በዓለም በተለያዩ አገሮች የሚዘጋጁ ኮንፈረንሶች፣ ዓውደ ርዕዮችና ፌስቲቫሎች አገሮች ራሳቸውን ለማስተዋወቅና አገልግሎቶቻቸውን ለመሸጥ የሚጠቀሙባቸው ዓይነተኛ መድረኮች ናቸው፡፡
እንዲህ ዓይነቱን መድረክ መጠቀም የአንድን አገር ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባለፈ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለመፍጠርና ለመታወቅ ዕድል የሚሰጥ ቢሆንም፣ በተለይ ታዳጊ አገሮች ዕድሉን ብዙም ሲጠቀሙበት አይስተዋሉም፡፡ ኢትዮጵያም ከእነዚሁ ልትጠቀስ ትችላለች፡፡
ኢትዮጵያ የቱሪዝምና የጉዞ ኢንዱስትሪዋን ይበልጥ ለማስተዋወቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ መድረኮች እምብዛም አለመገኘቷ፣ በዘርፉ በቅጡ እንዳትታወቅና ካላት የቱሪዝም ሀብት በብዛት እንዳትጠቀም ማድረጉን የፌስ ኦፍ ኢትዮጵያ ካልቸራል ኢቨንት ኦርጋናይዘርና ሥራ አስኪያጅ ደረጄ በለጠ ይናገራሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ ከዚህ ቀደም አሜሪካ፣ ደቡብ አፍሪካና በሌሎች አገሮች በተዘጋጁ የተለያዩ መድረኮች እምብዛም የኢትዮጵያን መንግሥት ወክሎ በቱሪዝሙ ዘርፍ የሚያስተዋውቅ አለመኖሩን መታዘብ ችለዋል፡፡ በእነዚህና በሌሎች መድረኮች መሳተፍ አለመቻሏም ኢትዮጵያን ካሏት የቱሪዝም ሀብቶች በብዛት እንዳትጠቀም እያደረገ ነው፡፡
መንግሥት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪዝም ሀብት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ መድረኮች ተጠቅሞ ለማስተዋወቅ አቅሙ ባይኖረው እንኳን፣ ፍላጎትና አቅሙ ያላቸውና በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሳተፉ በኤምባሲና በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ድጋፍ እንዲያገኙ በማበረታታት ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባዋል ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ባህሏንና የቱሪዝም ሀብቷን ልታስተዋውቅባቸው ከምትችልባቸው መድረኮች ኦል አፍሪካን ፌስቲቫል፣ ዓረቢያን ትራቭል ማርኬትና ሌሎችም የሚገኙ ሲሆን፣ በእነዚህ እምብዛም ስትሳተፍ አትታይም፡፡ ሰሞኑን በዱባይ የተከናወነው የቱሪዝምና የጉዞ ሀብትን ማስተዋወቂያና የንግድ ትስስር መፍጠሪያ መድረክም ኢትዮጵያ በመንግሥትና በግል ደረጃ ካልተማከለችባቸው መድረኮች አንዱ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ባህሏንና የቱሪስት መስህቧን ብታስተዋውቅበት በርካታ ቱሪስቶችን ለመሳብ ያስችላት በነበረውና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ዱባይ ከሚያዝያ 23 እስከ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ለ30ኛ ጊዜ በተከናወነው የዓረቢያን ትራቭል ማርኬት (ኤቲኤ) አለመሳተፏ፣ ለምን? የሚል ጥያቄ እንዳስነሳባቸው በሥፍራው ሲጎበኙ ያገኘናቸው ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያን የሚያውቁ የውጭ አገር ዜጎች ነግረውናል፡፡
በየዓመቱ በዱባይ የሚከናወነውን የጉዞና የቱሪዝም ንግድ መለዋወጫ መድረክና ኤግዚቢሽን ላለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት መጎብኘታቸውን የነገሩን የኤግዚቢሽኑ ጎብኚ፣ የኢትዮጵያን ስታንድ (ማስተዋወቂያ ሥፍራ) አለማየታቸው እንደሚቆጫቸው ነግረውናል፡፡
የዓረቢያን ትራቭል ማርኬት ኤግዚቢሽንና የንግድ ትስስር መፍጠሪያ መድረክ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ በቱሪዝምና ጉዞ የሚሳተፉ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ነው፡፡
ዘንድሮ በተካሄደው መድረክም ከአፍሪካ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከኤዥና ከሌሎችም አኅጉራት የመጡ ከ150 በላይ አገሮች ተሳትፈዋል፡፡ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ከ2,000 በላይ በቱሪዝምና ጉዞ ላይ የሚሠሩ ተቋማትም አገልግሎቶቻቸውን ያስተዋወቁ ሲሆን፣ ከ40 ሺሕ በላይ ጎብኚዎች እንደተሳተፉም የዱባይ ኢኮኖሚና ቱሪዝም ዲፓርትመንት አስታውቋል፡፡
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በአፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በናይጄሪያ፣ በኬንያና በጋና በቱሪዝምና በጉዞ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ዘርፍ እየተሰማራች መሆኑንም ዲፓርትመንቱ ጠቁሟል፡፡
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በሆቴል፣ በሪዞርትና በመሠረተ ልማት በአፍሪካ ኢንቨስት እያደረገች መሆኑን፣ በአፍሪካ የሚደረጉ ዋና ሁነቶችን ስፖንሰር በማድረግ እንደምትሠራና ራሷን እንደምታስተዋውቅም ጠቁሟል፡፡
በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የዱባይ ኮሌጅ ኦፍ ቱሪዝም ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ጋር በመተባበር ትምህርትና ሥልጠና የሚሰጥ ሲሆን፣ በእንዲህ ዓይነት መድረክ መገኘት ብዙ ዕድሎችን ወደ አገር ለማስገባት የሚያስችል ነው፡፡
በኢትዮጵያ በ13ቱም ወራት የተለያዩ የቱሪስት መስህብ የሚሆኑ ሁነቶች መኖራቸውን፣ እነዚህን አቀናጅቶ በዓለም አቀፍ መድረኮች በማስተዋወቅ ከቱሪዝሙ ብቻ ከየትኛውም የሀብት ምንጭ የተሻለ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል አቶ ደረጀ ይናገራሉ፡፡
በዓረቢያን ትራቭል ማርኬት የራሳቸው ማስተዋወቂያ መድረክ (ስታንድ) ኖሯቸው ሳይሆን፣ ተሳታፊ በመሆን ከኢትዮጵያ ወደ ዱባይ ያቀኑት የግራንድ ትራቭል ባለቤትና መሥራች አቶ መሐመድ ወርቁ እንዳሉት፣ ኤግዚቢሽኑ ስለተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከሚያውቁት በላይ እንዲያውቁና ባወቁት ልክ ዱባይን እንዲያስተዋውቁ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡
ለሠርግ፣ ለጫጉላ ሽርሽርና ከአገር ወጣ ብሎ ስለአዲስ የንግድ ሐሳብ ለመነጋገር የሚፈልጉ ግለሰቦች፣ ቤተሰቦችና ድርጅቶች ዱባይ መጥተው የት ቢያርፉ ውጤታማ ይሆናሉ የሚለውን ለማማከር መነሻ ሐሳብ እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
በጉዞ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቱሪዝም እንዲበረታታ የሚያስችል መንገድ መኖሩን ከዱባይ ልምድ መቅሰማቸውን፣ ኢትዮጵያም የጉዞ ኢንዱስትሪዋን ከቱሪዝም ጋር አስተሳስራ ከሌላው ዓለም ቱሪስቶችን ለመሳብ የምትማርበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከፍተኛ ሙቀት እያለ በርካታ ቱሪስቶች መሳብ ተችሏል ያሉት አቶ መሐመድ፣ በኢትዮጵያ በጣም ተስማሚ የአየር ንብረት እያለ ምን መሥራት ይቻላል የሚለው ሊሠራበት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአብዛኛው የምትጠቀመው በኮንፍረንስ ቱሪዝም መሆኑን፣ ታሪካዊ ቦታዎችን በደንብ ማስተዋወቅ ቢቻልና መዝናኛ ቦታዎች ቢስፋፉ የቱሪዝም ዘርፉ የበለጠ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበትና ኢኮኖሚው የሚያድግበት እንደሚሆን አቶ መሐመድ ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ በዱባይ በተካሄደው የዓረቢያን ትራቭል ማርኬት ከአፍሪካ ከተሳተፉ አገሮች ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ግብፅ፣ ሩዋንዳ፣ ዛምቢያ፣ ዙምባብዌና ሲሸልስ ይገኙበታል፡፡
በኤግዚቢሽኑ ማጠናቀቂያ ዱባይ ‹‹ቤስት ስታንድ ፎር ዱይንግ ቢዝነስ›› ሽልማት አግኝታለች፡፡