- መንግሥት የመረጣቸው የሕክምና ተቋማት ተቀባይነት አጠራጥሯል
- መንግሥት የማያውቀው ክፍያ በዶላር ሊከፈል መሆኑ ተጠቁሟል
የቤት ሠራተኞችንና የተለያዩ ሙያ ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን ወደ ዓረብ አገሮች መላክ መጀመሩን አስመልክቶ፣ ወደ ጆርዳን የሚላኩ ዜጎች የጤና ምርመራ የሚያደርጉባቸውን የሕክምና ተቋማት ለመምረጥ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ልዑክ፣ የጤና ተቋማትን ለመምረጥ እየሄደበት ያለውን ሁኔታ መንግሥት እንዲመረምረውና ቁጥጥር እንዲያደርግበት ተጠየቀ፡፡
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ግንቦት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ኢትዮጵያ መግባቱ የተገለጸው የጆርዳን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የጆርዳን አሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ልዑክ ቡድን፣ ከሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የተለያዩ የሕክምና ተቋማትን እየጎበኘ መሆኑን የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራና አሠሪ አገናኝ አንዳንድ ኤጀንሲዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
እንደ ኤጀንሲዎቹ ገለጻ፣ መንግሥት (ጤና ሚኒስቴር) ወደ ዓረብ አገሮች የሚላኩ (የሚሄዱ) ሠራተኞችን የጤና ሁኔታ የሚመረምሩ ከ60 በላይ የጤና ተቋማት የመረጠ ሆኖ ሳለ፣ አንዳንድ ላኪ ኤጀንሲዎችና የሕክምና ተቋማት በውጭ ካሉ ቀጣሪ ሠራተኞችና አሠሪ አገናኛ ኤጀንሲዎች ጋር በመመሳጠር፣ መንግሥት ያልመረጣቸው የጤና ተቋማት በራሳቸው (በጆርዳን ጤና ሚኒስቴር ሐኪሞች) የጤና ባለሙያዎች እንዲመረጡ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ማስደረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ከሚላኩት ሠራተኞች በጥቁር ገበያ እየተመነዘረ በጆርዳን ለሚገኘው የኤጀንሲዎች ማኅበር ስምንት ዶላር ከእያንዳንዳቸው ተላኪ ሠራተኞች እንደሚከፈልም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር እንደመሆኗ የውጭ አገር ዜጎች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡና ሲወጡ እንዲሁም የመጡበት ዓላማ መታወቅ ሲገባው ልዑክ ቡድኑ ሲገባ እንደማይታወቅና ለምን እንደመጣ ሳይገለጽ በድብቅ ለደላላ እየተከፈለ ለማኅበሩ ገንዘቡ እንደሚላክም አክለዋል፡፡
ልዑኩ በአገር ውስጥ ኤጀንሲ ወኪሎች በአዲስ አበባ ከተማ እየተዘዋወረ በመንግሥት ዕውቅና ያልተሰጣቸውን (ያልተመረጡትን) የሕክምና ተቋማት እየመረጡ ሲሆን፣ መስፈርት ያላሟሉ ተቋማት ለጊዜው እየተበዳደሩ እንዲያሟሉ እየተመቻቸላቸው መሆኑንም ኤጀንሲዎቹ ተናግረዋል፡፡
እያንዳንዱ የሚላክ ዜጋ ከ2,500 ብር በላይ ለምርምር እንደሚከፍልና ተመርምሮ ወደ ጆርዳን ከሄደ በኋላ በድጋሚ እንደሚመረመር ጠቁመው፣ አብዛኛዎቹ ቀደም ባሉት ዓመታት ‹‹ጋምካ GAMCA›› ይባል የነበረው የምርመራ ተቋም ያደርግ እንደነበረው ‹‹ምርመራው ትክክል አይደለም›› በማለት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሊደረጉ ስለሚችሉ፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ቅድሚያ ቁጥጥር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በጆርዳን ለሚገኘው የኤጀንሲዎች ማኅበር ከሠራተኞቹ ከሚያስከፍለው ገንዘብ ላይ ከጥቁረ ገበያ ዶላር በመግዛት የሚልኩት የሚመረጡት የጤና ተቋማት መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ የሚላኩት ሠራተኞች ለምርመራ ለሚከፍሉት ገንዘብ (2,500 ብር) ደረሰኝ እንደማይሰጣቸውና ምርመራውም ትክክለኛ ይሁን አይሁን እንደማይታወቅ ጥርጣሬያቸውን አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም መንግሥት በጤና ጥበቃ በተመረጡት የጤና ተቋማት ምርመራ እንዲደረግ ክትትል እንዲያደርግና የዜጎችን ደኅንነት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል፡፡
ጉዳዩ ይመለከተዋል የተባለውን ሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን ለማነጋገር ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡