- ባንኮች ለኮንስትራክሽን ግንባታ ዋስትና የሰጡት ገንዘብ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተጠቁሟል
የኮንስትራክሽን ዘርፉ በውጭ ሥራ ተቋራጮች ወረራ በሚባል ደረጃ በመያዙ፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ከጨዋታ ውጪ እየሆኑ መምጣታቸውን፣ የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማኅበር አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ሀብተ ሥላሴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ጊዜ አጠቃላይ የአገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ችግር ውስጥ ከመሆኑም በላይ፣ ለውጭ ኮንትራክተሮች የተከፈተላቸው የዕድል በር እነሱን እያፈረጠመ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን እየጎዳ ነው፡፡
‹‹በቅርቡ በተደረገ ጥናት እንዳየነው ትልልቅ ከሚባሉ የመንግሥት ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ድርሻ ሦስት በመቶ ብቻ ነው፤›› ያሉት አቶ ግርማ፣ በመንገድ፣ በሕንፃ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታና በመሳሰሉት የውጭ ኮንትራክተሮች በተለይ የቻይና ኮንትራክተሮች ሥራውን በሞኖፖል ይዘውታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሊሠሩት የሚችሉዋቸው ሥራዎች ሳይቀሩ ለውጭ ኮንትራክተሮች እየተሰጡ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ግርማ፣ አሁንም የተለያዩ የግንባታ ሥራዎች በከፍተኛ ዋጋ አንዳንዴም ያለ ጨረታ ለውጭ ኮንትራክተሮች እየተሰጡ ስለሆነ የአገር በቀል ኮንትራክተሮችን ችግር ማባባሳቸውን አስረድተዋል፡፡
‹‹በተለይ በመንገድ ሥራ ዘርፍ የቻይና ኩባንያዎች ገበያውን ይዘውታል፡፡ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያገኘነው ወቅታዊ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአሁኑ ወቅት በውጭ ኮንትራክተሮች እጅ ከሚገኙ 71 የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ 90 በመቶው በቻይና ኮንትራክተሮች የተያዘ ነው፤›› ሲሉ አቶ ግርማ የችግሩን ግዝፈት ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንገድ ሥራ ከተሰማሩት 31 የውጭ ኮንትራክተሮች ውስጥ 25ቱ የቻይና ኮንትራክተሮች እንደሆኑ፣ ከቻይና ኩባንያዎች ውስጥ ደግሞ ሲሲሲሲ፣ ሲሲኢሲሲ እና ቻይና ሬልዌይ ሰባተኛ ግሩፕ 77 ግንባታዎችን በመውሰድ ቀዳሚዎቹ እንደሆኑ ይነገራል፡፡
ሲሲሲሲ ሰባቱን መንገድ እየሠራ ያለው ከሃያ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሲሆን፣ ሲሲኢሲሲ ደግሞ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ሥራዎች ወስዶ እየሠራ መሆኑን፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ግን በመንገድ ሥራ ላይ ያላቸው ተሳትፎ እጅግ አነስተኛ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ በአብዛኛው ጨረታዎች ሲወጡ ለጨረታው እንደ መሥፈርት የሚቀመጡ መመዘኛዎች የአገር በቀል ኮንትራክተሮችን ተሳትፎ አናሳ እንዳደረገው ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡ በትልልቅ ጨረታዎች አገር በቀል ኮንትራክተሮች እንደሚሳተፉ የሚቀመጠው መሥፈርትም፣ የውጭዎቹ ኩባንያዎች ያለ ችግር ጨረታውን አሸንፈው ሥራውን ለመረከብ እያስቻላቸው ነው ብለዋል፡፡
‹‹አንዳንድ ፕሮጀክቶች የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች እንዳይገቡባቸው የተፈለገ ይመስላል፤›› ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኮንትራክተሮች ተናግረዋል፡፡ ለምሳሌ በኤርፖርት ማስፋፊያ ውስጥ ወደ 12 ከሚሆኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ውስጥ ሰባት ያህሉ ለቻይናው ሲሲሲሲ ኮንትራክተር ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ እነዚህ ወደ 800 ሚሊዮን ዶላር የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን፣ አሁንም በቀላሉ በአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሊከናወኑ እንደሚችሉ፣ ቀሪ ፕሮጀክቶችንም ይኸው የቻይና ኮንትራክተር ይሥራ ከተባለ የአሠራር ችግር መኖሩን የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የቻይና ኮንትራክተሮች በኮንስትራክሽን ዘርፉ ውስጥ በትሪሊዮን ብር የሚገመት ሥራ ያከናወኑና እያከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ኮንትራክተሮች፣ ያለውን ችግር በመረዳት አገር በቀል ኮንትራክተሮችን የሚደግፉ ሕግጋትን ማውጣትና ያሉትንም ማሻሻያ ማድረግ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በአጭር ጊዜ ይጠፋሉ ብለዋል፡፡
የውጭ ኮንትራክተሮች ተፅዕኖ ብቻ ሳይሆን በክልል አስተዳደሮች በባለቤትነት የተቋቋሙ የኮንስትራክሽን ድርጅቶችም፣ በግል ለተቋቋሙ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች ጫና እየፈጠሩባቸው እንደሆነ አቶ ግርማ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ለክልል የኮንስትራክሽን ድርጅቶች በቀጥታ የግንባታ ሥራዎችን በመስጠት፣ ኮንትራክተሮች ተወዳድረው ሥራ እንዳያገኙ እያደረገ በመሆኑ ብዙ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ከጨዋታ ውጪ እየሆኑ መሆኑንም አቶ ግርማ አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከዋጋ ንረትና ከመሰል ችግሮች ጋር በተያያዘ በርካታ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለማስረከብ ችግር መግጠሙን ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተቋረጡ ፕሮጀክቶችን ለሌላ ኮንትራክተር አሳልፎ መስጠት አገር እየጎዳ ነው ይላሉ፡፡ ሥራውን የያዙትን ኮንትራክተሮች አግባብቶ ሥራውን መጨረስ እየተቻለ፣ ውል አቋርጦ ለሌላው ኮንትራክተር ሲሰጥ እየተጠየቀ ያለው ዋጋ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ጉዳቱ አገርንም ተጨማሪ ወጪ ከማስወጣቱ በተጨማሪ ኮንትራክተሩም ከሥራ ውጪ እያደረገው መምጣቱን ያስረዳሉ፡፡
ይህ እየታወቀ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ውላቸው ከተቋረጠ በኋላ ለሌላ ኮንትራክተር በሚሰጡበት ጊዜ ከቀድሞው ዋጋ ሦስትና አራት እጥፍ የደረሰ ወጪ እያስወጣ ነው ብለዋል፡፡ ይህ እንዳይሆን ከነበሩ ኮንትራክተሮች ጋር በመደራደር ችግሩን መፍታት ቢቻል ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግሥትን ሀብት ያድን እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የአገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እጅግ ውስብስብ ችግር ውስጥ ያለ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግርማ፣ እነዚህን ችግሮች ይመለከታቸዋል ለተባሉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አቤት ማለታቸውንም አስረድተዋል፡፡
በተለይ የውጭ ኮንትራክተሮች ተፅዕኖ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ዝርዝር ማብራሪያ ያቀረቡ መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ ግርማ፣ አሁንም የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን የሚደግፍ አሠራርን ማጠናከር ካልተቻለ፣ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ዕጣ ፈንታ ውድቀት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በአንዳንድ ጨረታዎች ላይ የቻይና ኮንትራክተሮች ተፅዕኖ አይሎ መታየቱ፣ አቅም ያላቸው ኮንትራክተሮችን ሳይቀር እየፈተነ ነው ብለዋል፡፡
ትልቁንም ትንሹንም ፕሮጀክት ለውጭ ኩባንያዎች ከዚህ በኋላ እየሰጡ መቀጠል የአገር ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲወጣ እንደመፍቀድ የሚቆጠር በመሆኑ፣ መንግሥት ይህንን ጉዳይ በብርቱ ሊያስብበት እንደሚገባም ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡
የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች አሁን የገቡበትን ችግር በተመለከተ በችግሩና በመፍትሔዎቹ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የምሕንድስና ባለሙያ፣ አሁን በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ የሚታየው ችግር አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ ዘርፉ ለገጠመው ችግር በአፋጣኝ ምላሽ አለመስጠት ኮንትራክተሮቹን ብቻ ከሥራ ውጪ በማድረግ የሚቆም አይደለም፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላለበት ችግር ሊሰጥ የሚገባው ምላሽ በዘገየ ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሊጠፉ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ችግሩ ከእነሱ አልፎ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ጭምር የሚሸጋገር መሆኑን፣ በአሁኑ ወቅት ባንኮች ከኮንስትራክሽን ግንባታ ጋር በተያያዘ የሰጧቸው የተለያዩ ዋስትናዎች መጠን ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡
የግንባታ ሥራው ሲስተጓጎል አሠሪው ይህንን የተሰጠ ዋስትና ክፈለኝ ቢል፣ የትኛውም ባንክ በአንድ ጊዜ የማይከፈል በመሆኑ ለዚህ ጉዳይ የተለየ መፍትሔ መበጀት እንዳለበት አክለዋል፡፡
እንዲህ ያለውን ችግር የሚያሳይ ጥናት ለመንግሥት መቅረቡን ያስታወሱት ባለሙያው፣ በሌሎች አገሮች ተመሳሳይ ችግር ሲገጥም የወሰዷቸው የተለያዩ ዕርምጃዎችንም ማየት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡