Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያ ‹‹የሞርጌጅ›› ብድርን ዳግም የመለሰው ጎህ ባንክ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ጅማሮ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በከተሞች አካባቢ መሠረታዊ ከሚባሉ ችግሮች መካከል አንዱ የመኖሪያ ቤት ነው፡፡ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ችግሩ ብሶ ይታያል፡፡ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ አንዳንድ የተጀማመሩ ሥራዎች በታሰበው ልክ አለመሄዳቸው ችግሩን ማባባሱ ይጠቀሳል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለዓመታት ለቆጠቡ ዜጎች በትክክል ለማስተላለፍ የተፈጠረው መንገራገጭ በራሱ ከዚህ በኋላ የመኖሪያ ቤት ለማግኘት ያለውን ፈተና በእጅጉ እንዳባባሰው ይታመናል፡፡ 

ለዜጎች የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ አለማግኘት፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየገነቡ ለሕዝቡ ለማስተላለፍ የተጀመረው ሥራ አሁን ላይ በሩ እየተዘጋ መሆኑ የቤት ጉዳይ አሳሳቢ እንዲሆን እያደረገው ስለመምጣቱም ይታመናል፡፡ 

ችግሩ ገዝፎ ስለሚታይ በሪል ስቴት አልሚዎች የሚገነቡ ቤቶች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቁጥራቸው ጨምሯል ቢባልም፣ የእነዚህ ቤቶች ዋጋ አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ያላገናዘበና በርካታ የአሠራር ችግር የሚታይበት በመሆኑ፣ ሌሎች አማራጮች ካልታዩ ችግሩ የሚቀጥል መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡ የመኖሪያ ቤቶችን ችግር በመገንዘብ የበኩሉን ለማድረግ ወደ ሥራ የገባው የጎህ ቤቶች ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አስማረ እንደሚገልጹትም፣ የመኖሪያ ቤት ችግር እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ትልቁ ችግር ደግሞ ብዙው ኅብረተሰብ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ቢኖውም የአቅም ውስንነት ገድቦቷል፡፡

የቤት ዋጋ ለብዙዎች የማይቀመስ ስለሆነ ‹‹ቤት መግዛት አልችልም›› ወደሚል ተስፋ መቁረጥ የመሄድ አዝማሚያ እየታየ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሙሉጌታ፣ ይህንን አመለካከት ጭምር ለመቀየር በዘርፉ በርትቶ መሥራት ግድ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው በሪል ስቴት አልሚዎች የሚገነቡ ቤቶች ዋጋ ብዙዎችን ለመድረስ የሚያስችል በመሆኑ፣ ብዙ አማራጮች ሊታዩ መቻል እንዳለባቸውም የአቶ ሙሉጌታ ማብራሪያ ያመለክታል፡፡  

መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ወቅት በሪል ስቴት አልሚዎች የሚሸጡ ቤቶች ዝቅተኛ የሚባለው ለአንድ ካሬ ሜትር 100 ሺሕ ብር የሚጠየቅባቸው እየሆነ ነው፡፡ ይህ ዋጋም ቢሆን በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡ እንደ ግንባታው ቦታ ካሬ ሜትር ከ200 እስከ 250 ሺሕ ብር እየተጠየቀባቸው ያሉ የሪል ስቴት ቤቶች ብዙ ከከተማ ወጣ ያሉ ወይም ዳርቻ አካባቢ ካልሆነ፣ በካሬ ሜትር ከ100 ሺሕ ብር በታች ዋጋ ማግኘት እየተቻለ አለመሆኑም ይጠቀሳል፡፡ በመሆኑ ከዚህ ባነሰ ዋጋ ቤት ለማቅረብ የግንባታ ወጪያቸው የሚቀንስና በቴክኖሎጂ የታገዙ ጥራታቸውን የጠበቁ ግንባታዎችን ማካሄድ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ሥራ የገባው ጎህ ባንክም ይህንን ችግር በመገንዘብ አማራጭ የሚሆን ቤት በመገንባት ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የያዘውን ውጥን አንድ ብሎ ለመጀመር የሚያስችለውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ከተለመደው የሪል ስቴት የአገነባብ ሥልት ወጣ ባለ መንገድ ሥራውን ለማከናወንም ራሱን የቻለና እንደ እህት ኩባንያ የሚታይ የሪል ስቴት ኩባንያ በማቋቋም ሥራውን በጋራ ለመሥራት መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ በተግባር ወደ ሥራ መግባቱንም ይፋ ለማደረግ ጎህ ቤቶች ባንክ ከቤት አልሚዎች ጋር ቤቶችን ለማስገንባት የሚያስችለውን ስምምነት ከትናንት በስቲያ ተፈራርሟል፡፡ 

ስምምነቱን በተመለከተ ከተሰጠው ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው፣ ጎህ ቤቶች ባንክ፣ ጎህ ሀብት ልማትና ግብይት አ.ማ. ከተባለው ኩባንያ ጋር በመሥራት ቤቶቹን በባለቤትነት የሚያስገነባ ይሆናል፡፡ ለሚያስገነባው ቤት ደግሞ ባንኩ ፋይናንስ ያቀርባል፡፡ 

በዕለቱ ሌላው የተፈጸመው ስምምነት ደግሞ ጎህ ሀብት ልማትና ግብይት አ.ማ. የግንባታ ሥራውን እንዲያከናውንለት ኦቪድ ከተባለው የኮንስትራክሽን ኩባንያ ጋር ተፈራርሟል፡፡ ኦቪድ ኮንስትራክሽን ከሪል ስቴት ኩባንያው ጋር በገባው ውል መሠረትም በመደጋገፍ የሚገነቡትን የመጀመርያ ምዕራፍ የጎህ መንደር በ1.45 ቢሊዮን ብር ለመገንባት ውል ገብቷል፡፡

የጎህ ሀብት ልማትና ግብይት አ.ማ. ባለቤትነት የሚገነባው የመጀመርያው ምዕራፍ የጎህ መንደር 270 ቤቶችን የያዘ ሲሆን፣ ግንባታው በ18 ወራት ውስጥ ተጠናቅቆ ለቤት ፈላጊዎች የሚተላለፍ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡ ባንኩ ለቤቶች ግንባታ ዕድገትና ለተያያዥ ክንውኖች የሚረዳ ብድር ከማቅረብ ባሻገር፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ በያዘው ውጥን መሠረት፣ የመጀመርያ ምዕራፍ ግንባታውን ሳሪስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በግዥ ባገኘው ቦታ ላይ እንደሚያካሂድና ግንባታው የሚያርፈውም 2,851 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡ 

በዚህ የመጀመርያው ዙር ግንባታ ባለአንድ፣ ባለሁለትና ባለሦስት መኝታ ክፍል አፓርትመንቶችን የሚያስገነባ ይሆናል ተብሏል፡፡ እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለጻ፣ ይህ በጥምረት የሚገነባው ሪል ስቴት በዋጋ ደረጃም ቢሆን አሁን ገበያ ውስጥ ካለው ዋጋ በቀነሰ መልኩ የሚቀርብ ነው፡፡ ሥራውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ በቂ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል፡፡   

ከግንባታ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ ግንባታን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ ከባድ ከመሆኑ አንፃር፣ እንዲሁም በሪል ስቴት ልማት ደንበኞች የከፈሉበትን ቤት ማግኘት ከዓመታት እየጠበቁ ከመሆኑ አንፃር፣ ጎህ ባንክም እንዲህ ያለው ነገር ሊያጋጥመው አይችልም ወይ የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡  

ግንባታውን እንዲያካሂድ የተመረጠው ኦቪድ ኮንስትራክሽንም በአሁኑ ወቅት በርካታ ፕሮጀክቶች በእጁ ያሉ በመሆኑ፣ ‹‹እነዚህን ፕሮጀክቶች ይዞ የጎህ ቤቶች ግንባታውን በተባለው የጊዜ ገደብ መጨረስ ይችላል ወይ?›› የሚል ጥያቄም ቀርቧል፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች ቅድሚያ ምላሽ የሰጡት አቶ ሙሉጌታ፣ እንዲህ ያለው ሥጋት ተገቢ ቢሆንም፣ ጎህ ባንክ ከአጋሮች ጋር ለመሥራት ሲወስን እንዲህ ያለው ችግር እንዳይፈጠር በመግባባት ነው፡፡ 

ኦቪድ ኮንስትራክሽን የተመረጠበትም ምክንያት በዘርፉ ግንባታዎችን በቶሎ በማጠናቀቅ የሚያስረክብ በመሆኑ ጭምር ስለሆነ፣ በተያዘው ጊዜ ውስጥ ግንባታውን አጠናቆ እንደሚያስረክብ እርግጠኛ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል፡፡ በዚሁ ጉዳይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ያከሉት የጎህ የሀብት ልማትና ገበያ አ.ማ. ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ አሰፋ እንደገለጹት፣ ኩባንያቸው በዋናነት የተቋቋመው፣ በተለይ መኖሪያ ቤቶችን አልምቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ ሲሆን፣ ይህንንም ሲያደርግም የቤቶቹ ግንባታ በተያዘው ጊዜና በጀት እንዲያልቁ ለማስቻል ጭምር ነው ብለዋል፡፡ በጥምረት የሚገነባው የጎህ ሪል ስቴት አሁን በገበያ ላይ ካለው ዋጋ በሚቀንስ ዋጋ የሚያቀርብ መሆኑንም በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡ የቤት ችግር ከፍተኛ በመሆኑ በተለመደው የአገነባብ ሥልት ይዞ ችግሩን መቅረፍ ስለማይችሉ አዳዲስ ቴክኖሎዎችን የሚተገብር በመሆኑ ሥራውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ በቂ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል፡፡ ቴክኖሎጂን ተጠቅመን ጥራቱን የጠበቀ ግንባታ በፍጥነትና በተመጣጣኝ ዋጋ ቤቶቹን ማቅረብ ግድ ስለሚል፣ በዚሁ መሠረት ገንብቶ ማስረከብ እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል፡፡ 

የኦቪድ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አስማረ ዋለ በበኩላቸው፣ ኩባንያቸው ከተለመደው የኮንስትራክሸን ግንባታ ወጣ ባለ መልኩ ቴክሎጂዎችን በመጠቀም 24 ሰዓታትና በሳምንት ሰባት ቀናት የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ከተለመደው የኮንስትራክሽን የአሠራር ሲስተም ወጣ ባለ መልኩ ጥሩ በሆነ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ሲስተምና የጥራት ደረጃ በመገንባት ስሙን የተከለ በመሆኑ፣ በውለታው መሠረት ከምትጠብቁት በላይ ገንብቶ የሚያስረክብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ኦቪድ ኮንስትራክሽን ብዙ ፕሮጀክቶች ስላሉት ይህንን የቤቶች ግንባታ በጊዜው በማጠናቀቅ አይቸገርም ወይ ለሚለው ጥያቄ የኦቪድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ይኼ ሥጋት አይሆንም ይላሉ፡፡ እንዲያውም እንደ ኩባንያው ዝግጅት ብዙ ፕሮጀክቶችን እንፈልጋለን ያሉት አቶ አስማረ፣ ይህም የሚሆንበት የራሱ ምክንያት እንዳለው ነው የጠቆሙት፡፡ ኦቪድ ግሩፕ በሥሩ ዘጠኝ ኩባንያዎች ካሉት እነዚህ ኩባንያዎች የሚደገፉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ብዙ ፕሮጀክቶችን ለመሥራት የተዘጋጀን በመሆኑ፣ አሁን ያሉትን ፕሮጀክቶች እጥፍ በማድረግ የቤት ፈላጊዎችን ፍላጎት ለማርካት በሰፊው መዘጋጀታቸውን፣ ይህንንም ፕሮጀክት በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ ምንም ዓይነት ችግር እንደማይኖርባቸው አረጋግጠዋል፡፡  

በአሁኑ ጊዜ እነዚህን ቤቶች ለመረከብ ከአራት መቶ በላይ ቆጣቢዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ግንባታው እንደተጠናቀቀ በቅደም ተከተል የሚረከቡ ሲሆን፣ ለቀጣይ ፕሮጀክቶችም ቆጣቢዎች እየተመዘገቡ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ቤት ፈላጊዎቹ ከፕሮጀክቱ ቤት ለመግዛት ሲፈልጉ በጎህ ቤቶች ባንክ ዋና መሥሪያ ቤትና በቅርንጫፎች በመቅረብ መመዝገብ የሚገባቸው ሲሆን፣ ለሚገነቡ ቤቶች ብቁ ለመሆንም ቢያንስ የቤቱን ቅድመ ግምት ዋጋ 30 በመቶ አስቀድመው መቆጠብ እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል፡፡ ቤቱ ተጠናቆ በሚረከቡበት ጊዜም ባንኩ የግለሰቦችን የመበደር አቅም መሠረት በማድረግ ለቀሪው ክፍያ እስከ 30 ዓመት የሚከፈል ብድር እንደሚመቻች ታውቋል፡፡ የብድር ወለድ ምጣኔውም አሁን ባንኮች ከሚጠይቁ የብድር ወለድ ከሁለት እስከ ሦስት በመቶ ያነሰ ስለመሆኑ አቶ ሙሉጌታ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የጎህ ቤቶችን የቤት ግንባታ አሠራርን ለየት የሚያደርገው አንዱ ምክንያት ለገንቢውም ለቤት ፈላጊውም ፋይናንስ የሚቀርብ መሆኑ ነው፡፡ 

በመጀመርያ ዙር የሚገነቡ ቤቶች መካከለኛ ገቢ ላላቸው ቤት ፈላጊዎች መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥሩና ባንኩም ይህንን ተግባር በቀጣይ በአዲስ አበባ ከተማና በክልል ከተሞች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ ተገልጿል፡፡ አቶ ሙሉጌታ ለሪፖርት እንደገለጹትም፣ ይህንን እጅግ ሰፊ የሆነውን የቤት ፍላጎት ለመመለስ መሬት ማግኘት ከባድ ቢሆንም፣ አሁን የጀመሩትን ግንባታ ለማከናወን ቦታዎችን በመግዛት መጀመራቸውን፣ ነገር ግን ሥራውን ለማስቀጠል የመሬት አቅርቦት የግድ ይላል፡፡ ችግሩ የጋራ በመሆኑም በተሻለ የአገነባብ ሥልትና ከሌሎች በቀነሰ ዋጋ የቤት ልማታችንን ለማስቀጠል መንግሥት ቦታ በማቅረብ ድጋፍ በማድረግ ጥሩ ለውጥ ይመጣል ብለው ያምናሉ፡፡

ይህ ድጋፍ ዋጋ ለማረጋጋት ጭምር የሚያግዝ በመሆኑ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባም ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡ ኩባንያቸው በገባው ኃላፊነት መሠረተ ቤቶቹን የሚገነባ ሲሆን፣ ይህንን ሥራ ለማጠናከር ግን የመንግሥት ዕገዛ ግድ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ 

የማኅበረሰቡ መሠረታዊ ችግር በሆነው የቤት አቅርቦት ላይ በመሥራት የተቋቋመለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመተባበር ተግባሩን ይበልጥ አስፈላጊ ስለመሆኑም አመልክተዋል፡፡ 

በዚህ ጥምረት ቀጣይ ግንባታዎችን ለማከናወን ያለውን ዕቅድ በተመለከተ፣ መሬት ከመንግሥት የምናገኝ ቢሆንም፣ በየዓመቱ ሳይቋረጥ መገንባት ይቻላል፡፡ አሁን ግን ግንባታዎቹን የሚያካሂዱት ከግለሰብ ቦታ ለመግዛት እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

አዲስ አባባ አስተዳደር በቅርቡ ለሪል ስቴት አልሚዎች 70/30 በሚል አሠራር ቦታ በነፃ በማቅረብ ቤቶች 30 በመቶውን ለእነሱ ለመስጠት በተደረሰ ስምምነት ቦታ የተረከቡ አልሚዎች ቢኖሩም፣ ጎህ ቤቶች ባንክ ግን በዚህ አሠራር ውስጥ አልገባም፡፡ በዚህ አሠራር 30 በመቶን ግንባታ ለመንግሥት በመስጠት ቀሪውን እንዲሸጡ የሚያስችል ነው፡፡ ይህ አሠራር አዲስ በመሆኑና ጎህ ባንክ ባይካተትም ወደፊት ግን አዋጭ ከሆነ በዚህ ዓይነት መንገድ ግንባታዎችን በማካሄድ ጭምር ሥራውን የማስፋት ዕቅድ እንዳለው የአቶ ሙሉጌታ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡ አቶ ሙሉጌታ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ሦስቱ ተጨማሪ ኩባንያዎች ያደረጉትን ስምምነት በጎህ ቤቶች ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አስማረ፣ የጎህ ሀብት ልማትና ግብይት አ.ማ. ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ አሰፋና የኦቪድ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስማረ ዋለ ፈርመዋል፡፡ የእነዚህ ሦስት ኩባንያዎች ጥምረት ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ያሉት ነው ያሉት ጎህ ባንክ የቦርድ አባል ውብሸት ዠቅአለ (ዶ/ር፣ ኢንጂነር) ገበያውን ለማረጋጋት የሚል ዓላማ የያዘ መሆኑ ነው፡፡ 

በተለይ ከቴክኖሎጂ በመጠቀም ሥራውን በፍጥነት የሚሠራ በመሆኑ ለዚህም የግንባታ ግብዓት ቀድሞ በማዘጋጀት ወደ ሥራ የሚገባ በመሆኑ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል፡፡  

ጎህ ቤቶች ባንክ በአገራችን የመጀመርያውና ብቸኛው የግል የቤት ብድር አቅራቢ ባንክ ሆኖ፣ ከ8,000 በላይ በሆኑ ባለአክሲዮኖች 2014 ዓ.ም. አገልግሎት የጀመረ ሲሆን፣ ዘንድሮ እስከ ሦስተኛው ሩብ ዓመት ድረስ ለቤት ግንባታና ዕድሳት ተያያዥ ሥራዎች ብቻ የሰጠው ብድር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ሰዓትም ስምንት ቅርንጫፎቹን በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ከፍቶ እየሠራ ይገኛል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች