Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርተደራራቢ ፈተናዎች ከታላቁ ግድባችን እንዳያናጥቡን!

ተደራራቢ ፈተናዎች ከታላቁ ግድባችን እንዳያናጥቡን!

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ እንዲጀመር የመሠረት ድንጋይ በይፋ የተጣለበት 12ኛ ዓመት፣ ከሁለት ወራት በፊት ታስቦ አልፏል፡፡ ይህ በኃይል ማመንጫ አቅሙ በአፍሪካ ትልቁ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ አሥር ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች መካከል አንዱ የሆነው ፕሮጀክት ከፍትኛ የሕዝብና የመንግሥትን ትኩረት የሚሻ ነው፡፡ እናም እንደ አገር በተለያዩ ወቅታዊ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ስንውተረተር ታላቁን አሻራ እንዳንዘነጋው ማለት ነው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ፡፡

ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ከራሷ በሚፈልቀው የዓባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት የቆየውን የግብፅ ብቸኛ ተጠቃሚነትንና ኃያልነትን የሰበረ በመሆኑ፣ ክንውኑ ታሪካዊና የአሁኑ ትውልድ ትልቁ ቅርስ አድርጎታል፡፡ ይህ አገራዊ ሀብት የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የውኃ ሀብታቸው ያለ ጥቅም ለዘመናት ሲፈስ እያዩ ምንም ማድረግ ላልቻሉ የናይል ወንዝ ተጋሪ አገሮችም ጭምር ነው። እንዳለመታደል ሆኖ ቀጣናውም ሆነ እኛ ተረጋግተን እየቀጠልን አለመሆኑ እንጂ ግድቡ የመጪው ጊዜ ብርሃን መሆኑም አይቀሬ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የግድቡ ግንባታ አፈጻጸምና የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 12ኛ ዓመት በዓል በአከበረበት ወቅት፣ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ‹‹ግድባችን በተለያዩ አካላት የሚነሳበትን የሥጋት አጀንዳ ሁሉ መሬት ላይ በሚታዩ ክንውኖች እያከሸፈ በተቃራኒው የተፋሰሱ አገሮችን በጥቅም የሚያስተሳስር መሆኑ ታይቷል፤›› በማለት የተናገሩት ነባራዊው ሀቅ የሚያሳይ ነው። በቀጣይም ይህንኑ ሀቅ የሚያጠናክሩ ሥራዎችን መከወን እንደሚገባም በማሳሰብ ጭምር፡፡

ኢትዮጵያውያን በሙሉ በታላቅ ንቅናቄያችን “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን” በሚል ወኔ የተረባረብንበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረ እነሆ አሥራ ሁለት ዓመታት ሆኖታል ያሉት አቶ ደመቀ፣ አሥራ ሁለት የጥረትና የስኬት ብሎም የፈተና ጉዞ የታየባቸውን ዓመታት አሳልፈን በስተመጨረሻ የድል ዘመናት ላይ ደርሰናል ነበር ያሉት። አሁንም ግን ፈተናውና ወጀቡ ይቆማል ማለት እንደሆነ ሊጤን ይገባዋል፡፡

በዚህ ጉዞ ከሁሉ በላይ ሕዝባችን ዕውቀቱን፣ ችሎታውን፣ ገንዘቡንና ጉልበቱን ሳይሰስት ለታላቁ የሰንደቅዓላማ ፕሮጀክት አስተዋጽኦ አድርጓል። በየደረጃው ያለው አመራርም ወደር የለሽ ርብርብ አድርጓል ብለው፣ ይህን ግለት አጠናክሮ መቀጠል የትውልዱ አደራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ትኩረት ይኼው ተባብሮና ተደማምጦ ጅምሩን የመፈጸም ግዴታ መዘንጋት እንደሌለበት ማሳያ ነው።

ፈተናው ተለዋዋጭ ለመሆኑ ማሳያውም ከዚያ ጊዜ ወዲህ የፕሮጀክቱ ተቀናቃኝ መሆን የሚያምራት ሱዳን በእርስ በርስ ግጭት ታምሳለች፡፡ በአገራችንም የትግራይ ክልል ጦርነት ጋብ ቢልም፣ በአማራ ክልል መጠነኛም ቢሆን አለመግባባትና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተፈጥሯል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የፖለቲካ ግድያዎችና አገር ያልተረጋጋች የሚያስመስሉ ዕርምጃዎች መከሰታቸውም አልቀረም፡፡ የኦነግ ሸኔ ነገርም አለየለትም፡፡ እነዚህና መሰል ወቅታዊ መንገራገጮች ደግሞ ትኩረታችን ከታላቁ አሻራ ላይ ዞር እንዲል እንዳያደርጉ መታሰብ አለበት፡፡

በእርግጥ እስካሁን ባለው አገራዊ አቅም ሁሉ መሬት ላይ ያለው የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘ መሆኑ እጅግ አበረታች ነው። በቀጣይም ኅብረተሰቡ ለግድቡ ያለውን ፅኑ ድጋፍ በሚመጥን ደረጃ የማስተባበር ሥራዎችን ፈጠራ በታከለበት ሁኔታ ሊጠናከር ይገባዋል። ከአረንጓዴ አሻራ ሥራው ጋር በማያያዝ የተፋሰስ ልማቱ እንቅስቃሴም ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ እዚህ ላይ እንደ ሥጋት የሚነሳው ግን ሰው በኑሮ ውድነትና እንደልብ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት በመቸገር ምክንያት፣ የሚፈለገውን መዋጮ ማሰባሰብ የማይቻል መሆኑ ነው። መሰለቻቸቱም እንዳለ ግልጽ ነው፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ታላቅ አገራዊ ህልምና ተስፋ ነው፡፡ ግን በማንም ወገን ቢሆን ቸል ሊባል አይገባውም፡፡ የዛሬው ብቻ ሳይሆን የመጪውም ትውልድ ታላቅ አገራዊ የልማትና የዕድገት ራዕይ በተግባር የሚገለጽበት ግዙፍ ግድብ እንደ መሆኑ ከቁጥ ቁጥ ሥራ እየወጡ፣ የአገርን ሰላምና ደኅንነት ከማረጋገጥ ባሻገር አፍ ከልብ ሆኖ እሱ ላይ መረባረብ በተለይ ከመንግሥት የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 90 በመቶ እንደ ደረሰ መነገሩ ደግሞ ይበልጥ ሞራል የሚሰጥ ነው፡፡

ገና የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ‹‹መሐንዲሶቹም እኛ፣ አናጢዎቹም እኛ፣ ግንበኞቹም እኛ ሁነን፣ በታላቅ አገራዊና ሕዝባዊ መነሳሳት ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ በራሳችን አቅም፣ ያላንዳች የውጭ ዕርዳታና ዕገዛ እንሠራዋለን፤›› በማለት የተማመኑት ሕዝብን ነበር፡፡ እና ከፖለቲካ ሽኩቻና የዘውግ መጠላለፍ ወጥቶ ይህን ታላቅ ፕሮጀከት ከዳር ማድረስ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ነው የሚገባው፡፡ የትውልድ አደራ ተደርጎ መወሰድም አለበት፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጅምሩ ጀምሮ ብዙ ያከራከረ፣ ብዙ የተባለለት፣ በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ትኩረትን የሳበና ያነታርክ የነበረ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በራስዋና በልጆችዋ አቅም የጀመረችውን የግድቡን ግንባታ ቃሏን ጠብቃ ወደ ፍፃሜው ለማድረስ በትጋት እየሠራች ቆይታለች፡፡ ይህ ትግል ፍፃሜውን አግኝቶ የፕሮጀክቱን ፍሬ በተሟላ መንገድ መቅመስ የሚቻለው ግን፣ በተረጋጋ ውስጣዊ ፖለቲካና በተፅኖ ፈጣሪ ዲፕሎማሲ አገር መመራት ስትችል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አገራዊ ሁኔታውን መፈተሽ በዋናነት የብልፅግና ድርሻ ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከጅምሩ አንስቶ ኅብረተሰቡን ያስተሳሰረ ፕሮጀክት ነው ቢባልም፣ ሞቅ ቀዝቀዝ እያለም ቢሆን አሁንም በፋይናንስ ድጋፍም ሆነ በመንፈስ አንድነት ኅብረተሰቡን አስተሳስሮ በግንባታ ሒደት ላይ የሚገኝ ግዙፍ ሥራ ነው። ይሁንና አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው አካላትና ፖለቲከኞች የብሔር ፖለቲካ መሸቀጫ ለማድረግ ከመውተርተር አልቦዘኑም፡፡ እነዚህን መታገልም ያስፈልጋል፡፡

ግድቡ የእገሌ ነው፣ የአባ እገሌ ነው፣ ለእገሌም ምኑም አይደል እያሉ የምልዓተ ሕዝቡን አቅም ለመበታተንና ብዥታ ለመፍጠር ሲዳክሩም ታይተዋል፡፡ ያም ሆኖ እንኳንስ ለፕሮጀክቱ ቀረብ ያሉ አካባቢዎች ይቅርና በየትኛውም የአገራችን ሰማይ ሥር ቢሆን በኅብረተሰቡ ቀዳሚ ሥፍራ የተሰጠው፣ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ኃያል ሥፍራን የያዘ ፕሮጀክት እንደሆነ እየታየ ነው። ተጠናክሮ መቀጠል ያለበትም ይኼ ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክት ነው ከሚያስብሉት ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራውን ያሳረፈበት ስለሆነ ነው። አንዳንድ ሥራዎች በአገር ውስጥ ተቋራጭ (ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ) እዲከናወን በመሞከሩና በአስተዳደር መደነቃቀፍ መስተጓጎል ገጥሞት የነበረ ቢሆንም፣ ከለውጡ ወዲህ ቀላል የማይባሉ ማስተካከያዎች ተደርገው ሥራው መቃናት መቻሉም ሊካድ አይችልም፡፡ ይህንን እውነታ አጠናክሮ ከፍፃሜ ማድረስ የሚቻለው ግን እንደ መንግሥት ሳይዘናጉ በመረባረብ ነው፡፡

በተለያየ መንገድ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሲቪል ኮንትራቱን የወሰደው የጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ ለቆ እንዲወጣ ጫና ሲደረግበት ቢቆይም፣ ሥራውን በተሟላ አቅም እያከናወነ ወደ ፍፃሜው መድረሱም ትልቅ መተማመንን የሚፈጥር ዕርምጃ ነው፡፡ በተለይ ይህ ኩባንያ በኢትዮጵያ በርከት ላሉ ዓመታት የቆየ በመሆኑና ኢትዮጵያን በደንብ ስለሚያውቅ፣ ጫናውን ተቋቁሞ አብሮ በመሠለፉ ሊመሠገንና በታሪክም ሊጠቀስ እደሚገባው ነው የአገር ውስጥ የውኃ ባለሙያዎች የሚናገሩት፡፡

ከዚህ ባሻገር የግድቡ ሥራ በጠንካራና ልምድ ባለው ተቋራጭና በበርካታ የአገራችን መሐንዲሶች ጥረት እየተገነባ መሆኑ፣ የቴክኖሎጂ አቅምም ለማሳደግ እያስቻለ ነው፡፡ ለአገር ቀጣይ ዕድገትን የሚያረጋግጠው አስተማማኝ የሆነ የቴክኖሎጂ አቅም ሲኖረው በመሆኑም፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር መደረጉ ለትውልዱ ሌላው ትሩፋት ተደርጎ መቆጠርም አለበት፡፡ ነፃ ነን ማለት የሚቻለው በራስ አቅም መሥራት ሲቻል ብቻ ሳይሆን፣ በዘላቂነት ዕውቀትና ክህሎትን እያሳደጉ መዘለቅ ሲቻል ነውና፡፡

እንደሚታወቀው ፕሮጀክቱ ይጠናቀቃል ከተባለበት ጊዜ አንፃር በእጥፍ ዕድሜ ጨምሯል፡፡ ተጠናቆ በሙሉ አቅም ወደ ሥራ እስኪገባም ጥቂት ዓመታትን መጠየቁ አይቀርም፡፡ ከጊዜ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ዋናው ቁምነገር ግን የአቅም ውስንነቱና ኃይል የማመንጨት ሥራ ከታችኛው አገሮች ጋር በመመካከር የሚከናወን መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በትግል የታለፉ በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውም ነው፡፡ በቀጣይም ቢሆን ይኼ ይቀራል ተብሎ አይታሰብም፡፡

ግድቡን በስንት ዓመት በውኃ እንሙላው በሚለው ሙያዊ አጀንዳ ላይ ፖለቲካዊ ጫና እንዲያርፍበት ቀላል የማይባሉ ተፅዕኖዎች ሲደረጉ ቢቆይም፣ አገራችን በፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም ረገድ ከያዘችው አቋም ሳትናወጥ ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረጓም አይዘነጋም፡፡ በተለይ ግብፅን ከመሳሰሉ አገሮች ነገም ቢሆን በውስጥ ጉዳያችን ጭምር ጣልቃ እስከ መግባት የሚደርስ ተፅዕኖ በሦስተኛ ወገን ለመጫን መሞከሩም አይቀሬ ነው፡፡ ይህንን ጫና መመከት ደግሞ የትውልዱ ሌላኛው አደራ ነው፡፡

በተለይ ከታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ጋር ስምምነት የሚጠይቀው አጠቃላይ ግድቡን በውኃ የመሙላት ሒደት ዋነኛው ፈተና ሆኖ የመቆየቱን ያህል፣ ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዘ የውኃ ሙሊት ሲከናወን በአገሮቹ ላይ ምንም ዓይነት ሥጋት የሚፈጥር ፍሰት አለመታየቱ አንድ ማረጋገጫ ነበር፡፡ በቀጣይም ይኼንኑ ሀቅ በገቢር እያሳዩ ከቀውስ አልወጣ ላለው ቀጣናችን ተስፋ ሰጪ ማዕከል መሆን ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም የጋራ ርብርቡ መጠናከር አለበት፡፡

 እኛ ኢትዮጵያውያን በዓለማችን ረጅም በተባለው የዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመገንባት ከመወሰናችንና ግንባታው ከመጀመሩ በፊት፣ ከፍተኛ ቁጭት የነበረን መሆኑ ይታወቃል። በዓባይ ወንዝ ለዘመናት የነበረን ቁጭት ተወግዶ ግንባታውን በመጀመር የግንባታው ሒደት መፋጠኑ፣ ኢትዮጵያውያን እንደ አገር በአንድ ላይ ለአንድ ዓላማ የመቆማችንን፣ ለወደፊትም ይህን መንገድ የመከተላችን ዋነኛ ማሳያ እንደሆነ በሌሎች የጋራ ፕሮጀክቶቻችንና መስተጋብሮቻችን ማረጋገጥም ግድ ይለናል።

ስለሆነም ሁሉንም ነገር ስናሰላ ብዙ ውጣ ውረድ የነበረበትን ሒደት በማስታወስ ሊሆን ይገባዋል። በተለይም የዓባይን ወንዝ ለመገደብ ለግንባታ የሚሆን ገንዘብ በብድርም ሆነ በዕርዳታ እንዳናገኝ በርካታ ተፅዕኖዎች እንዳጋጠሙን ማስታወስ ብቻ ሳይሆን፣ ነገም ይኼ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ተረድቶ የውስጥ አቅምን ማጠናከር ትኩረት ማግኘት ይኖርበታል፡፡

በ12 ዓመታት እንደ አገር ያጋጠሙንን ቀላል የማይባሉ መሰናክሎችና ተግዳሮቶች ለመበጣጠስ ከተካሄዱት ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ጋር፣ የሕዝቡ ቁርጠኝነት ለውጤታማነቱ የላቀ ድርሻ ነበረው። በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት እንደ አገር ከተጀመረው ለውጥ ጋር ተያይዞ በተከሰቱት በርካታ ውጣ ወረዶች መሀል ሥራው እዚህ ደረጃ መድረሱ፣ መረጋጋትና መደማመጥ ቢቻል ተዓምር መሥራት እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው፡፡ እናም መልካም ጅምሮችን ለማስቀጠል መትጋት አሁን ካለው ትውልድ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

ሁሉም የአገራችን ሕዝቦች ዓይንና ጆሮ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጉባ ወረዳ ከዘለቀ ዓመታት ተቆጥረዋል። በአሁኑ ጊዜ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወደ ፍፃሜው እየተቃረበ ነው፡፡ ስለሆነም መላ ሕዝብ በተሳትፎው እንደ ጀመረው ለመጨረስ በተለያዩ መንገዶች ድጋፉን በማጠናከር የድርሻውን አጠናክሮ መወጣት አለበት። ይህ ብሔራዊ ፕሮጀክት ፍፃሜው ሩቅ እንደማይሆን ሁሉ ያንን ለማየት የማይጓጓ እንደሌለም የታወቀ ነው።

የአገራችንን ሰላምና ደኅንነት ብሎም የፖለቲካ መረጋጋት ማረጋገጥ እስከተቻለ ድረስ፣ ግድቡ ሲጠናቀቅም አካባቢው የሚኖረው ገጽታና ማራኪነት ከወዲሁ ተስፋ ሰጪ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በተለያዩ ዘርፎችም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል። በአካባቢው በግድቡ ምክንያት በሚፈጠረው ሐይቅ ለዓሳ እርባታና ለከፍተኛ የምርምር ሥራ አመቺ፣ እንዲሁም በተፈጥሮ ለበርካታ ተመራማሪዎች የምርምር ማዕከል ይሆናል። በዚህም ተስፋችን ዕውን ሆኖ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍፃሜ የተሻለች ኢትዮጵያን የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

ተደጋግሞ እንደተነገረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከፍታው 145 ሜትርና የጎኑ ርዝመት 1.8 ኪሎ ሜትር ሲደርስ፣ የሚከማቸው የውኃ መጠን የጣና ሐይቅን ሁለት እጥፍ ያህል መሆኑ ልብ የሚያሞቅ ነው። ግድቡ ሲጠናቀቅ 1,680 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ወደ 74 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜትር የውኃ መጠን ይኖረዋል መባሉም፣ ከአገራችን አልፎ ለቀጣናው ሥነ ምኅዳርም ሳይቀር ልዩ በረከት የሚያስገኝ መሆኑ እየተነገረ ነው።

ከግድቡ ወደኋላ ሜዳማ ሥፍራውን አልፎ በርቀት የሚታዩት አነስተኛ ተራራማ ሥፍራዎች ጭምር፣ ወደ 246 ኪሎ ሜትር ወደኋላ በሚሞላ የውኃ ሐይቅ ተሞልተው ደሴት ይሆናሉ። እነዚህ ድንቅ አካባቢዎች መሠረተ ልማትና አስፈላጊው የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ሲሟላላቸው፣ መጭውን ትውልድ እያማለሉ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚመጣ ጥርጥር የለውም፡፡

በአጠቃላይ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በየትኛውም ፈተና ይሁን ውጣ ውረድ ውስጥ፣ ወደር የማይገኝለት ብሔራዊ ፕሮጀክት መሆኑ ላይ ልዩነት አይኖርም፡፡ ቢኖርም ሐሳቡ መሸነፉ አይቀርም፡፡ አገራችን እንደ መቼውም ጊዜ ሁሉ የተለያዩ የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶች እየገጠሟት መሆኑን ሁላችንም ብንረዳም፣ በተስፋ ዓይናችን ልንመለከተው የሚገባ የጋራ ሀብታችንም ነው፡፡ እናም ለፈተናዎች ሁሉ ባለመበገር ፍፃሜውን ለማየትና አገራችንንም ወደ ተሻሉ ሌሎች ተጨማሪ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች ለመውሰድ መንጠላጠያ መሰላላችን ማድረግ ይገባናል፣ አንዘናጋ ለማለት እወዳለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...