Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ጎበዝ ይኼ ፖለቲካችን የካርታ ቁማር መሰለ እኮ፡፡ በአንድ ወቅት አሜሪካና አውሮፓ ሆነው በኅብረት የወያኔን ሥርዓት ስንታገል ነበርን የሚሉ ፖለቲከኞችና አጃቢዎቻቸው፣ በዘመነ ብልፅግና እንዳለ ግልብጥ ብለው የገቡበትን ፍጥነትና ብልጣ ብልጥት መቼም አንረሳውም፡፡ ራሳቸውን የጋዜጠኛ ካባ ካለበሱ አክቲቪስት ከሚባሉ ሸቃዮች ጀምሮ እስከ መሪዎቻቸው ድረስ፣ ከሥልጣኑም ሆነ ከበረከቱ ለመቋደስ የቀደማቸው አልነበረም፡፡ የ40/60 እና የ20/80 ቤቶችን እንደ ድርጎ ያገኙ፣ የባንክ ሒሳባቸው ውስጥ የደለበ ረብጣ የተሸጎጠላቸው፣ የአውሮፕላን ቲኬት ከእነ መስተንግዶውና ከእነ አበሉ እንደ ፀበል የተረጨላቸው ያሰሙት የነበረው ውዳሴና ሙገሳ መቼም አይረሳም፡፡ ለውጡ በሥርዓት ተጉዞ የሚፈለገው ውጤት እንዲገኝ ምንም ዓይነት ሚና ሳይጫወቱ ጊዜያቸውን በጭብጨባ ያሳለፉ ግለሰቦች፣ ድንገት ዛሬ ፊታቸውን አዙረው ለቅሶ ማሰማት ሲጀምሩ ድንቅ ይለኛል፡፡

መደገፍም ሆነ መቃወም መልክ ሲኖረው መልካም ነው፡፡ ግን መርህ አልባ ድጋፍና ተቃውሞ ነው ስልችት ያለኝ፡፡ ጋዜጠኛ ተብዬው የሙያ ሥነ ምግባሩን አስንቆ ባለሥልጣን ሥር ተጠልሎ ቆይቶ፣ አልመቸው ብሎ እንደገና የተቃርኖ ማላዘን ሲያሰማ ያስጠላል፡፡ ሁልጊዜ እነሱ የቆሙበት ቦታ ብቻ ብፁዕ እንደሆነ ሊነግሩን ሲፈልጉ ደግሞ ያንገሸግሻሉ፡፡ አንዱ ሰሞኑን ወጥቶ በአደባባይ ተቃውሞውን ማንባረቁ ምንም ችግር የለውም፡፡ ችግሩ ግን መጀመርያ ሲያጭበረብርበት የነበረውን ካርድ ከመጣሉ በፊት ይቅርታ መቅደም እንዳለበት ዘንግቶታል፣ ወይም ሆን ብሎ ያደናግራል፡፡ እንደ እሱ ዓይነት ብዙዎች አሉ፡፡ መጀመርያ ምክንያታዊ ሆነው ያጋጠማቸውን ይንገሩን፡፡ ሲመቻቸው ያጠገባቸውን ሳይመቻቸው በመዝለፋቸው ወይም በመስደባቸው ጀግና ለመሆን ሲሞክሩ ግን ያቅራሉ፡፡ ቅደም ተከተሉን ይዞ ለእውነትና ለመርህ መቆም እንጂ ድንገት ደርሶ አጉል አርበኛ መሆን ያሳቅቃል፡፡

ይህንን መረን የወጣ ድርጊት በተመለከተ ከዚህ ቀደም ብዙዎች ሲመረሩበት ብሰማም፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ጽንፍ የረገጡ ግለሰቦች ጉዳይ ግን ብሔራዊ መፍትሔ የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያውያን እንደ ጨው ከተበተኑበት አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅም ሆነ ደቡብ አፍሪካ በአገር የጋራ ጉዳይ ላይ መስማማት ጠፍቷል ማለት ይቻላል፡፡ እዚህ አገር ቤት ያሉ የእነሱ ቢጤዎችም ትንንሽ ችግሮችን በማጋጋል ወደር የላቸውም፡፡ እኔን የሚገርመኝ ግን እነሱን በጋራ የሚያስማማቸው ጉዳይ ሲኖር ጊዜያዊ ፍቅራቸው ጣሪያ ይነካና ይካካባሉ፡፡ ትንሽ ልዩነት ሲፈጠር ደግሞ የአባት፣ የእናትና የትውልድ ሥፍራ ስምና ማንነት እየተብጠለጠለ ይሰደባል፡፡ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ያፈነገጡ ብልግናዎች በስፋት ይቀርባሉ፡፡

አንድ ጊዜ አንዲት የእኔ ቢጤ ተራ ዜጋ፣ ‹‹ኧረ እባካችሁ ለእናት አገራችንና ለሕዝባችን ክብር ስትሉ ይህንን ብልግና አቁሙ…›› በማለት በፌስቡክ ላይ ተማፅኖ ታቀርባለች፡፡ አንዲት ገራገር ሴት ደግሞ፣ ‹‹እውነትሽን ነው እህቴ አገራችንን ማሳፈር የለብንም…›› በማለት ሐሳቧን ታዳብራለች፡፡ በዚህ መሀል አንዱ እንደ ፊጋ በሬ ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹የትኛው ሕዝብ? የትኛዋ አገር? የነፍጠኞቹ፣ የጠባቦቹ፣ የትምክህተኞቹ፣ ወይስ የምንዱባኖቹ…›› በማለት ነገር ሲያጋግል፣ ያደፈጠው ኃይል ከየምሽጉ ወጥቶ የተለመደው የብልግና ስድብ ተጧጧፈ፡፡ የዚያን ቀን ከአፄ ቴዎድሮስ እስካሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ድረስ ስማቸውና የትውልድ ቦታቸው እየተጠራ ተዘለዘሉ፡፡ ጭፍን ተቃዋሚውና ጭፍን ደጋፊው ፊት ለፊት ቢገናኙ ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር የሚለውን ሳስብ ያስደነግጠኛል፡፡

የሃይማኖት ጉዳይንም በተመለከተ ምዕመን ነን በሚሉ ግለሰቦች መካከል የሚካሄደው ጦርነት ቀረሽ ስድድብ አስፈሪ ነው፡፡ አንዲት የለየላት የፌስቡክ አርበኛ የሰውን ልጅ የእምነት ነፃነት በመጋፋት የምትተፋው መርዝ በራሱ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ለእሷ ምላሽ እንሰጣለን የሚሉ ደግሞ አላስፈላጊ ስድቦችንና ሌሎች ወገኖችን የሚያሳዝኑ ቃላት ይጠቀማሉ፡፡ ‹‹መናፍቅ››፣ ‹‹አሕዛብ››፣ ‹‹ፀረ ማርያም››፣ ‹‹መጤ››፣ ወዘተ ከመባባል አልፈው በብልግና ቃላት ይሞላለጫሉ፡፡ በፈጣሪ ፊት ለመቆም የሚያሳፍሩ ተግባራትን የሚፈጽሙ ግለሰቦች፣ ከእምነታቸው አንፃር ለቆሙለት የሃይማኖት ተቋም እንዴት ጠበቃ መሆን እንደሚችሉ ያስገርማል፣ ፈተናው በዝቷል፡፡

ይኼ ማኅበራዊ ሚዲያ ለደህና ነገር መጠቀሚያ መሆን ሲገባው፣ በርካታ አስተማሪ ሊሆኑ የሚችሉ የሚነበቡ ነገሮች እያሉ ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ ጠቃሚ መሆኑ እየተረሳ ነው፡፡ ማንም ሰው በአንድ ጉዳይ ላይ አንድ ሐሳብ ይዞ ሲመጣ የትችቱ መነሻም ሆነ መድረሻ የቀረበው ሐሳብ መሆን ሲገባው፣ ግለሰቡ ለምን እንዲህ ዓይነት አቋም ይኖርሃል ተብሎ ይሰደባል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጠበቃ ነን የሚሉ ወገኖች ሳይቀሩ፣ ግለሰቡን በሚፈጽመው ድርጊት ምክንያት መተቸት ሲገባቸው ለምን ይህንን ሐሳብ ታራምዳለህ? ለምን ይህንን ፓርቲ ትደግፋለህ? ለምን ከእኛ በተቃራኒ ትገኛለህ? ወዘተ እያሉ የራሱንና የዘር ማንዘሩን ድራሽ ያጠፋሉ፡፡ ‹‹ሆዳም፣ ባንዳ፣ የጠላት ተላላኪ፣ ቅጥረኛ፣ ተንበርካኪ፣…›› እያሉ ሰድበው ለሌላ ሰዳቢ ይሰጡታል፡፡

የዋሆቹ ሴቶቻችን ፌስቡክ ላይ ፎቶዋቸውን ሲለጥፉ አድናቂዎቻቸው ‹‹አሪፍ…›› እያሉ ሲያሞግሱ፣ ጽንፈኞቹ ደግሞ በስድብ ያሸማቅቁዋቸዋል፡፡ በእርግጥ አንዳንዶቹ፣ ‹‹ሌላ ነገር ፍለጋ›› እስከሚያስመስልባቸው ፎቶግራፎቻቸውን ሲለጥፉ መካሪ የላቸውም ያስብላል፡፡ ነገር ግን ማንም ሰው ‹‹መብቴ ነው›› እስካለ ድረስ መብቱን ማክበር ማንን ይጎዳል? የዛሬ ዓመት ገደማ ይመስለኛል አንዲት ጓደኛችን ‹‹ፕሮፋይል ፎቶ›› ለውጣ በአዲስ ገጽታ የልደቷ ቀን ትቀርባለች፡፡ የሚያውቋት በሙሉ ‹‹መልካም ልደት›› በማለት መልካም ምኞታቸውን ይገልጹላታል፡፡ አንድ ጽንፈኛ ፖለቲካ ወፈፍ ያደረገው ታዋቂ ጋጠወጥ፣ ‹‹ቅዳሜና እሑድ ሳይቆጠር 50 ዓመት እንደሞላሽ እነዚህ የወንድ ያለህ የሚሉ ዓይኖችሽ ያሳብቃሉ…›› በማለት ሲሰድባት ለካ ታውቀው ኖሮ፣ ‹‹እንደ ሰው ለመተቸት ትናንት ከአገርህ ሰርቀህ ያሸሸኸውን ገንዘብ መልስ…›› ስትለው ሹልክ ብሎ ጠፋ፡፡ ሌብነትን ተሸክሞ ለትችት አደባባይ መውጣት እንዲህ ያዋርዳል፡፡ ገዥውን ፓርቲ ተጠግተው የአገሪቱን መሶብ ሲገለብጡ የነበሩ፣ ዞር ብለው ሌላ ባለመሶብ እያማተሩ ሲፈራገጡ አሁንስ በቃ ማለት ተገቢ መሰለኝ፡፡

                                   (ንጉሤ ወርቅአፈራሁ፣ ከገርጂ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...