Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› የቴሌ ብር ወይስ የኢትዮጵያ ብር?

በሙሉጌታ ኢተፋ (ዶ/ር)

የዓለም አገሮች ሁሉ የራሳቸው የሆነ ሕጋዊ ገንዘብ አላቸው፡፡ በተለያዩ ምክንያት ጥቂት አገሮች ውስጥ ለመኖርና ለመንቀሳቀስ ዕድል ገጥሞኛል፡፡ አንድም አገር ውስጥ የራሳቸውን ሕጋዊ ገንዘብ አንቀበልም የሚሉ አልገጠመኝም፡፡ በአውሮፖና በአሜሪካ መኪና ሳሽከረክር ቤንዚን ለመቅዳት የአገሮችን ሕጋዊ ገንዘብ ኩፓንና ክሬዲት ካርድ ቼክም ተጠቅሜአለሁ፡፡ ምርጫው የኔ ነበር በኢትዮጵያ ብር ላይ ‹‹ላምጪው እንዲከፈል ሕግ ያስገድዳል›› ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ የገንዘባችን የመግዛት አቅም መች ይሻሻል ይሆን እያለ ይጠብቃል እንጂ ብሩ ተቀባይነት የለውምና ቴሌ ብር ፈልጋችሁ አምጡ የሚል ትዕዛዝ ይገጥመናል ብሎ አልጠበቀም፡፡ የብር የመግዛት ኃይል ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆለ መሄዱ አንሶ ብሩንም መጠቀም አትችሉም የሚል ዱብ ዕዳ መጣበት ለዚህ ነው ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› የተባለው፡፡ ሕጋዊ የኢትዮጵያ ብር ተሸክሞ ቴሌ ብር ፍለጋ መሄድ በምንም መመዘኛ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ወሳኞቹ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ሲያደርጉ ሕግ መጣሳቸው ታውቋቸው ይሆን? ወይስ ከሕግ በላይ ብንሆንም የሚጠይቀን ሰው የለም በሚል እብሪት ኖሮባቸው ይሆን?

በአሁኑ ጊዜ ትኩረቱ ግሽበትን በመቀነስ የገንዘቡን ተፈላጊነት ከፍ ማድረግ ሲገባው ገና ምንነቱ ያልታወቀ ቴሌ ብር ፍለጋ ሂዱ ማለቱ በተዘዋዋሪ መንገድ የገንዘባችንን ዋጋ ዝቅ ማድረግ አይሆንም ወይ? የአንድ አገር ሕጋዊ ገንዘብ ክብር አለው፣ ሁሉም ሰው ማክበር አለበት፡፡ ‹‹ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበልም›› ይባል የለም፡፡ ቴሌ ብር መጠቀሙ ይቀለኛል ጊዜዬን ይቆጥብልኛል የሚል ሰው ካለ ዕድሉ እንዲኖረው ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡ ዋናው ነገር ተጠቃሚዎችን ምርጫ ማሳጣት ተገቢ አይደለም፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ሁሉ በአውሮፖና በአሜሪካ በሦስት አራት መንገድ ቤንዚን መግዛት ይቻላል፣ ሌላም ምርጫ ሊኖር ይችላል፡፡ ያለ በቂ ምክንያት ሰውን መገደብ ምን አመጣው?

መገበያያ ገንዘብ ብር እስከሆነ ድረስ ለምን ለቤንዚን በተለይ በቴሌ ብር ሆነ ሲባል አንዳንድ ሰዎች ሰው ብዙ ብር በኪሱ ተሸክሞ እንዳይሄድ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህማ ሠንጋ ሲገዛ 70,000 እና 80,000 ሺሕ ብር ተሸክመው አይደለም ወይ ገበያ የሚወጣ ሲባል መልስ የላቸውም፡፡ ሕጋዊ ገንዘቡን በሁሉ ቦታ እንዳይሠራ ማድረግ ባንኮችን ሌሎች የገንዘብ ተቋማት መቃወም አለባቸው፡፡ ሕጋዊ ገንዘቡን መንግሥት ማስከበር ሲገባው ሌላ አማራጭ ፈልጉ መባሉ ያስገርማል፡፡

ከዚህ በፊት ቤት ሠርተው የሚሸጡ ሰዎች (Real States) የቤቱን ዋጋ ተመን በኢትዮጵያ ብር ሳይሆን በአሜሪካ ብር ስለሆነ የት ነው ያለነው ማለታችን አልቀረም፡፡ እንዲያውም አንድ ሪል እስቴት በውጭ ገንዘብ ለሚከፍሉት 35 በመቶ ቅናሽ ይደረጋል እያለ ሲያስተዋውቅ ሕገወጥ ነው እያልን ስንተቸው አየር ላይ ማዋሉን አስቀርቷል፡፡

በዲጂታል አሠራር ከእኛ በጣም ልቀው የሄዱ አገሮች ሕጋዊ ገንዘባቸው ወደ ዲጂታል ተለውጦ ዜጐችን ምርጫ የማያሳጡበት ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ እኛ ደግሞ ይህን ሽግግር ለማድረግ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ አገልግሎት ሰጪዎችና አገልግሎት ተቀባዮች በቂ ዝግጅት እንደሌላቸው ሁለት ቀን በሁለት ቤንዚን ማደያዎች ያደረኩት ክትትል ዝግጅት እንደሚጐድለው በግልጽ ያሳያል፡፡

ለማንኛውም ከአንድ የአሠራር ዘዴ ወደ ሌላ አሠራር ዘዴ ሲለወጥ በአንድ ጊዜ ሳይሆን በጥቂት ቤንዚን ማደያዎች ተጀምሮ ችግሮቹ ተጠንተው መፍትሔ እያገኙ ቢሄዱ ውጤቱ የበለጠ ሊያምር ይችል ነበር፡፡ ለአገሩ እንግዳ የሆነ የቴክኖሎጂ ጉዳይ ስንወስን በብዙ አቅጣጫ ማየት ተገቢ ነው፡፡ አሁን ግን በችኮላ የተወሰነ ይመስላል ‹‹ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል›› ይባል የለም፡፡ ስለዚህ እንደገና ቢታይ መልካም ነው፡፡

በሁለት ቀን በሁለት ቤንዚን ማደያዎች ያደረግሁት ክትትል የሚያሳየው ትርምስና ግራ መጋባት በሰፊው ይታያል፡፡ ሠራተኞች ቶሎ መሥራት ስላልቻሉ የወረፋውን መብዛት ያማርራሉ፡፡ ቅልጥፍናው ከወትሮው በጣም የቀነሰ ነው ይላሉ፡፡ ጥቂት ወጣት ሴቶችና ወንዶች የቴሌ ብር ሠራተኞች ሁኔታውን ለማጥናትና ተጠቃሚውን ለመርዳት ውር ውር ይላሉ፡፡ በምዕራቡ አገር የወረቀት ብር መጠቀሙ የቀረ አስመስለው ሲያወሩ ሰምቼ ከእውነት የራቀ መሆኑን ባስረዳም በቅርብ ወደ ውጭ አገር ስላልወጣሁ ራሴንም ተጠራጥሬ በቅርብ አውሮፖና አሜሪካ የነበሩት ወዳጆቼ ጋር ስልክ ደውዬ በዩሮም በዶላርም ቤንዚንና ሌላም ነገር ሁሉ መግዛት እንደሚቻል ነገሩኝ፡፡  እንዲሁም አንዱ ወዳጄ በዚያው ዕለት ሚያዚያ 18 ቀን ከECA ቤንዚን ማደያ በብር እንደከፈለ ነገረኝ፡፡ ለዲጂታል አሠራርም ECA እንደሚቀርብ ማጤን ተገቢ ነው፡፡ የማያቁትን ማውራት አዲስ ነገር አይደለም በሚዲያም ብዙ እየሰማን ነው፡፡

የማያውቁትን ማውራት ጋር የተያያዘ አንድ ፈገግ የምታሰኝ ቀልድ ላውጋችሁ፡፡ በደርግ ዘመን ‹‹የቡናና ሻይ ሚኒስቴር›› የተባለ መሥሪያ ቤት ተቋቁሞ አንድ ሃምሳ አለቃ የደርግ አባል ሚኒስትር ሆኖ ይሾማል፡፡ በቡና ላይ የሚደረግ ስብሰባ በአንድ ምሥራቅ አፍሪካ አገር ይደረጋል፡፡ የኢትዮጵያ ተራ ሲደርስ ሃምሳ አለቃው ሚኒስትር በኢትዮጵያ ቡና ተተክሎ በአንድ ዓመት ውስጥ ብዙ የቡና ምርት እንደተገኘ በሰፊው እያብራራ ለተሰብሳቢዎች ያስረዳል፡፡ የአንድ አገር ተወካይ የሥነ ሥርዓት መብት ይጠይቅና ቡና የመጀመሪያ ፍሬ ለመስጠት ሦስት ዓመት እንደሚፈጅ ይገልጽና ምናልባት ኢትዮጵያ ቡና በአንድ ዓመት ፍሬ እንዲያፈራ አዲስ ሳይንሳዊ ዘዴ አግኝታለች ያለበለዚያ የኢትዮጽያ ተወካይ የማያውቀውን ያወራል ሁለተኛ ትክክል ስላልሆነ እንዲቀመጥ አድርገው ብሎ ሊቀ መንመሩን እንደጠየቀ ይቀለዳል፡፡

የቀልዱ መልዕክት ግልጽ ነው፡፡ ያለ እውቀት ያለቦታው መሾም አገርን ይበድላል፣ ያዋርዳል ለማለት ተፈልጐ ነው፡፡ የሰሙትንና ያዩትን በቂ ግንዛቤ ሳይወስዱ ሥራ ላይ ማዋል ‹‹ሲሉ ሰምታ ዶሮ…›› ሁኔታውን ሳይገልጸው አይቀርም፡፡

የአሠራሩ ለውጡ ለሕዝብ በትክክል ባይገለጽም ቅልጥፍናን ዕውን ለማድረግ ጊዜውን ለመቆጠብ ነው ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ የሆነው ተቃራኒው ነው፡፡ መኪና ነጂዎች ሠልፍ ላይ አራት አምስት ሰዓት ስላጠፋ ጊዜያቸው በመባከኑ ሲበሳጩ ይስተዋላል፣ በየቴሌ ቢሮዎች ቴሌ ብር ለመግዛት ያለው ሠልፍ ቀላል አይደለም፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ተጠቃሚዎች ምርጫ ይኑራቸው ነው፡፡ የተለያዩ ሰዎች የተለየዩ አማራጮችን መጠቀም ይፈልጋሉ፡፡ ብዙ አማራጮች ሊኖር ይችል ነበር፡፡ እንደ አማራጭ ለምሣሌ ባንኮች ኩፖን እያተሙ ለተጠቃሚዎች ቢሸጡ፣ በዛሬው ጊዜ ከ500 ብር በታች ቤንዚን መግዛት ብዙም ስለማያስኬድ ባለ 500 ብር እና ባለ 1000 ብር ኩፖን ለተጠቃሚዎች ቢያቀርቡም ሞባይልን ጨርሶ መጠቀም የማይፈልጉትን ይገላግላል፡፡ ለአንዳንድ አስቸኳይ ጉዳይ ደግሞ ቢሆንስ እስከ 1000 ብር ድረስ በጥሬ ብር መግዛት ቢቻል እንዲሁም ክሬዲት ካርድ መጠቀም የሚቻልበት ሁኔታ ቢፈጠር ለተጠቃሚዎች ምርጫ ይሰጣል፡፡ በቴሌ ብርና በባንክ ቤንዚን መግዛት ማለት አስፈላጊ ያልሆነ ጫና በመኪና ነጂዎች ላይ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህን ውሳኔ ሲያደርጉ የመብት ጥሰት እንዳደረጉበት ታውቋቸው ይሆን? አንድ ሰው ሞባይል ፎን ወይም ባንክ አካውንት እንዲኖረው ግዴታ የለበትም፡፡ መኪና ለመንዳት የቤንዚን መግዣ ገንዘብ ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ሚሊዮን ተኩል መኪኖች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የአንድ ሚሊዮን ተኩል ሰዎች መብት መጣስ አያስደንቅም የባሰም አለ የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ይህም የመብሸቅ አባባል ነው እንጂ የመብት መጣስ በፀጋ የመቀበል ጉይይ አይደለም፡፡ ከዴሞክራሲ መገለጫዎች አንዱ ለዜጋው ምርጫ እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ ምርጫ ማሳጣት ግን የመብት ጥሰት ነው፡፡ ምርጫ ማጣትና ጊዜን ማባከን ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን አገርም ትጎዳለች፡፡ የአምራች ዜጐች ጊዜ መጥፋት በአገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ የሥራ ጊዜ በቤንዚን ሠልፍ ላይ ማባከን ስለሌለበት በጥብቅ ታስቦበት ሁኔታው እንዲሻሻል ማድረግ ከሚመለከታቸው ሰዎች ሁሉ ይጠበቃል፡፡

በኢትዮጵያችን የምንጨቃጨቅበት የጠፋ ይመስል በሆነ ባልሆነ ሰዎችን የሚያስከፋ ሁኔታ መፍጠር ማንንም አይጠቅምም፡፡ በዚህ የቴሌ ብር ጉዳይ የመሻሻል ዕርምጃ ለመውሰድ ከሆነ በተጠና መልክ ሆኖ ተጠቃሚዎችን በማያስከፋና በማይጐዳ መልኩ ጊዜን በማያቃጥል መንገድ አስፈላጊ ያልሆነ መጉላላትን በሚያስወግድ መልኩ ቢሆን አገልግሎት ሰጪዎችንና ተገልጋዮችን ይጠቅማል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ቅድሚያ ማግኘት ያለባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እዚህ መዘርዘሩ ቦታው አይደለም፡፡ ግሽበት የተነሳበት ምክንያት ከገንዘብ ጋር ስለሚያያዝ ነው፡፡ ግሽበትን በተመለከተና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ የሕዝቡ ብሶት ብዙ ነው፡፡ ብሶት ላይ ብሶት መጨመር ግን አስፈላጊ አይደለም፡፡ የሕዝቡን ብሶት ለማቃለል ብዙ ርቀት መሄድ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት እየሞከረ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ የብሶት ቅደም ተከተል ብንመለከት ግን ቤንዚን እንዴት ይቀዳ የሚል እንደማይሆን በቅንነት የሚያስቡ ሰዎች ሁሉ ያውቁታል ብሎ መገመት አያዳግትም፡፡ የግሽበት ጉዳይ ቅድሚያ የሚሻ ስለሆነ ነው የተነሳው ቅድሚያ ባልሆኑ ነገሮች ላይ የአምራች ዜጋ ጉልበትና ጊዜ መባከን የለበትም፡፡ የቅድሚያ ጉዳይ ሲነሳ ከሰው ወደ ሰው ከቦታ ወደ ቦታ ከጊዜ ወደጊዜ ሊለያይ ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ግን አብዛኛውን ሕዝብ የሚመለከቱ ቅድሚያዎች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ባሁኑ ጊዜ ግሽበት ከእነርሱ አንዱ ስለሆነ ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ፡፡

ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት በቂ ጥናት ተደርጓል ማለት አልችልም፡፡ በሁለት ቤንዚን ማደያዎች ያሉትን አገልግሎት ሰጪዎችና ተቀባዮችን አነጋግሬአለሁ፡፡ ነገር ግን በየደረጃ ያሉትን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሁሉ አነጋግሬአለሁ ማለት አልችልም፡፡ ነገር ግን ብዙ ወዳጀቼ ጋር በሰፊው ተወያይተንበታል፣ አንድም ሰው ሁኑ ጊዜ በየቤንዚን ማደያዎች የሚደረጉትን ደግፎ ያነጋገረኝ የለም፡፡ የተመለከትኳቸውና የሰማኋቸው ነገሮች ግን ለምን ለማለት ከበቂ በላይ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያችን ለምን ማለት በጣም አልተለመደም ዋጋም ያስከፍላል፡፡ ኢፍትሐዊ ነገር ሲደረግ ለምን ማለት በእኔ አስተያየት የዜግነት ግዴታ መወጣት ነው፡፡ የእኔን ትዝታ ለማከል በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለምን በማለቴ ዋጋ አስከፍሎኛል፡፡ ግን በዚህ ምክንያት ቅሬታ ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ ኢሰብዓዊና ኢፍትሐዊ ነገሮች ሲከሰቱ ለምን ባልል ኖሮ የሕሊና ወቀሳ ይሰማኝ ነበር፡፡ አሁን በስተርጅናም ለምን ማለት ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ቤንዚን ሲቀዳ ምርጫ ማሳጣት በእኔ ግምት ኢፍትሐዊ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ኢፍትሐዊነትን ያለመቃወም የዜግነት ግዴታን አለመወጣት ነው፡፡ በሰላምና በቅንነት መቃወም መሻሻልን ሊያስከትል ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሙሉጌታ ኢተፋ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሰላም ተቋም የቦርድ ሊቀመንበር ሲሆኑ የቀድሞ ዲፕሎማቶች ማኅበር (Forum for The Study of Foreign Policy) ሦስት ዓመት በአባልነት ሰባት ዓመት በሊቀመንበርነት አገልግለዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በፈረንሳይ፣ በስፔን በፖርቱጋል፣ በቫትካንና ዩኔስኮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገራቸውን አገልግለዋል፡፡ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በማታና በጐልማሶች ትምህርት በዲንነት አገልግለዋል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት