Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹‹ሆድ ለባሰው…!››

ሰላም! ሰላም! እንዴት ነው ክራሞታችሁ? ክራሞታችሁ ስል በጋራ እየሆነልንና እየሆነብን ያለውን ስለማውቅ፣ በገዛ ኑሮዋችሁና ሕይወታችሁ ውስጥ ያለውን ነው የምጠይቃችሁ፡፡ አንዱ በቀደም ዕለት ጣደፍ ጣደፍ እያለ ሲራመድ ሌላው ደግሞ ጠባቡን መንገድ ዘግቶበት ተገትሯል፡፡ ‹‹አቶ እከሌ እባክህ አንዴ ታሳልፈኝ?›› ይለዋል፡፡ ያኛው ደግሞ፣ ‹‹ለማያልፍለት ኑሮ ከምትጣደፍ ለምን እንደ እኔ ተገትረህ ሰላማዊ ሠልፍ አስመስለን ብሶታችንን አንገልጽም?›› ብሎት እርፍ፡፡ እንዲህ ዓይነት ክራሞትም አለ ለማለት ያህል ነው፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ በወዲያኛው ሳምንት ሜይዴይን አስመልክቶ፣ በሰላማዊ ሠልፍ ለመንግሥት አንገብጋቢ ጥያቄዎችን አቀርባለሁ ያለው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ሠልፍ በተከለከለ ማግሥት ነው እንግዲህ ሰውዬው የመንደር ጠባብ መንገድ ዘግቶ የቆመው፡፡ ይህንን ድንገቴ ነገር የነገርኩት ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደግሞ፣ ‹‹ሰፊውን ጎዳና ስትከለከል በጠባቡ ጎዳና ድምፅህን ለማሰማት መፍጨርጨርህ አይቀርም…›› እያለ ነገር ጣል ሲያደርግብኝ፣ እንዴት ነው ነገሩ ብሶት ያለው ሁሉም ቦታ ነው ወይ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ አንዱን እያነሳሁ ሌላውን እየጣልኩ፣ የሩቁን ከቅርቡ እያመሰካከርኩና ያለንበትን አጠቃላይ ሁኔታ እያነፃፀርኩ ባስበው ደከመኝ፡፡ ያደክማል!

የእኛ ድካምማ የተለየ እየሆነ ነው። እኔማ አንዳንዴ አጉል ስጠራጠር ምን እንደማስብ ልንገራችሁ? የዛሬን አያድርገውና ቀደም ባሉት ጊዜያት አገር በቀል ነገር እንደምንወደው ምንም ነገር አንወድም ነበር። ታዲያ አሁን ይኼው ስሜት ተመልሶ መጥቶ አቴናዎች ከክርስቶስ ልደት በፊት ያስተዋወቁትን ዴሞክራሲ ሽረን የራሳችንን ‹‹ዴሞክራሲ›› እየፈጠርን ይሆን ብዬ አስባለሁ። እውነቴን እኮ ነው፡፡ ነገር እንጂ ቴክኖሎጂ መፍጠር ስላልፈጠረብን ከዚህ ሌላ ምን ማሰብ ነበረብኝ? ይኼው ታዲያ እኛም በብሶት መብሰልሰል አይታክተን፣ እነሱም ማነፍነፍ አይታክታቸው ቴአትር ቤት ልንገባ ብንሠለፍም የሠልፍ ፈቃድ መጠየቃችን አይቀርም እላለሁ። ‹‹አንተ ልጅ አንበርብር፣ ብሶታችሁ እኮ የፖለቲካውን ማገር ሳይታከክ ማኅበራዊ መስሎ ቢቀርብ ሰሚ አታጡም ነበር…›› የሚሉኝ አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው። ባሻዬ እኮ የገባቸው ናቸው። ‹‹እውነቴን ነው አይደል? እንኳንስ መንግሥት ከስንቱ ጋር የሚነታረከው ቀርቶ ግለሰብ ሳይቀር ባለችው ነገር ስትመጣበት አይመቸውም፡፡ መንግሥት ትንሽ ብሶት ከፖለቲካ ጋር ለዋውሰህ ከምታቀርብለት፣ ትልቁን ብሶት አስተዛዝነህ እንደ ተራ ጉዳይ ስትደቅንለት በፈገግታ ያስተናግድሃል፡፡ ምክንያቱ ምን መሰለህ አቀራረብ ነው፡፡ ከአቀራረብ ችግር እኮ ነው ሆድና ጀርባ መሆን የበዛው…›› ሲሉ ባሻዬ እሳቸው ብቻ የገባቸው ይመስሉ ነበር፡፡ እውነቴን ነው!

መቼም ይህች አገር የማትታወቅበት ነገር የለም አይደል? አብዛኛው ታዲያ ስለራሳችን ያመንናቸው ውሸቶች መሆናቸው በጣም ያሳፍረኛል። ይሁን ግድ የለም ወደ እሱ አይደለም ልመጣ የፈለግኩት። እኛን ጨምሮ በአጠቃላይ የታዳጊ አገሮች ‘ብራንድ’ ሊባል ስለሚቻለው ‘ክልክል ነው!’ ስለሚባለው ችግራችን ላጫውታችሁ ነው። ‘ግድግዳው በሙሉ ተሞልቶ በክልክል፣ የቱ ነው ትክክል?’ ያለው ገጣሚ ትዝ ካላችሁ። እኛ እንደሆነ ልክ ልካችንን የሚነግረንን እያወቅነው ባለማወቅ፣ እያስታወስነው ባለማስታወስ የተካንን ነን። የዛሬ አራት ወር ገደማ ምን ሆነ መሰላችሁ? አንድ በሰዓት ቀልድ የማያውቅ ሀብታም ደንበኛዬ፣ እንኳን ለባለቤቱ ለተመልካች የሚያሳሳ ቪላ ሊሸጥ ፈልጎ ወደ እሱ እጣደፋለሁ። ታዲያ ሀብታም ያለ ቦሌ ከባህር የወጣ ዓሳ ይመስል ሌላ ሠፈር እንገናኝ ብሎ እንደማይቀጥራችሁ፣ ከእኔ የበለጠ ምስክር ማቅረብ የምትችሉ አይመስለኝም። በእግሬ ሱክ ሱክ እያልኩ እየተጓዝኩ ሳለሁ ድንገት መንገድ ተዘጋ ተባለ። የመኪናውን መስሏችሁ ነው? እንዲያማ ቢሆን ምን ይኼን ሁሉ አስወጋኝ። እኛን እግረኞቹን ፊታችሁን ዙሩ ወደ ውስጥ ግቡ እያሉ ያካልቡን ጀመር። ክቡሩ የሰው ልጅ እንደ መንጋ ምናምን ምናምኑ ሥር ተሰግስጎ ቁልጭ ቁልጭ ሲል በፈርዖን ዘመን ያለን መሰለኝ። ‹‹የዘንድሮው ደግሞ የተለየ ነው። አብዛኞቹ  መሪዎች ኑሯቸው የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነውና ዴሞክራሲ ወደኋላ መራመድ አለበት?›› ይላል ከተሰበሰብነው አንዱ። ሌላው ደግሞ ‘መቆም ክልክል ነው!’ የሚል ጽሑፍ ተደግፈን መቆማችንን አስተውሎ፣ ‹‹አንደኛውን ለምን መኖር ክልክል ነው አይሉንም?›› እያለ ብቻውን ይስቃል። ‹‹እኔስ?›› አለች አንዷ ኮስተር ብላ። ‹‹እኔስ ሰሞኑን የባለመኪኖችን እንግልትና ‘መንገድ ሊዘጋ ነው’ በተባለ ቁጥር ያለባቸውን ወከባ እያየሁ እንኳንም መኪና የለኝ እያልኩ ስፅናና ነበር። እና አሁን እግሬን ማማረር አለብኝ ማለት ነው?›› ብላ እጅግ በተደነቀ መንፈስ ታወራለች። ሌላው ደግሞ፣ ‹‹እኔን የገረመኝ ይኼን በመሰለ መንገድ የወጣው የአይቻልም ሕግ ብዛት ነው። ተመልከቱ ‘መዞር አይቻልም!’፣ ‘መቆም አይቻልም!›› እያሉ የሚከለክሉ ምልክቶችን ቆጥሮ ያስቆጥራል። እኔ አሥር ጊዜ ሰዓቴን አያለሁ። የቀጠረኝ ሀብታም ጥሎኝ ቢሄድስ? የዘንድሮ ሀብታም መቼ ሰው ያፍራል ብላችሁ ነው? ዋናው ጉዳዩ ገንዘብ ላይ ነው!

በየሄድንበት መላመድ እንችልበታለን። በተለይ ሐሜትና አሉባልታ ከሆነ ፍቅራችን ይደራል። ባለሥልጣኖቻችን ወይ አያልፉ ወይ አያሳልፉ ተገትረን ቆመን ልናድር መሆናችንን የተገነዘብኩት የሚባለውን ሰምቼ ስጨርስ ነው። ‹‹እኔ የማውቀው ሕግ የሰው ልጅ አገልጋይና አቅጣጫ ጠቋሚ ሆኖ ነው እንጂ አትለፍ፣ አትቀመጥ፣ አትቁም እያለ የነፃነት ፀር ሲሆን አይደለም…›› ብሎ ሳይጨርስ አንዱ ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ሁላችንም የምናውቀው እንዲያ ነው ወንድሜ። ይልቅ ሊገርምህ የሚገባው ስንት ከሕግ በላይ መኖር የለመደ ባለበት አገር፣ ተራው ሰው ላይ ጥቃቅንና አነስተኛው ሕግ በርትቶ መተግበሩ ነው። ‘ምንድነው ስትል?’ ቢሮክራሲ ትባላለህ። ይሠሩልናል ብለን የሾምናቸው ሹማምንት እኛ ከኑሮ ጋር የሞት የሽረት ትግል ላይ እንዳለን እያዩ፣ እነሱ የሞቀ ቤት ተቀምጠው ስለሕግ የበላይነት ለማስተማር ይዳፈሩናል…›› ብሎ ይናገራል። የሕዝብ ብሶትና የሐምሌ ዝናብ አንዴ ከጀመረ ማባሪያ የለውም አይደል? በቃ ትንሹ ትልቁ የመጣለትን ሳያረቅ መናገሩን ተያያዘው። ታዲያ ወዳጆቼ መርጦ መስማትን የመሰለ ምንም ነገር የለም፡፡ መስማት ብቻ ሳይሆን መዋልንም ይጨምራል። ‹‹አደራ ‘ብላክ ሊስት’ ውስጥ የገባው በርከት ስላለ የምትውላቸውን ሰዎችም እየመረጥክ…›› ያለችኝ ውዷ ማንጠግቦሽ ናት። ጦሱ እንደ ውርስ ከአንዱ ላንዱ ሲሆን እያየች እንዴት አታስጠነቅቀኝ? ለማንኛውም መንገዱ ሲከፈትና ከታጎርንበት ስንወጣ የመሰነባበቻ ነው መሰል አንዱ፣ ‹‹ተመሥገን! እንኳን ‘ኦክስጅን’ በአንተ እጅ ሆነ…›› እያለ ሽቅብ ሰማይ ሰማይ እያየ ብሶታችንን ቆሰቆሰው። ‘ሕግ የሕዝብ አገልጋይ እንጂ ቀንበር መሆኑ ይብቃ!’ የሚል ጥቅስ በአዲሱ አውራ ጎዳና ላይ መጻፍ አማረኝ፡፡ አምሮት እንዳይገልህ እንዳትሉኝ አደራ!   

ቀጠሮዬ ቦታ ስደርስ እንደገመትኩት ሰውዬው ጥሎኝ አልሄደም። እንዲህ ያለ የሀብታም ትዕግሥት ካየሁ ዘመን ስለሌለኝ ወይም ዓይቼ ስለማላውቅ ሊሆን ይችላል፣ በመገረም የሚለዋወጠውን ገጽታዬን መቆጣጠር አቃተኝ። ለነገሩ ትዕግሥት በማጣት ሀብታምና ደሃን መለየት አቅቷል፡፡ ‘ዓባይን በአንድ ቀን ካልሆነ’ ባዮችን ስታዩ፣ ‘ሱሪ ባንገት ካላጠለቅን’ ባዮች መስከን አቅቷቸው በሙስና ሐይቅ በአደባባይ ሲንቦጫረቁ ስታዩ ጉድ ማለት የልባችሁን አያደርስላችሁም። ምሁሩ የባሻዬ ልጅማ ይኼንን ነገር ባነሳሁበት ቁጥር፣ ‹‹ሮም በአንድ ቀን የተገነባች ይመስል ሁሉንም ነገር ዛሬ ማለታችን ይገርማል። ነገ ዓይንህ ይበራልሃል ሲባል ዛሬን እንዴት አድሬ እንዳለው ዓይነ ሥውር መሆናችን ያሳዝነኛል…›› ይለኝና ይተክዛል። የሚሸጠው ቪላ ባለቤት፣ ‹‹እኔ ምልህ?›› ሲለኝ ጭልጥ ካልኩበት የልቤ ወግ ነቃሁ። ‹‹…አደራህን እንደ ምንም ብለህ ነገ ወይ ዛሬ ሳትል ገዥ ፈልገህ ማግኘት አለብህ…›› ብሎኝ ዙሪያውን ገልመጥ ገልመጥ እያደረገ ካበጠረ በኋላ፣ ‹‹የሰሞኑን አየር መቼም አልነግርህም። በጣም ሳትሞቅ በጣምም ሳትበርድ ለብ ማለቱ ሳይሻል አይቀርም ብዬ ነው ያን የመሰለ  ቪላ ልሸጥ የተነሳሁት…›› ሲለኝ ‘ፈሪን ከውኃ ውስጥ ያልበዋል በማለት ባሻዬ የሚተርቱት ተረት መጣብኝ። ታዲያ እኔም፣ ‹‹ራስህን ራስህ እያወቅክ ሌላ ነገር ካልሠራህ ለምን ቤትህን ትሸጣለህ?›› አልኩት ኮስተር ብዬ። ‹‹አይታወቅም እባክህ። የዘንድሮ ዱብ ዕዳ መምጫው ምን ይታወቃል?›› ሲለኝ ወዲያው ወቅት እየተከተለ የሚፈጠረው መደናገርና መደናገጥ ከማናውቀው ነገር ጋር ትግል እንደተጀመረ ውስጤን ይሰማኝ ጀመረ። አድርጎት ነው አትሉም!

ወደ መሰነባበቻን ሰዓት ላይ ነን። የቪላውን አሪፍነት እያወራሁ የገዥ ያለህ ስል አንድ ወዳጄ፣ ‹‹አንበርብር ከበርቴው ሁሉ ባንክ ያለ ብሬን ምን ላድርገው እያለ በሚባዝንበት ጊዜ፣ ገና ከአፍህ ከመውጣቱ በሺዎች ባትከበብ ምን አለ በለኝ…›› ሲለኝ፣ ተሸቀዳድሞ የተገኘውን እየገዙ ንብረት የሚይዙ እንደበዙ በዙሪያዬ ወሬው ደራ፡፡ ወዳጄ እውነቱን ሳይሆን አይቀርም አልኩላችሁና ቁጭ ብዬ መጠበቅ ጀመርኩ። ከአፍታ በኋላ የድለላ ስልኬ በገዥዎች ተጨናነቀች። እኔና ሻጭ የመጡትን አሠልፈን ከጨረታ የማይተናነስ ሒደት አስጀመርን፡፡ በመጨረሻም ሻጭ ከሚፈልገው በላይ ሲሳይ ስላገኘ  ለተሻለው ሸጦ ኮሚሽኔ ወደ አካውንቴ ተላከ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በሦስት ቀናት ውስጥ ነበር፡፡ ጎበዝ ሰው እጅ ያለው ገንዘብ ከምታስቡት በላይ ነው፡፡ በተለይ ጥቂቶች የማተሚያ ማሽን ያላቸው ይመስል ይህንን ሚሊዮን የሚሉትን ቁጥር በሦስት አኃዝ አስደግፈው ሲጠሩት፣ እነሱ ከማርስ የመጡ እንጂ እዚህች ምስኪን አገር ላይ የሚኖሩ አይመስሉም፡፡ ‹ብሶት የወለደው የእንትን ሠራዊት…› ይል ከነበረው ጀምሮ እስካሁኑ ‹የሕዝብ ነፃነት ታጋይነት› ድረስ ብልጦች ከመጠን በላይ ሸቅለዋል፡፡ የዋሆች ደግሞ ‹አይነጋም ወይ ሌሊቱ…› እያሉ ዛሬም ይቆዝማሉ፡፡ ብሶት ውስጥ ሆነውም ጥርሳቸውን ያንቀራጭጫሉ፡፡ ወይ ነዶ!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደውሎልኝ በጥብቅ እንደሚፈልገኝ አሳወቀኝና ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን አመራሁ። ሳገኘው፣ ‹‹በሰላም ነው በጥብቅ እፈልግሃለሁ ያልከኝ?›› ብዬ ብጠይቀው ‹‹አዎ!›› አለኝ ቢራውን እያጋመሰ። ‹‹ምንድነው እሱ?›› አልኩት በጤናው ስላልመሰለኝ። ትናንት ሲስቅ ያያችሁት ሰው ነገ ለቀብሩ ድረሱ በሚባልበት ጊዜ፣ ጤናውን ካልተጠራጠርኩ ምኑን ልጠራጠር ኖሯል? እንደ ገንዘብ ግሽበቱ የሰውንም ጤና እንዲህ ነው ብሎ መናገር ከባድ ሆነ እኮ። ታዲያ እንደ ገመትኩት ሳይሆን፣ ‹‹ኧረ ደህና ነኝ። ብቻ የእዚህ ግሮሰሪያችን ነገር አስደንቆኝ ነው። ትዝ ካለህ እኛ መምጣት የጀመርን ሰሞን ባዶ ነበር…›› ሲለኝ፣ ‹‹አሁን ለዚህ ነው እንደዚያ እፈልግሃለሁ ብለህ ስሮጥ የመጣሁልህ?›› ብዬ አኮረፍኩት። ‹‹አንበርብር እኔማ ሰው ያለ አንድ ነገር ባንኮኒ ላይ አይሰየምም የሚል እምነት ስላለኝ፣ ስለዚህ ብሶት ስለወለደው የመጠጥ ገበያ የታዘብኩትን ላካፍልህ ነው…›› አለኝ። ‹‹የምን ብሶት?›› አልኩት ከፊታችን ያለው ግንቦት ሃያ ትዝ እያለኝ፡፡ ‹‹የፍትሕ መጓደል ብሶት፣ የቤት ችግር ብሶት፣ የኑሮ ውድነት ብሶት፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ብሶት፣ የሰብዓዊ መብት መጓደል ብሶት፣ በአጠቃላይ የኑሮና የፖለቲካ ብሶት…›› አለኝ። እሱ እያወራ እኔ ደግሞ በሐሳብ ጭልጥ ብዬ ነበር። ታዲያ ይኼ ‘ብሶት የወለደው ኑሮ?’ ነው የሚባለው ወይስ ‘ብሶት ያባባሰው ኑሮ?’ ምርጫውን ለእናንተው፣ ግን ‹‹ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው…›› የተባለው ለእኛ ይሆን እንዴ? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት