አማራ ብቻውን በመወራጨት የሚፈታቸው ችግሮች የሉም ይላሉ፡፡ የአማራ ፖለቲካ መደማመጥና አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ መገንባትአቅቶታል ሲሉ መሠረታዊ ያሉትን ችግርም ያነሳሉ፡፡ አማራ ጠንካራ አመራር ከፈጠረ ግን የመደማመጡን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ አማራ አሉኝ የሚላቸውን በርካታ ጥያቄዎች ለማስመለስ ቀላል እንደሚሆን ይገምታሉ፡፡ የዛሬው ቆይታ ዓምድ እንግዳ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በሦስተኛ (ፒኤችዲ) ዲግሪ ለመመረቅ ትምህርታቸውን በማገባደድ ላይ ያሉት የቀድሞ የብአዴን አመራር አባል አቶ ቹቹ አለባቸው ናቸው፡፡ በ2001 ዓ.ም. ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ተመርቀዋል፡፡ በሕግ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ2006 ዓ.ም. ተቀብለዋል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. እስከ 1988 ዓ.ም. የኢሕዴን ታጋይ የነበሩት አቶ ቹቹ፣ የጠገዴና የአርማጭሆ ወረዳ አስተዳዳሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በጎንደር ከተማ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የከንቲባው አማካሪ ነበሩ፡፡ በክልል ደረጃ ደግሞ የአማራ ክልል ከተማ ልማት፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄና የአማራ ሕዝብን የተመለከቱ በርካታ የፖለቲካ ጉዳዮችን ያብራሩበት አቶ ቹቹ ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሪፖርተር፡- የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ምንድናቸው?
አቶ ቹቹ፡- የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ምንድናቸው የሚለውን ጉዳይ ለመመለስ መነሻ ማድረግ ያለብን መዋቅራዊ የሆኑ ነጥቦችን ነው፡፡ በግለሰቦች ደረጃ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እነዚህ/እነዚያ ናቸው እየተባለ የሚነሳውን ወይም ስምንት ናቸው፣ አሥር ናቸው፣ ሦስት ናቸው በሚል የሚሰጡ አስተያየቶችን አይደለም ማየት ያለብን፡፡ ይህ እንዲያውም የማኅበረሰቡን መሠረታዊ ጥያቄ መልኩን እያሳጣው ይመስለኛል፡፡ እኔ በግሌ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ብዬ የምወስዳቸው በ12ኛው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ድርጅታዊ ጉባዔ የፀደቁ አጀንዳዎችን ነው፡፡ በድርጅት ደረጃ የፀደቁና የአማራ ሕዝብ መታገያ ተብለው ሕዝቡም በግልጽ የሚያውቃቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች የአማራ ሕዝብ አታጋይ ድርጅት በሆነ ፓርቲ የፀደቁ ተቋማዊ መሠረት ያላቸው ናቸው፡፡ የአማራ ሕዝብን ጥያቄዎች ለመዘርዘር በእነዚህ ተቋማዊ በሆኑ ጥያቄዎች ላይ መመሥረት ተገቢ ነው፡፡
በዚህ ድርጅታዊ ጉባዔ እኔም አንዱ ተሳታፊ ነበርኩ፡፡ በደንብ እንደማስታውሰውም ስድስት ጥያቄዎች ነበሩ በወቅቱ የተነሱት፡፡ ፓርቲው የሚታገልባቸውና ሕዝቡን የሚያታግልባቸው ተብለው ስድስት ጥያቄዎች ፀድቀዋል፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ የሕገ መንግሥት መሻሻል ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ የመጀመሪያው ተብሎ የተቀመጠበት ምክንያትም፣ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ሲፀድቅ የአማራ ሕዝብ የተሳተፈበት አይደለም እንዲሁም መሠረታዊ መብቶቹን እየጎዳ ይገኛል በሚል ነው፡፡ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት እኔን አይወክልም በሚል መንፈስ ወይም ከአማራ ጥቅም ብቻ ሳይሆን፣ ለአገር አንድነትም አይበጅም በሚል ነው ድርጅቱ ያፀደቀው፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነትና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የማይበጅ በመሆኑ ለአማራ ሕዝብ ጥቅም ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ለአገር ሲባል ሊሻሻል ይገባል የሚል ጥያቄ ነው ያነሳው፡፡ ይህንንም ለማድረግ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ እንታገላለን የሚል ነበር የመጀመሪያው ነጥብ፡፡
ሁለተኛው ጥያቄ የእኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ጉዳይ ነው፡፡ ሁላችንም እንደምንገነዘበው ባለፉት 30 ዓመታት የአማራ ሕዝብ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውም ሆነ በማኅበራዊ ዘርፉ ተገፍቻለሁ ወይም እኩል ተጠቃሚነት ተነፍጌያለሁ በሚል ቅሬታ ሲያሰማ ነው የኖረው፡፡ በ2008 ዓ.ም. የደረስንበት የመሠረታዊ ለውጥ ጥያቄ አንዱ ምንጭ ይህ ነበር፡፡ በፖለቲካው ረገድ፣ በአስተዳደሩ፣ በወታደራዊው፣ በሲቪሉም ሆነ በደኅንነቱ አማራ ተገፍቻለሁ ብሎ ያምናል፡፡ ይህ ደግሞ መሻሻል እንዳለበት ሲጠይቅ ኖሯል፡፡ ከመሠረተ ልማት አገልግሎት አንፃርም ተጎድቻለሁ ሲል ነበር፡፡ በመብራት፣ በቴሌኮም፣ በውኃ፣ በመንገድ፣ በጤና፣ በትምህርትና በመሳሰሉት አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች የተገፋ ማኅበረሰብ ነው፡፡ ይህንንም ለማስተካከል እንታገላለን በሚል ነው በሁለተኝነት የማኅበረሰብ ጥያቄ ተደርጎ የተወሰደው፡፡
በሦስተኛ ደረጃ በጉባዔው የተቀመጠው ደግሞ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩለት መታገል ተብሎ ነው፡፡ ይህ እንደሚታወቀው አገራዊ ችግር ነው፡፡ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ጉዳይ የአማራ ሕዝብ ብቻም ሳይሆን የሁሉም ነው፡፡ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶች በአገር ደረጃ አስከፊ ሁኔታ ላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ እንደ አገርም የኢትዮጵያን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ ከዚያም በላይ ደግሞ አማራ ብሔርን መሠረት አድርጎ ብዙ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ጥሰት ሲፈጸምበት የቆየ ሲሆን፣ በአማራ ክልል ደግሞ አስቸጋሪና አሰቃቂ የሆኑ የመብት ጥሰቶች ተስፋፍተው ነበር፡፡ ፓርቲው ይህን የማረምና የማስተካከል ብቻ ሳይሆን ዳግም እንዳይከሰት የማድረግ ግብ ይዞ ጉዳዩን የአማራ ሕዝብ የመታገያ አጀንዳ አድርጎት ነበር፡፡
በአራተኛነት የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ተብሎ የተነሳው ነጥብ ደግሞ ከክልሉ ውጪ የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ደኅንነት፣ መብትና ጥቅም እንዲከበር የማድረግ ጉዳይ ነበር፡፡ እጅግ ብዙ የአማራ ሕዝብ የአማራ ከሚባለው ውጪ ተሰራጭቶ የሚኖር ነው፡፡ ከአማራ ክልል ውጪ በሚኖርበት ወቅት ደግሞ ደኅንነቱ አይጠበቅለትም፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ይነፈጋል፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅሞቹም አይከበሩም በሚል ነው ይህ ጉዳይ የሕዝብ ጥያቄ ተደርጎ የተቀመጠው፡፡ የአማራ ሕዝብ ከክልሉ ውጪ መሰቃየቱና መንገላታቱ ዛሬም ድረስ እንደቀጠለ ነው፡፡ አራተኛው የሕዝብ ጥያቄም ከክልሉ ውጪ የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ደኅንነት፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ጉዳይ ተብሎ ነው የተቀመጠው፡፡
አምስተኛው የትግል አጀንዳ ተብሎ የተቀመጠው ደግሞ የወሰንና የማንነት ጥያቄ ነው፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ የወልቃይት፣ የራያ፣ የመተከልና ደራ የሚባሉ አካባቢዎች የወሰን ጥያቄዎች አልተመለሱም፡፡ ከፊሎቹ በጉልበት ከፊሎቹም ያላግባብ ከአማራ ተነጥቀዋል የሚል ቅሬታ አለ፡፡ አንዳንዶቹ በውይይት ቢባልም ነገር ግን የአማራን ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት የማይወክሉ አመራሮች በነበሩበት ጊዜ ያለ ሕዝብ ፈቃድ የተካለሉ በመሆናቸው፣ እነዚህን በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ታግለን እናስተካክላለን የሚል የትግል አጀንዳ ነው፡፡
ስድስተኛው የአማራ ሕዝብ የትግል አጀንዳ ደግሞ የተዛቡ ትርክቶችን ማረምና ማስተካከል የሚል ነው፡፡ አማራን ጨቋኝ፣ በዝባዥ፣ ለዚህች አገር ችግር የመጀመሪያ ተጠያቂ አድርጎ የመሳል ነገር በተለያየ መንገድ እስከዛሬም ቀጥሏል፡፡ በአማራ ላይ የተዘሩ የተዛቡ ትርክቶች እንዲታረሙና እንዲስተካከሉ ማድረግ የትግል ጉዳይ ተደርጎ ነው የተወሰደው፡፡ እነዚህ ስድስቱ በድርጅት የፀደቁ የአማራ ሕዝብ የትግል አጀንዳዎች ተብለው የተቀመጡ ነጥቦች ናቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ነጥሮ የወጣና እንደ ሰባተኛ ሆኖ የወጣ እኔም የማምንበት ጉዳይ አለ፡፡ የአማራ ሕዝብ የህልውና አደጋ ገጥሞታል የሚል አጀንዳ አሁን የሕዝብ ጥያቄ ሆኖ መጥቷል፡፡ አማራ በየትኛውም ቦታ ይሳደዳል፣ ይፈናቀላል፣ ይታሰራል ብሎም ይገደላል፡፡ ይህ ደግሞ የህልውና ሥጋት እየገጠመን ይገኛል የሚል ጥያቄን ፈጥሯል፡፡
ይህ አጀንዳ በዚያ ድርጅታዊ ጉባዔ የፀደቀ ባይሆንም የብዙዎች ጥያቄና ብዙዎችን የገዛ ጉዳይ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በተጨባጭና በተግባር የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ሆኖ መወሰድ ያለበት የመታገያ ነጥብ ነው፡፡ እኔም የማምንበት አጀንዳ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ስድስቱ ጥያቄዎች በድርጅት ጉባዔ የፀደቁና አንዱ በተጨባጭ በተግባር እየታየ ያለ ነጥብን ጨምሮ፣ በአጠቃላይ ሰባት የትግል አጀንዳዎች ተብለው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- እንዴት ነው እነዚህ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ማድረግ የሚቻለው? አሁን ባለው የተበታተነ የትግል ሁኔታ እነዚህን አጀንዳዎች ወደፊት አምጥቶ ምላሽ ማግኘት ይቻላል?
አቶ ቹቹ፡- አሁን ባለው የትግል ሁኔታ እነዚህ ስድስት/ሰባት መሠረታዊ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የመመለስ ዕድላቸው በጣም የጠበበ ነው፡፡ አሁን ባለው አያያዛችን ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት በጣም የሚዘገይ ይመስለኛል፡፡ ሁለት ምክንያቶችን ለዚህ ሥጋት ማስቀመጥ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በአማራ ክልል በአሁኑ ጊዜ መደማመጥ የለም፡፡ ልሂቃን በሚባሉ ፖለቲከኞች፣ በወጣቱ፣ በአክቲቪስቱ፣ በአጠቃላይ እንደ ማኅበረሰብ የመደማመጥ ችግር ገጥሞናል፡፡ መደማመጥና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መመሥረት ካልቻልን እንዲህ ዓይነት መሠረታዊ ጥያቄዎች አይመለሱም፡፡ በአማራ ውስጥ የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር አልተቻለም፡፡ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ስትፈጥር ትደማመጣለህ፣ በአጀንዳዎች ላይ ትግባባለህ፣ በትግል ሥልቱ ላይም ትግባባለህ፡፡
አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ገንብቶ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ መፍጠር ባልተቻለበት ሁኔታ፣ የእነዚህ ጥያቄዎች ጉዳይ አንድም ጭራሹኑ ተዳፍኖ መቅረት ሊሆን ይችላል፡፡ ተዳፍኖ ከመቅረት በተጨማሪ ምላሽ ለማግኘት አርባና ሃምሳ ዓመታት ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ የፖለቲካ ማኅበረሰብ አለመፍጠራችን አለመደማመጥ በመፍጠሩ በመሪና በተመሪ መካከል፣ በምሁሩና በአክቲቪስቱ መካከል ምንም ዓይነት መደማመጥ እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ይህ አለመደማመጥ ጥያቄዎቹ እንዳይመለሱ ትልቅ እንቅፋት ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሁለተኛውና መሠረታዊ ብዬ የማስቀምጠው ደግሞ የአማራ ክልል የገጠመው የአመራር ክፍተት ችግር ነው፡፡ ምክንያቱም የአመራር ክፍተት ችግር ባይኖር የመጀመሪያውን አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመገንባትና የመደማመጥ ችግር ለመፍታት በቀለለ ነበር፡፡ አደገኛውና ትልቁ ችግር የአመራር ክፍተት ችግር ነው፡፡ ከሰኔ 15 ግድያ በኋላ የአማራ ክልል በጣም ጠንካራ አመራሮችን አጥቷል፡፡ የአማራ ክልል እስከ ትናንት ድረስ በጣም ትልልቅ አመራሮችን እየበላ ነው የመጣው፡፡ መሪውን እየበላ የሚሄድ ክልል በመፍጠራችን የአማራ ሕዝብ በከፍተኛ ሁኔታ የኮር አመራሮች ችግር አጋጥሞታል፡፡
ይህ ደግሞ ብዙ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ ከእነዚህ አንዱ የአማራ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተደማጭ እንዳይሆን አድርጓል፡፡ የአማራ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዳይሆንም አድርጎታል፡፡ እነዚህ የተዛመዱ ሁለት ምክንያቶች ማለትም አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ አለመፍጠርና የአመራር ክፍተት ችግር ከላይ ያነሳናቸው የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንዳይመለሱ ፈተና ይፈጥራሉ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ካልተስተካከሉ የአማራ ሕዝብን ጥያቄዎች የማስመለስ ጉዳይ እጅግ ከባድ ይሆናል፡፡ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ በግሌ ጥያቄዎቹ መመለሳቸውን እጠራጠራለሁ፣ ካልሆነም የሚመለሱበት ጊዜ እጅግ የዘገየ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- የአማራ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ወደ አንድነት ኃይሎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያጋደለ ነው ይባላል፡፡ የአማራ ማኅበረሰብ የራሱ የፖለቲካ ጥያቄዎች ካሉት ወደ አንድነት ፖለቲካ ማጋደሉ አስፈላጊ ነው? አማራን የአንድነት ፖለቲካ ጠበቃ ያደረገው ማን ነው?
አቶ ቹቹ፡- የአማራ ፖለቲካ ከብሔር ይልቅ ለአንድነት ፖለቲካ ቅርብ ነው፡፡ አሁን በአማራ ስም የሚደራጁ የፖለቲካ ኃይሎች እየመጡ ቢሆንም፣ ነገር ግን በጽሑፍም ሆነ በሌላ የሚታገሉበትን መንገድ ብናይ ዞሮ ዞሮ የአንድነት ፖለቲካ ላይ የሚወድቅ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ታሪክና ሥሪት ነው የዚህ ገፊ ምክንያት የሚሆነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ታሪክና ሥሪት የኢትዮጵያን አንድነት ከመፍጠር ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት መሠረት በመጣል የአማራ ኃይሎች ግንባር ቀደም ሆነዋል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ የጀመሩትን ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ጥረት አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ቅርፅ በመፍጠር አፄ ምኒልክ አጠናክረውታል፡፡ ይህ ደግሞ አባቶቻችን የመሠረቱት አገር የሚል ሥነ ልቦና በአማራ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ያደረገ የታሪክ አጋጣሚ ነው፡፡ አማራ አባቶቹ የመሠረቱት አገር እንደ ዋዛና እንደ ቀልድ ስትፈርስም ሆነ ስትበተን ፈጽሞ የማየት ፍላጎት የለውም፡፡ የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ታሪካዊ ግዳጅና ኃላፊነት አለብኝ ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ በዚህ የተነሳ የአማራ ሕዝብ አንድነትን ለሚያጠናክር እንጂ፣ አንድነትን ያላላል ለሚባለው ፖለቲካ ድጋፍ አይሰጥም፡፡
ሁለተኛው የአማራ ሕዝብን ለአንድነት ፖለቲካ እንዲያጋድል የሚያደርገው ደግሞ ሕዝቡ የሚኖርበት ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ነው፡፡ ዛሬ አማራ ተብሎ የሚጠራው ሕዝብ በኢትዮጵያ እስከ 50 ሚሊዮን የሚገመት ነው፡፡ በክልሉ ከሚኖረው ሕዝብ በተጨማሪ እጅግ በርካታ ቁጥር ያለው የአማራ ማኅበረሰብ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተሰራጭቶ ይኖራል፡፡ ግማሽ አካሉን ትቶ በብሔር ፖለቲካ ለመታጠር ተጨባጩ የአማራ ነባራዊ የአኗኗር ሁኔታ አይፈቅድለትም፡፡ ስለሆነም እነዚህ ሁለት ምክንያቶች ከብሔር ፖለቲካ ይልቅ ወደ አንድነት ፖለቲካ እንዲሄድ አማራን ያስገድዱታል፡፡ የአንድነት ፖለቲካ ኃይሎች ከአማራ ፖለቲካ ኃይሎች ጋር በተለያዩ መንገዶች እንዲቀራረቡ ሁኔታዎች ያስገድዳሉ፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት ማፅናት የሁለቱም ፖለቲካ ኃይሎች ተመሳሳይ ግብ በመሆኑ በዚህ ይገናኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ የአማራ ፖለቲካ የአንድነት ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በአማራ ሕዝብ ላይ እንደ ማኅበረሰብ እየደረሱ ያሉ በደሎችና ችግሮችን መፍታት ላይም ያተኮረ ነው፡፡
የአማራ ሕዝብ ከሌሎች በተለይም ከኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች ጋር ተመሳሳይ አጀንዳ ቢኖረውም፣ በተናጠል ደግሞ ከላይ ያነሳናቸውን ዓይነት የማኅበረሰብ ጥያቄም አለው፡፡ ስለዚህ የአማራ ሕዝብ ትግል መንታ መንገዶችን ይዞ የሚሄድ ነው፡፡ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ እንድትኖር፣ እንድትፀና፣ እንዳትፈርስና ችግር እንዳይገጥማት ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ከላይ ያልኳቸው ሁለት ምክንያቶች ያስገድዱታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በራሱ በአማራነቱ ላይ ተነጣጥረው የመጡ ችግሮች ስለገጠሙት እነሱንም ለመታገል ይገደዳል፡፡ የአማራ ፖለቲካ ሁለት ዓይነት ወይም መንታ ገጽታ ያለው ነው፡፡ በአንድ ወገን ኢትዮጵያዊነትን ማፅናት ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ አማራነትንም የማፅናት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ ወገን ከአንድነት ኃይሎች ጋር በጋራ ለመቆም የሚችልበት መሠረት አለው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን በማፅናት ጉዳይ ሁለቱ ኃይሎች በጋራ ሊታገሉ ይችላሉ፡፡ የአማራ ፖለቲካ ኃይል ከአንድነት ኃይሎች ጋር ብቻ ሳይሆን፣ በሌላ ወገን ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችም ጋር በጋራ የሚያቆሙ በርካታ አጀንዳዎች እንዳሉትም መረሳት የለበትም፡፡
የአንድነት ፖለቲካ ኃይሎች ከአማራ የፖለቲካ ኃይሎች ጎን ለመቆምና በጋራ ለመታገል ወለም ዘለም ሲሉ ይታያሉ፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ የአማራ ፖለቲካ የብሔር/የማኅበረሰብ ጥያቄንም የያዘ ስለሚሆንባቸው ነው፡፡ በአማራነት የሚደርስበት ጥቃት በመኖሩ፣ የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች እነዚህ አማራነትን ማዕከል ያደረጉ ጥያቄዎችን ለማንሳት ይገደዳሉ፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት የመፅናት ጉዳይ ሁለቱ ኃይሎች ቢቀራረቡም፣ ነገር ግን የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች የሚያነሱት ብሔር/ማንነት ተኮር ጥያቄ እያስፈራቸው የአንድነት ፖለቲካ ኃይሎች ከአማራ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በጋራ ለመሥራት ሲቸገሩ ይታያል፡፡ የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ሲፈጠር ሁለቱ የፖለቲካ ኃይሎች በተናጠል የሚያወጧቸው መግለጫዎችም ሆነ የሚይዟቸው አቋሞች ሲመሳሰሉ ይታያል፡፡ የአማራ ሕዝብን የተመለከቱ ጥያቄዎች ሲነሱ ግን ሁለቱ የፖለቲካ ኃይሎች በጋራ በተመሳሳይ ለመቆም ፈተና ሲገጥማቸው ነው የሚታየው፡፡
ያም ሆነ ይህ ግን አማራ ይህችን አገር ብቻውን አልፈጠራትም፡፡ ኢትዮጵያን አንድ በማድረጉ ሒደት የመሪነት ሚና ተጫውቷል ቢባልም ነገር ግን ትግሬውም፣ ኦሮሞውም፣ ሲዳማውም ሆነ ሶማሌው ኢትዮጵያን አንድ በማድረጉ ሒደት በግንባር ቀደምትነት ተሳትፈዋል፡፡ ኢትዮጵያን በመፍጠሩ ሒደት ሁሉም ሕዝቦች እኩል ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ ጉዳይ አማራ ብቻ ጠበቃ፣ አማራ ብቻ ተቆርቋሪ ተደርጎ የሚወሰድበት ሁኔታ የለም፡፡ በዚህ መንገድ የሚያስቡ ካሉም ስህተት ነው፡፡ አማራ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በጋራ ሆኖ ኢትዮጵያን እንደ መሠረታት ሁሉ፣ ዛሬም ከሌሎች ጋር በጋራ ቆሞ ነው ሊጠብቃት የሚችለው፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ አማራን ብቻ ጠበቃ አድርጎ የሚወስድ አማራ የለም፣ ካለም ስህተት ነው፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ግን አማራ የኢትዮጵያ ጉዳይ የእኔ ብቻ ነው ይላል እያሉ ሲፈርጁን አያለሁ፡፡ ይህ ግን ፍፁም ስህተት ነው፡፡ አማራ የኢትዮጵያ ጠበቃ እኔ ብቻ ነኝ አይልም፡፡ አብረን ነው የሠራናት፣ አብረን ነው የምንኖርባት፣ አብረን ነው የምንጠብቃትና የምናፀናት ነው የሚለው፡፡ የአማራ ፖለቲካ ኃይሎች ትክክለኛ አተያይ ይህ ነው ብዬ ነው የማምነውም፣ የማውቀውም፡፡ በጥቂት ግለሰቦች ወይ በጥቂት ቡድኖች ከዚህ የተለየ አመለካከት ከተንፀባረቀ አላውቅም፡፡ ነገር ግን እኔ በግሌ እስከማውቀው ድረስ አማራ ኢትዮጵያን የሁሉም የጋራ ቤት አድርጎ የሚመለከት ፖለቲካ ነው የሚያራምደው፡፡
ሪፖርተር፡- የአንድነት ፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ ሌሎች ኃይሎች የአማራን ፖለቲካ የሚረዱበት መንገድ ከዚህ የተለየ የሚሆንበት አጋጣሚ የለም?
አቶ ቹቹ፡- ሁለት ነገሮችን ማንሳት አለብን፡፡ የአማራ ፖለቲካ ለአንድነት ፖለቲካ የቀረበ እንደሆነ ሁሉም ይረዱታል፡፡ አማራ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተሰራጭቶ የሚኖርና ኢትዮጵያን በመገንባት ሒደት ታሪካዊ ድርሻ አለኝ በሚል ስሜት፣ ከብሔር ይልቅ ለአንድነት ፖለቲካ መጠጋቱን ሁሉም ይገነዘባል፡፡ ይህ ለአንድነት ኃይሎች ችግር ሆኖ አያውቅም፡፡ ነገር ግን የአማራ ክልል የሰከነ ፖለቲካ የለውም፡፡ የአማራ ሕዝብ የተረጋጋ መሪ የለውም፡፡ ይህ ሌሎችን በአማራ ፖለቲካ ላይ እንዳይተማመኑ ያደርጋል፡፡ ከግብ ለመድረስ የሚያስችል፣ አርዓያ የሚሆን ወይም የሚመራ ነው ብለው አይገምቱም፡፡ የአንድነት ፖለቲካ ኃይሎች የአማራ ፖለቲካ ለአንድነት ቅርብ እንደሆነ በማመኑ ላይ ጥርጣሬ የላቸውም፡፡ ነገር ግን የአማራ ፖለቲካ አለመስከኑ፣ የተረጋጋና ብቁ መሪ ማጣቱም ሆነ የራሱን መሪዎች እየበላ መምጣቱ በሙሉ ልብ ከአማራ ፖለቲካ ኃይል ጎን ተባብረው እንዳይቆሙ ያደርጋቸዋል፡፡ የአማራ ፖለቲካ የጠራ መስመር ይዞ ራሱን ችሎ ከቆመ፣ መተማመንና አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ከገነባ፣ እንዲሁም ጠንካራ አመራርና አደረጃጀት ከፈጠረ ከአማራ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ለመሠለፍ ብዙም ችግር የሚገጥማቸው አይመስለኝም፡፡ በክልሉ የተረጋጋ ፖለቲካ አለመፈጠሩ፣ የራሱን አመራር እየበላ የመጣ ፖለቲካ መኖሩ፣ በታሪኩና በሚገባው ልክ በአገር ደረጃ ተፅዕኖ የሚፈጥር አለመሆኑ ከአማራ ፖለቲካ ጎን ቆመው ሌሎች እንዳይታገሉ አድርጓቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ለአማራ ሕዝብ እንታገላለን የሚሉ እንደ አማራ ብልፅግና፣ እንዲሁም አብን የመሳሰሉ ኃይሎች የሚገፉ ከሆነ አማራን ማን ነው የሚሰበስበው? የአማራ ፖለቲካ ትግል ወዴት የሚያመራ ይመስልዎታል?
አቶ ቹቹ፡- ጠንካራ መሪዎች ማግኘቱ አይቀርም፡፡ ነገር ግን መሪዎች የሚገኙት በትግል ሒደት በመሆኑ ረዥም የትግል ሒደት ሊጠይቅም ይችላል፡፡ አሁን ያለው ችግር ግን ዋጋ ያስከፍለናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በዚህ ውጣ ውረድና ቀውስ ውስጥም ቢሆን አማራንም ኢትዮጵያንም የሚሰበስብ መሪ ይገኛል፡፡ ጊዜ ይወስዳል እንጂ ሁኔታዎች አስገድደውት አማራ ወደ አንድ የመሰባሰቡና የመምጣቱ ነገር አይቀሬ ነው፡፡ በአብንም ሆነ በሌሎች የአማራ ፖለቲካ ኃይሎች፣ እንዲሁም በአማራ ማኅበረሰብ ዘንድ ትልቁና ገዢ ሆኖ የሚመጣው የመታገያ አጀንዳ የህልውና አደጋ የሚለው እየሆነ ይመጣል፡፡ አማራ ተሰባስቦ ካልቆመ ተፅዕኖ መፍጠርም፣ ራሱን ማቆየትም ሆነ አገሪቱን መጠበቅም የሚከብድበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ የህልውና ጉዳይ ከሁሉ በላይ ገዥ እየሆነ መጥቶ የአማራን ፖለቲካ ልሂቃን፣ ምሁራንና የማኅበረሰብ ጠበቆች የሚያሰባስባቸው አጀንዳ እየሆነ ይሄዳል፡፡
ወደው ሳይሆን በህልውና ጥያቄ አስገዳጅነት የአማራ ኃይሎች ይሰባሰባሉ፡፡ ምክንያቱም የህልውና ጥያቄ እስካልተመለሰ የሕገ መንግሥት ጥያቄ የቅንጦት ጥያቄ እየሆነ ይሄዳል፡፡ በግድ መሰባሰብ ይመጣል፣ መሪም ይመጣል፡፡ የምንከፍለው መስዋዕትነት ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ አለመደማመጡ፣ ወዲህ ወዲያ ማለቱም ሆነ መረባበሹ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ነገር ግን በሒደት አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ወደ መገንባቱና መሰባሰቡ የማይቀር ይሆናል፡፡ መሪና ተመሪን መፍጠር ሲቻል ማለትም ሥርዓት ባለው መንገድ አመራርና ተመሪን ማበጀት ሲቻል፣ እነዚህን ችግሮች የምንሻገራቸው ይመስለኛል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ዋጋ መክፈልችን የሚቀጥል መስሎ ይታየኛል፡፡
ሪፖርተር፡- የአማራ ክልል ከጎረቤት ክልሎች ጋር የሚወዛገብባቸው የወሰን ጥያቄዎች በምን መንገድ መፈታት አለባቸው? የአማራ ፖለቲካስ ከሌሎች ማኅበረሰቦች የፖለቲካ ፍላጎት ጋር በምን መንገድ ተግባብቶና ታርቆ መሄድ ይችላል?
አቶ ቹቹ፡- የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ሲናገሩ ብዙዎቹ ችግሮቻችን ከውጭ ናቸው ብለው ነበር፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ከላይ የቆጠርኳቸው የአማራ ሕዝብ ሰባት ጥያቄዎች ብዙዎቹ በሌሎች ክልሎችና በፌዴራል መንግሥቱ ትብብር የሚፈቱ ናቸው፡፡ ይህ የአማራን ሕዝብ ችግር ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ ሕገ መንግሥቱን ውሰድ፡፡ የአማራ ሕዝብ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የፌደራል መንግሥቱና ሁሉም ክልሎች ካላመኑበት ሊፈታ የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ ከአማራ ክልል ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይን ተመልከት፡፡ ሌሎች ክልሎች ካልተሳተፉበት በቀላሉ የሚሳካ አይደለም፡፡ የወሰንና የማንነት ጥያቄም ብቻህን በአማራ ክልል ብቻ የምትፈታው አይደለም፡፡
ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በተመለከተ በአንፃራዊነት በክልሉ ልታሰፍን ትችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በመላ አገሪቱ ያሉ ክልሎችን ያከበረ የዴሞክራሲ ፍላጎት ይታያል፡፡ የህልውና ጥያቄ አለ ሲባልም ከክልሉ ውጪ የሆነ ሥጋት ነው እየተነሳ ያለው፡፡ አማራ ክልል ከጎረቤት ክልሎች፣ ከሌሎች ክልሎችም ሆነ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር የግዴታ የሰመረ ግንኙነት መፍጠር መቻል አለበት፡፡ የአማራ ክልል ከጎረቤቶቹ ከአፋር፣ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከሶማሌም ሆነ ከሌሎቹ ክልሎች ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሰመረ ግንኙነት ካልፈጠረ ችግሮችን ለመፍታት ቀልል አይሆንም፡፡ በራሱ እጅ ያሉ ጉዳዮችን፣ የውስጥ አንድነትን፣ የውስጥ ጥንካሬንና መግባባትን በመፍጠር በራሱ አቅም ሊፈታ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከእሱ እጅ ውጪ ያሉ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት የሌሎች ክልሎችን ትብብር፣ ቀናነትና ድጋፍ ይፈልጋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ፖለቲካ የሚወሳሰበው ከሌሎች ክልሎች ጋር ባለው ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፣ ከሌሎች አገሮች ጋርም ተጎራባች በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ ክልሉ ከኤርትራና ከሱዳን ጋር ድንበር ተጋሪ በመሆኑ ከውጭ የሚመጡ ጉዳዮችንም በተመለከተ ጥንቃቄ የተሞላው ፖለቲካ ነው መከተል ያለበት፡፡ ከሌሎች ክልሎች ጋርም ሆነ ከሌሎች አገሮች ጋር ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብ ያስፈልጋል፡፡ የአማራ ችግር በውስጣዊ አንድነት መጠናከር ብቻ አይደለም የሚፈታው፡፡ ለውጫዊ ጉዳዮችም ትኩረት በመስጠትና በጥንቃቄ በመያዝ ጭምር ነው የሚፈታው፡፡
ሪፖርተር፡- ለአማራ ፖለቲካ የሚበጀውና መፍትሔው ምንድነው ይላሉ?
አቶ ቹቹ፡- የአማራ ፖለቲካ የመረበሽ፣ የመታመንና የመጠናከር ችግር ነው ገጥሞት ያለው፡፡ እነዚህ ችግሮች ደግሞ የሕዝቡ ጥያቄዎች እንዳይመለሱ እንቅፋት ሆነዋል፡፡ ለዚህ የመጀመሪያው መፍትሔ ጠንካራ አመራር መፍጠር ነው፡፡ ጠንካራ አመራር ካለ የማትፈታው ችግር የለም፡፡ የጠንካራ አመራር ግንባታ ደግሞ በሁለት መንገዶች የሚታይ ነው፡፡ ብቃትና ልምድ ያለው አመራር መገንባት የሚሉ ናቸው፡፡ ከወረዳና ከዞን ጀምሮ እስከ ክልልና አገር ጠንካራ አመራር የመገንባት ልምድ ሊጠናከር ይገባል፡፡ የአማራ ፖለቲካ በዚህ ላይ ቢያተኩር ከአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች መመለስ በተጨማሪ፣ ለኢትዮጵያ መፅናትና አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል፡፡
በአማራ ፖለቲካ ቅድሚያ የሚሰጠው የአመራር ጉዳይ ነው፡፡ በሁለተኝነት ግን መደበኛና የሰመረ የመሪና የመሪ ግንኙነት መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡ በአመራርና በማኅበረሰቡ መካከል ጠንካራና መግባባት የሰፈነበት ግንኙነት መገንባት ካልተቻለ፣ ጠንካራና ልምድ ያለው መሪ ቢኖርህም ዋጋ ላይኖረው ይችላል፡፡ ይህን ለመፍጠር መሪው መልካም አስተዳደርና አሳታፊነትን ማስፈን ይጠበቅበታል፡፡ ሰዎችን ማግለል አያስፈልግም ዴሞክራሲያዊና ሁሉንም አሳታፊ ሥርዓት መገንባት በየደረጃው ካለው አመራሩ ይጠበቃል፡፡
ሕዝቡ ደግሞ ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣ አርሶ አደሩ፣ ተማሪው ሁሉም አመራሩን መደገፍ ይጠበቅበታል፡፡ አመራርን በመግደል፣ በመስደብ፣ በማንቋሸሽና በማዋረድ የሕዝቡ ጥያቄዎች ሊመለሱ አይችሉም፡፡ ኅበረተሰቡ አመራሩን መደገፍ መቻል አለበት፡፡ የአመራሩና የሕዝቡ መግባባት ሲፈጠር አንድነቱ ይመጣል፡፡ አንድነቱ ከተፈጠረ ደግሞ ጠንካራ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባትም ሆነ የአማራ ጥያቄዎችን ለማስመለስና በኢትዮጵያም ፖለቲካ ተፅዕኖ ለመፍጠር እንችላለን፡፡ የዚህ ማሰሪያው ግን መደማመጥና መከባበር ያስፈልጋል ነው የምለው፡፡ መዘላለፍ፣ መፈራረጅም ሆነ መገዳደል የአማራን ጥያቄ ያዘገያሉ እንጂ ለማስመለስ አያግዙም፡፡