ከሰሞኑ የማዕከላዊ ምክር ቤት ስብሰባ ማካሄዱን በማስታወቅ ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. መግለጫ የሰጠው ኅብር ኢትዮጵያ ፓርቲ፣ በልዩ ሁኔታ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ (Extraconstitutional Amendment) ማድረግ በኢትዮጵያ አስፈላጊ ነው አለ፡፡ ከሰሞኑ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ይዞት የመጣው በልዩ ሁኔታ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የማድረግ አጀንዳ፣ ፓርቲው ለረዥም ጊዜ ሲያቀነቅነው የቆየ መሆኑን በመግለጫው ገልጿል፡፡
ሕገ መንግሥቱ ራሱን ለማሻሻል ፍፁም ዝግ የሆነ ሕገ መንግሥት መሆኑን የጠቀሰው ኅብር ኢትዮጵያ፣ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር ደግሞ በልዩ ሁኔታ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ መንገዶችን መከተል አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል፡፡
ፓርቲው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባተኮረው መግለጫው፣ ፓርቲውን ስለማጠናከርና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጋራ ስለመሥራትም አቋሙን አንፀባርቋል፡፡
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽንን በተመለከተ የመንግሥት ጥላ ያጠላበት መሆኑን ያስታወቀው ፓርቲው፣ የአገሪቱን የፖለቲካና የሚዲያ ምኅዳር እየተዘጋ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ኃላፊ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር)፣ ‹‹እውነት የሚናገሩና ሕዝብ የሚያደምጣቸው የሚዲያ ሰዎችና ፖለቲከኞች እየታደኑ ነው›› ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ማንነት ተኮር ጥቃትና ግጭት መበራከቱን ኅብር ኢትዮጵያ ገልጾ፣ ይህ ደግሞ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የሚታይ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ይልቃል (ኢንጂነር) ይህን በተመለከተ የአማራ ክልል የቅርብ ጊዜ ሁኔታ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
‹‹በአማራ ክልል እየተወሰዱ ያሉ ተከታታይ ዕርምጃዎች ሆን ተብሎ ያን አካባቢ ለማድቀቅ የታሰቡ ይመስላሉ›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ለሁለት ዓመታት የሽግግር ጊዜ አስተዳደር የመመሥረት ጉዳይን ፓርቲው ሲጠይቅ መቆየቱን በመግለጫው ተነስቷል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር ዕለት ተዕለት እየተወሳሰበ የሚሄድ ቀውስ መሆኑን ያስታወቀው ፓርቲው፣ ይህ ደግሞ መንግሥትን ከሚመራውም ሆነ ከሌሎች ፓርቲዎች የተናጠል አቅም በላይ ነው ብሏል፡፡
ለዚህ ሲባል የሽግግር ጊዜ መንግሥት የመመሥረት ጉዳይ መፍትሔ ነው ሲል ያቀረበው ፓርቲው፣ ሁሉንም ያካተተ የሽግግር ጊዜ አስተዳደር ማቋቋም ብቸኛው አማራጭ መሆኑን አስታውቋል፡፡