Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለአረንጓዴ አሻራ የወጣውን ወጪ የሚያጠና ተቋም ተመረጠ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ በልማት አጋሮች፣ በመንግሥትና በኅብረተሰቡ የወጣውን ወጪ ዋጋ የሚያጠና ተቋም ተመረጠ፡፡

የአረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር)፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እየተተገበረ ያለው በኢትዮጵያውያን ቢሆንም፣ ነገር ግን ፈሰስ እየተደረገ ያለው ገንዘብ ትንሽ አይደለም ብለዋል፡፡

የዓለም ባንክ፣ የኖርዌይ፣ የስዊድን፣ የጀርመን፣ የእንግሊዝ መንግሥታትና ሌሎች አገሮችና ተቋማት ለአጠቃላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ለደን ልማት የሚያደርጉት ድጋፍ እንዳለ ሆኖ፣ ማኅበረሰቡ ከሚያበረክተው ነፃ ጉልበት ጋር ተደምሮ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ፈሰስ እየተደረገ መሆኑን አደፍርስ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ ከላይ ለተገለጹት ጉዳዮች ምን ያህል ነው የወጣው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ አገራዊ ጥናት ለማድረግ፣ ‹‹ሲፎር›› የሚባል ተቋም መመረጡንና ጥናቱ ሲጠናቀቅ ወጪው በአኃዝ ተደግፎ እንደሚገለጽ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ የደንና የአረንጓዴ ሽፋን ለማሳደግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አማካይነት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በ2011 ዓ.ም. መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ባለፉት አራት ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን የግብርና ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

መንግሥት በተጠቀሱት አራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዶ 25 ቢሊዮን የሚደርስ ችግኝ መተከሉን ቢያስታውቅም፣ ከቁጥሩ ተዓማኒነት ጋር የሚሰነዘሩ ጥያቄዎች ይሰማሉ፡፡

አደፍርስ (ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት ከቁጥር ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ጥያቄዎች እንደሚሰሙና በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝ እየፈላ ነው ወይ? የት ነው እየፈላ ያለው? ማን ነው እያፈላ ያለው? በምን ሀብት ነው እየፈላ ያለው? የሚሉ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እንደሚነሱ ገልጸዋል፡፡

‹‹ችግኝ መቁጠር አስቸጋሪ አይደለም፣ አገሪቱ ውስጥ ያሉ ችግኝ ጣቢያዎችን መቁጠርና በችግኝ ጣቢያ ውስጥ ስንት ችግኝ ነው የሚፈላው የሚለው መልስ በቂ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የቁጥሮችን ተዓማኒነት ለመጨመር ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኝ፣ ከእነዚህም አንደኛው ችግኝ ጣቢያዎች ካርታ እንዲኖራቸው ማስቻል ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡ ለአብነትም በደቡብ ክልል የሚገኙ ዋና ዋና የችግኝ ጣቢያዎች ካርታ እንዲዘጋጅላቸው እንደተደረገና ይህም መገኛቸውን፣ ባለቤትነታቸውንና ስፋታቸውን እንዲታወቅ ከማስቻሉም በላይ፣ በስፋታቸው ምን ያህል ችግኝ በዓመት ማፍላት እንደሚቻል የሚታወቅበት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

መረጃው ከቀበሌ ወደ ወረዳ፣ ከወረዳ ወደ ዞን፣ ከዞን ወደ ክልል ከመጣ በኋላ በክልሎች ተጠናቅሮ በፌዴራል ደረጃ የአረንጓዴ አሻራ ኮሚቴ እጅ እንደሚደርስ የኮሚቴው ሰብሳቢ አስታውቀዋል፡፡ አክለውም ወደ ታች በመውረድም ከተለያየ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የተውጣጡ ባለሙያዎች ክልሎች ላይ ሄደው የችግኝ ጣቢያዎች ላይ ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ግንቦት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በሳይንስ ሙዚየም በአረንጓዴ አሻራ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ሲያካሂድ ንግግር ያደረጉት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ በየዓመቱ 92 ሺሕ ሔክታር የሚገመት የደን መጠን ይጨፈጨፍ እንደነበር አስታውሰው፣ ነገር ግን በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት በተደረገው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ቁጥሩ ወደ 32 ሺሕ ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በየዓመቱ ከአንድ ሔክታር በላይ ይሸረሸር የነበረው የአፈር መጠን ከ130 ቶን ወደ 42 ቶን መቀነሱን፣ አገሪቱ የደን መጨፍጨፍን በመቀነሱ ምክንያት በዓለም አቀፍ ዕውቅና ከማግኘቱ ባሻገር ከካርቦን ንግድ በ100 ሚሊዮኖች የሚቆጠር ክፍያ ማግኘት መጀመሯን ግርማ (ዶ/ር) አክለዋል፡፡

በአንደኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋትና በአራቱ ዓመታት በተለይም ከጥራት ካለው የዛፍ ችግኝ እጥረት፣ እንዲሁም ለሥነ ምኅዳር ተስማሚነት የሆኑ ዕፅዋቶች አመራረጥ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን በማረም፣ ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች