የሕዝብና ቤት ቆጠራ፣ እንዲሁም የግብርና መረጃ ቆጠራ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ እንደሚካሄድ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የ2015 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን፣ ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ ነው ይህ የተገለጸው፡፡
የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ የሚካሄድ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ቆጠራ ከተካሄደ ሁለት አሠርት ዓመታት ሊሞሉት ትንሽ ቀርቶታል፡፡
ለረዥም ጊዜ ሳይካሄድ የቆየውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለማካሄድ በቂ ዝግጅት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ተቀባይነት ያገኘ ቆጠራ በአንድ ጊዜ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በተወሰኑ ቀናት መከናወን ያለበት በመሆኑ፣ ወደ ሥራ ገብቶ በአንዴ ቆጥሮ ለማጠናቀቅ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው ሳይካሄድ መቆየቱን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ በተለያዩ የአገሮቹ አካባቢዎች ያሉ የፀጥታ ሁኔታዎች የሚሻሻሉበት ሁኔታ እየተጠበቀ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፣ በመጪዎቹ ዓመታት ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም. ባለው የመንግሥት ኢንቨስትመንት ዕቅድ ውስጥ ቆጠራው ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ይከናወናል ብለዋል፡፡
በሦስት ዓመቱ የመንግሥት የኢንቨስትመንት ዕቅድ ውስጥ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ልማት ፕሮግራም የተቀረፀ በመሆኑ፣ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የሕዝብና ቤት ቆጠራን ጨምሮ በርካታ ሌሎች ያልተከናወኑ ቆጠራዎች እንደሚካሄዱ አብራርተዋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና በመንግሥት አስፈጻሚው በኩል ጥቅም ላይ ይውላሉ ተብለው ወደ አገር ቤት የገቡ ነገር ግን የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና በጤና፣ በግብርና፣ እንዲሁም በማዕድን ተቋማት የተከለከሉ ኬሚካሎች በተለያዩ ቦታዎች ተከማችተው እንደሚገኙ ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኬሚካሎቹን ለማስወገድ በአገር ውስጥ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ ወደ አውሮፓ ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል ተልከው እንደሚወገዱ የማድረግ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ኬሚካሎቹን ጭኖ ወደ አውሮፓ አገሮች ልኮ ለማስወገድ የሚያስፈልገው ገንዘብና ወደ አውሮፓ የሚያጓጉዘው መርከብ በሚያልፍባቸው አገሮች ሁሉ ፈቃድ መጠየቅ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ይህን ችግር በዘለቄታዊ መፍትሔ በአገር ውስጥ ማከናወን ስለሚያስፈልግ፣ በ2016 ዓ.ም. የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የበጀት ዕቅድ ውስጥ በማካተት አደገኛ ኬሚካሎችን ማስወገድ የሚቻልበት ቦታ ማዘጋጀት፣ አስፈላጊውን መሠረተ ልማት ለመገንባት ጥናት ማስጀመር የሚያስችል ሥራ ተካቶ ቀርቧል ሲሉ አስረድተዋል፡፡