Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊመሻሻል የሚጠይቀው ለኤችአይቪ ኤድስ የሚለቀቅ ፈንድ አስተዳደር

መሻሻል የሚጠይቀው ለኤችአይቪ ኤድስ የሚለቀቅ ፈንድ አስተዳደር

ቀን:

በርካታ ሕፃናትን ያለ ወላጅ አስቀርቷል፡፡ ሕፃናቱ ወደው ባላመጡት በሽታ ተሰቃይተዋል፣ ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ ከዛሬ 25 ዓመታት በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ እንደ ቅጠል ረግፈዋል፡፡ ‹‹ምን መዓት መጣ›› ተብሎ በየአድባራቱና በየገዳማቱ እግዚዖታ ተደርጓል፡፡ በየመስጊዱ አላህን ያልተለማመነና ያልተማፀነ ነበር ለማለት አያስደፈርም፡፡

ስለኤችአይቪ ቫይረስ ግንዛቤ ለመስጠት የሚመለከተው ሁሉ በየፊናው ተረባርቧል፡፡ ከጥበብ ዓለም ጎራ ብንል እንኳን፣ ሙዚቀኞች ስለቫይረሱ አስከፊነትና ማግለልም እንደማይበጅ ዘምረዋል፡፡ ከእነዚህም ዜማዎች ውስጥ ዘሪቱ ከበደ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ፀደኒያ ገብረ ማርቆስ፣ አብዱ  ኪያር፣ ሚካኤል በላይነህ ኃይልዬን ጨምሮ ሌሎችም የተሳተፉበት ‹‹ማለባበስ ይቅር›› ብለው ያዜሙት ይገኝበታል፡፡

ኤችአይቪ ኤድስ በኢትዮጵያ መከሰቱ የታወቀው በ1970ዎቹ መገባደጃ ቢሆንም፣ ወረርሽኙን የመከላከል ጥረቶች የተጀመሩት በ1980ዎቹ ነው፡፡ ምላሹ ወደ ላቀ ደረጃ የተሸጋገረው ደግሞ ከ1990 ዓ.ም. በኋላ መሆኑ ይታወቃል፡፡

- Advertisement -

በዚህም የሥርጭትና የሞት መጠኑን መቀነስ ተችሎ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ነገሮች እየተቀያየሩ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኤችአይቪ ኤድስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን፣ ቫይረሱንም ለመከላከል እንዲሁም ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት መቀዛቀዙ ችግሩን ማባባሱን እየተነገረ ይገኛል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኤችአይቪን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቀመጡትን  ግቦች ለመምታት የነበረው ትጋትና ግስጋሴ በአሁን ጊዜ አይታይም፣ በጀቱም ቀንሷል፡፡ እናም በዚህ ምክንያት የሚሊዮኖች ሕይወት ለአደጋ ተጋልጧል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኤችአይቪ ኤድስ መቆጣጠሪያና መከላከያ ፈንድ ከ2011 ዓ.ም. እስከ 2014 ዓ.ም. የሥራ ክንውኖች የኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰሞኑን ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ቋሚ ኮሚቴውና ባለድርሻ አካላት የኦዲት ግኝቱን አስመልክቶ አሥራ አንድ ጥያቄዎች ለጤና ሚኒስቴር አቅርበዋል፡፡

ለሚኒስቴሩ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ለኤችአይቪ ኤድስና መከላከል የተሰበሰበው ሀብት፣ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም የሚያስችል የተዘረጋ ወጥ የሆነ አሠራር አለመኖር፣ በየክልሎች ያልተወራረዱ ሒሳቦች መኖራቸውን፣ ከ2011 ዓ.ም. እስከ 2014 ዓ.ም. ወቅታዊና ችግር ፈቺ ጥናት አለመደረጉና የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ አለመሰጠቱ፣ በጽሕፈት ቤቱ ለመድኃኒት ግዥና አቅርቦት የተያዘ ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ካለመዋሉና በትክክል ስለመሠራጨቱ የሚከታተልበትና የሚያረጋግጥበት አሠራር ዝቅተኛ መሆኑና ሌሎች ጉዳዮች ይገኙበታል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴውና ከባለድርሻ አካላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከል የሚደረግ የፈንድ አጠቃቀምና አፈጻጸም ላይ ሰፊ ክፍተቶች አሉ፡፡

እነዚህን ክፍተቶች ለመመለስ ሚኒስቴሩ ክልሎች ድረስ በመውረድ እየሠራ ሲሆን፣ ክልሎች ላይ ያለው አቅም ግን በየጊዜው እየተሻሻለ ቢመጣም፣ አሁንም ችግሩ አልተፈታም ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ በክልሎች ለተለያዩ ፕሮግራሞች የሚውል ገንዘብን በተመለከተ በሚፈለገው ፍጥነት ሥራዎች ተሠርተው የማለቅና የማወራረድ ሒደቱ ክፍተት እንዳለበት አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል በየወሩ ከመንግሥት ሠራተኞች ተቆራጭ የሚደረገው አንድ በመቶ የሚሆነው ገንዘብ ለአገልግሎት እየዋለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከየተቋማቱ የሚሰበሰበው ብር ሥራ ላይ የሚውለው እንዴት ነው የሚለውን ለመመለስ፣ በቀጣይ ከታሰበው የፈንድ አስተዳደር ማቋቋም ጋር በማያያዝ ይሠራል ብለዋል፡፡

የፌዴራል መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ እንደተናገሩት፣ ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተለያዩ ተቋሞች ፈንድ ተደርጎ ለክልሎች የተመደበው ገንዘብ ከአንድ ዓመት በላይ በባንክ ተቀምጧል፡፡

ይህ በጤና ሚኒስቴር በኩል የሚደረገው ቁጥጥርና ክትትል አናሳ መሆኑን ያሳያል ያሉት ዋና ኦዲተሯ፣ በሌላ መልኩ ከክልሎች ያልተሰበሰበ ገንዘብ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ ገንዘብ መኖሩን ጠቅሰው፣ ከሒሳቡ ጋር ያልታረቀ ደግሞ 1,147 ብር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል በራስ አቅም ችግሮችን ለመፍታት ተብሎ በየተቋማቱ የሚሰበሰበው አንድ በመቶ የሚሆነው ገንዘብ አፈጻጸም በሚኒስቴሩ በኩል በግልጽ አለመቀመጡን ወ/ሮ መሠረት ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው፣ የጤና ሚኒስቴር በቀረበበት የኦዲት ግኝት ላይ የሠራቸው ማሻሻያዎች ቢኖሩም በፈንድ አጠቃቀም ግን የአመራርና የአሠራር ክፍተቶች አሉበት ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በቀጣይ ሚኒስቴሩ መሥራት አለበት ብለው አቅጣጫ ከሰጡባቸው መካከልም፣ በየክልሉ ያልተሰበሰቡ ሒሳቦች በሦስት ወራት ውስጥ ዕልባት እንዲያገኙ፣ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ለኤችአይቪ ኤድስ የሚሰበሰበው ገንዘብ አጠቃቀምን በተመለከተ አሠራርና የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ በሦስት ወራት ውስጥ እንዲቀርብና የፈንድ አጠቃቀምን በተመለከተም በክልሎች ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲዘረጋም አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም በየክልሉ ያለና ከጥቅም ያልዋለ ተቀማጭ ገንዘብ ተገቢው ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ከጥቅም እንዲውል ተደርጎ የአፈጻጸም ሪፖርቱ በሦስት ወራት ውስጥ እንዲላክ ሲሉ አቶ ክርስቲያን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይም ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ምርመራ፣ ድጋፍና እንክብካቤ የሚያገኙበት ሥርዓት እንዲዘረጋ፣ የፈንድ አሰባሰብ ስትራቴጂም በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ እንዲተገበር በሰጡት አቅጣጫ ላይ አመላክተዋል፡፡

በሌላ በኩል የጤና ሚኒስቴር የኦዲት ማሻሻያ መርሐ ግብሩን በአሥር ቀናት ውስጥ እንዲያዘጋጅ፣ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ደግሞ በየሦስት ወሩ ለቋሚ ኮሚቴው፣ ለዋና ኦዲተር እንዲሁም ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲልክ የፈንድ ሥርጭት አጠቃቀም ፍትሐዊነት፣ ተደራሽነትና ኤችኤይቪ ኤድስን በመከላከሉ ረገድ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በትኩረት እንዲሠራ አቶ ክርስቲያን አሳስበዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኤችአይቪ ኤድስ በሽታ ከ40 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በ2021 መጨረሻ 38.4 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ