Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ውኃ በወንፊት!

ጉዞ ከሽሮሜዳ ወደ ሜክሲኮ። ወርኃ ግንቦት ሊጋመስ ተቃርቦ ረፋድ ላይ ሕዝበ አዳም ለኑሮ ትግል ተሠልፎ ታክሲ ይጠብቃል። ቀስ በቀስ የታክሲ ፈላጊው ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ሠልፉም እየረዘመ ነው። ‹‹በሠልፍ ዕድሜያችን ይለቅ?›› ሲል አንድ ቀጭን ረዥም ወጣት፣ ‹‹አሁንማ ዋናው ክረምት ከገባ አለቀልን…›› ይለዋል አብሮት የቆመ ወዳጁ። ‹‹ስንቱ ተፈጥሮን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ በሚኖርበት ዘመን የእኛ ኑሮ ክረምት ሲሆን በጋ፣ በጋ ሲሆን ክረምት መሆኑን መቼ ይሆን የሚያቆመው? ወይ አገሬ እውነት ምን እየሠራን ይሆን ይኼ ሁሉ ዘመን ያለፈብሽ?›› ትላለች ከወጣቶቹ አጠገብ የቆመች ቆንጆ። ብቻ እሷን ዞሮ ሳያይ የማያልፍ አላፊ አግዳሚ የለም። ‹‹በጣም እንጂ፣ ሦስት ሺሕ ዘመን ተኝተን ነበር ያሳለፍነው፡፡ በዚህ ዘመን ግን ሦስት ደቂቃ ጭንቅ ሆኖብናል። ዕድሜ ለፌስቡክና ለዩቲዩብ አሁን ደግሞ መተኛት ብቻ ሳይሆን መጣድም አብዝተናል…›› ይላታል በወዲያ በኩል አጠር ጠየም ያለ ጎረምሳ። እንዲህ እንዲህ እያለ ጨዋታው ሲደራ አንዲት ሚኒባስ ታክሲ መጥታ ከፊት የነበርነውን አፍሳ ጫነችን። ጉዟችን ሲጀመር ቁልቁለት የበዛው ነበር፡፡ መቼም ከዳገት ሳይሻል አይቀርም!

አብረውን የተሳፈሩት ባለባርኔጣ አዛውንት ታዘብኩት ያሉትን ነገር ጮክ ብለው ሁላችንም እየሰማናቸው ያወሩናል። ‹‹እንዲያው እንዲህ ሕዝብ ብቻ ይሁን አገሩ? እግዚኦ፣ አይ ስምንተኛው ሺሕ? ማንም ያልነበረበት ሠፈር እንዲህ በሰው ይሞላ? ይኼ እኮ ድሮ ጫካ ነበር…›› ይላሉ አጠገባቸው ወደ ተቀመጠው ወጣት ዞረው። ‹‹ይገርምሃል ያኔ እትዬ እከሊት፣ አቶ እከሌ፣ ጋሽ እንትና በቃ ሌላ አልነበረም እኮ…›› ይላሉ እንዳሻቸው ትዝታና ትዝብት መሀል እየተወራጩ። ከወደኋላ መቀመጫ፣ ‹‹ለማንኛውም መንግሥት ቢያስብበት ጥሩ ነው። የእስካሁኑ ይበቃል…›› ትላለች አንዷ። ‹‹የእስካሁኑ ምን ነበር?›› ይጠይቃታል አጠገቧ ከተቀመጡ ተሳፋሪዎች አንዱ። ‹‹በቂ የመኖሪያ ቤቶች መገንባት አለመቻል፣ ዘርፈ ብዙ የሥራ ዕድሎች በአጥጋቢ ሁኔታ አለመፍጠር፣ ይህን ተከትሎም ስደት በአስከፊ ሁኔታ ጣራ መንካቱ ነዋ፡፡ መንግሥት የሕዝቡን ቁጥር ዕድገት ዓይቶ፣ አጥንቶ፣ ገምቶና አቅዶ ስላልተዘጋጀ እኮ ነው ዛሬ እንዲህ እኛም ሆንን እሱ የምንጫጫው…›› ስትል፣ ‹‹ቁጥራችን እንዲህ እየጨመረ የሚሄድ ከሆነ ግን ከህንድና ከቻይና በመቀጠል ልንጠራ እንችላለን፡፡ ዋናው ነገር በመብዛታችን አገሪቱ አታልቅም…›› ይላል ሌላው። የማንሰማው የለም እያልን እኛም እንኮመኩማለን። ጨዋታ የማያልቅበት አገር!

‹‹አታልቅም ማለት ምን ማለት ነው?›› ስትለው አጠር ቀጠን ያለች ኮረዳ፣ ‹‹ተሠርታ አታልቅም ነዋ። ቁጠባው አያልቅም፣ መንገዱም አያልቅም፣ የዋጋ ግሽበቱም አይቀዘቅዝም፣ እንዲያው ምን አለፋሽ በቃ ተጀመረ ያልሽው ሁሉ ዑደቱ ይቀጥላል ማለቴ ነው…›› ይላል ወጣቱ ጫን ባለ ድምፅ። ‹‹አዬ!›› ብለው አዛውንቱ ባርኔጣቸውን አንስተው ጉልበታቸው ላይ አስቀመጡት። ‹‹እንዲያው የሚገርመኝ ድሮ እኛ ‘ልጅ በዕድሉ ያድጋል’፣ ‘ልጅ ፀጋ ነው’፣ ‘ልጅ ምንም ቢሆን ሥጋ ነው አይከዳም’ እያልን ባለማወቅ ፈለፈልነው። እኛስ ባለማወቅ ነው፣ ዘመኑም ደግ ነበር። የአሁን ዘመን ሰው ግን ምን እንደሆነ አላውቅም…›› ብለው በቁጭት ተብሰለሰሉ። ከኋላ መቀመጫ ፊት የተመጡት ቆንጅዬዋ ልጅና ጎልማሳው ናቸው። ‹‹እኔን የሚገርመኝ…›› ትላለች እሷ። ‹‹ለመቆጠር አስቸግረን በ‘ነው!’ ‘አይደለም!’ አኃዛችን እስኪያጨቃጭቅ የምንሮጠው የት ለመድረስ ነው?›› ስትለው ጎልማሳው በፌዝ ሳቅ፣ ‹‹ህንድና ቻይና ጋ ነዋ…›› አላት። የእዚህኛው ደግሞ በሀብት ይሁን በሕዝብ ብዛት የታወቀ ነገር አልነበረም። ጠያቂዋ ቆንጆ ሳትወድ በግዷ ፈገግ ስትል አየናት። እንዲህ ነው የዚህ አገር እውነት ሳይወዱ በግድ ፈገግ ያሰኛል!

ድንገት አጠገቤ የተቀመጠ ወጣት፣ ‹‹አሁንማ ወሬያችን መቀየር አለበት፡፡ የሕዝብ ቁጥር ሳይሆን ሊያሳስበን የሚገባው፣ ሕዝባችን እንዴት በክብር መብቶቹ ተጠብቀውለት መኖር ይገባዋል የሚለው ጉዳይ ነው…›› ሲል የታክሲውን ተሳፋሪዎች ባልታሰበው አጀንዳ የደነገጡ መሰሉ። ‹‹አድርጎት ነው? ስንቱን ጧሪ ቀባሪ ያሳጣ፣ ስንቶችን ሕፃናት ያለ አባት ያ ለእናት እያስቀረና ጎዳና ላይ የበተነ ነቀርሳ፣ እውነት አድርጎት ነው? ይህንን የተበላሸ ፖለቲካ አስተካክሎ በሥርዓት ለመኖር ነው መታሰብ ያለበት…›› ትላለች ጠና ያለች ሴት ከወደ ጋቢና። ‹‹ምን ዋጋ አለው? ከአገርና ከሕዝብ ደኅንነትና ጥቅም በላይ ራሳቸውን ያሳበጡ እንዲተነፍሱ ካልተደረገ ምኞት ምን ዋጋ አለው? ለሕዝብ ቆመናል፣ የሕዝብ ድምፅን የሚሉ ወስላታ ፖለቲከኞች በሕዝብ ድምፅና መብት ላይ ባያላግጡ ነበራ…›› ሲላት የምንሰማው ደግሞ አብሯት ጋቢና የተቀመጠ ተሳፋሪን ነው። ኑሮና ፖለቲካ ድንበር አበጅተው የማይኖሩ የወዳጅ ባላንጦች መሆናቸውን ለመናገር ፈልጎ ይመስላል። እንዲያ ነው!

ጎልማሳው ከመሀል ወንበር፣ ‹‹እኔ ግን በአሁኑ ጊዜ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የምለው በሕግና በሥርዓት መኖር እንዴት መለመድ እንዳለበት ነው፡፡ ሌባ ሹም፣ ሌባ ነጋዴ፣ ሌባ ፖለቲከኛ፣ ሌባ ምሁር ተብዬ… እንደ አሸን በሞሉባት አገር ውስጥ ሕግና ሥርዓት ከሌለ ሌላው ዋጋ ቢስ ነው…›› ሲል ተሳፋሪዎች በሙሉ ትኩር ብለው እያዩት ሳል አንድ ወጣት፣ ‹‹ማለት?›› በማለት ጠየቀው። ‹‹እንዴ አታይም እንዴ ሕገወጡ ከመሬት ወረራ እስከ በጀት ዘረፋ፣ ሕዝብ ፍትሕ ከመንፈግ እስከ በጉቦ ማሰቃየት፡፡ በዚህ ሁኔታ አገር አትፈርስም? ሞራል አንደኛውን አፈርድሜ በልቶ መከራ አናይም? ፈሪኃ ፈጣሪ ጠፍቶ ምን ልንሆን ነው? ሹመኛው እንዲያገለግል ከተሾመበት ሕዝብ ላይ በአደባባይ ያለ ጉቦ አልሠራም ብሎ እግዚኦ በሚያስብለን ዘመን፣ አንደኛውን ሞራላችን ላሽቆ እርስ በርስ ስንዛረፍና ስንፋጅና አይታይህም?›› ብሎ ሐሳቡን ሲያብራራ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ይከበር ዘንድ በነበረን ቀና ፍላጎት የሰማነው መሰልን፡፡ እርግጠኛ መሆን አንችልማ!

አራት ኪሎ ስንደርስ ታክሲያችን ወራጆች ስለነበሩ ቆመች። ከኋላ ወንበር ላይ ተቀምጠው የነበሩ ሦስት ተሳፋሪዎች ወርደው በምትካቸው ሁለት ወንዶችና አንድ ሴት ወጣቶች ተሳፍረው ጉዟችን ቀጠለ። ጭውውቱም አዲስ የገቡት ተሳፋሪዎች ሆነ። ‹‹ታዲያ እንዴት ነው? ማለቴ የሥራው ነገር?›› ትላለች ሴቷ መሀላቸው ተቀምጣለች። አንደኛው፣ ‹‹ከቻልን የራሳችንን ሥራ ለመሥራት እያሰብን ነው። ካልሆነ ግን ወይ ወደ ቀን ሥራ ወይ ወደ ጥቃቅንና አነስተኛ እንሰማራለና…›› ሲላት ልጅት ከአንጀቷ ከት ብላ ትስቃለች። ተሳፋሪዎች ጆሮአቸውን ቀስረው ያደምጣሉ። ታክሲያችን ቁልቁለቱን ተያይዘዋለች፣ መንገዳችን እየተጋመሰ ነው። ‹‹በዘንድሮ ኑሮ የሚያበላውን እንደኛ መርጠሽ ካልተማርሽ በኋላ ማጣፊያው ያጥራል…›› የሚላት ደግሞ ከወዲያ በኩል አብሯት የተቀመጠው ወጣት ነው። ‹‹አይ ዩኒቨርሲቲ፣ በቃ እንዲህ ሆድ መሙያ ሆኖ ይቅር?›› እያለ ጎልማሳው ስሜት የተቀላቀለበት ንግግር ይናገራል። ‹‹ምን እናድርግ ድህነታችን እኮ ነው…›› ትለዋለች ከጎኑ ቆንጅት። አስታዋሽ አይጥፋ!

መቼም ጥፋታችን ሁሉ ሰበብ አያጣውም። ‹‹እኔስ የዛሬ ልጆች እንደምታሳዝኑኝ ሌላ ማንም አያሳዝነኝ። በዚህ ሌባው በሚከብርበት፣ ሕገወጡ የነብይ ያህል ተቆጥሮ ታፍሮ በሚኖርበት አገር ተስፋ ሳትቆርጡ ‘ተምሬ ያልፍልኛል’ ብላችሁ ስትተጉ ሳይ በጣም ታሳዝኑኛላችሁ፣ ታስደስቱኝማላችሁ። ብቻ የዚህ አገር ነገር እንዲህ ሆኖ ስለማይቀር ጠንክሩ። ዕውቀትና አዋቂ የሚከበሩበት፣ እውነትና ፍትሕ የሚነግሡበት ጊዜ ይመጣል። ግድ የለም…›› ይላሉ አዛውንቱ ወጣቶቹ ላይ ዓይኖቻቸውን እያፈራረቁ። የሚያዩት ሌላ የሚያስቡት ሩቅ የሆነባቸው ወጣቶች ደስ እያላቸው ይሰሙዋቸዋል። ተስፋን በተስፋ ከመጠበቅ ሌላ ለሰው ልጅ ምን ትርፍ አለውና፡፡ ተስፋ ባይኖር ኖሮ ሕይወት መራራ ነበር የሚሆነው፡፡ እውነት ነው! 

ወደ መዳረሻችን እየተጠጋን ነው። ሜክሲኮ በሚሄድ፣ በሚመጣው፣ በሚወርደውና በሚሳፈረው ደምቃለች። ከላይ የከበደ ጥቁር ደመና አለ። ወያላውና ሾፌሩ፣ ‹አንድ እንድገም ወይስ እዚሁ እንሸጋሸግ?› ይባባላሉ። እነሱ ስለሥራቸው ሲነጋገሩ ተሳፋሪዎች እየከፋ ስላለው የኑሮ ውድነት መነጋገር ቀጠሉ። ‹‹እንዴት ነው ይኼ ጀርባ አጉብጥ ኑሮ የሚቻለው ጎበዝ?›› ይላል አንዱ ከወደ ኋላ መቀመጫ። ‹‹ኤድያ፣ መንግሥት መፍትሔ ይሰጠኛል ብለህ ስትጠብቅ የበለጠ ጎባጣ ሆነህ እንዳትቀር?›› ትላለች ቆንጅት። ‹‹እውነት ነው፣ እኛ ከመንግሥት የምንፈልገው የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ተቀርፈው ዕንባችን ሲታበስ፣ ፍትሕ በየዘርፉ ስትነግሥ፣ ሁላችንንም በእኩልነት የሚያኖር ሥርዓት በጋራ ሲገነባና በአጥንት ቆጠራ መጠቃቀም ሲቆም ነው…›› እያለ ጎልማሳው ሊቀጥል ሲል ያላስቻለው ደግሞ እያቋረጠ፣ ‹‹የትምህርት ጥራት ሲሻሻል፣ የነዋሪዎች የቤት ችግር ሲቀረፍ፣ የሕግ የበላይነት ሲሰፍን፣ በሴራ ፖለቲካ ወገኖቻችንን መፍጀት ሲቆም ማየት ነው…›› እያለ ቀጠለ። ታክሲያችን መቆሚያዋን አመቻችታ ወያላው፣ ‹‹መጨረሻ!›› ሲለን አዛውንቱ እንደ ቀልድ፣ ‹‹ዋናው ለውጥ የሰው ሳይሆን የአስተሳሰብ ነው፣ የጠራ አስተሳሰብ ከሌለ ነገራችን ሁሉ ውኃ በወንፊት መቅዳት ነው…›› ብለው ቀድመውን ወርደው ተራመዱ። እኛም እንደሳቸው በየፊናችን። መልካም ጉዞ!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት