Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊኢትዮጵያ መድኃኒት ከተለማመደ ቲቢ ጫና ተርታ ወጣች

ኢትዮጵያ መድኃኒት ከተለማመደ ቲቢ ጫና ተርታ ወጣች

ቀን:

በዓለም ውስጥ መድኃኒት የተለማመደ ቲቢ ጫና ባለባቸው 30 አገሮች ተርታ ተሠልፋ የነበረችው ኢትዮጵያ ከተርታው ለመውጣት በቅታለች፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ተርታ ልትወጣ የቻለችው ባለፈው አሠርት በዚሁ በሽታ ሳቢያ ይከሰት የነበረውን የሞት መጠን በዓመት ወደ ስድስት በመቶ፣ በበሽታው የሚያዘውን ደግሞ አራት በመቶ ዝቅ በማለቱ ነው፡፡

ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት መስጠት፣ የጤና ተቋማት መስፋፋት፣ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች በቲቢ በሽታ ላይ ርብርብ የሚያደርጉበት መደላድል መመቻቸትና በየደረጃው የሚገኙ የጤና ተቋማት አመራሮች የቲቢ በሽታን ለመከላከል ያሳዩት ቁርጠኝነት ኢትዮጵያ ትገኝበት ከነበረበት ተርታ ለመውጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

የአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ከሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት በተናበበና በተቀናጀ መልኩ የሚያካሂዱት የክሊኒካል ላቦራቶሪ ሥራ ውጤታማ መሆንና የአጋር አካላት ድጋፍና ዕገዛ ከተጠቀሰው ተርታ የመውጣትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡

- Advertisement -

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አፈወርቅ ካሱ (ፕሮፌሰር) እንደገለጹት፣ መድኃኒት የተለማመደ ቲቢ የዘመኑ ትልቅና ገዳይ በሽታ ነው፡፡ በዓለም ውስጥ በዓመት ከአሥር ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በዚህ በሽታ ይያዛሉ፣ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደገሞ ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ፡፡

በዚህም የተነሳ የዓለም ጤና ድርጅት በሽታውን እ.ኤ.አ. በ2035 ከዓለም ለማጥፋት የሚያስችል ስትራቴጂ ማውጣቱን ገልጸው፣ አገሮች በወረዱላቸው ስትራቴጂ መሠረት ፕሮግራሞቻቸውን እየቀረጹና እያደራጁ የሕክምና፣ የምርምርና የመከላከል ሥራዎችን በመከናወን ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያም አገራዊ የመከላከል ስትራቴጂ እንዳዘጋጀች ይህንንም ከዓለም አቀፉ ድርጅት ስትራቴጂ ጋር በማጣመር ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና በተዋረድ ያሉት የጤና ተቋማት እየተናበቡ እንዲንቀሳቀሱ የሚደረግ አካሄድ እንዳመቻቸች ነው ያመለከቱት፡፡

የዘመኑ የምርመራ፣ የሕክምና፣ የመከላከልና የፈጠራ ሥራዎችንም ማዳበር ይህንን አስከፊ በሽታ ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ብሎም ለማጥፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ከሌሎች አጋር ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር በቅርቡ ያካሄደው የክሊኒካል ሙከራ ሥራ ‹‹ላንሴት›› በሚባል ትልቅ የዓለም ምርምር ጆርናል ላይ ታትሞ መውጣቱን፣ ወዲያው በሳምንቱ የዓለም ጤና ድርጅት መድኃኒት የተላመደ የቲቢ ሕክምና ትኩረት የዓለም ሰነድ አድርጎ ለዓለም አገሮች ማሠራጨቱን ነው የተናገሩት፡፡

ይህም የሚያሳየው ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ የምርምር ተቋማት የሚሠሩትና በዚህም የደረሱበት ውጤት ለአገር ብቻ ሳይሆን ለዓለም መፍትሔ እየሆነ መምጣቱን እንደሚያመለክት ከዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የዛሬ 22 ዓመት የቲቢ አማካሪ ኮሚቴ አቋቁሞ በዓመት አንድ ጊዜ የዓለም የቲቢ ቀን በሚከበርበት ወቅት የቲቢ ፕሮግራም ኃላፊዎች፣ በቲቢ ዙሪያ የሚሠሩ ተመራማሪዎች፣ አገርንም ተቋማትን የሚደግፉ አጋር አካላት ያሉበትን የምክክር መድረክ በማዘጋጀት የተሞክሮና የልምድ ልውውጥ እንዲዳብር ማድረጉን ነው የተናገሩት፡፡

‹‹ለአሥራ ሰባት ጊዜ ከተካሄደው ከዚህ ዓይነቱ የምክክር መድረክ የተገኘው ትምህርት ቲቢ ፈቃድ ሳይጠይቅ ድንበር የሚሻገር በሽታ መሆኑ ተደርሶበታል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በዙሪያዋ በርካታ ጎረቤቶች ያሏት አገር ናት፡፡ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ የቲቢ ፕሮግራም ከጎረቤቶቿ የተናበበ መሆን ይገባዋል፤›› ብለዋል፡፡

የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ ክልላዊ ቲቢ ጥምረት ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው የመጀመርያ ጉባዔ ዋና ዳይሬክተር አፈወርቅ ካሱ (ፕሮፌሰር) እንዳብራሩት፣ የጥምረቱ አባል ከሆነው አጋር አንድ ዜጋ የቲቢ መድኃኒት ጀምሮ ወደ ሌላው የጎረቤት አገር ቢሄድ ምንም ዓይነት እክል ሳይገጥመው በሄደበት አገር ሕክምናውን ማግኘት ይችላል፡፡

ለዚህም ዕውን መሆን የተጀመረውን ጥምረት ማጠናከርና የጥምረቱ አባል አገሮች የሕክምና ፕሮቶኮል የተናበበ መሆን እንደሚገባው ነው ያመለከቱት፡፡ ከዚህም ሌላ ጥምረቱ ዘላቂ ለውጥ ማምጣት እንዲችል፣ የአንድን አገር ተሞክሮ ወደ ሌላው አገር ማሻገርና የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው ስትራቴጂ መሠረት ቲቢን ለመቆጣጠርና ለማጥፋት እየተካሄደ ባለው ሥራ ሁሉም ባለሙያ የራሱን አሻራ ማኖር እንዳለበት ከዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ በጤና ዙርያ የምርምር ሥራ ከሚያከናውኑ መንግሥታዊ ተቋማት መካከል አንድ የሆነው የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የተቋቋመው ከ53 ዓመት በፊት ሲሆን፣ የተቋቋመውም በሥጋ ደዌ በሽታ ዙሪያ ምርምር ለማካሄድ እንደነበር፣ አሁን ግን ከሥጋ ደዌ በሽታ አልፎ በሌሎች በርካታ በሆኑ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ዙሪያ ጥናትና ምርመራ በማካሄድ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የግሎባል ፈንድ አስተባባሪና የጤና ሚኒስትር ደኤታ ዋና አማካሪ አበራ በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ባለፉት አሥር እና ሠላሳ ዓመታት ውስጥ በተካሄደው ቅንጅታዊ አሠራር የቲቢ በሽተኞች ቁጥር በመቀነስ ብዙዎችን ከሞት ማትረፍ ተችሏል ብለዋል፡፡

መድኃኒት የተላመደ ቲቢ ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆኑ መጠን፣ ከሕክምናው ባሻገር ብቸኛው መፍትሔ ጥምረት ፈጥሮ በጋራ መንቀሰቀስ መሆኑንና ይህም እየተገበረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጥምረቱ አባል የሆኑትም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን መሆናቸውን ዋና አማካሪው ገልጸው፣ ከእነዚህም አገሮች የተውጣጡ 22 የቲቢ ፕሮግራም መሪዎች በጉባዔው መሳተፋቸውን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...