Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከ200 ሺሕ በላይ የትግራይ ክልል ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ መጀመሩን መንግሥት አስታወቀ

ከ200 ሺሕ በላይ የትግራይ ክልል ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ መጀመሩን መንግሥት አስታወቀ

ቀን:

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተሳተፉ ከ200 ሺሕ በላይ የትግራይ ክልል ተዋጊዎች ሥልጠናና ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ፣ የፌዴራል መንግሥት ገንዘብ መድቦ የተሃድሶ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የፌዴራል መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተሳተፉ ተዋጊ ኃይሎችን፣ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችንና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ 250 ሺሕ የሚደርሱ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት፣ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ለመጀመር 29.7 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው በቅርቡ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የመልሶ ግንበታ ፕሮግራም መነደፉንና በቀጣይ አጠቃላይ ዕቅድ በቀጣይ ሳምንት ይፋ እንደሚደረግ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የተናገሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቀት ከዓለም ባንክ በተገኘ የ300 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት በአፋር፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የመልሶ ማቋቋም ሥራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀት፣ ፕላንና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ባቀረቡበት ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ነው፡፡

አቶ አህመድ በክልሎች የተቋማት መዋቅር ግዝፈትና የተሿሚዎች ቁጥር እየጨመረ ምመጣት ለበጀት ፍላጎት ማደግ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፣ የፌዴራል መንግሥቱ በተለያዩ ምክንያቶች ለመንግሥት ሠራተኞቻቸው ደመወዝ መክፈል ለተሳናቸው ክልሎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሰባት ቢሊዮን ብር ማበደሩን አስታውቀዋል፡፡

በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር መሠረት በጀት የተደለደለላቸው ክልሎች፣ ከማዳበሪያ ዕዳና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ደመወዝ መክፈል እንዳቃታቸው የገንዘብ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ወደ ክልሎች ሀብት ማስተላለፍ የሚችለው በተቀመጠለት የበጀት አዋጅና ቀመር መሠረት ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ክልሎች በተለይም የደቡብ ምዕራብ፣ የሲዳማ፣ እንዲሁም ነባር ክልሎችም ጭምር ደመወዝ የመክፈል ጫና ውስጥ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡

 ለዚህ የገንዘብ እጥረት ጫና የፌዴራል መንግሥቱ ገንዘብ መስጠት የሚችልበት አግባብ ሕግ የሌለ በመሆኑ፣ የተወሰኑትን በተለይም የከፋ ችግር ላለባቸው ክልሎች ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ የፌዴራል መንግሥት ማበደሩን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጫና ነባር ክልሎችም ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ጋር ተገናኝቶ ለገጠማቸው ችግር፣ እንደ ማስታመሚያ የሚሆን ብድር መሰጠቱን አቶ አህመድ ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥቱ የማስታመምና የማስታገሥ ሥራ የሚሠራ ቢሆንም፣ አካሄዱ በዚህ መቀጠል እንደሌለበት ጠቅሰው፣ ክልሎች በተለየ ትኩረት የሀብት ማመንጨት አቅማቸውን የበለጠ ሊያሳድጉ ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ አህመድ አክለውም በክልሎች እየተፈጠረ ያለ ተቋማዊና የሰው ኃይል መዋቅር እጅግ በጣም በመግዘፉ የተሿሚዎች ቁጥር እያደገ መሆኑን አክለዋል፡፡

የመንግሥት ተቋማት በአገር ደረጃ ያበጡት በክልሎች መጠን መጨመር እንጂ በፌዴራል መንግሥቱ ምክንያት አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፣ የፌዴራል መንግሥቱ የአስፈጻሚውን ቁጥር ከ190 ወደ 112 ቢቀንስም የክልሎች ግን አሁንም እየሰፋ በመሆኑ መዋቅራቸውን አሁንም መልሰው መፈተሽ አለባቸው ብለዋል፡፡

በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ከመንግሥት መጠባበቂያ ገንዘብ 18 ቢሊዮን ብር በተጨማሪነት እንደተመደበላቸው ተገልጿል፡፡

ክልሎች የዞንና የወረዳ አደረጃጀት ላይ ትኩረት ሰጥተው የለውጥ ሥራ ማከናወን እንደሚኖርባቸው የገለጹት አቶ አህመድ፣ አሁን ለተፈጠረው የደመወዝ  መክፈል ችግር በአዋጅ የተፈቀደው አሠራር የፌዴራል መንግሥት አበድሯቸው መልሰው እንዲከፍሉ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነ አብራርተው፣ የአዳዲስ የክልልነት ጥያቄ ጉዳይም ክልሎች ያላቸውን አቅም ያገናዘበ መሆን እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...