣጥ ይዞ ለአካባቢው የሚያዳላ አድርጎ የሚያሰብ እንዳለ ሁሉ፣ የአካባቢንም የፌዴራልንም መንግሥታዊ አውታራትን የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርካቦች አድርጎ የሚያይ ወይም የፌዴራል መንግሥት ቁንጮን ሁሉን አድራጊና ማስደረግ የሚችል አድርጎ የሚያስብ ብዙ ነው፡፡ ግለሰቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬም የሁሉ አዛዥ ተደርጎ ነው የሚታይ፡፡ ለአካባቢ አስተዳደር መቅረብ ያለባቸው ጥያቄዎች/አቤቱታዎች በሕዝብ በተወካዮች አባላት ጭምር ፓርላማ ውስጥ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲቀርቡ መስማት እንግዳም፣ አስገራሚም አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁሉ ነገር ቁልፍ በእጁ ያለ የሚል ግንዛቤን የሚሽር የሥልጣኖች አተገባበር ፈክቶ እስካልወጣ ድረስም ይህ ለምን ሆነ ብሎ መፍረድም ያስቸግራል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር የሁሉ መንግሥታዊ አካላት መሪዎች አለቃ ዓይነት ነገር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለካቢኔ አባላቱ ለፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ ሥልጠና ሲሰጥ ዓይተናል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲገመግምና ሲያፋጥጥ ዓይተን አናውቅም፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ክቡርነታቸው በሆነ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ግንዛቤ (ብርሃን የሚሆን) እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ሆነው ሲሠሩ ነው የምናውቀው፣ ከሞላ ጎደል፡፡
 • የ2013/14 ምርጫ ‹‹ታሪካዊ ነው! ሕዝብ በመረጠው መተዳደር ጀመረ›› ሲባል፣ ከቀድሞው የኢሕአዴግ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ሥውር ቁጥጥርና ሸፍጥ በአያሌው በቀነሰበት ሁኔታ ሕዝብ ካርዱን ምርጫ ሳጥን ውስጥ ከተተ፡፡ የከተተውም ተቆጠረለት ከማለት የዘለለ እውነት የለውም፡፡ ታሪካዊው ምርጫ ፓርቲዎችን ባሏቸው ሐሳቦችና ዕቅዶች አወዳድሮ ይበጀኛል ያለውን ዕቅድ የመረጠበት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ሕዝቦች የተሳሰረ ህልውና ለማስቀጠል የተሻለ የቅንብር አቅም ያለው የትኛው ነው ብሎ የመረጠበት ነበር፡፡ የፌዴራላዊነታችን አስተሳሰብና አሸናሸን ብሔርተኛ እንደ መሆኑም፣ የፓርቲ ቅርንጫፎች ጎጥና ብሔረሰብ ገብ ነበሩና የፓርቲ መረጣው ዞሮ ዞሮ ብሔረሰባዊ/አካባቢያዊ የዝምድና አዚም ያለበትም መሆኑ አይቀሬ ነበር፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ በሦስት ዓመታት ውስጥ የሚሻሻልበት ነገር ካልመጣ በቀር፣ መጪው የ2017 ዓ.ም. ምርጫም በእነዚህ ሁለቱ ሰበዞች ከመወሰን የሚያመልጥ አይመስልም፡፡ ዕቅዶች ተወዳድረው የተሻለን ዕቅድ ከመምረጥ ፋንታ ብልፅግና ፓርቲን ኢትዮጵያን በዝንጉርጉር ጥንቅር በማንፀባረቅ አቅም የሚፎካከረው አጥተን እሱኑ በመምረጥ የመገደብ ዕድል አለ፡፡ ይህ እስከ ጎደለ ድረስም የአንድና የሁለት ማኅበረሰቦች የቁጥር ግዝፈት ባለባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚካሄደው የምርጫ ውድድር ማኅበረሰባዊ ዝምድና ላይ ከመንጠላጠል አያመልጥም፡፡ ይህ እስከ ቀጠለ ድረስ አንጓላይ አስተሳሰብን ማዳከም ያስቸግራል፡፡ ዴሞክራሲያዊ የእኩልነት ስሜትን ሁሉም ሰው የሚጋራው ማድረግ ከባድ ይሆናል፡፡
 • ክፍልፋይ ብሔርተኝነት የማኅበረሰቦችን ዝምድና በዋናነት በቋንቋ መመዘኛ የመዘነ ግልብ (የተሳሳተ) ግንዛቤ ፈጥሯል፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ ብሔረሰረቦች በተቀላቀለ ወሰንተኝነትና በከተማ ዕድገት የፈጠሩትን የተዛነቀ ዝምድና አርዷል፣ በጥብጧል፡፡ ተመልሶ እንዳይጠገንም እያወከ ይገኛል፡፡ ይህንን ገመና አቅፎ ከከተሜነት (ከመሰባጠር/መዛነቅ) ጋርና ከኢንዱስትሪያዊ መስፋፋት ጋር የሚጣጣመውንና አብሮ የሚጎለምሰውን ዴሞክራሲ መገንባትም አስቸጋሪ ነው፡፡

ለ) እስካሁን ያልነውን ጠቅለል ብናደርገው፣ የዴሞክራሲ ጅምራችን የሰላም መናወጥ ገጥሞት የቆየ ብቻ ሳይሆን የኢዴሞክራሲና የፀረ ዴሞክራሲ ጭርንቁሶችም ያሉበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ አነጋገር በቤታችን ውስጥ ብዙ የሚጣሉ ነገሮች ገንቢነትም አፍራሽነትም፣ ወደፊት መሄድም ወደ ኋላ መሄድም፣ ሰላም በጥባጭነትም ሰላምን የመገንባት ጥረትም፣ ሕጋዊነትና ሕገወጥነትም፣ አምባገነናዊና ዘፈቀዳዊ ሥራዎችም፣ በሙሰኝነት/በአድሏዊነት መጠቃቀምና በሥራ/በችሎታ ማደግም በተበላለጠ ጥልቀትና ስፋት ይላፋሉ ማለታችን ነው፡፡

እነዚህን ነጥቦች የደረደርነው አራት ያህል ቁምነገሮችን ለማስጨበጥ ነው፡፡

 • ኢትዮጵያ በነበረችበትና ባለችበት ሁኔታ ሰላምና መረጋጋቷን የማይጠቅም ‹‹መረጃ›› እና አስተያየት እየለቀቁ ሕግ ያከበረም ሆነ ያላከበረ ቁንጥጫ ሲመጣ፣ ‹‹አምባገነንነት መጥቷል! መንግሥት መብት ማክበረም ማስከበርም አልቻለም! ሥልጣን መልቀቅ አለበት!!…›› የሚል ጩኸት የሚያደምቁ ሰዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት በአገር ወዳድ የኃላፊነት ስሜት የማይመሩ (በየትም በምንም መንግሥትን በማሳጣት ተግባር የተጠመዱ) ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ዴሞክራሲ እየገነባሁ ነው›› ማለቱ ወንጀል የሆነ ይመስል፣ ካልክማ በሚል ማፋጠጥ ዴሞክራሲ ከጎለበተባቸው አገረ መንግሥታት የሚጠበቁ ተግባሮችን ሁሉ አሳየና ይላሉ፡፡ እነዚህ ፍላጎታቸው የዴሞክራሲን ልምላሜ ማገዝ ሳይሆን፣ መንግሥትን የዴሞክራሲ ፀር አድርጎ ማጠልሸት ነው፡፡
 • የተወሰኑት ደግሞ በምዕራብ ዴሞክራሲ ውስጥ ‹‹የመረጃ መብት››፣ ‹‹ሐሳብን የመግለጥ መብት››፣ ወዘተ የሚባሉትን ነገሮች በቁማቸው ወስደውና በምዕራብ ሚዲያ ላይ ሲሰተሩ የሚያዩዋቸውን የመረጃና የሐሳብ ግትልትሎች እኛም ቤት አይቅሩ የሚሉ፣ አገራዊ ጥቅምን የሚመለከቱ ጉዳዮች እንደ አርቲ ቡርቲ ዜናዎች በምዕራብያውኑም ዘንድ ዝም ብለው እንደማይለቀቁ (የሚሸመቀቁ፣ ሳስተውና ተቆነጣጥረው ብቻ ይፋ የሚወጡ ነገሮች እንዳሉ) የማያውቁ የዋሆች ናቸው፡፡ ያላጤኑ የዋሆች ናቸው፡፡ እነዚህ የዋሆች ከኢትዮጵያ ደኅንነትና እውነታ አኳያ መረጃዎችን የመገምገምና የማሸት ኃላፊነት እንዳለባቸው ባለማወቅና በምዕራባያውያን ሚዲያና አደባባዮች ያዩትን የማድረግ ወጉ አይቅረን ሲሉ አገራቸውንም ራሳቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ፡፡
 • ሌሎቹ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ገና ጥሬ መሆኑን የሚያውቁ፣ ግን የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ በምዕራባዊ ዘይቤ ሊቀርፁ የሚፈልጉና ለዚህም ውጤት ከ‹ጋዜጠኝነት› አኳያ የሥራ ኃላፊነቱን ለራሳቸው የሰጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ‹‹ዕለታዊ›› በሚል መድረክ መረጃ በአግባቡ ያገኙለትንም ያላገኙለትንም መረጃ ዕለት በዕለት እያመሰኩ በአንድ ጊዜ ሁለት ነገሮችን ሊያሳኩ ይሞክራሉ፡፡ በአንድ በኩል ‹‹እንደምጠረጥረው/እንደመሰለኝ… እኛ ባገኘነው መረጃ መሠረት…›› እያሉ ወሬና ትንታኔ እየቸረቸሩ መተዳደሪያቸውን ያሟላሉ፡፡ በሌላ ጎን ራሳቸውን አተልቀው ከአገር ወዳድነት በዘለለ ባላቸው የፖለቲካ አቋም የሕዝብን አመለካከትና የመንግሥትን አካሄድ ለመቃኘት ይደፍራሉ፡፡ በዚህም ተግባራቸው በአንድ ጊዜ አዎንታዊና አሉታዊ በሆነ የአገም ጠቀም ሥራ ያንገላታሉ፡፡
 • የታጠቁ ተኳሾች በኃይልም በድርድርና በሰላም ጥሪም ወደ ሰላማዊ ኑሮ እየመጡ ያሉበት የአሁኑ ምዕራፍ ለኢትዮጵያ ሌላ ውድ ጊዜ ነው፡፡ ኢኮኖሚን የማንሰራራት፣ መልሶ ግንባታንና የተናጋ ኑሮን መልሶ የማቋቋም ሥራዎች ላይ የመረባረብና ሰላምን እንዲዘልቅ አድርጎ የመገንባት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ አገራዊ ጥቅም አኳያ ኃላፊነትን ለመወጣት አድርጎ የመገንባት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ አገራዊ ጥቅም አኳያ ኃላፊነትን ለመወጣት ከእስካሁኑ ልምድ ሁለት ነገሮችን ጋዜጠኞችና አንቂ ነን ባዮች መማር አለባቸው፡፡ በቅድሚያ እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ የጅምር ዴሞክራሲ ኑሮ ይቅርና ዴሞክራሲ መኖሪያችን ከሆነ መቶ፣ ሁለት መቶ ዓመት ሞላን በሚሉት አገሮችም ያለው የሕግ ጥበቃ ጥንቃቄን የሚያስረሳ አይደለም፡፡ ሕግ በጣሱ የሕግ ሰዎችና በሕገወጦች ስንቶች ትናንትናም ሆነ ዛሬ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስተውሎ የመብት አጠቃቀምን ከጥንቃቄ ጋር ማዛመድ ይገባል፡፡ ሁለተኛ ፀረ ዴሞክራሲያዊነትን፣ ኢዴሞክራሲያዊነትን፣ ሕገወጥነትን፣ ማናለብኝነትንና የልሽቀት ባህልን በብልኃት እየታገሉ አገራችንን በዴሞክራሲና በልማት ግስጋሴ በማራመድ ተግባር ውስጥ ሚናን በዝርዝር ነድፎ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ምን ያህል ብዙ ሥራ እንዳለ ለመጠቆም የሰውን ባህል ከማሳደግ አኳያ አንዲት ቅንጣቢ ነገር እንደ ምሳሌ ላንሳ፡፡ የከተማ ጎረምሶቻችን በጋራ ገበታ ላይ ያላቸው አበላል፣ በፊልሞቻችን ውስጥ በየምግብ ቤት አካባቢ ከእጅ አስተጣጠብ እስከ ጉርሻ አጠቀላለልና አስተኛኘክ ከጎዳና ልጆች ዘይቤ ያልራቀ ጉድ አለበት፡፡ ይህን ጉድ የኢትዮጵያን አብሮ መብላት ባህልን ምን ያህል ያንፀባርቃል? የሚያኮራ ወይስ ገጽታን የሚያጎድፍ? አብሮ መብላት ወይስ ፋንታ የመሻማት ግብግብ? በወጉ ማኘክ የሌለበት የሽሚያ መብል ምን ያህል የጤና ጉዳት ያመጣል?…

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...