Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለመርሆቻቸው ታማኝ ከሆኑ የማኅበረሰቡን እምነት ያገኛሉ›› አቶ ሔኖክ መለሰ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት

አቶ ሔኖክ መለሰ የዕድሜያቸውን ግማሽ ያህል በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች ውስጥ መሥራታቸውን ይናገራሉ፡፡ አሁን ላይ ደግሞ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ በምክር ቤቱ ሥራዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት መቼ ተመሠረተ? ዓላማውስ ምን ነበር?

አቶ ሔኖክ፡- የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የተቋቋመው አዲስ በወጣው አዋጅ ቁ11/13 2011 ዓ.ም. በአንቀጽ 85 መሠረት በታኅሣሥ ወር 2013 ዓ.ም. ነው፡፡ ዓላማውም በኢትዮጵያ ያሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ለማስተባበርና ለመወከል እንዲቻል፣ ራስን ለማስተዳደርና ለመቆጣጠር አሳታፊነትና ግልጽነት እንዲኖር፣ የሥነ ምግባር ደንብ በማዘጋጀት በሁሉም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንዲተገበር ለማድረግ ነው፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣንን ማማከር፣ ዕውቀትን ማደራጀትና ማሸጋገር ከተደራጀው ዕውቀት ላይ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የውትወታና የፖሊሲ ድጋፍ ማድረግ፣ የድርጅቶችን ሥራ መደገፍና ማስተዋወቅ እንዲሁም ድርጅቶችን የመጠበቅ ሥራን ታሳቢ አድርገን ነው ያቋቋምነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምክር ቤቱ ምን ያህል አባላትን ይዟል? በምን ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው?

አቶ ሔኖክ፡- በፌዴራል ደረጃ ተመዝግበው የሚገኙ ከ4,400 በላይ የሚገኙ ሁሉም የሲቪል ማኅብረሰብ ድርጅቶች የምክር ቤቱ አባል ናቸው፡፡ በክልል ደረጃ የተመዘገቡትን ወደ ምክር ቤቱ እንዲመጡ በእዚያው ያሉበት ክልል ድረስ በመሄድ የምክር ቤት አባል ቢሆኑ የተሻለ ጥበቃ ሊያገኙና ችግራቸውንም ለማስረዳትና ለመቅረፍ እንደሚችሉ በማወያየትና በማስረዳት አባል እያደረግን እንገኛለን፡፡   

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጀቶች ምን ያህል ካፒታል እንዳላቸው በእናንተ በኩል ይታወቃል?

አቶ ሔኖክ፡- የሚያፈሱት መዋዕለ ንዋይ በጣም በርካታ ነው፡፡ ትክክለኛውን ቁጥር ለማወቅ ምክር ቤቱ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ እነዚህ በርካታ ድርጅቶች ያልተሰማሩበት የሥራ መስክ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ በጤናው፣ በግብርናው፣ በትምህርትና በምርምር ዘርፍ በአካል ጉዳተኞች፣ በሴቶችና በዴሞክራሲ ግንባታ እየሠሩ የሚገኙ ናቸው፡፡ በአዲሱ አዋጅ ከወጣ በኋላ ደግሞ በሰብዓዊ መብት ላይ ሥራ የጀመሩ አሉ፡፡ የቀድሞቹ ደግሞ ወደዚህ አድማሳቸውን እያሰፉ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በሲቪል ድርጅት ላይ እምነት የለንም የሚሉ አሉ፡፡ ምክር ቤቱ ይህን አመለካከት ከመቀየር አኳያ ምን እየሠራ ነው?

አቶ ሔኖክ፡- ሲቪል ድርጅት ለመርሆቻቸው ታማኝ መሆን አለባቸው፡፡ በሚሠሩት ሥራ ላይ የሚመለከታቸውን የሥራ ኃላፊዎች፣ በአካባቢው ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችንና ሌሎችንም አሳታፊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አብዛኛዎቹ የሲቪል ድርጀቶች ይህን ሳይተገብሩ በመቆየታቸው የሚሠራውም የማይሠራውም አሉታዊ ስም እንዲኖራቸው ሆነዋል፡፡ ምክር ቤቱ ከተቋቋመ በኋላ ከሠራቸው ሥራዎች አንዱ ለሲቪክ ማኅበራት የተሰጠው ስም እውነት ነው ወይ? የሚል ነው፡፡ በመንግሥትም ይሁን በማኅበረሰቡ ዘንድ ስለ ሲቪል ድርጅት ግልጽ የሆነ ዕይታ እንደሌለ ለመገንዘብም ችለናል፡፡ ይህንን ችግር ለማስተካከል ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የሲቪል ድርጅቶች ሳምንት በሚል የሚከበረው ነው፡፡ በቅርቡም ከመቶ በላይ የሚሆኑ ድርጅቶች የሚሳተፉበት፣ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት፣ የሚገመግሙበት፣ የመንግሥት ኃላፊዎችና ድርጅቶች እየሠሩ ባሉበት ሥፍራ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ዓለም አቀፍ እንዲሁም የአገር ውስጥ ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚገኙበት ነው፡፡ በዚህም ማኅበረሰቡም አመለካከቱን ያስተካክልልናል ብለን እናምናለን፡፡ ከሲቪል ድርጅቶች ባለሥልጣን ጋር በመተባበርም ለሚዲያና ለሚመለከታቸው ክፍሎች ዓመታዊ የሥራ ጉብኝት በማዘጋጀት ለኅብረተሰቡ እየተሠሩ ያሉትን ሥራዎች ተደራሽ ለማድረግ እንጥራለን፡፡ በርካታ ሥራዎችን በመሥራት የነበረውን ስም በመቀየር ተዓማኒነት እንዲመጣ እየሠራን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ቀውሶችና ጦርነቶች እየተከሰቱ ይገኛል፡፡ በዚህም በመንግሥትም ይሁን በግለሰብ ደረጃ እጅ እያጠረ ነው፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት የአገር ውስጥ ረጂዎችን ለማበርከትና አገር በቀል ሲቪል ሶሳይት ድርጅት እንዲፈጠር ምክር ቤቱ ምን እየሠራ ነው?

አቶ ሔኖክ፡- እስካሁን ባለው በርካታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ድጋፋቸውን የሚያገኙት ከውጭ ነው፡፡ ይሄ ድጋፍ አሁንም በጣም ያስፈልጋል፡፡ በተለይ አሁን አገራችን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹ የሰብዓዊ ዕርዳታም ይሁን የልማት ተግባራት አሉ፡፡ በእርግጥ የአገር አቀፉን ሁኔታ ስናይ በርካታ ድጋፍ የሚሹ ያሉ ሲሆን፣ በተለይ በጤና ዙሪያ ኮቪድና ያልታቀዱ በሽታዎች፣ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት እንዲሁም ረጂዎች ቅድሚያ በሚሰጡት ጉዳይ ዕርዳታ እየቀነሰ ነው፡፡ ወደፊትም ከዚህ በላይ ይቀንሳል የሚል እምነት አለን፡፡ ለዚህም ሁለት ነገሮችን እየሠራን እንገኛለን፡፡ አንደኛው አገር በቀል ድርጅቶች እንዲበራከቱ ለማስቻል በዓለም አቀፍ ድርጅት ከሚመጣው ዕርዳታ 25 በመቶ ለአገር በቀል ድርጅት ወይም በታችኛው ዕርከን ላይ ላለ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲውል ቅስቀሳና ውትወታ እየሠራን ነው፡፡ ሌላው ማኅበረሰቡ እየመጣ ያለውን ነገር እንዲያውቅና በተለይ በኢትዮጵያ ያለውን የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ባህል እንዲያዳብር የምንሠራው ነው፡፡ ይህንን የሚሠሩ ባለሥጣኑን ጨምሮ ዳይሬክቶሬት እየተቋቋመ ሲሆን፣ ምክር ቤቱም ይህንን ሥራ ለሚሠሩ ሁሉ ሙሉ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ይህ አደገ ማለት ደግሞ የምንፈልገውን የገንዘብ ሀብት መሰብሰብና በቀላሉ ማግኘት ያስችለናል፡፡ ይህ አንዱ ጫናውን ለመቀነስ የምንሠራው ሥራ ነው፡፡ ሌላው የአገር በቀል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚሠሩትን ሥራ ማስተዋወቅና ሌሎች እንዲበረታቱ ምክር ቤቱ የሚሠራው ነው በራሳቸው ሥራውን ወደ አደባባይ በማውጣት አገር ውስጥ ሀብት በማሰባሰብ ትልቅ ሥራ እየሠሩ ያሉ እንደ መቄዶንያ ዓይነት አገር በቀል ድርጅቶችን መመልከት ይቻላል፡፡ ይህ ግን በቂ አይደለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህል ደረጃውን በጠበቀና በተጠያቂነት በመሥራት በጊዜ ሒደት የውጭውን ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻል እንኳን መጠኑን መቀነስ ያስችላል፡፡ ይሄ ደግሞ በራስ የመተማመን ሁኔታውን ከመጨመሩም በላይ የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ እንደሚባለው ቀስ በቀስ ጥሩ ውጤት ይመጣል ብለን እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- የሲቪል ማኅበረሰብን ድርጅቶችን በሚመለከት የፖሊሲ አለመጣጣም አለ ይባላል፡፡ ቢያብራሩልን?

አቶ ሔኖክ፡- ይህን በሚመለከት ሁለት ነገሮችን መመልከት እንችላለን፡፡ ድርጅቶችን ለመቆጣጠር የወጣውና የሚገዙበት ቀደም ብሎ በተለይ 621/2001 በሚባለው አዋጅ መሠረት ከበጎ አድራጎት ጋር የተያያዘ የሕግ ማዕቀፍ ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ እንደገና እንደ አዲስ ተከልሶ የወጣው 11/13/2011 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚገዙበት ሲሆን፣ እንደ ሕግ በእኛ በኩል ምንም ችግር የለም፡፡ ምናልባት እንደ ችግር ሊነሳ የሚችለው የፖሊሲ ችግር ‹‹የማኅበረሰብ አካታችነት›› የሚባለውና ዜጎችን እንዲሳተፉ የሚያደርገው ነው፡፡ ይህ ገና በሒደት ላይ ያለና በውይይት ላይ ያለና ያልፀደቀ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምክር ቤቱ ችግር አለብኝ ብሎ የሚያነሳው ምንድነው?

አቶ ሔኖክ፡- ምክር ቤቱ በአገራችን ለመጀመርያ ጊዜ የተቋቋመ ነው፡፡ ማኅበራትን የሚያስተባብረውና የሚያቀናጀው ይኸው ምክር ቤት ነው፡፡ እንደ ሲቪል ሶሳይቲ ድርጅት ደግሞ በሰብዓዊ መብት፣ በዴሞክራሲና በሰላም ግንባታ ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ላይ ዕውቀትንም ልምድንም በማካፈል አሁን አገሪቱ ከለችበት ችግር ቶሎ እንድትወጣ የመሥራት ፍላጎት ያለን ቢሆንም፣ ይህንን ያለመረዳት ችግር አለ፡፡  ሌላው ምክር ቤቱ አገር አቀፍ በመሆኑ ብዙ ምላሽ የሚሹ ጉዳዮች ከምክር ቤቱ ይጠበቃሉ፡፡ እነዚህ ብዙ ሀብት፣ ገንዘብና ተሽከርካሪ የሚፈልጉ በመሆናቸው ለእኛ ተግዳሮት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየቀነሰ የመጣው የመርዳት ፍላጎት እንዲሁም በአገር ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ያለው የሰላም ዕጦት ምክር ቤቱ እንደ ችግር የገጠመው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ከመንግሥት ወይም ከተቆጣጣሪው ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

አቶ ሔኖክ፡- ምክር ቤቱ የተሻሻለው ሕግ ከወጣ በኋላ በጥሩ እየሠራ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ከዚህ ምክር ቤት መቋቋም በፊትም ከሲቪል ማኅበረሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ጥሩ እየሠራ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ከምክር ቤቱ ጋር ያላቸው ሥራ ተደጋጋፊ ቢሆንም፣ ሁለታችንም የየራሳችን መርሆች ያሉን በመሆኑ፣ እሱን መሠረት ባደረገ ግንኙነት በአሁኑ ሰዓት ጥሩ የሚባል ግንኙነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ምክር ቤቱ ወደፊት ምን ለመሥራት አስቧል?

አቶ ሔኖክ፡- በመጀመርያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አገራዊ እንደመሆኑ አገራዊ ምላሽ የሚሰጥ ተቋም ማድረግ ዋናው ዕቅዱ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ሥራው ዕለት ተዕለት የሚሠራ ሳይሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ስትራቴጂክ የሆኑ ሥራዎች ላይ በሰላም፣ በሰብዓዊ መብቶች እንዲሁም የዴሞክራሲ ልምምዶች እንዲዳብሩ አተኩሮ የሚሠራ ይሆናል፡፡ በቅርቡም በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑና በሌሎችም የሚሠራ ሥራ ላይ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር ተሳታፊ መሆን ጀምሯል፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች ምክር ቤቱ ከመቋቋሙ በፊት እርስ በርስ የማይስማሙ ሥራቸውም ተደጋጋሚ በመሆኑ ሥራቸው የማይታይ ነበር፡፡ ይህንን ሥራ ከመንግሥት፣ ከሕዝብ ፍላጎትና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ጋር የማሳለጥ ሥራ እየሠራን ለውጥ ማምጣት እንፈልጋለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...