Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርግማሽ ጎፈሬ ግማሽ ልጬ የሆነው የአዲስ አበባ ሰው ተኮር ፕሮጀክት

ግማሽ ጎፈሬ ግማሽ ልጬ የሆነው የአዲስ አበባ ሰው ተኮር ፕሮጀክት

ቀን:

በቶፊቅ ተማም

ከዛሬ አንድ መቶ ሰላሳ ስድስት ዓመታት በፊት በአፄ ምኒሊክ መናገሻ ከተማ የሆነችውን አንኮበር ጥለው ወደ አዲስ ዓለም አቀኑ፡፡ መቼስ እንጦጦ የሰማይ ጫፍ የወጡ ያህል ቁልቁል አገሩን ለመመልከት ምቹ ነው፡፡ እናም ለንጉሠ ነገሥት ምቹ ቦታ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ከተራራው ጫፍ ቁልቁል የሚታየው ጥቅጥቅ ጫካና አልፎ አልፎ ደግሞ ወለል ያለው ሜዳ ቀልባቸውን ሳይዘርፈው አልቀረም፡፡ ከሜዳዎች ሁሉ ደግሞ ጎበዛዝቱ በጉግስና በገና ጨዋታ ጉልበትን የሚፈትሹበት፣ የሚወድቁና የሚነሱበት መቦረቂያቸው ነው፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን ፍልውኃ ፊን ፊን ወደ የሚልበት መስክ ወረዱ፡፡ እዚያም ብዙ ለዓይን የሚስብ የተፈጥሮ ውበት ነበረው፡፡ እቴጌይቱ ግን ከዚህ በፊት ዓይተዋት የማያውቋት አንዲት ልዩ አበባ ማረከቻቸው፡፡ ‹‹አዲስ አበባ›› አሏት፡፡

አዲስ አበባ እንዲህ ተቆረቆረች፡፡ ኅዳር 14 ቀን 1879 ዓ.ም. አዲስ አበባም የንጉሠ ነገሥቱ መናገሻና የኢትዮጵያ ዋና ከተማነት ሥፍራ ያዘች፡፡ ይህች የአገሪቱ ርዕሰ ከተማ የሆነቸው አዲስ አበባ የብዙ ብሔራዊና ፖለቲካዊ መስታጋብሮች መከወኛ፣ የአፍሪካ ርዕሰ መዲና፣ ብሎም የበርካታ ዲፕሎማቶችና ዲፕሎማሲያዊ ተቋማት መገኛ ሆነች፡፡ ከተማዋ በብዙ መንግሥታት ሥር የመተዳደር ዕጣ የደረሳት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በገዥው ፓርቲ ብልፅግና ሥር በመተዳደር ላይ ትገኛለች፡፡ የወቅቱ የከተማዋ አመራሮች ከቀደምት አቻ አመራሮችም በተለየ ሁኔታ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አገር ወዳድ ባለሀብቶችን የበለጠ በመቅረብና በማስተባበር፣ የኅብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች እየከወኑ ነው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ እያከናወናቸው ካሉ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ከዚህ ቀደም በግለሰቦች፣ በሃይማኖት ተቋማትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ይተገበር የነበረውና ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ወጥ በሆነ መንገድ በመንግሥት ቁርጠኝነትና ከፍተኛ ድጋፍ  በቀድሞ ምክትል ከንቲባ ታለ ኡማ (ኢንጂነር) የተጀመረው የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ይጠቀሳል፡፡ ይህም ለበርካታ ወላጆች ዕፎይታን የሰጠና ተማሪዎች የተሻለ የትምህርት አቀባበል ኖሯቸው ብቁ ዜጋ ይሆኑ ዘንድ ዕድል የከፈተ ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩም ወደ አራት ቢሊየን ብር ገዳማ በዓመት ለተማሪዎች ምገባ እየወጣ ሲገኝ፣ በዚህም ከ700 ሺሕ በላይ ተማሪዎች መመገብ ተችሏል፡፡ በዚህም ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ፣ ውጤታቸውን በማሳደግ የመድገምና የማቋረጥ ምጣኔን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል፡፡ በምገባ ፕሮግራሙ ከ16 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ እናቶች የሥራ ዕድል ሲፈጠር፣ ይህም በጎ ሥራ በቅርቡ በጣሊያን ሚላን በተካሄደው የአመጋገብና ሥነ ምግብ ዘርፍ አዲስ አበባ ከ133 ከተሞች ተወዳድራ የሚላን ፓክት (Millan Urban food Policy Pact) 2022 አሸናፊ እንድትሆን ማስቻሉ ይታወሳል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የከተማ አስተዳደሩ ቀላል ሊባል የማይችል ወጪ በማውጣት፣ ለተማሪዎች የደንብ ልብስና የትምህርት ቁሳቁስ በየዓመቱ በማዳረስ ላይ ነው፡፡ ይህም ለወላጆች ቀላል ሊባል የማይችል ዕፎይታን ሰጥቷል፡፡

ከምገባው ጎን ለጎን ሊነሳ የሚችለው ሰው ተኮር (Human Oriented) ተግባራት መካከል ለአረጋውያንና ለአቅመ ደካሞች በቀን አንድ ጊዜ፣ ንፁህ ምግብ ያለ ምንም ችግር በክብር እጃቸውን ታጥበው የሚያገኙበት የምገባ ማዕከል ማቋቋም ሲሆን፣ ይህም እስካሁን በከተማው ወደ 15 ገደማ የምገባ ማዕከላት ተቋቁመው በቀን 30 ሺሕ ዜጎች የምገባ አገልግሎት እያገኙበት ነው፡፡ ይህም ከተሠሩ መልካም ተግባሮች መካከል ይጠቀሳል፡፡

ሌላው በከተማ አስተዳደሩ እየተሠሩ ካሉ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች መካከል በተለይ ለአቅመ ደካሞች  የቤት ዕድሳት ተግባራት ሲሆን፣ ይህንን  በጎ ተግባር  ሌሎች ተቋማት በግል ተነሳሽነት እየተገበሩት ይገኛሉ፡፡ ይህም የሚያስመሠግን ተግባር ነው፡፡ ለዜጎች የተመቸ ከባቢን ከመፍጠር አንፃር በጎ ፋይዳ ሲኖረው፣ ከዚሁ ጎን ለጎን የተቋማት ማስፋፊያ ግንባታ በተለይም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ በአብነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ይህም ፈረቃን በማስቀረት  በትምህርት ጥራት ላይ የተሻለ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡

ሌላው በየጊዜ እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማርገብ በማሰብ በከፊልም ቢሆን የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የገበያ አማራጮችን በማስፋት ረገድ የምርት አቅርቦትን በስፋትና በጥራት፣ እንዲሁም በአነስተኛ ዋጋ እያቀረበ ሲገኝ ለዚህም ማሳያ ከ130 በላይ አማራጭ የእሑድ ገበያዎች በመፍጠር የኑሮ ውድነትን ጫና ለመቀነስ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም በተለይ ምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ የሚታየውን ረዥም የገበያ ሰንሰለት ለማሳጠር፣ ወደ አምስት ገደማ የሚሆኑ ግዙፍ የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከላት በመገንባት ላይም ነው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በክረምት ብቻ ይደረግ የነበረውን የበጎ ፈቃድ ሥራን በበጋውም ይተገበር ዘንድ እየሠራ ነው፡፡ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን በአግባቡ ለመከወን በማሰብ አስተዳደሩ የኅብረተሰብ ሥራ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ ኮሚሽን በማቋቋም፣ ዘርፈ ብዙ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ሠርቷል፡፡ ከተማዋን የበጎ ፈቃደኞች ከተማ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ሲገኝ፣ በዚህም ባለፉት የክረምት ወቅቶች ከአንድ ሚለዮን በላይ ወጣቶች በማሳተፍ በሰብዓዊና ማኅበራዊ አገልግሎት፣ በአረንጓዴ ልማትና በአካባቢ ጥበቃ፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በጤና አገልግሎት፣ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኞች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች የመኖሪያ፣ እንዲሁም የማዕድ ማጋራት ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን በዚህም ከፍተኛ ሊባል የሚችል የመንግሥት ወጪን ማዳን አስችሏል፡፡

ሌላው የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ያለ ሰው ተኮር ፕሮጀክት የከተማ ግብርና ሲሆን፣ አስተዳደሩም ይህን በደንብ ለማሳለጥ በማሰብ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በዚህም ዜጎች በአነስተኛ ቦታ የተለያዩ ምርቶችን እንዲያለሙ በማድረግ፣ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ማቃለል እየተተገበረ ነው፡፡ ቀላል ሊባል የማይችል ቁጥር ላላቸው ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ሲያስችል፣ በመንግሥትና በግል ተቋማት ያሉ ክፍት ቦታዎች በከተማ ግብርና ሥራዎች እንዲሸፈኑ በማድረግ የተሻለ የመሬት አጠቃቀም መፍጠር ተችሏል፡፡ ከዚህ ባለፈም በተለይ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰው ሕዝብ ቁጥር እያየለ በመምጣቱ፣ ለመዲናዋ የምግብ ፍላጎት የሚውል ተጨማሪ ምርት በማስፈለጉ ይህንን ምርት ለማቅረብ ዕገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መንግሥት ለሚቀጥሉት ዓመታት ለመተግበር ባቀደው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር አማካይነት፣ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡ ከተማዋ በተለይ በዶሮና በዕንቁላል ፍላጎት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ በመፍጠር፣ የዕንቁላልና የዶሮ ሥጋ አቅርቦት ላይ የበኩሉን ሚና መጫወት አስችሏል፡፡ የዳቦ አቅርቦትን በተመለከተ ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር በየክፍላተ ከተሞች አነስተኛ የዳቦ ፋብሪካዎች በመገንባት፣ ከዓመታት በፊት በቀን ከ300 ሺሕ የማይበልጠውን የዳቦ አቅርቦት በአሁኑ ወቅት  ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዳቦ ለኅብረተሰቡ ማቅረብ የሚያስችል አበረታች ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ዓመታት ከመንግሥት በጀት፣ እንዲሁም  ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር እየሠራቸው ያሉ ሰው ተኮር ተግባራት የሚያስመሠግኑ ቢሆንም፣ ከዚህ በተቃራኒ ከተማዋን የጥበብ ከተማ ከማድረግና የጥበብ ጉዳዮችን በአግባቡ ከመደገፍ አንፃር ክፍተቶች በጉልህ የሚታዩ ሲሆን፣ የተወሰኑትን በዚህ ጽሑፍ ለመጥቀስ እሞክራለሁ፡፡

የመጀመርያው በተለይ የተጀመሩ ንባብ ተኮር የሆኑ ፕሮግራሞች በአግባቡ መደገፍና ክትትል ማድረግ፣ ደራሲያን ከአንባቢዎች ጋር ተገናኝተው ስለሥራዎቻቸው የሚነጋገሩበትና ከአድናቂዎች ጋር የሚገናኙበት፣ ሥራቸውን የሚያካሂዱበት መድረክ እንዲመቻች መደረጉ ያስፈልጋል፡፡ ከዓመታት በፊት በተለይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲና ሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች ይደረጉ የነበሩ የመጻሕፍት ዳሰሳና ውይይት ተቋርጠዋል፡፡ በቅርቡ የተጀመረውና ለጥበብ ፍቅር ባላቸው የዋሊያ መጻሕፍት ባለቤት መልካም ፈቃድ በየሳምንቱ እንዳለጌታ ከበደ (ዶ/ር) አጋፋሪነት የተለያዩ ደራሲያንን በመጋበዝ ይደረግ የነበረው ዳሰሳና ውይይት፣ በአካል ከሚታደሙ ታዳሚዎች ባለፈ ፕሮግራሙ በአግባቡ ተቀርፆ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጭና በመላው ዓለም ያሉ ታዳሚዎች የሚከታተሉት ድንቅ ፕሮግራም ነበር፡፡ ቢሆንም ከከተማ አስተዳደሩም ይሁን በቂ ድጋፍ ከሌሎች ባለማግኘቱ ሳቢያ በነበረበት ግለት መቀጠል ያልቻለ ሲሆን፣ በፕግራሙ ከብዙ ደራሲያን ጋር በመገናኘት ስለሥራዎቻቸውና ስለሥነ ጽሑፍ የመወያየት ፍላጎት ያላቸው የመጻሕፍት አፍቃሪያን ይህ ዕድል እየመከነባቸው ነው፡፡ እነዚህን መሰል ፕሮግራሞች በአግባቡ ሊደገፉና በከተማው በሁሉም አቅጣጫዎች በሚገባው ልክ ሊስፋፉ ይገባል፡፡

ሌላው የከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ገጽታ ለመለወጥ የተለያዩ የአረንጓዴ ሥፍራዎችን ማስዋብ፣ ፓርኮችንና አደባባዮችን እየገነባ ቢሆንም፣ ቦታዎቹ የከተማው ነዋሪዎች የሚቆዝሙባቸው ሳይሆኑ ለአማተር ከያንያን እንዲሁም ለግል የኪነ ጥበብ ኢንተርፕራይዞች ዕድል መስጠት ይገባል፡፡ እነዚህ አደባበዮች የተለያዩ የኪነ ጥበባት ፕሮግራሞች ማለትም የባህልና ዘመናዊ ውዝዋዜ፣ የሥነ ጽሑፍና የሰርከስ ትርዒት የሚታይባቸው መድረክ እንዲሆኑ መሥራት ሲያሻ፣ የከተማ አስተዳደሩ ፍላጎትና ተሰጥኦ ላላቸው አማተር ከያኒያንና የኪነ ጥበብ ቡድኖች በቂ ድጋፍ አላደረገም፡፡  የነገ የአገር ተረካቢ የከነ ጥበብ ባለሙያዎች ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት፣ ብሎም ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡባቸው መድረክ ማመቻቸት  ይገባዋል፡፡ ይህ መሆን ካልቻለ በቀጣይ ለአገር ብዙ ሊሠሩ የሚችሉ ብቁ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ማግኘት አዳጋች ይሆናል፡፡

ሌላው የኪነ ጥበብ አንጓ የሆነውን ቴአትር ስንመለከት የከተማ አስተዳደሩ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ታሪካዊውን የአገር ፍቅር ቴአትር ቤት በማሳደስ ወደ ሥራ ማስገባቱ በአዎንታዊ ጎኑ ሲጠቀስ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ዕድሳት የተደረገለት የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ወደ ቀድሞ ሥራው ወደ ቴአትር ማሳየት መመለስ አለበት ይህ ባይሆን እንኳ ጠንከር ያሉ የኪነ ጥበብ ፕሮግራሞች እንዲካሄዱበት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት፣ ለከተማው የኪነ ጥበብ ዕድገት የራሱ አበርክቶ እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ባለፈ በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ የነበረው በተለምዶ ሰይጣን ቤት በመባል ለሚታወቀው ሜጋ አንፊ ቴአትር (ዋፋ ሲኒማ) ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ወደ ቀድሞ የኪነ ጥበብ ተግባሩ በማስገባት፣ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ በተለይ አማተር ከያንያን ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ብሎም ለከተማው ነዋሪ የጥበብ ፕሮግራሞች መመልከቻ አማራጭ እንዲሆን ማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ባለፈም የከተማው ነዋሪ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመሆኑ በከተማ አስተዳደሩ ተገንብተዋል የተባሉ አንፊ ቴአትሮች፣ እንዲሁም ሌሎችን ወደ ሥራ ማስገባትና የጥበብ ማዕከላት ተዘጋጅተው ኅብረተሰቡ ከኪነ ጥበብ ትሩፋት ይቋደስ ዘንድ ተጨማሪ ሥራዎች መሥራት ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩል የከተማ አስተዳደሩ የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ቢኖር፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ እያሳየ  ያለው የኅትመት ዋጋ ነው፡፡ ይህም በመነቃቃት ላይ ያለውን የንባብና የመጻሕፍት ኅትመት ጉዳይ የበለጠ እየተፈተነ ሲሆን፣  በከፍተኛ ሁኔታ በናረው የኅትመት ዋጋ ሳቢያ ደራሲያን መጻሕፍት ማሳተም እየተሳናቸው ነው፡፡ ተደራሲያንም አዳዲስ ሥራዎች ለማግኘት አዳጋች እየሆነባቸው ነው፡፡ ይህን ለመቅረፍ የተሻለ ሥነ ጽሑፋዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸውን መጻሕፍት ሊያበረክቱ የሚችሉ አቅም ያላቸው ደራሲያንንና የጥበብ ባለሟሎች የሚበረታቱበት ሥርዓት ዘርግቶ፣ የሥነ ጽሑፍ አበርክቷቸውን ወደ አንባቢያን በተመጣጣኝ ዋጋ ይደርስ ዘንድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ድጋፍ ማድረግ ይገባል፡፡ በአገሪቱ ሥነ ጽሑፍ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመቅረፍ መንቀሳቀስ በአሁኑ ወቅት ለአፍታ ቸል ሊባል የማይገባው ጉዳይ ነው፡፡

በመጨረሻም የከተማ አስተዳደሩ በተወሰኑ ሁኔታ ከላይ እንደተጠቀሰው በተለይ  ለየት ባለ አቀራረብ ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር እየሠራቸው ያሉ ሰው ተኮር ተግባራት የሚያስመሠገኑና የበለጠ ሊጠናከሩ የሚገባቸው ሲሆን፣ ከዚህ በመለስ ከተማ አስተዳደሩ ኪነ ጥበብ ለማኅበረሰብ ግንባታና ለአገር ልማት ያለውን ፋይዳ በአግባቡ ዋጋ መስጠት ይገባል፡፡ በተለይ የግሉን ዘርፍ የበለጠ በመሳብ በኪነ ጥበብ ዘርፉ እንዲሳተፍ በሮችን በመክፈት የጀመራቸው በተለይ ሰው ተኮር ተግባራት ምሉዕ ያደርጋቸው ዘንድ በኪነ ጥበብ አፍቃሪያን ስም ጥያቄ አቀርባሉ፡፡ ይህ መሆን ባልቻለበት ሁኔታ  የከተማ አስተዳደሩ ሰው ተኮር የልማት ተግባራት ግማሽ ጎፈሬ ግማሽ ልጩ ከመሆን አያመልጡም፡፡ የጀመራቸው በተለይ ቁስ ላይ ብቻ ያተኮሩ ውብ ከተማን ለመፍጠር በማለም እያከናወናቸው ያሉ ከተማን የማስዋብና ሌሎች በቅርቡ በስፋት ሊተገበሩ ዝግጅት እየተደረገባቸው ያሉ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች፣ ያለ ኪነ ጥበብ ምሉዕ እንደማይሆኑ በግርድፉም ቢሆን በምትገልጸው ዘመን አይሽሬ የደራሲ በዓሉ ግርማ ግጥም ለሐሳቤ መቋጫ ላድርግ፡፡ ሰላም!

ከጎራው ዘልቄ እስኪ ልነጋገር

ካለሰው ቢወዱት ምን ያደርጋል አገር

 ሕንፃው ምን ቢረዝም ምን ቢፀዳ ቤቱ

 መንገዱ ቢሰፋ ቢንጣለል አስፋልቱ

 ሰው ሰው ካልሸተተ ምንድነው ውበቱ

የኔ ውብ ከተማ የኔውብ አገር

የሰው ልጅ ልብ ነው

የሌለው ዳርቻ የሌለው ድንበር

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...