Tuesday, May 28, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በታሪክ ውስጥ የመሪው ሚና እጅግ የላቀ ነው

በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ

ግለሰቦች በአንድ አገር ታሪክ ውስጥ  ትልቅ ሥፍራና  ዘመን የማይሽረው  ስም ሊኖራቸው የሚችለው ለመላው ዜጋ ጥቅም፣ ለአገራቸው ክብርና ልዕልና መወገናቸውን የሚያሳይ ተጨባጭ ድርጊት ሲፈጽሙና ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን ሠርተው ሲያልፉ ነው።

ቀዳማዊ ምኒልክ፣ ንጉሥ ላሊበላ፣ አፄ ፋሲል፣ አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስ፣ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞተው እንኳን ታሪክና ትውልድ የማይረሳው፣ በምድሪቱ ገጽ ላይና በየትውልዱ ላይ አትመው የሄዱት መልካምና ክፉ አሻራ አላቸው።

የአገር መሪዎች ለሚመሩት  ሕዝብ  ያበረከቱትን መልካም ሥራና በተቃራኒው ደግሞ የፈጸሙትን እኩይ ተግባር ታሪክ በየጊዜው መዝግቦ ያስቀራል። በግልጽ አስቀምጠው የሄዱት አሻራ ማንነታቸውን ይመሰክራል። መሪዎች ለሚመሩት ሕዝብ፣ ምን እንደቸሩለትና በተቃራኒው የሕዝቡን ባህልና ቋንቋ እንደሽፋን በመጠቀም፣ እንዲሁም በውሸት በተካኑ ካድሬዎቻቸው በመደለል  በስሙ ነግደው እያተረፉ ሆኖም ግን በሰቆቃውና  በጠኔው እየተሳለቁ፣ ግፍ ሲፈጽሙበት እንዲኖሩ፣ አገርን በዝብዘው ባለአገሩን ፍፁም አደህይተው – እነሱ እንደበለፀጉ … ታሪክ ሳያዳላ መዝግቦ ለትውልዱ እነሆ ማለቱ አይቀርም። ታሪክን  የወገኑ ታሪክ ጸሐፊዎች ሲጽፉት ሊያዛቡት ይችላሉ። እውነተኛ ታሪክ ግን በትውልድ ቅብብሎሽ በሰው ልብ ውስጥ ታትሞ፣ ለትውልድ እየተላለፈ  ለዘላለም እንደሚኖር የነገ አፈሩ የዛሬው ትውልድ  መዘንጋት የለበትም።

  ዝንጉ ካልሆንን፣ የሩቁን ትተን የቅርቡን የመለስ አገዛዝን ትሩፋትና ከሞተ በኋላ  የቀጠለውን ውርስ ሥራውን (ሌጋሲውን)  ብናስተውል፣ የምናዝንበት ክፉ ሥራ ከመልካሙ ሥራው በእጅጉ ልቆ በእያንዳንዳችን ልቦና ውስጥ ታትሞ እናገኘዋለን።

መለስ በኢትዮጵያዊው ጥቁር ዓባይ መጠቀም መብታችን እንደሆነ በተግባር ማሳየቱ (የረዳውን የዓለም ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ ማለትም የግብፅን አብዮት፣ የሙስሊሙን ብራዘርሁድ መሪ የሙርሲን አስተዋጽኦና የአሜሪካን የዓረቡ ዓለም የምታራምደውን የሴራ ፖለቲካ አልዘነጋሁም) ከመልካሙ ሥራው በዋነኝነት ቢጠቀስም፣ አገርን በጎሳ ሸንሽኖ የሕዝብ ለሕዝብ ፍቅር እንዲሸረሸር በማድረግ፣ አገር እንድትፈራርስ መንገድ መጥረጉ፣ ‹‹ቤኒሻንጉል ላይ የተጀመረው ታላቅ ግንባታ ፋይዳው ምንድነው?›› የሚያሰኝ ነው (አገርን ከፋፋይ የቋንቋ ፌደራሊዝም ፈጥሮልን በጎሪጥ እንድንተያይ ያደረገን መለስ ዜናዊ ነው)፡፡  ለዚህ ነው የመለስ አገዛዝ ሲነሳ ዘረኝነቱና የጭካኔ ክፉ ድርጊቱ ደምቆ የሚታየን ።

   ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ፣ በቀጠለው ‹‹የውርስ አገዛዝም ›› ሲቀነቀን የነበረው ዋልታ ረገጥ  ብሔርተኝነት ነው። ይህ ዋልታ ጫፍ ላይ የቆመ ፀረ ፍቅር የሆነ፣ ጠባብ  ብሔርተኝነት  ምን ያህል የአንድነትና የኅብረት ጠላት፣ የግጭትና የሰላም ዕጦት መንሥዔ፣ እንዲሁም የደም ነጋዴዎች ማትረፊያ እንደነበረ፣ ገጣሚና ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም፣ ‹‹ከአሜን ባሻገር››  በተሰኘ መጽሐፉ በገጽ 11 ላይ  እንዲህ በማለት ይገልጸዋል።

‹‹በዘመናችን ብሔርተኝነት ማለት፣ ሳይደክሙ፣ የሌሎችን የድካም ውጤት መቀማት መሆኑንን አውቃለሁ። አንድ ሰው በግሉ ስኬት መቀዳጀት ሲያቅተው፣ በጥረታቸው ብልጫ ያስመዘገቡ ግለሰቦችን ስኬት ወደ ብሔር ስኬት ለውጦ ባዶነቱን ለመሙላት ይሞክራል። ሌላውእልም ያለ ፈሪ ሆኖ ሳለ የበላይ ዘር እያለ ይፎክራል። ብብቱ ውስጥ ገብተው ካልደገፉት በቀር አልጋ ላይ መውጣት የማይችለው ሰውዬ፣ አበበ ቢቂላ በተነሳ ቁጥር ‹‹አበበ ኬኛ›› ብሎ ይኩራራል። በላይና አበበ ያስመዘገቡት ድል፣ በላብና በደም የተገኘ የግለሰብ ጥረት ውጤት ነው። ድል በዘር አይተላለፍም። የአባቶች ታላቅነት በዘር ወደ ልጆች የሚተላለፍ ቢሆን ኖሮ ግሪኮች በዛሬÀ የአውሮፓ እግር ሥር እንደ ጉድፍ ወድቀው ባልተገኙ ነበር። ብሔርተኝነት የግለሰብ ጥረትን ሰርቆ የራስን ድክመት  ለመሙላት የሚደረግ መሰሪ እንቅስቃሴ ነው። (ንቃት አልባ መንጋን በስሜታዊነትና በፍላሎት እየኮረኮረ፣ ያለአንዳች አምክንዮ ለስግብግብ ግቡ ለጥፋት የሚያሠልፍ ነው።) ቅንፍ ውስጥ ያለው ሐሳብ የጸሐፊው ነው።

   ‹‹ከውስጥ አዋቂ የሰማሁት አንድ ገጠመኝ ምስክር ይሁነኝ። የአንድ የብሔር ጎበዝ አለቃ የሆነ ሽማግሌ በኢትዮጵያ በአንዱ ክፍል ይኖራል። ሁለት አርብቶ አደር ብሔሮች በግጦሽ ሳር ወይም በውኃ ምክንያት ይጣላሉ። ይኼኔ ይህ ሽማግሌ በዘመናዊ ላንድ ክሩዘር ወደ አዲስ አበባ ተጠርቶ ይመጣና ግጭቱን እንዲያቆም ትዕዛዝ ይተላለፍለታል። ለግጭት መቆጣጠሪያም ተብሎ ዳጎስ ያለ ብር በሰፊው ኪሱ ውስጥ ሻጥ ይደረግለታል። ሽማግሌው ወደ ግጭቱ ቦታ ተመልሶ ከተቃራኒው ወገን የተሠለፉትን አቻ የጎሣ መሪዎች ይጠራና ከተመደበለት ጉርሻ ያካፍላቸዋል። እነሱም በራሳቸው መንገድ የተቀሰቀሰውን ግጭት ያበርዱታል።

  የጎሳ መሪ ሽማግሌዎች ገንዘባቸው ሲያልቅ እንደገና ግጭቱን ይቀሰቅሱታል። ጎበዛዝት ይዘነጣጠላሉ፡፡ ጎጆዎች ይቃጠላሉ፡፡ የአዲስ አበባው መንግሥት ባለሥልጣናት ሽማግሌውን እንደገና ጠርተው ይለማመጡታል። የደም ገንዘብ የለመዱ ሰላምን አርቀው ይቀብሯታል።…››

   በመለስ ዜናዊ የአገዛዝ ዘመንና ከሞተም በኋላ በወራሴ መንግሥቱ በየክልሉ  የቀጠለው፣ እንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪ ድርጊት ነበር ። ይህንን አሳፋሪ  ድርጊትና ሌሎች የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመቃወም፣ ወጣቶች ታላቅ ትግል አድርገው፣ በመስዋዕትነታቸው የዘረኞችን ወንበር ከተቸከለበት እንዲነቀል አድርገዋል።

   እነዚህ የአገራችን ወጣቶች፣ የተደራጀ  ፓርቲ ስለሌላቸው ‹‹ቤተኛ ባይተዋር የነበሩት›› (የመደመር መንገድ ገጽ ሦስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ራሳቸውን እንደገለጹት) ከለውጥ ፈላጊው ወጣት ጋር በህቡዕ በማበር፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ ነፃነት በመወገን፣  የመለስ ዜናዊ ሌጋሲን በታላቅ ጥንቃቄ እንዲቀበር በማድረግ፣ የመሪነት መንበሩ ላይ ‹‹የለውጡ አመራር ሰጪ ነን አገርን ወደ ሁለተናዊ ብልፅግና እናሻግራታለን›› በማለት መቀመጣቸውን አንዘነጋም (የለውጥ ኃይሎቹ  መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. የመሪነት ሥልጣንን እንደያዙ ይታወቃል)፡፡

   የመለስ ዜናዊን የውርስ መንገድ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ሲያስቀጥሉ የነበሩት (ኋላ ላይ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ተብሎ ነበር)  ከአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት ተላቀናል፣ ለውጥን ፈላጊ የውስጥ አርበኞች ነበርን በማለት በአደባባይ ምለውና ተገዝተው፣ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ በማድረጋቸውና የፈጠራቸውን እግዚአብሔርን በበዓለ ሲመታቸው ወቅት  በማክበራቸው ድፍን ኢትዮጵያ ልባዊ ድጋፉን  ከአራት ዓመት በፊት  መስጠቱን አይዘነጋም።

 በኢትጵያ ዘመናዊ ታሪክ፣ ከ1966 ዓ.ም. በኋላ፣ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር  መለስ ዜናዊ፣ በጠብመንጃ  ነው ሥልጣንን የያዝዋት። በሕዝብ ፈቃድና በምርጫ ከጅምሩ ሥልጣንን አልያዙም። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም በጠብመንጃና በካድሬ በተሞላው እስከዛሬም ለሴራ ፖለቲካ ብሎ ቀበሌን ሙጥኝ ብሎ ባለው፣ ገዢ ፓርቲ  ኢሕአዴግ ይሁንታ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት። ሥልጣናቸውን በሕዝባዊው ንቅናቄ አስገዳጅነት በመልቀቃቸው፣ በእሳቸው እግር የተተኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በኢሕአዴግ ውስጥ የተደረገውን የለውጥ ትግል ከጓዶቻቸው ጋር ሆነው ለድል በማብቃታቸው ነው፣ ለመሪነት የበቁት። ወያኔን  እጁን  ጠምዝዞ ከሥልጣን እንዲወርድ ያስገደደውን ሕዝብ ተገን አድርገው ነው፣ የአገር መሪነቱን በአራቱ የኢሕአዴግ ፓርቲዎች  ትንቅንቅ አማካይነት፣ ከፓርቲያቸው ኦሕዴድ እኩል   የብአዴንን ታላቅ ድጋፍ አግኝተው ነው ሥልጣንን ከወያኔ መዳፍ ፈልቅቀው እጃቸው ውስጥ ያስገቡት። …

  በኢትዮጵያ ታሪክ በትክክለኛ፣ ነፃ፣ ተዓማኒ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ምርጫ ወደ መንበሩ ላይ የመጣ መሪና በሕግ የበላይነት  የሚያምን ነፃ የሆነ ጠንካራ ተቋማትን  ያደራጀ መንግሥት እንዳልነበረ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በመደመር መንገድ መጽሐፋቸው ገልጸዋል።

  ይህንን እውነት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ፣ ለኅትመት ባበቁት የመደመር መንገድ መጽሐፋቸው በገጽ 357 ፣   ኢትዮጵያ የተዘፈቀችበትን ችግር ከግሪክ አፈ ታሪክ ‹‹የዳና ኢደስ የሽቁሩ እንሥራን እና የ50 ሴቶችን፣ በሽቁር እንሥራ ውስጥ ዘላለም ዓለማቸውን ውኃ በመገልበጥ እንዲሞሉ የተደረገበትን ትርክት›› በማስቀደም፣ በተቋማት ጥንካሬ የሚያምን   መንግሥት ለመገንባት ቆርጠው መነሳታቸውን  በገደምዳሜ አሳውቀውናል። እጠቅሳለሁ፡-

‹‹… ብልህነት ስለጎደለን በየጊዜው እሷን ይሞላልናል ያልነውን ውኃ ከማመላለስ በዘለለ ቆም ብለን እንስራችን ስለምን አልሞላችም ብለን አልጠየቅንም። የማትሞላበትን ሽንቁሯን አውቆ ሊደፍንላት የሞከረ የለም። 1960ዎቹ አብዮት አካሂደናልእንስራው ውኃ እንዳልተጨመረበት ጎዶሎ ነው። 1997 ምርጫ ደግሞ ይሞላዋል ያልነው ቀርቶ ያለውንም አንጠፍጥፎ  እንስራውን ጭራሽ ባዶ አደረገው። ኢትዮጵያን ለመገንባት፣ ይህችን ለዘመናት የጎደለች እንስራችንን ለመሙላት ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል። ያደረግናቸው ሙከራዎችን ሁሉ ግን እንደ አፈ ታሪኩ ሽንቁር እንስራ መሙላት ሆኖብናል።

‹‹… ሕጋዊነት፣ ሙያተኝነትና ተቋማዊ አሠራር ሥር ይዘው በተቋቋሙባቸው አገሮች፣ የፖለቲካ መዋቅሩ ፣ ሥርዓቱ፣ ደንቡ፣ መአረጉና የመሳሰሉት አሠራሮች ቋሚና እንደ መሬት ዘላቂ ናቸው። የባንዲራቸው ዕድሜ በመቶና በሺ ለሚቆጠር ዓመታት ሊዘልቅ ይችላል። የሕዝብ መዝሙሩ አያሌ ትውልድ አገልግሎ ገና የልጅ፣ ልጅ  ልጆች ሊዘምሩት ይችላሉ። የከተሞች፣ የመንገዶች፣ የትምህርት ቤቶች፣ ስምና ባለቤትነት በመካከለኛው ፍለ ዘመን የጀመረ ሊሆን ይችላል። ባልታሰቡ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሳቢያ የሚለወጡ አንዳንድ ጉዳዮች ሊኖሩ ቢችሉምአብዛኛው ነገር  ትውልድን በቋሚነት እንዲያገለግል ሆኖ የተዘጋጀ ነው። …›› (ዝኒ ከማሁ)

   ከዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕይታ ተነስተን፣ መጽሐፋቸውን በጥሞና አንብበን፣  በጠቅላይ ሚኒስትሩ ህሊና ውስጥ ያለውን የታላቅ አገር የመፍጠር ራዕይ መመልከት እንችላለን። (ሰው መሆናቸውን ግን አንዘንጋ፡፡ ፍፁምነትም ከሰው አይጠበቅም፡፡ …)

     ነፍስ ኄር መስፍን ወልደ ማርያም (ፕሮፊሰር) ‹‹እንዘጭ እንቦጭ›› በማለት ከገለጹት፣ በሕዝብ ስም ከሚነግድ ሥርዓት፣ ወደ ሕዝብ አገልጋይ ሥርዓት  በብልሃት መሻገር እንደሚያስፈልግ ላስታውሳቸው ግን እወዳለሁ።

   ይህንን የምለው፣ እያንዳንዱ ሰው ያለውን የግል ሐሳብ፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ መውደድና መጥላት በማክበር ነው። ህሊናው በመጥፎ ሐሰብ የታጨቀ፣ የሰውነት ትርጉሙ ያልተገለጠለት፣ ሌባና  ስግብግብ በቋንቋ ነጋጅ ፖለቲከኛ፣ ይህ እውነት ከቶም አይገባውም። … ለዚህም ነው፣ ቅኔያዊ ግጥሜን ‹‹እንጉርጉሮ›› በማለት ለጽሑፊ መግቢያ ያደረግኩት፡፡

   ለማንኛውም ከላይ ያነሳኋቸውን ጭብጦች በማስተዋልና በታሪክ ውስጥ የግለሰቦች ሚና ከፍተኛ መሆኑንን በማስተዋል፣  የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአምስት ዓመታት የመሪነት ዕድል ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ  ሲሰጥ ቢያንስ በለውጡ መጀመርያ በ2010 ዓ.ም. አምስት ወራት የተናገሩት ግምት ውስጥ አስገብቶ ነው፡፡ ከመጋቢት መጨረሻ እስከ ነሐሴ ወር ድረስ ማለት ነው።)

  የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ሐሳብ መለዋወጥ ከምን የተነሳ እንደሆን በበኩሌ ግልጽ አልሆነልኝም። ምናልባት ዛሬ ለሆዳቸው ብቻ በሚያስቡ እጅግ ስግብግብ በሆኑ አቻ ጓዶቻቸው ሴራ ተጠልፈው ሊሆን ይችላል። አልያም የማኬቬሊን ምክር የወቅቱን የፖለቲካ ትኩሳት በመለካት  ሴጣንም መልዓክም የመሆን ሚናን እየተጫወቱ ሊሆን ይችላል፡፡ የእያንዳንዳችን ህሊና ለሌለው ከአድማስ ባሻገር በመሆኑ ሰዎች በተፈጥሯቸው አወዛጋቢ ናቸው።

በሕይወት የሌሉ የዓለም መሪዎችን ታሪክ ስታነቡ እያንዳንዱ መሪ የሚያወዛግብ ታሪክ እንዳለው ትገነዘባላችሁ። ይህ የታወቀ ቢሆንም በእኛ አገር ዛሬ የደቦ የመንግሥት አመራር ብቅ እያለ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ሦስት የቋንቋ ነገሥታት በደቦ ሲመሯትና ሲንጧት እያስተዋልን ነው። አገር በደቦና በቲፎዞ ብዛት  ሳይሆን  በታላቅ ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ችሎታ፣ ክህሎትና ተሰጥኦ ባላቸው ግለሰቦች ስትመራ ነው፣ ብልፅግናዋ እውን የሚሆነው። ይህንን እውነት ከቻይና፣ ከጃፓን፣ ከሩሲያ … ከአውሮፓና አሜሪካ ብልፅግና ማረጋገጥ ይቻላል።

   የስታሊን አገርን ታላቅ የማድረግ ህልም የዛሬዎቹ ሶቬቶች አይረሱትም። የጆርጅ ዋሽንግተንን የነፃነት ትግልና የአሜሪካ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንትነቱን አሜሪካውያን ለዘላለም ያስታውሱታል። የሮማን ኢምፓየር ታላቅነትና ጁሊየስ ሲዛርን ማን ይረሳል። የግሪክ ጥበበኛ መሪዎችንና ንጉሥ ላሊበላንም እዚህ ላይ መጥቀሱ መልካም ነው። ደሞም ህንድ እንደ መሀተመ ጋንዲ ዓይነት መሪ፣ አፍሪካ ደግሞ  እንደ ኔልሰን ማንዴላ ዓይነት ይቅር ባይ ፃድቅ ሰው እንደነበራት አስታውሱ።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles