- 62 ቢሊዮን ብር ለውጭና አገር ውስጥ ብድር መክፈሉን ገልጿል
መንግሥት በ2015 ዓ.ም. ይከናወናሉ ተብለው ዕቅድ ተይዞላቸው የነበሩ የተለያዩ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ወደ መጪው በጀት ዓመት በማሸጋገር፣ 18 ቢሊዮን ብር ገንዘብ መቆጠብ መቻሉን የገንዘብ ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ይህንን ያስታወቁት የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀት፣ ፕላንና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርቡ ነው፡፡ በ2015 ዓ.ም. በፓርላማ ፀድቀው ዕቅድ ተይዞላቸው ነገር ግን ጨረታ ያልወጣላቸው፣ ያልተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ከባለበጀት መሥሪያ ቤቶችና ከክልሎች ጋር በቂ ንግግር በማድረግ ወደ መጪው በጀት ዓመት እንዲሸጋገሩ በማድረግ ገንዘብ መቆጠብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ ይህንን ቢሉም የቋሚ ኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ወንድወሰን አድማሴ፣ ‹‹ከክልሎች ጋር በቂ ንግግር በማድረግ ፕሮጀክቶች ለቀጣይ ዓመት እንደተሸጋገሩ በሚኒስትሩ በተገለጸው ጉዳይ ላይ እንደ ቋሚ ኮሚቴ ጥርጣሬ አለን፤›› ብለዋል፡፡
የፓርላማ አባላቱ የሕዝብ ውክልና ሥራ ለማከናወን ወደ ተመረጡበት አካባቢ ሲሄዱ፣ ታጠፉ የተባሉ የፌዴራል ፕሮጀክቶች ለምን እንደታጠፉ ክልሎች መረጃ የላቸውም ብለዋል፡፡
በመሆኑም የፕሮጀክቶች መሰረዝ መሥፈርትና ፍትሐዊነት አለመጓደሉ በግልጽ መታየት አለበት ያሉት አቶ ወንድወሰን፣ ለአብነት በአንድ አካባቢ ሁለት ፕሮጀክቶች ከተያዘላቸው ረዥም ጊዜ ቆይተው ወደ ሥራ ሊገቡ ነው ሲባል እንደገና መታጠፋቸውንና ይህ አሠራር ፍትሐዊነትን እንዴት ላያጓድል ይችላል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፣ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ቅደም ተከተል ማውጣት የሚያስፈልግ በመሆኑ በስምምነት የተፈጸመ የፖለቲካ ውሰኔ ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የተደረገው የጊዜ ሽግሽግ እንጂ ፕሮጀክቶቹ ታጥፈው ባለመሆኑ የጎላ የፍትሐዊነት ጥያቄ አያስነሱም ሲሉ አክለዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የፌዴራል መንግሥት ለ2015 ዓ.ም. ዘጠኝ ወራት 446.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን፣ ይሰበሰባል የተባለው አጠቃላይ የገቢ መጠን ከታክስ 400 ቢሊዮን፣ ከታክስ ካልሆኑ 38.8 ቢሊዮን ብር፣ ከውጭ አገሮች የሚገኝ ቀጥታ የበጀት ድጋፍ ዕርዳታ 7.7 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ በተጠቀሰው ጊዜ የተገኘው ገቢ በአጠቃላይ 296 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ይህ ገንዘብ የተሰበሰበው 282 ቢሊዮን ብር ከታክስ፣ 14 ቢሊዮን ብር ታክስ ነክ ካልሆኑ ገቢዎች እንደሆነ፣ ከውጭ አገሮች የቀጥታ በጀት ድጋፍ ግን ምንም አለመገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከውጭ አገሮች በቀጥታ በጀት ድጋፍ ይመጣ የነበረው ገንዘብ ከሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተገናኘ ከልማት አጋሮች ጋር በነበረ ያልተገባ ጫና ምክንያት፣ አንዳንዶቹ የበጀት ድጋፍ በማቆማቸው እንደሆነ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ከመንግሥት ግምጃ ቤት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለፌዴራልና ለክልል መንግሥታት 722 ቢሊዮን ብር ፀድቆ ነበር፣ ከዚህ ውስጥ ለፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ከተፈቀደው 503 ቢሊዮን ብር ውስጥ 307 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለክልል መንግሥት ከተያዘው 219 ቢሊዮን ብር ውስጥ 150 ቢሊዮን ብር መለቀቁን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል አገሪቱ ለውጭና ለአገር ውስጥ ብድር በዓመቱ 125 ቢሊዮን ብር ለመክፈል ታቅዶ፣ በዘጠኝ ወራት ለውጭ ብድር 29 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለአገር ውስጥ ብድር 33.3 ቢሊዮን ብር ተከፍሏል ብሏል፡፡
የፌዴራል መንግሥት በዘጠኝ ወራት በቀጥታ በጥሬ ገንዘብ 266 ቢሊዮን ብር ወደ ማዕከላዊ ግምጃ ቤት ያስገባ መሆኑን፣ በተቃራኒው 459 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን፣ የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን ከአገር ውስጥ ብድር 194 ቢሊዮን ብር እንደተወሰደ አስረድተዋል፡፡
ለበጀት ጉድለቱ ብድሩ የተገኘው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ለፋይናንስ ተቋማት ከተሸጠ የትሬዠሪ ቦንድና ትሬዠሪ ቢል መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በዘጠኝ ወራት ውስጥ በዕርዳታና በብድር 2.9 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ በዕርዳታ 1.4 ቢሊዮን ዶላር፣ በብድር 404 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ ከዚህ በፊት ቃል የተገባ የውጭ አገሮች በብድርና በዕርዳታ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ፍሰት ታቅዶ፣ ከዕርዳታ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ከብድር ደግሞ 426 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል ሲሉ አክለዋል፡፡ ለአፈጻጸሙ ማነስ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተገናኘ አገሮች ገንዘብ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዘጠኝ ወራት ከልማት አጋራት ይገኛል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ገንዘብ ባለመገኘቱ በጀት ላይ ተጨማሪ ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ፣ ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የድህነት ደረጃ ተባብሶ ብዙ ዜጎች ወደ ከፋ ድህነት ውስጥ መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡