Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊእየተንሰራፋ የመጣው የአደንዛዥና የአነቃቂ ዕፆች ተጠቃሚነት

እየተንሰራፋ የመጣው የአደንዛዥና የአነቃቂ ዕፆች ተጠቃሚነት

ቀን:

በኢትዮጵያ የአልኮል ይዘት ያላቸውን መጠጦች እንዲሁም አደንዛዥና አነቃቂ ዕፆችን የመጠቀም ልምድ፣ በተለይም በወጣቶች ዘንድ እየጎላ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ዕድሜው ከ20 ዓመት በታች የሆነ፣ እነዚህን አነቃቂና አደንዛዥ ዕፆችንና የአልኮል ይዘት ያላቸውን መጠጦች መጠቀሙ፣ የአንጎል ዕድገት (ብስለትን) በቀጥታ ከመጉዳቱም በላይ፣ ዕድሜና ፆታ ለማይለዩት ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎችና ለዘላቂ ጉዳት የሚዳርግ ነው፡፡

የሬናሰንት የአዕምሮ ጤናና የሱስ ተሃድሶ ማዕከል መሥራች፣ አማካሪና የሥነ አዕምሮ ባለሙያ ሰለሞን ተረፈ (ፕሮፌሰር) እንደሚናገሩት፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እጅግ አደገኛ የሆነው ኮኬይን የተባለው አደንዣዝ ዕፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር በተለይም በአዲስ አበባ እየተበራከተ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለይም ወደ ደቡብ አሜሪካ በረራ ከጀመረ ወዲህ፣ በቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ፍተሻ የሚያዘው የኮኬይን መጠን፣ እጅግ በጣም መጨመሩን ሰለሞን (ፕሮፌሰር) ገልጸው፣ ዕፅ ወደ አገር ውስጥ እየገባና በከፍተኛ ሁኔታ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን፣ የዘርፉ ባለሙያዎችም በዚህ ተጎጂ የሆኑ ሕሙማንን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያስተናገዱ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

አደንዛዥና አነቃቂ ዕፆችና የአልኮል ይዘት ያላቸው መጠጦች ለአዕምሮ ሕመም መከሰትና መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን፣ ጦርነትና ሌሎች ጫናዎች በስፋት መታየታቸውም ለአደንዛዥ ዕፆች ተጠቃሚነትና ለአዕምሮ ሕመም እንደሚዳርጉ ጠቁመዋል፡፡

ችግሮቹን ለመቅረፍ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ቢታወቅም፣ ከችግሩ መንሠራፋት አንፃር በትኩረት እየሠሩበት ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡

ችግሩን በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ሬናሰንት የአዕምሮ ጤናና የሱስ ተሃድሶ ማዕከልን መክፈታቸውን የሚያስረዱት ሰለሞን (ፕሮፌሰር)፣ ሬናሰንት መታደስን፣ እንደገና በኃይል መሞላትንና ወደ ሙሉ የቀድሞ ሰብዕና መመለስ የሚል አቻ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል፡፡

‹‹በሬናሰንት የተሃድሶ ማዕከል አንድ ሰው ወደ ቀድሞ ጤናማ ማንነቱ እንዲመለስ ይደረጋል፤›› ይላሉ፡፡

በለገጣፎ የተገነባው የአዕምሮ ጤናና የሱስ ተሃድሶ ማዕከል በአንድ ጊዜ 25 ሰዎችን አስተኝቶ አገልግሎት መስጠት የሚችል ሲሆን፣ ወደ ማዕከሉ የሚገቡ ሰዎች የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነትና የሱስ ተጠቂነት ምርመራና ሕክምና፣ የሱስ ተሃድሶ፣ የአዕምሮ ጤንነት ምርመራ ሕክምና አገልግሎቶችን ያገኛሉ፡፡

አገልግሎቱን ከጀመረ ጥቂት ወራትን ያስቆጠረው የሱስ ተሃድሶ ማዕከል፣ ከሳምንት አስቀድሞ በይፋ ሲመረቅ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንዲሁም የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ተገኝተዋል፡፡

ማዕከሉ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የአልኮልና የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነትን፣ እንዲሁም የአዕምሮ ጤና መቃወስን ለማከምና የተሃድሶ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ሊያ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

‹‹በራሱ ባህል የሚኮራ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ፣ ኃላፊነት የሚሰማው ብሎም አገሩ የሚወድ ብቁ፣ ጤናማና አምራች ዜጋ በማፍራት ረገድ አዎንታዊ አስተዳደግን ከማጠናከር ጎን ለጎን፣ ለወጣቶችና ታዳጊዎች ሰብዕና ግንባታ ተግባራት አሁንም ወደፊትም ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ኤርጎጌ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

 ከቤተሰብ ጀምሮ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎችም አካላት በጋራ በመረባረብ ትውልድንና አገርን ከጥፋት የመታደግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ማዕከሉ ሲመረቅ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር  እንደ ሬናሰንት ያሉ የአዕምሮ ጤናና የሱስ ተሃድሶ ማዕከላትን በቅርበት በመከታተል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ያስታወቁት ሚኒስትሯ፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላትም ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...