በአበበ ፍቅር
በዓለም የከተሞች መስፋፋት፣ የኢንዱስትሪ ማደግ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምጥቀትና የአኗኗር ሁኔታ መዘመን የሰው ልጆች የረዥም ዕድሜ ባለፀጋ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ አረጋውያን በዕድሜና በሌሎች ተጓዳኝ ምክንያቶች ለተለያዩ ችግሮች ሲጋለጡ ይስተዋላሉ፡፡
በተለይ ከኅብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤ መለወጥ ጋር በተያያዘ ከሚደርስባቸው ሥነ ልቦናዊ ድቀትና የጤና መታወክ እንዲሁም ጧሪና ደጋፊ በማጣት መሠረታዊ ፍላጎታቸውን እንኳን ለማሟላት የሚቸገሩና ኑሮአቸውን በመከራና በሰቀቀን የሚያሳልፉት በርካታ ናቸው፡፡
አረጋውያን በሁለንተናዊ መልኩ ድጋፍና እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም በተለይ ደግሞ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኛ አረጋውያን እንዲሁም ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው እንዲሁም በጦርነትና በግጭት የተፈናቀሉ አረጋውያን የተለየ እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው እሙን ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው ስምምነት መሠረት፣ ማናቸውም ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆናቸው ሁሉ ‹‹አረጋዊ›› ተብለው እንዲጠሩ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያም ስምምነቱን ተቀብላ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች፡፡
በኢትዮጵያ ለችግር የተጋለጡ ከሰባት ሚሊዮን በላይ አረጋውያን እንደሚገኙ ሔልፕኤጅ ኢንተርናሽናል የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባቀረበው ጥናታዊ ጽሑፉ አመልክቷል፡፡
ተቋሙ ባስጠናው ጥናት መሠረትም በአዲስ አበባ 77.6 በመቶ፣ ኦሮሚያ 31.8፣ አማራ 54.2 በመቶ፣ በደቡብ 41 በመቶ አረጋውያን ከአንድና ሁለት በላይ በሽታዎች እንደሚጠቁም አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ከኢኮኖሚያዊ ችግርና እንዲሁም በማኅበረሰቡ ዘንድ ከሚደርስባቸው መገለል በተጨማሪ፣ በፖለቲካዊ ዘርፉም ቢሆን በቂ የሕግ ጥበቃ ማግኘት አለመቻል የፖሊሲ ማዕቀፎች ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች የተግባራዊነት ችግርና አረጋውያንን አለማካተት የሚሉት ችግሮች በስፋት እንደሚስተዋሉ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
በተለያዩ አካላት ከአረጋውያንና ከማኅበራቸው ለሚነሱ ጥያቄዎች ወቅታዊና ተገቢ ምላሽ በሚመለከተው አካል እንደሚያገኙ አመልክቷል፡፡
ብሔራዊ የአረጋውያን ማኅበርን ጨምሮ በአብዛኛው የአስተዳደር ዕርከን ያሉ የአረጋውያን ማኅበራት የተሟላ ቢሮ እንኳን እንደሌላቸው፣ በአንዳንድ ወረዳዎችም አረጋውያኑ የሚቀበሩበት ቦታ እስከማጣት መድረሳቸውን በጥናታዊ ጽሑፉ ተመላክቷል፡፡
ሔልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ጥናታዊ ጽሑፉን ያቀረበው፣ ግንቦት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. የወደቁትን አንሱ ከሚባለው የነዳያን መርጃ ማኅበር ጋር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ነው፡፡
በርካታ አረጋውያን ካለባቸው ኢኮኖሚያዊ ችግር የተነሳ የዕለት ኑሯቸውን ለመምራት ካለመቻላቸው ባለፈ፣ ባሉበት አካባቢ መቆየት ስለማይችሉ ከገጠር ወደ ከተማ እንደሚሰደዱ፣ ችግሩን ለመከላከልና ለማቆም እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ካለው ችግር ጋር አለመመጣጠኑ ተጠቁሟል፡፡
የተመረጡና አዋጭ የሆኑ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድረግ የአረጋውያንን ኑሮ ለማሻሻል መሥራት ካልተቻለ፣ በአሁን ወቅት የሚታዩት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እየተበራከቱ እንደሚሄዱም አያጠያይቅም ተብሏል፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚንቀሳቀሱ ተቋማት አንዱ የሆነው የወደቁትን አንሱ የነዳያን ማኅበር በከፋ ችግር ውስጥ ያሉ አረጋውያንን በማሰባሰብና ከወደቁበት በማንሳት፣ የተስተካከለና ጤናማ ሕይወትን እንዲኖሩ ለማድረግ እየሠራ ነው ሲሉ የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ሸዋታጠቅ ተናግረዋል፡፡
ማኅበሩ የአዕምሮ ጉዳት ያለባቸውን ጨምሮ የአካል ጉዳተኞችን የሚያነሳ ሲሆን፣ በይበልጥ ትኩረት የሚሰጡት ግን ለአረጋውያን እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹አረጋውያን ከኅብረተሰቡም ከሆነ ከሚመለከተው አካል ተገቢው ትኩረት እየተሰጣቸው አይደለም፤›› ያሉት አቶ አብነት፣ ማኅበራቸው በአሁኑ ጊዜ ማዕከል አስገንብቶ ከ200 በላይ የሚሆኑ አረጋውያንን እየተንከባከበ መሆኑን፣ በተጨማሪም ከማዕከሉ ውጭ ሆነው በተመላላሽ አገልግሎት የሚያገኙም እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
የወደቁትን አንሱ የነዳያን ማኅበር አረጋውያንን የሚንከባከቡ ነርሶችንም የአጭር ጊዜ ልዩ ሥልጠና በመስጠት የሕክምና ዕርዳታን እየሰጡ እንደሆነ የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ተናግረዋል፡፡
ሠልጣኞቹ ከዚህ በፊት በሙያው የተመረቁ ሲሆን፣ በማኅበሩ የተሰጣቸው ሥልጠናም አረጋውያንን በተለየ ሁኔታ ለመንከባከብ የሚያግዛቸው ነው፡፡
ሥልጠናው ቀጣይነት ያለው ሲሆን፣ አረጋውያን በዘርፉ በሠለጠኑ ነርሶች በመታገዝ ሙሉ የጤና ክብካቤ ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት የራሱ ክሊኒክ ያለው ሲሆን፣ በቀጣይም ሆስፒታል ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አቶ አብነት ገልጸዋል፡፡
አረጋውያንን ተንከባክቦ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን፣ የሥራ ዕድልን በመፍጠር ማሠራት እንደሚቻልም በውይይቱ ተነስቷል፡፡
በዚህም አረጋውያን ያላቸውን መልካም ተሞክሮ ለወጣቱ ትውልድ እንዲያስተምሩ የሚደረግ ሲሆን፣ ገንዘብ በብድር ወስደው መሥራት ለሚችሉትም የብድር አገልግሎት እንዲመቻችላቸው ይደረጋል ተብሏል፡፡
እንደ ማሳያም ብድር ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ የገቡ አረጋውያን ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውም ተወስቷል፡፡