Thursday, May 30, 2024

የአማራ ጥያቄ በኢትዮጵያ ፖለቲካ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አንዳንዶች አማራ የሚባል የብሔር ማንነት የለም ቢሉም፣ በኢትዮጵያ አማራ ነኝ የሚልና በአማራነት የሚጠራ ማኅበረሰብ መኖሩን ማንም ሊፍቀው አልቻለም፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር ስትመሠረት ጀምሮ ከሌሎች ሕዝቦች እኩል አስተዋጽኦ ሲያደርግ መኖሩ ብዙዎችን ያግባባል፡፡

አማራ በዓድዋ ተራሮች፣ በማይጨው ሜዳዎችም ሆነ በኦጋዴን በረሃ ኢትዮጵያን ለማፅናት ሲል መስዕዋትነት መክፈሉን የሚጠራጠሩ ታሪክ አላዋቂዎች መሆናቸውም ይነገራል፡፡

አማራ በኢትዮጵያ እንደ አንድ ማኅበረሰብ ህልውና ያለው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የራሱ የፖለቲካ ጥያቄዎች ያሉት መሆኑም በስፋት ይወሳል፡፡  

በኢትዮጵያ የሥር ነቀል ለውጥ ጥያቄ ባቆጠቆጠባቸው ከፋሽስት ጣሊያን መባረር በኋላ በነበሩ ዓመታት፣ የአማራ ማኅበረሰብም እንደ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የፖለቲካ ጥያቄን ሲያነሳ መኖሩ ይታወቃል፡፡ በትግራይ የወያኔ አመፅ፣ በባሌ የኤልከሬ አመፅ፣ በሲዳማና በሌሎች አካባቢዎች የሥር ነቀል ጥያቄዎች በሚቀጣጠሉበት በዚያ ዘመን፣ በጎጃም ገበሬዎችና በወሎ የጁ አካባቢም የለውጥ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር፡፡

ከብላታ ተክለወልድ ሀዋሪያት እንዲሁም ከብርሃኑ ድንቄ (አምባሳደር) ጀምሮ በተለያዩ ወቅቶች 225ኛውን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴን ዙፋን የተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች በሚነቀንቁበት ወቅትም፣ የአማራ ልጆች ተሳታፊ እንደነበሩ ታሪክ ያወሳል፡፡

በወንድማማቾቹ መንግሥቱና ገርማሜ ንዋይ የ1953 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበሩ እንቅስቃሴዎች የአማሮች ተሳትፎ እንደነበርም ይነገራል፡፡

ከ1957 ዓ.ም. ጀምሮ ለአሥርት ዓመታት በቀጠለውና የዘውዳዊ ፊውዳላዊ ሥርዓትን ከኢትዮጵያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ባስወገደው የተማሪዎች ፖለቲካ እንቅስቃሴ ወቅትም ቢሆን፣ በአማራነት የሚጠሩ ተማሪዎች የነቃ ተሳትፎ እንደነበራቸው የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በመነሳትም ኢትዮጵያ አሁን ለደረሰችበት የፖለቲካ ምዕራፍ ከሌሎች ሕዝቦች እኩል አማራ ድርሻ እንዳለው በርካቶች ይገልጻሉ፡፡

ይሁን እንጂ ባለፉት 30 ዓመታት የአማራ የፖለቲካ ጥያቄ ሲነሳ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ የሥርዓተ መንግሥት ጠንቅ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ መኖሩን በርካቶች ይናገራሉ፡፡ የአማራ ጉዳይ ሲነሳ ፀረ ፌዴራላዊ ሥርዓትና የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ፀር ሆኖ መቅረቡ ይሰማል፡፡ ይህ ለምን ሆነ ለሚለው ጉዳይ ደግሞ የአማራ ፖለቲከኞች የተለያዩ አስተያየቶች ነው የሚሰጡት፡፡

ከአብን መሥራቾች አንዱና የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ጋሻው መርሻ፣  አማራ ጥያቄ ቢኖረውም ጥያቄውን አፍኖ እንዲኖርና በዳይ ተብሎ በጠላትነት እንዲፈረጅ ሆን ተብሎ መሠራቱን ያስረዳሉ፡፡

‹‹የአማራ ሕዝብ በወያኔና እንደ ኦነግ ባሉ አጋሮቹ በከፍተኛ ደረጃ ስሙ እንዲጠፋና ዘር ማጥፋት እንዲፈጸምበት ሲቀሰቀስበት የኖረ ሕዝብ ነው፤›› በማለትም አቶ ጋሻው ይናገራሉ፡፡

ይህን አስተያየት የሚያጠናክር ሐሳብ የሚሰጡት የቀድሞ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ታጋይና ከፍተኛ አመራሩ አቶ ቹቹ አለባቸው በበኩላቸው፣ በአማራ ሕዝብ ላይ የተዛቡ ትርክቶች መፈጠራቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹አማራን ጨቋኝ፣ በዝባዥ፣ ለዚህች አገር ችግር የመጀመርያ ተጠያቂ አድርጎ የመሳል ነገር በተለያየ መንገድ እስከ ዛሬ ቀጥሏል፤›› ሲሉ ነው አቶ ቹቹ የሚያስረዱት፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሉዓለም ገብረ መድኅን፣  የአማራ ሕዝብ ‹ፀረ ኢስታብሊሽመንት› ወይም አሁን ያለው ብሔር ተኮር ፌዴራላዊ ሥርዓት ጠንቅ አድርጎ የመሳል ዝንባሌ የተፈጠረው በራሱ በፖለቲካው ሥነ ባህሪ እንደሆነ ያስቀምጣሉ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ አማራጭ ፓርቲያዊ ሁነት ላይ ከመመሥረት ይልቅ በሐሰተኛ ታሪክ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ በማኅበረሰቦች ግንኙነትና በአገረ መንግሥት ምሥረታ ሒዳት ላይ ቅራኔ በመፈልፈል እሱን መታገያ ሲያደርግ ኖሯል፡፡ ከ1960ዎቹ ጀምሮ የመጣው ብሔር ተኮር ፖለቲካ በጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ላይ የቆመ በመሆኑ፣ በዳይ ብሎ በፈረጀው አማራ ላይ የአጥቂነት ባህሪ ይታይበታል፡፡ ይህ የውሸት ትርክት ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ በዚህ የተነሳ የኢትዮጵያን ማኅበረ  – ፖለቲካ ችግር ለመፍታትና ሁሉም ብሔረሰቦችን የተሟላ መብት ለማጎናፀፍ የታገለው የአማራ ሕዝብ፣ ‹ራሱ ችግር› ሆኖ እንዲታይ የተሳሳተ ትርክት ተፈጥሮበታል፤›› በማለት ነው አቶ ሙሉዓለም የተናገሩት፡፡

በርካታ የፖለቲካ ሀያሲያን እንደሚናገሩት፣ የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች እኩል ኢትዮጵያን ለማቆምና ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ እንዲቆይ መስዕዋትነት ሲከፍል ኖሯል፡፡ በኢትዮጵያ ለሥር ነቀል የፖለቲካ ለውጦች በተደረጉ ትግሎችም የአማራ ሕዝብ አሻራ ማሳረፉ ጎልቶ ይወሳል፡፡

በኢትዮጵያ ከሌሎች ሕዝቦች ጎን ሆኖ ዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲፈጠር አማራ መታገሉም ተደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡ አሁን ያለውና የብሔር ብሔረሰቦችን መብት አጎናፅፏል የሚባለው የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር አማራ ይብዛም ይነስ አስተዋጽኦ አድርጓል የሚለው ጉዳይ ገዥ ሆኖ ይነገራል፡፡

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት በሰፈነው የፖለቲካ ሥርዓት አማራ መብቶቹንም ሆነ ጥቅሞቹን አጥቶ ነው የኖረው የሚለው ስሞታ በአማራ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ ተደጋግሞ ይደመጣል፡፡ ይህ ከምን የመጣ ነው?  ለሚለው ፖለቲከኞቹ የሚሰጡት ምላሽ በርካታ ነው፡፡

‹‹ሕገ መንግሥቱ ሲቀረፅ የአማራ ሕዝብ ተወካዮች አልነበሩም፤›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ ጋሻው፣ ይህንን ሕገ መንግሥት ተመርኩዞ የተፈጠረው ሥርዓተ መንግሥት ‹‹ለአማራ ሕዝብ መገደል፣ መሳደድ፣ ሀብትና ንብረት መነጠቅ ዋና ምክንያት ሆኗል፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ይህን ሐሳብ በሌላ መንገድ የሚያጠናክሩት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሉዓለም፣ በድኅረ 1983 ዓ.ም. የዘመነ ኢሕአዴግ ፖለቲካ የተፈጠሩ ሁኔታዎች የአማራ ጥያቄዎችም ሆኑ ጥቅሞችና መብቶች ታፍነው እንዲኖሩ ማድረጋቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹በድኅረ 1983 ዓ.ም. የተፈጠረው ሥርዓት የሐሰተኛ ጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክቶች ፈጥሯል፤፡፡ አማራውን ‹ነፍጠኛ›፣ ‹ትምክህተኛ›፣ ‹መጤና ሰፋሪ› የሚል የፍረጃ ስያሜ በመስጠት አማራ መብቱን ከመጠየቅ ታፍኖ እንዲኖር ተደርጓል፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡

‹‹በእነዚህ ዓመታት የአማራውን ጥያቄ ማንሳት የሌሎችን መብት ማፈን ተደርጎ ተወስዶ ነበር፤›› የሚሉት አቶ ሙሉዓለም፣ ይህ ሁኔታ አሁንም ቢሆን መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ አማራው በጥርጣሬ እንዲታይ ጥያቄዎቹም አሁን ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ጠንቅ ሆነው እንዲታዩ በረቀቀ ሁኔታ ሲደረግ መኖሩን ያሰመሩበት ተንታኙ፣ ‹‹አማራውን ፀረ ኢስታብሊሽመንት አድርገው የሚያዩት ወገኖች በበጎች ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን ችሎት የተቀመጡ ተኩላዎች ናቸው፤›› ሲሉም ተችተዋል፡፡

አቶ ሙሉዓለም እንደሚሉት ለእኩልነትና ለነፃነት ሲታገል የኖረው አማራ አሁን  በከባድ ሁኔታ የህልውና አደጋ እንዲጋረጥበት ተደርጓል፡፡ ይህ ደግሞ አማራ ጥያቄ እንዳያነሳ በማሸማቀቅ ወይም በመፈረጅ ሊሳካ የሚችል አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

አማራ ድምፁን እንዳያሰማ ሆን ተብሎ የማሸማቀቅ ዘመቻ ይካሄድበታል ከሚለው ጎን ለጎን፣ አማራ እንደ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ራሱን እንዲያጠናክርና እንዳይደራጅ ዘመቻ ሲካሄድበት ኖሯል የሚለውን ጉዳይ የአማራ ፖለቲካ ልሂቃን በሰፊው ያነሳሉ፡፡ ከአንጋፋው የአማራ ነፃነት ጥያቄ አንሺና የመላው አማራ ድርጅት  (መአሕድ) መሥራች አሥራት ወልደየስ (ፕሮፌሰር) በረቀቀ ሁኔታ ሕይወታቸው እንዲያልፍ መደረግ ጀምሮ፣ የአማራን ጉዳይ ይደመጥ ብለው የጮሁ ድምፆችን በተለያዩ ጊዜያት የማፈንና የማስወገድ ዘመቻ ሲካሄድ መኖሩን በርካቶች ይናገራሉ፡፡

የአማራ መብት ይከበር ያሉ ሁሉ በየጊዜው ዘመቻና ጥቃት ሲደርስባቸው ኖሯል ከሚለው በተጨማሪ፣ አማራው መደራጀትና መጠናከርን ሲከለከል መኖሩን በርካቶች በችግርነት ያነሱታል፡፡ የአማራ ትግል በተደራጀና በተጠናከረ መንገድ እንዳይደረግ ደግሞ ውስጣዊና ውጫዊ የሆኑ እንቅፋቶች መኖራቸውን ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የሚስማሙበት፡፡

አቶ ጋሻው እንደሚናገሩት፣ የአማራ ሕዝብ እንዳይደራጅና እንዳይጠናከር የሚያደርጉ በትንሹ ሦስት እንቅፋቶች አሉ፡፡

‹‹የአማራ ፖለቲካ የአልፎ ሂያጅ ፖለቲካ ሆኗል፡፡ አማርኛ የሚናገር ሁሉ የሚያቦካውና የሚፈተፍተው ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል ማኅበረሰቡን እንዳይደራጅና መሪ እንዳይኖረው በአማራ መሪዎችና በፖለቲካ ተቋማት ላይ ዘመቻ ይካሄዳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአማራ ሕዝብ መደራጀትና መጠናከርን በሥጋትነት የሚያዩ ወገኖች ከውጭ የተለያዩ አሻጥሮችና ዘመቻዎች ያካሂዳሉ፡፡ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የአማራ ማኅበረሰብ መሪ አልባ እንዲሆንና ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ተነጣጥሎ እንዲኖር የሚያደርጉ ወገኖችም አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች በአማራ ሕዝብ ስም እየማሉ አማራን ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በማጋጨት፣ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ፍትሐዊ ሆኖ እንዳይታይ ይሠራሉ፤›› በማለት ነው አቶ ጋሻው በሰፊው ያብራሩት፡፡

ይህን ሐሳብ የበለጠ የሚያጠናክሩት አቶ ሙሉዓለም በበኩላቸው፣ የአማራ ሕዝብ የጥላቻ ፖለቲካ እንዲሆን ከውጭም ሆነ ከውስጥ ያሉ ኃይሎች የተጠናከረ ዘመቻ ሲከፍቱ መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹የአማራ ጠላቶች ልዩ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩት የአማራን ሕዝብ አንድነት ማናጋት ነው፡፡ የአማራን አንድነት ማናጋትና ማዳከም ኢትዮጵያን ለማፍረስና ጥቅማቸውን ለማሳካት አመቺ ነው ብለው ያስባሉ፤›› የሚሉት አቶ ሙሉዓለም፣ ይህ ደግሞ በፈረንጅ ቅኝ ገዥ ኃይሎች የሐሰት ድርሳናት ሲጻፍ የኖረና የአገር ውስጡም እነዚህኑ ሰነዶች ዋቢ በማድረግ የሚያቅደው ጉዳይ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

አቶ ቹቹ በበኩላቸው የአማራ ሕዝብ ጠንካራ አመራር ከፈጠረ የተባለውን ችግር ጨምሮ፣ የሚገጥሙትን ሌሎች እንቅፋቶችም በቀላሉ መሻገር ይችላል የሚለውን ሐሳብ አጉልተው ያነሳሉ፡፡

‹‹አማራ ጠንካራ መሪ ከፈጠረ የአማራ ፖለቲካ የጠራ መስመር ይዞ ራሱን ችሎ ይቆማል፡፡ መተማመንና አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ይፈጥራል፡፡ ይህን መፍጠር ከተቻለ ደግሞ አማራ በክልሉ የተረጋጋ ፖለቲካ መፍጠር ብቻ ሳይሆን፣ በፌዴራል ደረጃ በሚገባው ልክ ተፅዕኖ መፍጠርም ይችላል፤›› በማለት ነው አቶ ቹቹ ያብራሩት፡፡

በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት ተፈጠሩ ሲባሉ የሚሰሙ ችግሮች ከክልሉ አልፎ ለመላ አገሪቱ አደጋ ይጋብዛሉ የሚል ሥጋት ከብዙ ወገኖች ይሰማል፡፡ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ጠፍቷል፣ እንዲሁም ሕገወጥነትና ሥርዓት አልበኝነት ነግሷል የሚለው ስሞታ ጎልቶ ይሰማል፡፡

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአማራ ክልል ካጋጠመው የከፍተኛ አመራሮች ግድያ ጀምሮ እስከ ቅርብ ሰሞኑ የአቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ ድረስ፣ የአማራ ክልል ፖለቲካ በደም መፋሰስ የተሞላ እየሆነ ነው የሚል ሥጋት ይነሳል፡፡ የአማራ ክልል ፖለቲካ በግድያ የሴራ ንድፈ ሐሳቦች ተደጋግሞ ሲነሳ ይሰማል፡፡ የአማራ ክልል ፖለቲካ ከግድያ ሴራዎች በተጨማሪ፣ በየጊዜው በሚቆሰቆሱ ግጭቶችና ቀውሶች እየተሞላ ነው የሚለው ጉዳይም እንዲሁ፡፡  

የአማራ ክልል በቀውስ ውስጥ መዘፈቅ ደግሞ ከክልሉ ውጭ የሚኖረውን የአማራ ማኅበረሰብ ጉዳይ የሚያወሳስብ መሆኑ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ በፌዴራል ደረጃ ሊፈጠር ከሚችለው ቀውስ በተጨማሪም የአማራ ክልል ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚያገናኝ እንደመሆኑ፣ ክልላዊ ቀውሱ ድንበር ተሻግሮ ቀጣናዊ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል የሚል ግምትም እያሳደረ ነው፡፡

ከጎረቤት አገሮች ጋር ብቻም ሳይሆን እንደ ትግራይ ካሉ አጎራባች ክልሎች ጋር ክልሉ የገባበት ውጥረት የአማራን ፖለቲካ የበለጠ እንደሚያወሳስበው ነው የሚገመተው፡፡

የአማራ ፖለቲካ ልሂቃን በተለያዩ አቅጣጫዎች ውጥረትና ግጭት ውስጥ የገባውን የአማራ ክልል ችግር ዳር ቆሞ እያራገበ እሳቱን የሚሞቅ እንጂ፣ ቀረብ ብሎ ለመፍታት የሚሞክር ኃይል አለመታየቱ ሥጋቱን እንዳተለቀው ይናገራሉ፡፡ በአማራ የፖለቲካ ልሂቅ (በውጭም ሆነ በአገር ቤት) ባለው መካከል መደማመጥ መጥፋቱ፣ በመሪና ተመሪው መካከል መግባባት አለመኖሩ፣ በማኅበራዊ አንቂውና ፖለቲከኛው፣ በምሁሩና በወጣቱም ሆነ የማኅበረሰብ ጠበቃ ነኝ በሚለው መካከል መግባባት አለመፈጠሩ ሁሉ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ እንዳይደመጥ እያደረገው መምጣቱን ከባድ አደጋ ሲሉ በርካቶች ያስቀምጡታል፡፡

ፖለቲካ የመደራደርና የሰጥቶ መቀበል ውጤት መሆኑን የሚናገሩት አቶ ጋሻው፣ ‹‹ይህ የሚወሰነው ደግሞ ባለህ የጩኸት ልክ ሳይሆን እጅህ ላይ ባለው ነገርና በመደራደር አቅም ነው፤›› በማለት ያስቀምጡታል፡፡ ለአማራ ሕዝብ የሚጠቅመው፣ ‹‹ጠላት ቀንሶ ወዳጅ የማብዛት ፖለቲካ ነው፤›› ሲሉ ያከሉት አቶ ጋሻው፣ እርስ በርስ መደማመጥን ከመፍጠር በተጨማሪ ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋርም ወዳጅነትና አጋርነት ማጠናከር ጠቃሚ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡

አቶ ሙሉዓለም በበኩላቸው፣ ‹‹የአማራ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኃይሎች ከተሽኮርማሚነት ወጥተው የአማራን ጥያቄ ያለ ይሉኝታ ወደፊት በማምጣት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ማድረግ ካልቻሉ ማኅበረሰቡ የገጠመው የህልውና አደጋ ይከፋል፤›› በማለት ነው የሚናገሩት፡፡

ጊዜ የሚፈጅም ሆነ ከባድ መስዕዋትነት የሚጠይቅ ቢሆንም የአማራ ሕዝብ ጠንካራ መሪ ማፍራቱ እንደማይቀር የሚገምቱት አቶ ቹቹ፣ አማራ በመጨረሻ ተገዶ ወደ አንድነትና ወደ ሰከነ ፖለቲካ እንደሚመጣ ያስረዳሉ፡፡

‹‹አማራ የገጠመው የህልውና አደጋ ገዥ ሆኖ ይወጣል፡፡ ለአማራ ቆመናል የሚሉ ኃይሎችም እንዲሰባሰቡ ያስገድዳል፤›› በማለት ነው አቶ ቹቹ የተናገሩት፡፡

አማራ በአሁኑ ወቅት ከህልውና አደጋ በተጨማሪ ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል፣ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ልሁን፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቼ ይከበሩ፣ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ አማሮች መብትና ጥቅም ይከበር፣ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎቼ ይፈቱ፣ እንዲሁም የተዛቡ ትርክቶች ይታረሙ የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንዳሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ በ12ኛው የብአዴን ድርጅታዊ ጉባዔ ጭምር የፀደቁና መዋቅራዊ በሆነ መንገድ የአማራ ሕዝብ መታገያ አጀንዳዎች ተብለው የተቀመጡ መሆኑን ነው አቶ ቹቹ ያስረዱት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -