የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን መደበኛና ኢመደበኛ አደረጃጀት ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ፣ ሁሉን አቀፍ አካታች ምክክር እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ዓርብ ግንቦት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፣ በተለያየ ሁኔታ ለአገራዊ ምክክሩ አመቺነት ዋና መተዳደሪያ ያላቸው ሰዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ዕድሮች፣ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ አባቶች፣ እናቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራን፣ የንግድ ማኅበረሰብ፣ የተገለሉና ተፈናቃዮች በተለያዩ መንገዶች ይሳተፋሉ ብሏል፡፡
ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በጋምቤላ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በሐረሪ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከየማኅበረሰብ ክፍሎቹ ተሳታፊዎችን መለየት እንደሚጀምር ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
የምክክር ኮሚሽኑ ሥራውን የሚጀመረው በወረዳዎችና በልዩ ወረዳዎች ከሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሆኑን፣ የልየታው ሒደት የሚከናወነው በክልሎቹ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም የዞን ማዕከል ከተሞች እንደሆነ በመግለጫው ተብራርቷል፡፡
በወረዳ የተለዩት የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ወደ ክልል በመሄድ፣ በክልሎች ከተወከሉ የባለድርሻ አካላት ተወካዮች ጋር በመሆን አጀንዳዎች በማሰባሰብ ሒደት ላይ እንደሚሳተፉ ተመላክቷል፡፡ በተመሳሳይ በፌዴራል ደረጃም የሚወከሉ ባለድርሻ አካላት በተወካዮቻቸው አማካይነት በአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የማኅበረሰብ ክፍሎች በኮሚሽኑ ጠያቂነት እያንዳንዳቸው 50 ሰዎችን ከየወረዳቸውና ከየኅብረተሰቡ ክፍላቸው ወክለው እንደሚልኩ ተገልጿል፡፡
የኮሚሽኑ በተሳተፊ ልየታ ተባባሪ አካላት ያግዙኛል ያላቸው የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር፣ የኢትዮጵያ አገር አቀፍ የዕድሮች ማኅበራት ጥምረት፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የወረዳ (ልዩ ወረዳ) አስተዳደር ተወካዮችና እንደ አካባቢው ዓውድ የጎሳ መሪዎች ናቸው ተብሏል፡፡