Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአፍሪካ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ አኅጉራዊ ሁነት በአዲስ አበባ ሊዘጋጅ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመት የምሥረታን በዓል መሠረት በማድረግ ተገማች ባልሆነው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል? በሚለው ላይ የሚመክር ዓለም አቀፍ ኤክስፖና የምክክር ሁነት መዘጋጀቱን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ይኼን ያስታወቀው የአፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ታሳቢ በማድረግ ከአጋር ተቋማት ጋር በመሆን ‹‹ዋን አፍሪካ ኤክስፖ›› በሚል ርዕስ ሊዘጋጅ ስለታሰበው ዓለም አቀፍ ኤክስፖና የፓናል ውይይትን አስመልክቶ፣ ማክሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል በተሰጠ የጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አባቢ ደምሴ (አምባሳደር)፣ የአፍሪካ ዕድገት ሁኔታን በተመለከተ እ.ኤ.አ በ2063 አጀንዳ እንደተቀመጠው አፍሪካ በኢኮኖሚ፣ በባህል፣ በቴክኖሎጂና አቅሟ ይቀየራል ተብሎ እንቅስቃሴ እየተደረገ ቢሆንም ተግዳሮቶቹ ብዙ ናቸው ብለዋል፡፡

‹‹ተግዳሮቶቹን ለማሸነፍ የመጀመርያው ያለውን ሀብት፣ የሰው መተባበር፣ አጋርነትንና አብሮነትን ይጠይቃል፤›› ሲሉ አባቢ (አምባሳደር) አስረድተዋል፡፡

ተገማችነት በሌለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ አፍሪካ እንደ አኅጉር እንዴት አድርጋ ብትወዳደር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ትሆናለች የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ ነው ያሉት አምባሳደሩ፣ በውስብስብና መገመት በማይቻለው ዓለም ውስጥ በአፍሪካ ያለውን እምቅ ኢንቨስትመንት፣ የባህል፣ የቱሪዝም፣ የንግድ ሀብቶች እንዴት ተደርጎ ጥቅም ላይ መዋል ይችላል? ምን መደረግ አለበት የሚለው ጥያቄ መሰንዘር ከጀመረ ውሎ ያደረ ነው ብለዋል፡፡

በሌላው ዓለም ላይ ያለውን ገበያ የመጠቀም ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ በአፍሪካ ውስጥ ያለውን ግዙፍ ገበያ፣ እንዲሁም በመሀል ያለውን ነፃ የንግድ ቀጣና ትስስርን በተመለከተ ከግንቦት 14 ቀን አስከ ግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በሳይንስ ሙዚየም በሚካሄደው ሁነት በአኅጉሪቱ እስካሁን የተሠሩት ሥራዎች ምንድናቸው? በቀጣይ ምን ሊደረግ ይገባል? በሚሉና ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አፍሪካ አገሮች ድርሻ ላይ ምክክር እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

በሳይንስ ሙዚየም ይካሄዳል በተባለው ኤክስፖ የአፍሪካ የቢዝነስ ድርጅቶች፣ በአገር ውስጥ በንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሥራ ፈጣሪዎች፣ እንዲሁም ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የተጋበዙ ግለሰቦች ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡

በኤክስፖው አፍሪካዊ ምርቶችና አገልግሎቶች ከሚተዋወቅበት ኤግዚቢሽን በተጨማሪ በአፍሪካ ውስጥ በአሠራሮች፣ በፖሊሲዎች፣ በስትራቴጂዎች፣ በመሠረተ ልማት፣ በፋይናንስ፣ በንግድ ቀጣናና ኢንቨስትመንት በእያንዳንዱ አገር ላይ እንዴት እየተሠራ ነው በሚለው ላይ በባለሙያዎች የተዘጋጀ ጽሑፍ የሚቀርብበት ፎረም እንደሚዘጋጅ ተነግሯል፡፡

 በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አብዱ ያሲን (አምባሳደር)፣ ከሳይንስ ሙዚየም በተጨማሪ በአፍሪካ ኅብረት ዋና ጽሕፈት ቤት የሚዘጋጅ ዝግጅት እንደሚኖር ገልጸው አጠቃላይ ዝግጅቱ፣ ‹‹የአፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ሲከበር አጋርነት ማሳየት አለብን፤›› በሚል ርዕስ በበላይ አካላት ታስቦና ተጠንቶ የተዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ የተለያዩ ሚሲዮኖችም እንደሚሳተፉበት አክለዋል፡፡

‹‹ዋን አፍሪካ›› በሚል የሚዘጋጀው ኤክስፖ ዋና ዓላማው የአፍሪካ ኅብረትን ዓላማ ወይም የ2063 ስትራቴጂ ፕሮግራምን ማዕከል ያደረገና ፓን አፍሪካኒዝምን መሠረት ያደረገ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የዋን አፍሪካ ኤክስፖ የቦርድ አባል አቶ ሳሙኤል መብራቱ በሸራተን አዲስ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፣ ኤክስፖው አፍሪካውያን ለ60 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ለፖለቲካና ለዲፕሎማሲ እንደሚገናኙት ሁሉ ለቢዝነስም ተገናኝተው አብሮ ለመሥራት ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች